
ደቡብ ሱዳን በሌላ የአፍሪካ ሀገር ዜጋ ምክንያት ዜጎቿ የአሜሪካ ቪዛ መከልከላቸውን ቅሬታዋን ገለጸች። የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላዲ ማርኮ ሩቢዮ ደቡብ ሱዳናውያን ቪዛ እንደሚከለከሉ አስታውቀዋል። ውሳኔውን ያሳለፉት ደቡብ ሱዳን ከአሜሪካ የተባረሩ ዜጎቿን አልቀበልም ብላለች በሚል ነው። ወደ ደቡብ ሱዳን መንግሥት በበኩሉ ከአሜሪካ የተላከው ሰው የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ዜጋ በመሆኑ ምክንያት ግለሰቡን አለመቀበሉን የደቡብ ሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።” ግለሰቡ ለተጨማሪ ምርመራ ወደተላከበት ሀገር ተመልሷል” ሲልም አስታውቋል።
ዶናልድ ትራምፕ መልሰው ሥልጣን ከያዙ በኋላ አሜሪካ ቪዛ በመከልከል የአንድን ሀገር ዜጎች ባጠቃላይ ዒላማ ስታደርግ ይህ የመጀመሪያው ነው። ትራምፕ ስደተኞችን በጅምላ እንደሚመልሱ ሲዝቱ ቆይተዋል። የደቡብ ሱዳን ዜጎች በአጠቃላይ አሜሪካ እንዳይገቡም የሚታገዱ ይሆናል።
አሜሪካ ያባረረችውን ግለሰብ ደቡብ ሱዳን ባለመቀበሏ ማርኮ ሩቢዮ የደቡብ ሱዳንን የሽግግር መንግሥት ወቅሰዋል።”የሚተባበሩ ከሆነ በቀጣይ ውሳኔው ሊቀለበስ ይችላል” ብለዋል። ደቡብ ሱዳን ግን የሀገሯ ዜጋ ባልሆነ ሰው ምክንያት የጅምላ ውሳኔ መተላለፉን ተቃውማለች። ግለሰቡ ኮንጓዊ መሆኑን የሚያሳይ መረጃ ለአሜሪካ መላኩም ተገልጿል።
የደቡብ ሱዳን የማስታወቂያ ሚኒስትር ማይክል ማኩይ ሉት፣ ለኤፒ እንደገለጹት አሜሪካ “በውጥረት ውስጥ ሳለን ስህተት ለማግኘት እየሞከረች ነው”። የደቡብ ሱዳን የመጀመሪያ ምክትል ፕሬዚዳንት ሪክ ማቻር በቁም እስር መዋላቸውን ተክሎ ደቡብ ሱዳን ዳግመኛ ወደ እስር በእርስ ጦርነት እንዳትገባ ስጋት አለ። ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር፣ ሪክ ማቻርን ነውጥ በማስነሳት ከሰዋል።
አሜሪካ ከአስቸኳይ ጊዜ ሠራተኞቿ ውጭ ያሉ ሠራተኞች ከደቡብ ሱዳን እንዲወጡ ባለፈው ወር ትዕዛዝ ሰጥታለች። ከዚህ ቀደም ደቡብ ሱዳናውያን በአሜሪካ ለተወሰነ ጊዜ የሚቆዩበት ፈቃድ እንደነበራቸው የዘገበው ቢቢሲ ነው።
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 1 ቀን 2017 ዓ.ም