የሴቶችን እኩልነት ባህል ማድረግ ለምን ተሳነን?

የሴቶችን እኩልነት ለማረጋገጥ፤ ለአመራርነት ማብቃት፤ የሀብት ማፍራትና ተጠቃሚነት እንዲሁም በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ሴቶች ብቁ እንዲሆኑና ወደፊት እንዲወጡ ሲባል በሀገርአቀፍ ደረጃ በርካታ ፖሊሲዎች፤ አዋጆች፤ ደንቦችና መመሪያዎች ወጥተዋል። በተለያዩ መንገዶችም ለመተግበር እየተሞከረ ይገኛል፡፡ በተሰራው ሥራም በአመራርነት ደረጃ ጥቂት ቢሆኑም ሴቶችን ማየት ተችሏል። በተለያዩ መስኮች በኃላፊነት ደረጃም እንዲሁ የሚታዩ እንቅስቃሴዎች አሉ። በፖለቲካው ዘርፍ የሴቶች ተሳትፎ ቢኖርም ያን ያክል የሚያኮራ አይደለም። በአጠቃላይ የሴቶች ተሳትፎ በማኅበራዊ፣ በፖለቲካውና በኢኮኖሚ ዘርፉ በታሰበው ልክ ጎልቶ አይታይም። ወደ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጎራ ሲባል ደግሞ ጭራሽ የሴቶች ተሳትፎ በጥያቄ ውስጥ ይሆናል።

የሴቶችን እኩልነት ማረጋገጥ፣ የሴቶች እኩል ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት እንዲኖር ይፈለጋል። አዋጆች መመሪያዎች ሁሉ ጸድቀዋል። በዚህ ዙሪያ ውይይቶች ይደረጋሉ። የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች ይካሄዳሉ። በተለይ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን ምክንያት ተደርጎ ሰፋፊ ሥራዎች ሁሉ ይሰራሉ። ሆኖም ግን ውጤቱ የታሰበውን ያህል አይደለም። ለምን የሚለው ጥያቄ ደግሞ ምላሽ ማግኘት አለበትና ዛሬ ይሄንን ርዕሰ ጉዳይ በማንሳት ከተለያዩ የሥራ ኃላፊ ሴቶች ጋር መወያየት መርጠናል።

የሴቶችን እኩልነት ማረጋገጥ በወረቀት ላይ መስፈሩና በንግግር በየአዳራሹ ከማንሳት ባለፈ በሚፈለገው ልክ ተግባራዊ ሆናል፤ ሴቶች እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ ሆነዋል ብሎ አፍ ሞልቶ መናገር አይቻልም። አሁንም ከንግግር አልፎ ባኅል ሆኖ በሥራ አልተተረጎመም፡፡ ለመሆኑ ችግሮቻቸውን የሚፈቱባቸው መንገዶችን ባኅል አድርጎ መቀጠሉ ለምን ከበደ የሚሉና መሰል ጥያቄዎችን በማንሳት በዘርፎች ላይ ከሚሰሩ ባለድርሻ አካላት ጋር ቆይታን አድርገናል፡፡

ወይዘሮ ዮሀናን ረታ ይባላሉ፡፡ የጎልደን ስታር ኮሌጅ፤ የጎልደን ብሪጅ ሥልጠናና ማማከር ድርጅት ባለቤትና ሥራ አስፈጻሚ እንዲሁም የአፍሪካ ሄርቴጅ ሴንተር በካናዳ ግሎባል አምባሳደርና በሴቶች ዙሪያ የተለያዩ ጥናትና ምርምሮችን የሚያደርጉ ባለሙያ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ የሴቶችን መብት ለማስጠበቅና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ፖሊሲዎችን ከመቅረጽ፤ አዋጆችን ከማውጣትና ደንቦችና መመሪያዎችን እንዲተገበርና መመሪያ ከመቅረጽ አንጻር ክፍተቶች አሉ ለማለት እንደሚቸገሩ ይናጋራሉ፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ነገሮች ከሞላ ጎደል በበቂ ሁኔታ ለሴቶች ተጠቃሚነትና ተሳታፊነት ጥሩ ተደርገው ተዘጋጅተዋል፡፡ ዋናው ችግር የሚሆነው ባኅል አድርጎ ለለውጣቸው መሥራቱ ላይ ነው። በፖሊሲው፤ በአዋጁ፤ በደንቡና መመሪያው ልክ ትግበራው አይታይም። ይህ ደግሞ በተለያየ ምክንያት ተጽዕኖ ተፈጥሮበት እንደሆነ ያብራራሉ፡፡

እንደ እርሳቸው ሀሳብ፤ የመጀመሪያው እንደ ሀገር ያለው ለሴቶች የሚሰጠው ቦታ አናሳ መሆኑ ነው፡፡ ስለሴቶች ሲነሳ በአብዛኛው ያለው አመለካከት የተዛባ ሀሳብ የያዘ ነው፡፡ ሴት ልጅ ዋና ኃላፊነቷ ተደርጎ የሚወሰደው ልጆችን መንከባከብና በቤት ውስጥ ያሉ ሥራዎችን መስራት ነው፡፡ ወጥታ ሠርታ እንድትገባ ከቤተሰብ እስከ ማኅበረሰብ አይፈቅድላትም፡፡ መሻሻሎች ቢኖሩም በራሷ ተማምና ወጥታ ሰርታ እየገባች ከሆነ ደግሞ የተለያዩ ቅጽል ስሞች ጭምር ይወጣላታል፡፡ ለአብነት በሥራ ምክንያት አምሽታ ስትገባ ወንዱ ምንም ሳይሰራ እየጠበቃት እርሷ ‹‹ወንዷ የቤት ውስጥ ሥራ ለማን ትተሸ ቆየሽ›› እና መሰል ቁጣ ይጠብቃታል፡፡ በዚህም የራሷን አሻራ በማኅበራዊው ዘርፍ፤ በኢኮኖሚና ፖለቲካዊ መስክ እንድትሳተፍ እድሎችን ማንም አይሰጣትም፡፡

ባህል የሚያድገው ዘወትር በሚነገረንና እየኖርነው በምንሄደው ነገር ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ለሴቷ የሚነገራት እንደማትችል፤ የእርሷ ድርሻ ውስን እንደሆነና ለዚያውም ከቤት ውስጥ ያላለፈ እንደሆነ ነው፡፡ ማንኛውንም ሥራ ከእርሷ በላይ እንዳልሆነ አይነገራትም፡፡ ይህ የሚሆነው ለወንዱ ብቻ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በራስ የመተማመኗን ሁኔታ ይወስድባታል፤ ወጥታ እንዳትሰራ ይገድባታል። ትንሽ ስትፍጨረጨር ደግሞ የሚያሸማቅቁ ነገሮች ይበረቱባታል፡፡ ከዚያም አለፍ ሲል ኃላፊነቷን ለመቀማት የሚጣጣሩ አካላት ይበዛሉ፡፡ ስለዚህም አቅሙም ችሎታውም ቢኖራት ሊመራላት የሚችልና የሚረዳት ሰው በብዛት አለማግኘቷ በሁሉም ዘርፍ ላይ ልቃ እንዳትወጣ ይገድባታል። «አልችልም እንድትልም» ያደርጋታል ይላሉ።

ሁሌ የግዞት ኑሮ እንድትኖር በማኅበረሰቡ ዘንድ የተፈረደባት መሆኗ፤ የራሷ ገቢ እንዲኖራት እድሎች አለመመቻቸታቸው፤ ለማኅበረሰብ የሚተርፍ ሥራ እንዳትሰራ ያደረጓት ስለመሆናቸውም ወይዘሮ ዩሐና ይናገራሉ። እርደእርሳቸው ሀሳብ ነገሮችን ባህል አድርጎ ለመሄድና የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሴት ልጅ ማኩረፊያ እንኳን የሚሆን የራሷ የገቢ ምንጮች ሊኖራት ይገባል፡፡ በገቢዋ የተሻለች እንዳትሆን ባንኮች ሳይቀሩ አመኔታቸውን ሊሰጧት ያስፈልጋል፡፡

ለሴት ልጅ ብድር ማግኘት አዳጋች ነው። በማኅበረሰቡ ምልከታ ወንድ ከሆነ ሰርቶ ይመልሳል፤ ሴት ከሆነች ደግሞ ላትመልስ ትችላለች ይባላል። ይህ ደግሞ ብዙ ጊዜ ከተፈጥሮ ጋር ይተሳሰራል፡፡ ሴት ወልዳ ