‹‹ኢትዮጵያ ወደ ቻይና እና ሞንጎሊያ የተቀቀለ ሥጋ መላክ መጀመሯ ትልቅ ስኬት ነው›› – አምባሳደር ድሪባ ኩማ የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር

አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ካከናወነቻቸው ተግባራት ውስጥ አንዱና ትልቅ ስኬት ነው የተባለለት ወደ ቻይና እና ሞንጎሊያ ጥራቱና ደኅንነቱ የተረጋገጠ የተቀቀለ ሥጋ መላክ መጀመሯ ነው ሲሉ የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ድሪባ ኩማ አስታወቁ፡፡ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ከሚሌ ኳራንታይን 400 ሺህ የቁም እንስሳት ጤንነታቸው ተረጋግጦ በባለሥልጣኑ ሰርተፍኬት ወደ ውጭ ሀገር በመላክ ከ28 ሚሊዮን ዶላር በላይ መገኘቱን አመለከቱ፡፡

አምባሳደር ድሪባ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳስታወቁት፤ ባለሥልጣኑ፣ ከግብርና ሚኒስቴር እና ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጋር የ2017 በጀት ዓመት የስድስት ወር ግምገማ እንዳመለከተው ከያዛቸው እቅዶች 96 በመቶውን ማሳካት ችሏል። ከእነዚህ ሥራዎች ውስጥ አንዱና ትልቁ ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ጥራቱና እና ደኅንነቱ የተጠበቀ የተቀቀለ ሥጋወደ ቻይና መላክ መጀመሯ ተጠቃሽ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የተቀቀለ ሥጋ ወደ ቻይና ብቻ ሳይሆን ወደ ሞንጎሊያም መላክ ጀምራለች ብለዋል፡፡

አምባሳደር ድሪባ፣ ትልቁ ስኬት ነው ብለን የምንለው የሥጋ ምርታችን ወደ ቻይና እንዲገባ ማድረግ መቻላችን ነው፡፡ ከዚሁ ከሥጋ ምርት ጋር በተያያዘ የቻይና ኤክስፐርቶች ወደ ሀገራችን መጥተውና ያለውን ሁኔታ አይተው ማስተካከል የሚገባንን ምክረ ሃሳብ ሰጥተውናል ብለዋል፡፡

“እኛ ደግሞ ቻይና በምትፈልገው የሥጋ ንግድ ሥርዓት መሠረት በመቃኘታችን ቻይናውያን ተቀብለው ውል መፈራረም ችለናል፤ በመሆኑም በአሁኑ ጊዜ ሥጋ ወደ ቻይና መግባት ጀምሯል” ሲሉ ገልጸዋል፡፡

እርሳቸው እንደተናገሩት፤ የተቀቀለ ሥጋ ወደ ቻይና ብቻ ሳይሆን ወደ ሞንጎሊያም መላክ ተጀምሯል፡፡ ከዚህ በፊት ኢትዮጵያ የምትልከው ዓረብ ሀገር ብቻ ነው፡፡ ወደ ቻይና መላክ የተጀመረው በዚህ ዓመት ነው፡፡

የኢትዮጵያን ንግድ ከደኅንነትና ከጥራት አኳያ ለማገዝ የሚከናወን ሥራ መኖሩን ጠቁመው፣ እነዚህ በስድስት ወራት ውስጥ ከተሳኩ ትልልቅ ሥራዎች ውስጥ የሚጠቀሱ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ሌላው ሚሌ ላይ በተከፈተው ኳራንታይን ከ400 ሺህ ከብቶች በላይ ወደ ውጭ ሀገር በመላክ ከ28 ሚሊዮን ዶላር በላይ ማግኘት መቻሉን አምባሳደር ድሪባ ተናግረዋል፡፡

ይህ ኳራንቲን 400 ሺህ እንስሳት ወደ ውጭ ሀገር የተላከው ለመጀመሪያ ጊዜ ዘንድሮ መሆኑን አመልክተው፣ ከዚህ በፊት የቁም እንስሳቱ ወደ ውጭ ሀገር ይወጡ የነበረው በኮንትሮባንድ መሆኑን ጠቅሰዋል። በአሁኑ ጊዜ ግን የሚሌ ኳራንታይን በመኖሩ ትልቅ ሥራ መሥራት አስችሎናል ሲሉም አስረድተዋል፡፡

እርሳቸው እንዳሉት፤ 400 ሺህ የቁም እንስሳት መዳረሻቸው አብዛኞቹ ዓረብ ሀገራት ነው፡፡ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ እንዲሁም ወደ ጅቡቲም ጭምር ኤክስፖርት የተደረጉ ናቸው፡፡ በአብዛኛው የኢትዮጵያ ከብቶች እስከ ሳዑዲና ኦማን ድረስ ይዘልቃሉ፡፡

በአጠቃላይ የኢትዮጵያን ድንበር አቋርጠው በሕጋዊ መንገድ እንዲወጡና ለኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ እንዲያስገኙ የተደረጉት ከ400 ሺህ በላይ ከብቶች መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

በሕገ ወጥ የመጓጓዙ ነገር ቀርቷል ማለት ሳይሆን፤ ሙሉ በሙሉ አለመቀረፉ ልብ ሊባል ይገባል ያሉት አምባሳደሩ፤ የኮንትሮባንዱ ፈተና አሁንም አለ፡፡ በእርግጥ የእኛ ሥራ የሕገ ወጥ ንግዱ ላይ ሳይሆን፤ የጥራት ቁጥጥር ላይ ነው ሲሉ ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡

እንደ አምባሳደሩ ገለጻ፤ ባለፈው ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ በሚሌ ኳራንታይን ሥራ የጀመርንበት ጊዜ ነው፡፡ ዓመቱን ሙሉ 300 ሺህ ያህል ከብቶችን ወደ ውጭ ልከን በዓመቱ መጨረሻ የተገኘው 18 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን፣ ዘንድሮ ግን ገና በግማሽ ዓመቱ ከ400 ሺህ በላይ ከብቶች ተልከው ከ28 ሚሊዮን ዶላር በላይ ተገኝቷል፡፡

ይህ ለውጥ የመጣው ከውጭ ምንዛሪ ማሻሻያው ጋር ተከትሎ መሆኑን ጠቁመው፤ ከሁሉ በላይ ደግሞ የሚሌ ኳራንታይን መከፈቱ እንስሳቱ ታክመውና ጤንነታቸው ተረጋግጦ በኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን ሰርተፍኬት ድንበር አቋርጠው እንዲወጡ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት፡፡

እንደ አምባሳደሩ ገለጻ፤ የእንስሳት ንግዱ አሁን ሥርዓት እየያዘ ነው፡፡ ነገር ግን አሁንም ብዙ ክፍተት አለ፡፡ በሕገ ወጥ መንገድ በኬንያም በሱማሌም የሚወጡ አሉ፡፡ በመሆኑም የእንስሳት ንግዱ የበለጠ ሥርዓት እንዲይዝ በአሁኑ ጊዜ ኳራንታይኖች እያስገነባን እንገኛለን፡፡ በሀገሪቱ ወሳኝ በሚባሉ ቦታዎች አስገንብተን ከዚህ በኋላ በሙሉ በኳራንታይን እንዲወጡ እናደርጋለን ብለዋል፡፡

ከተገነቡ ኳራንታይን ውስጥ አንዱ የሚሌው ሲሆን፣ በግብርና ሚኒስቴር አማካኝነት ጅግጂጋ የተገነባው፣ ዘንድሮ ወደ እኛ ካስተላለፈ ተቀብለን አገልግሎት እንጀምራለን፡፡ በሞያሌ በኩልም የኳራንታይን ግንባታ እናስጀምራለን ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን ከተቋቋመ ሦስት ዓመት ሞልቶታል ያሉት አምባሳደር ድሪባ፤ ከተሰጡት ተልዕኮዎች መካከልም ሁሉንም የግብርና ግብዓት ጥራት እና ደኅንነትን መቆጣጠር እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን  መጋቢት 27 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You