
የዛሬዋ የስኬት እንግዳችን ወይዘሮ ሳራ ሃሰን ይባላሉ። በተለያዩ ድርጅቶች ውስጥ የአክሲዮን ባለድርሻ እንዲሁም አመራር ሆነው ይሰራሉ፤ ከዚህ በተጨማሪም በበርካታ መንግስታዊና የግል ተቋማት ውስጥ በቦርድ አባልነትና አመራርነት ያገለግላሉ።
በአሁኑ ወቅት እየሰሩባቸው ካሉ ተቋማት መካከልም የሰበታ አግሮ ኢንዱስትሪና የናብሎ አስመጪና ላኪ ድርጅት፣ በሪልስቴት ዘርፍ የተሰማራው አፍሪካን ሆልዲንግ ኩባንያ ይጠቀሳሉ።
የተወለዱት በምስራቅ ኢትዮጵያ ደደር ከተማ ሲሆን፣ እድሚያቸው ለትምህርት እንደ ደረሰ ግን መላ ቤተሰባቸው ወደ ድሬደዋ በመግባቱ የቅድመ መደበኛና አንደኛ ትምህርታቸውን በምስራቋ የፍቅር ከተማ ድሬዳዋ ነው የተከታተሉት።
የድሬዳዋ ቆይታቸውም በቤተሰቦቻው የሥራ ባህሪ ምክንያት አልዘለቀም፤ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ከሁለተኛ እስከ ዘጠነኛ ክፍል በአሳይ የህዝብ ትምህርት ቤትና በቦሌ መሰናዶ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል።
ከአስረኛ ክፍል አንስቶ ያለውን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ የተማሩት ነፃ የትምህርት እድል በማግኘታቸው በአሜሪካ ኒዮርክ ከተማ ነው። በአሜሪካም ብዙ ሳይቆዩ ኑሯቸውን ካናዳ ሞንትሪያል ግዛት አደረጉና በጌጣጌጥ ዲዛይን ሥራ ሰለጠኑ። ለአንድ ዓመት ያህል በሰለጠኑበት ትምህርት ከሠሩ በኋላ ዳግም ወደ ትምህርት ዓለም ተመልሰው የፋርማሲስት ትምህርት ለማጥናት ዩኒቨርሲቲ ገቡ።
በመካከል ግን ወደ ትዳር መግባት የግድ ሆነና ትምህርታቸውን ለማቋረጥ ተገደዱ፤ የልጆች እናት ቢሆኑም አብረዋቸው ለነበሩት ወላጅ እናታቸው የልጆቻቸውን ኃላፊነት በመተው ያቋረጡትን ትምህርት ቀጠሉ። ጎን ለጎን በትርፍ ሰዓታቸው እየሠሩ ዲግሪያቸውን ያዙ። በዚህም አልተወሰኑም፤ ተጨማሪ ዲግሪ በሳይኮሎጂ ትምህርት ለመያዝ ቻሉ።
እንግዳችን እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ልጅ ዶክተር ወይም ኢንጅነር የመሆን ህልም ነበራቸው። በምህንድስናው ዘርፍ ተሰማርተው ለሀገራቸው ስልጣኔ ወሳኝ ሚና በመጫወት አንቱ መባል የዘወትር መሻታቸው እንደነበር ያስታውሳሉ።
ወይዘሮ ሳራ ምንም እንኳን እንዳሰቡት ዶክተር ወይም ኢንጅነር መሆን ባይችሉም በጌጣጌጥና ፋርማሲ ትምህርቶች በቀሰሙት እውቀት ስኬታማ ለመሆን ቆርጠው ተነሱ። በካናዳ በሚገኙ የጤና ተቋማት ላይ ጥሩ እየተከፈላቸው የመሥራት እድል ቢኖራቸውም፤ ወደ ሀገር ቤት በመመለስ ለወገናቸው መሥራት የቀን ተቀን ህልማቸው ሆነ። በተለይ ደግሞ እንደ እናት ያሳደጓቸውን እህታቸውን የማገዝ ጉጉቱ ስለነበራቸው ከመላ ቤተሰባቸው ጋር ጓዛቸውን ሸክፈው ወደ እናት ሀገራቸው ተመለሱ።
በአሁኑ ወቅት ሰበታ አግሮ ኢንዱስትሪን በምክትል ፕሬዚዳንትነት ይመራሉ። ‹‹እኔ ከውጭ ስመለስ እህቴ ማማ ወተት ድርጅትን ከፍታ ስለጠበቀችኝ እሷን ለማገዝና ለፍታ እንዳሳደገችኝ የልፋቷን ዋጋ መክፈል አለብኝ ብዬ ነው ድርጅቱን የተቀላቀልኩት›› የሚሉት ወይዘሮ ሳራ፤ የድርጅታቸውን ሼር በማግኘት አሠራሩን ወደ ማዘመንና ምርታማነቱን ወደ ማሳደግ መግባታቸውን ይጠቅሳሉ።
