
ኢትዮጵያ በፋሽን ኢንዱስትሪው በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ መሆን የምትችልበት ሰፊ እድል አላት። ይሁን እንጂ በአፍሪካ ደረጃ እንኳን ተወዳዳሪ መሆን አልቻለችም። ለዚህም ሁለት አበይት ምክንያቶች ይጠቀሳሉ። የመጀመሪያው ያለንን ሀገራዊ እምቅ ሀብት አለማወቃችን ነው። ያወቅነውን አለመጠቀማችን ደግሞ ሌላው ሲሆን የመጀመሪያውን ግንብ ደርምሰው የሚገቡ ቆራጥ የዘርፉ ባለሙያዎች ባለመኖራቸው ነው።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ይህ እየተቀየረ የመጣ ይመስላል። በዘመናዊው የፋሽን ኢንዱስትሪ ሰቅዞ ከያዘን ድንዛዜ ነቅተው የሚያነቁ የፋሽኑ ዓለም ጀግኖች ከየአቅጣጫው እየወጡ ወደ ውድድሩ ሜዳ መትመም ጀምረዋል። ከእነዚህም መካከል ሁለቱ የኢትዮጵያ የዘመናዊ ፋሽን የፊት ደጀን አርበኞች ተጠቃሽ ናቸው።
በፋሽን ኢንዱስትሪው ምንም ከማይታይበት ድንግዝግዝ ጨለማ በድፍረት ዘልቃ በመግባት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን የበቃችውና የመጀመሪያዋ የኢትዮጵያ የዘመናዊ ፋሽን ድልድይ መሆን የቻለችው ዲዛይነር ገነት ከበደ በጉልህ ትጠቀሳለች። ከ30 ዓመታት በፊት ገነት ፓራዳይዝ የተሰኘውን ድርጅት መስርታ የኢትዮጵያን የባሕል አልባሳት በዘመናዊ መንገድ እያዘጋጀች ለዓለም አቀፍ ገበያ ታቀርባለች። በዓለማችን ከፍተኛ ነዋይ በሚፈስበት የፋሽን ኢንዱስትሪ ውስጥም ተቀባይነትን ማግኘት ችላለች። በተለይ የምትታወቅበት ደግሞ በባሕላዊ የሽመና ውጤቶች ዘመናዊ የሙሽራ እና የሚዜ አልባሳትን በመስራት ነው።
ኢትዮጵያዊቷ እውቅ ዲዛይነር ገነት ከበደ የፋሽን ጥበብን በጣሊያን እና አርጀንቲና ተምራ ወደ ሀገሯ ትመለስ እንጂ፣ ለፋሽን እና ለዲዛይን ጥበብ ያላት ፍቅር የሚጀምረው ገና ከልጅነቷ ነው። ገነት ፋሽን በሚል ስያሜ የሚታወቁ የተለያዩ በባሕላዊ ጨርቆች የተሰሩ አልባሳት ለገበያ በማቅረብ ትታወቃለች። የሽመና ጨርቆች በዘመናዊ መልክ በስፋት እንዲመረቱ እና ለገበያ እንዲቀርቡ የማድረግ ሂደቱ ተጀመረ እንጂ ገና ምኑም አልተነካም በማለትም ዘርፉን ለመለወጥ ትልቅ ጥረት አድርጋለች።
በዚህ ዘርፍ ውስጥ እሷና እሷን መሰል ጥቂት ዲዛይነሮች ብቻ የኢትዮጵያን የፋሽን ኢንዱስትሪ ለማሳደግ በቂ እንዳልሆኑ የምታምነው ገነት፣ ጥረቷ ያላትን እውቀትና ልምድ ለሌሎች ለማካፈል የማሰልጠኛ ትምህርት ቤት እስከ መክፈት የደረሰ ነው። ሥራዎቿን እና በዘርፉ ያበረከተችውን አስተዋፅኦ የሚዘክር ታላቅ የፋሽንና የሙዚቃ ትርዒት በየጊዜው ይዘጋጃል። ከዚህ የፋሽን ትርዒት የሚሰበሰበው ገቢም በካንሰር በሽታ ለተጠቁ ሕፃናት ሕክምና የሚውል መሆኑ ባለውለታ ያደርጋታል።
ሌላኛዋና የኢትዮጵያ የዘመናዊ ፋሽን የፊት ደጀን አርበኛ ደግሞ የዊን ፒስ መስራቿ ሞዴልና ዲዛይነር ሰናይት ማሪዎ ናት። ደከመኝ ሰለቸኝ ሳትልም በትጋትና ጥረት የፋሽን ኢንዱስትሪው አንድ እርምጃ ወደፊት እንዲሄድ አድርጋዋለች። ዊን ፒስ የተሰኘውን ድርጅት በማቋቋም የኢትዮጵያን የባሕል አልባሳት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የማድረግ ራዕይ ሰንቃ በፋሽን ገበያ ላይ በመንቀሳቀስ ትታወቃለች። ሞዴልና ዲዛይነር ሰናይት እንዴት ወደዚህ ሙያ እንደገባች ስትናገርም “በአንድ ወቅት ጣሊያን ሀገር ነበርኩኝ፣ በዚያ ሰዓት ሙያውና እውቀቱ እንዳለኝ ባስብም በትንሹ ከመሞካከር ውጭ እዚህ ደረጃ ላይ ግን እንደርሳለሁ ብዬ አንድም ቀን አስቤ አላውቅም ነበር። ታዲያ ሁል ጊዜ በጣሊያን ጎዳናዎችና በሄድኩባቸው ቦታዎች ሁሉ አለባበሴን፣ ቁመቴን፣ እንዲሁም የሀበሻ መልኬን የተመለከቱ ሞዴል ነሽ?