ትራምፕ ተጨማሪ 50 በመቶ ታሪፍ ቻይና ላይ እንደሚጥሉ አስጠነቀቁ

ዶናልድ ትራምፕ ተጨማሪ 50 በመቶ ታሪፍ ቻይና ላይ ለመጣል ዝተዋል። ቻይና ወደ አሜሪካ የምትልካቸው ሸቀጦች ላይ ቻይና የጣለችው 34 በመቶ ታሪፍ የማይነሳ ከሆነ ተጨማሪ 50 በመቶ ታሪፍ ቻይና ላይ እንደሚጥሉ አስታውቀዋል። ባለፈው ሳምንት ቻይና ላይ ለጣሉት ታሪፍ በምላሹ ቻይና 34 በመቶ ታሪፍ እንደምትጥል አስታውቃለች። ትራምፕም ቻይና የጣለችውን የአጸፋ ታሪፍ እስከ ማክሰኞ ድረስ ካላነሳች 50 በመቶ ተጨማሪ ታሪፍ እንደሚጥሉ አስጠንቅቀዋል።

ትራምፕ የጣሉትን ታሪፍ በተመለከተ በአሜሪካ የቻይና ኤምባሲ “የምጣኔ ሀብት ጭቆና ነው። መብታችንን ከማስጠበቅ ወደኋላ አንልም” ሲል ምላሽ ሰጥቷል። ትራምፕ ተጨማሪ 50 በመቶ ታሪፍ ቻይና ላይ ከጣሉ የአሜሪካ ተቋማት ከቻይና የሚያስገቡት ምርት በአጠቃላይ 104 በመቶ ታሪፍ የተጣለበት ይሆናል። ይህም የዓለም ሁለት ትልቅ ምጣኔ ሀብት ሀገራትን የንግድ ጦርነት እንዳያባብስ ተሠግቷል።

ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ገጻቸው “ከቻይና ጋር ስለ ታሪፍ እንድንነጋገር የተያዘው ዕቅድ ተሰርዟል” ብለዋል። ከሌሎች ሀገራት ጋርም ስለ ታሪፍ የሚደረግ ድርድርን ለጊዜው መግታታቸውን አክለዋል። “ብዙ፣ ብዙ ሀገራት ከእኛ ጋር ለመደራደር እየመጡ ነው። ፍትሐዊ ድርድሮች ይሆናሉ” ብለዋል።

ቻይና የአጸፋ ታሪፍ እንዳትጥል ቢያስጠነቅቁም ቻይና ግን ታሪፍ ለመጣል ወስናለች። የቻይና ኤምባሲ ቃል አቀባይ ሉ ፔንግዩ “ቻይናን ማስፈራራት ትክክለኛ አካሄድ አይደለም።

አሜሪካ ራስ ወደድ ፍላጎቷን ሌሎች ሀገራትን እየጎዳች ማስፈጸም ትፈልጋለች” ብለዋል።

ትራምፕ በበኩላቸው “36 ትሪሊዮን ዶላር እዳ ያለብን ያለ ምክንያት አይደለም። ቻይና እና ሌሎችም ሀገራት ጥሩና ፍትሐዊ ስምምነት ላይ መድረስ አለባቸው። አሁን ጊዜው አሜሪካ ትቅደም ነው” ብለዋል።

በዋናነት ምርታቸውን ወደ አሜሪካ የሚልኩ የቻይና ፋብሪካዎች ዋነኛ ተጎጂ ይሆናሉ። ቻይና ኤሌክትሮኒክስ፣ የእንጨት ምርት፣ መኪና እንዲሁም ሌሎችም ሸቀጦች ወደ አሜሪካ ትልካለች።

የትራምፕን ታሪፍ ተከትሎ በዓለም አቀፍ የስቶክ ገበያ ላይ መዋዠቅ ታይቷል። የገበያ መቀዛቀዝም ተስተውሏል። የአሜሪካ ስቶክ ገበያን ጨምሮ ዋና ዋና የአውሮፓ የስቶክ ገበያዎች አሽቆልቁለዋል። ትራምፕ ታሪፍን በተመለከተ ከሀገራት ጋር የሚደረገው ድርድር ከተወሰነ ጊዜ በኋላ እንደሚቀጥል መግለጻቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 1 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You