ድርጅቱን የመምራት ኃላፊነትን ከእህታቸው ከተረከቡት እለት ጀምሮ ላለፉት 17 ዓመታት በተለይ የማማ ወተት ምርታማነትን ከማሳደግና ጥራቱንና ደረጃውን ጠብቆ ተደራሽ እንዲሆን በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ጥረት አድርጌያለሁ ብለው እንደሚያምኑ ይናገራሉ።
የድርጅቱን አጠቃላይ አሠራር ከማዘመንና ከማስፋፋት ባሻገር የአውሮፓና አሜሪካ የወተት ቴክሎጂዎችን በማስመጣት ለሕብረተሰቡ ጤናማና ጥራቱን የጠበቀ ወተት ለማቅረብ ብዙ ሠርተዋል። ከዚህ ውስጥ ደግሞ አዳዲስ የማሸጊያ (ፓኬጂንግ) ቴክሎጂዎችን በማስመጣት ደንበኞቻቸውን ለመሳብ የሚያከናውኑት ተግባር ወሳኝ ለውጥ እያመጣላቸው ይገኛል። በተለይም ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የወተት ጥራት መፈተሻ ላብራቶሪ ማቋቋማቸው ከድርጅቱ አልፎ እንደ ሀገር ላሉ የወተት አግሮ ኢንዱስትሪዎች አገልግሎት መስጠት የሚችል በማድረግ ተጠቃሽ ሥራ መሥራታቸው ይገለጻል።
ይህንን ተከትሎ ሰበታ አግሮ ኢንዱስትሪ ዘንድ ዓለምአቀፍ የጥራት ሥራ አመራር እና ዓለምአቀፍ የምግብ ደህንነት ሥርዓት እንዲሁም ያፈራቸውን አሠራሮች ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ እና የሌሎች ሀገራትን ልምድ እና ተሞክሮ በመቅሰም በ2017 ዓ.ም የምርት እና አገልግሎቱን ጥራት ለማስጠበቅ ዓለምአቀፍ የጥራት ሥራ አመራር እና የምግብ ደህንነት ሥርዓት /food safety and Quality Management system/ እንዲሁም የፋይናንስ ሥርአቱን ለማዘመን እና ህጋዊ አሠራሮችን ወጥ በሆነ መልኩ ለመተግበር /Enterprise Resource Planning (ERP)/ ሲስተሞችን በመተግበር ረገድ ላከናወነው ተግባር የወይዘሮ ሳራ ሚና የላቀውን ድርሻ ይይዛል። ድርጅቱ እነዚህን ሁለት ዓለም አቀፍ የጥራት አሠራር ሥርአቶች በመዘርጋቱ ከሰሞኑ ከኢትዮጵያ ተስማሚነት እና ምዘና ድርጅት የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት ማግኘት ችሏል።
በሌላ በኩልም ከመኖ ዋጋ መወደድ ጋር ተያይዞ ድርጅቱ ላሞችን በስፋት ከማርባት ይልቅ ከአርሶ/ አርብቶ አደሮች ወተት እየተረከበ ጥራቱን በመፈተሽና በማቀነባበር የገበያ ተደራሽነቱን ለማስፋት እያከናወነ ባለው ተግባር እሳቸው ወሳኝ ሚና ተጫውተዋል።
ከዚሁ ጎን ለጎን በድርጅቱ የእንስሳት ማዳቀያ ማዕከል በመገንባት የላሞቻቸውን የወተት ምርታማነት ለማሳደግ እንዲሁም ማዕከሉን ኮርማዎች ለአድላቢዎችና ለአርሶአደሩ በመሸጥ ምርታማነት ላይ ሀገራዊ ፋይዳ ያለው ሥራ እያከናወነ ባለው ተግባርም የእሳቸው ሚና ከፍተኛ ነው ብለው እንደሚያስቡም ይገልጻሉ።
ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሚያደርገውን የእውቅና ሰርተፍኬት ማግኘቱ ምርቱን ወደ ውጭ በመላክ ለሀገር የውጭ ምንዛሬ የማስገባት እድል እንዳለው ጠቅሰው፣ በቅድሚያ የሀገር ውስጥ ያለውን ሰፊ ፍላጎት ለማርካት ትኩረት አድርጎ እንደሚሠራ ወይዘሮ ሳራ ይናገራሉ።
እሳቸው እንዳሉት፤ በአሁኑ ወቅት ሰበታ አግሮ ኢንዱስትሪ ( ማማ ወተት) በቀን ከ150 ሺ ሊትር በላይ ወተት እና የወተት ተዋፅኦ ምርቶችን የማቀነባብር አቅም ያለው ሲሆን፣ ከ400 በላይ ለሚሆኑ ቋሚ ሠራተኞች የሥራ እድል እና ከ50 ሺ በላይ ለሚሆኑ አርብቶ/ አርሶ አደሮች የገበያ ትስስር ፈጥሯል። በቀጣይም በዘርፍ ተጨማሪ ኢንቨስትመንቶችን በማድረግ ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር እየሠራ ይገኛል።
የስኬት እንግዳችን በወተት ኃብት ልማት ሥራ ላይ ብቻ አልተወሰኑም። ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ ደግሞ ከአራት አጋሮቻቸው ጋር በመሆን ‹‹ናብሎ›› የተባለ አስመጪና ላኪ ድርጅት ከፍተው እየሠሩ ናቸው። ይህም ድርጅት ከ40 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል ፈጥሯል። አስመጪና ላኪ ድርጅቱ የጥራጥሬና ቅባት እህሎችን እንዲሁም ምርጥ ዘር ወደ ውጭ በመላክ ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ግኝት አስተዋፅኦ እያበረከተም ነው። ከዚህ ባሻገርም መድኃኒት ከውጭ የሚያስመጣና የህክምና መሳሪያዎችን የሚያመርቱ ሁለት ድርጅቶችን አክሲዮን ገዝተው እየሠሩም ይገኛሉ።
ወይዘሮ ሳራ በሰበታ አግሮ ኢንዱስትሪም ሆነ ከሌሎች አጋሮች ጋር በሚሠሩባቸው ተቋማት ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን በመወጣት ረገድ በአርአያነት ይጠቀሳሉ። ሁሉም ድርጅቶቻቸው በመንግሥትም ሆነ በማህበረሰቡ ለእርዳታ ድጋፍ በተጠየቁ ቁጥር ቀድመው ይደርሳሉ።
ድርጅቶቹ ባሉባቸው አካባቢዎች የሚገኙ አቅመ ደካሞችንም በመደገፍ ረገድ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እያበረከቱ ናቸው። ልበ ሩህሩህና ታታሪ ሠራተኛ ስለመሆናቸው በተለያዩ አካላት የሚጠቀሱት እንግዳችን፣ ከዚህም በላይ በተለያዩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና የሙያ ማህበራት ላይ በቦርድ አባልነት በመሥራትም ስማቸው ይጠቀሳል።
ከእነዚህም መካከል የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የቦርድ ሥራ አስፈፃሚነታቸው በዋነኝነት ይጠቀሳል፤ በፌዴሬሽኑም ለአራት ዓመታት አገልግለው በቅርቡ ደግሞ ለተጨማሪ አራት ዓመታት እንዲያገለግሉ ተመርጠዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ ተገንብቶ በቅርቡ ወደ ሥራ የገባው የነገዋ የሴቶች ተሃድሶና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል የቦርድ አመራር ሆነው እየሰሩም ይገኛሉ። ማእከሉ የመጀመሪያ ዙር ሰልጣኞችን ሲያስመርቅ በገቡት ቃል መሰረት 16 ሰልጣኞችን በኃላፊነት በመረከብ፤ መኖሪያ ቤት ተከራይተውና በተሰጣቸው ሼድ መሳሪያዎችን ሁሉ በግላቸው ወጪ በማውጣት በጨርቃ ጨርቅ ስፌት ሥራ ላይ እንዲሰማሩ በማገዝ ትልቅ ሥራ እየሠሩ ይገኛሉ።
ይህም ብቻ ሳይሆን ለሰልጣኖቹ የገበያ ትስስር በመፍጠር ያለስጋት እንዲያመርቱና ተጠቃሚነታቸውን እንዲያጎለብቱ በማድረግ ለሀገር አኩሪ አስተዋፅኦ እያበረከቱ ናቸው።