…ግን ለምን ሞዴል አትሆኚም?… የሚሉኝ ሰዎች በዙ። እኔም ያለኝን ነገር ትልቅ ደረጃ ላይ ማድረስ እንደምችል አመንኩ።” በማለት ትገልጻለች።
ገና ወደሥራው ሳትገባ በሰዎች ዘንድ ተቀባይነትና የሞዴልነትን ማዕረግ ያገኘችው ሰናይት፣ ጊዜዋን ሳታባክን ወዲያው ወደ ሞዴሊንግ ሙያ ገባች። ለተወሰኑ ዓመታትም ስኬታማ ሊባል በሚችል መልኩ በዚያው ሙያ ቆይታ ከዚያም ወደ ዘመናዊ የፋሽን ኢንዱስትሪ በዲዛይነርነት ተቀላቀለች። ሁለቱም ሙያዎች ተያያዥ ቢሆኑም ወደ ሁለተኛው ሙያ እንድታደላ ያደረጋት አንድ ጉዳይ ገጥሟት ነበር።
በወቅቱ ሰናይት የልጅ እናት ሆነችና ለተወሰኑ ጊዜያት ከሞዴሊንጉ በመራቋ የሰውነት ቅርጿም ከሞዴልነት ዓለም ቀስ በቀስ እያሸሻት እንደሆነ ተመለከተች። ወደ ፋሽን ዲዛይነርነት ብትገባ ስኬታማ መሆን እንደምትችል ስለተረዳችም ከሞዴልነት ወደ ፋሽን ዲዛይነርነት ቀየረች። ሌላው እንደ ምክንያትነት የምታነሳው ሞዴል በነበረችበት ወቅት ኬንያ፣ ናይጄሪያ፣ ጋናና ሌሎችም የአፍሪካ ሀገራት የባሕል አልባሳቶቻቸውን ለዓለም ገበያ ሲያቀርቡ ትመለከት ስለነበረ ኢትዮጵያስ ከእነርሱ የተሻለ ሀገራዊ ሀብት እያላት በፋሽን ኢንዱስትሪው ለምን የበታች ሆነች? የሚል ቁጭት በውስጧ አደረ።
አብዛኛዎቹ የአፍሪካ ሀገራት የባሕል አልባሳቶቻቸውን ሰርተው ለዓለም ገበያ ለማቅረብ ጥሬ እቃውን የሚወስዱት ደግሞ ከኢትዮጵያ ነበር። ይባስ ብሎም መልሰው የሚሸጡት ለእኛው ነው። ይህም መንፈሳዊ ቅናት ስላሳደረባት ዐይኗን ሳታሽ በቀጥታ ወደሙያው ገባችበት። በአንድ ወቅት አንድ ልብስ ነጮቹ ለብሰውት ሲታዩ በማሕበራዊ ሚዲያዎች ብዙዎች እየተቀባበሉም በአድናቆት ብዙ ነገር ብለውለታል።
ነጮች ስላዩትም የጀርመን ባንዲራ የሚመስላቸውም ነበሩ። ነገር ግን ልብሱ ከወላይታ ‘ድንጉዛ’ የተሰራ፣ ፈጠራውም የዲዛይነሯ ሰናይት የመጀመሪያ ሥራ ነበር። ዊን ፒስ ፋሽንን ለመመስረት አቅሙን ያገኘችውም ከዚህ በኋላ ነበር። በፈጠራዎች የተካነችው ዲዛይነሯ ከእንሰት በአልኮል ታጥበው ከድንች ጋር በመቀላቀል በርካታ ሥራዎችን መስራት ችላለች። የተለያዩ የሀገር አልባሳትን በመስራት ለዓለም አቀፍ ገበያ ታቀርባለች። ፓሪስ፣ ሚላን፣ ኒውዮርክ፣ ከአፍሪካ ደግሞ ጋና፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ናይጄሪያን ጨምሮ በተለያዩ ሀገራት በመዘዋወር ሥራዎቿን ለማሳየት በቅታለች። በምታደርገው እንቅስቃሴም በናይጄሪያ፣ ጋና፣ አሜሪካና በኢትዮጵያ አቢሲኒያ አዋርድ ላይ የተለያዩ ሽልማቶችን አግኝታለች።
የእነዚህ የዘመናዊው ፋሽን የፊት ደጀን፣ ጀግና አርበኞች ሀገራችን ኢትዮጵያ በባሕላዊው የፋሽን ዓለም የነበራትን ሉአላዊነት ለማስጠበቅ ይታገላሉ። እኛም የእነርሱን አርአያነት እንከተል። ሰጪዎች እንጂ ተቀባዮች እንዳንሆንም፣ ለሀገራችን የፋሽን ኩራት ዋልታ እንቁም።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 29 ቀን 2017 ዓ.ም