ድጋፋቸውን በተጠየቁበት ቦታ ሁሉ እውቀታ ቸውን፤ ጉልበታቸውንና ገንዘባቸውን በመስጠት የሚታወቁት ወይዘሮ ሳራ፤ ከተጠቀሱት ተቋማት በተጨማሪ ከሶስት ሺ በላይ አባል ያሉትና በመዲናዋ በሪል ስቴት ዘርፍ ላይ ተሰማርቶ የሚገኘው አፍሪካን ሆልዲንግ ኩባንያም የቦርድ ሰብሳቢ ሆነው እየመሩ ይገኛሉ።
ይህም ድርጅት ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል እየፈጠረ ያለ ተቋም ሲሆን፣ በተለይ እንጦጦ ላይ ቅጠል ለቅመው ይተዳደሩ የነበሩ 100 እናቶች እንጀራ ጋግረው እንዲያከፋፍሉና የባልትና ውጤቶችን እንዲያመርቱ የሥራ እድል ፈጥሮላቸዋል።
ወይዘሮ ሳባ በተመሳሳይ በቅርቡ ደግሞ የኦሮሚያ ዲያስፖራ ማህበር የቦርድ አባል እንዲሁም የኢትዮጵያ ሴት ነጋዴዎች ማህበር ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ተመርጠዋል።
በሀገር ወዳድነታቸው የሚታወቁት ወይዘሮ ሳባ፣ አዋጭና ጠቃሚ ነው ባሉት የንግድ መስክም ሆነ የበጎ አድራጎት ሥራ ላይ ሁሉ በጋራ መሥራትን ይመርጣሉ። ምክንያታቸው ደግሞ በጋራ መሥራት ውጤታማ ያደርጋል የሚል ነው። አንዱ የሌላውን ክፍተት በመሙላት ትልቅ ደረጃ መድረስ ይቻላል ብለው ስለሚያምኑ እንደሆነ ይገልጻሉ።
‹‹የጋራ ሥራ ምንም እንኳን ይዞት የሚያመጣው የራሱ ችግር ቢኖረውም፤ በግሌ ግን አንድ ተቋም ብቻዬን ከፍቼ ብሠራና አጋር ባይኖረኝ ኖሮ አንድ ቦታ ተወስኜ ስለምቀር ለሀገር ማበርከት ያለብኝን አስተዋፅኦ እንዳላበረክት ያደርገኝ ነበር›› ይላሉ። የጋራ ሥራ ከሌሎች እውቀትና ልምድን በመቅሰም የተሻለ በመሥራት ውጤታማ እንዲሆኑ እንዳደረጋቸውም ተናግረዋል።
ወይዘሮ ሳራ በጋራ የሚሠሩባቸውን የቢዝነስ ተቋማት የማስፋት ፍላጎት እንዳላቸውም ጠቁመዋል። በተለይም ሰበታ አግሮ ኢንዱስትሪ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆን ለማድረግ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
በሌሎች አዳዲስ የሥራ መስኮች ላይ ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸው ሲሆን፣ በዋናነት ከውጭ የሚመጡ የኢንዱስትሪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርቶች በመተካት እንዲሁም ምርቶቹን ወደ ውጭ በመላክ ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት ወሳኝ ሚና ለመጫወት አቅደዋል።
‹‹ኢትዮጵያ የብዙ ወጣቶች እናት ናት›› የሚሉት እንግዳችን፤ በተለይ መሥራት የሚችለው የሰው ኃይል ቁጥር ከፍተኛ እንደመሆኑ ይህንን የሚመጥን የሥራ እድል መፍጠር ከመንግሥትም ሆነ ከግሉ ዘርፍ ይጠበቃል ሲሉም አስታውቀዋል።
ከዚሁ ጎን ለጎን ግን ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል በአንድ ሙያ ከመወሰን ይልቅ አዋጭ በሆኑ ዘርፎች ላይ በመሰማራት ከጠባቂነት አስተሳሰብ ሊወጣ እንደሚገባ ያስገነዝባሉ። ‹‹በተለይም ጊዜው የቴክኖሎጂ እንደመሆኑ በእጃቸው ባለስልክ በመጠቀም የገቢ ማስገኛ ሥራዎችን መሥራት ይገባቸዋል›› በማለት ምክራቸውን ለግሰዋል።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 22 ቀን 2017 ዓ.ም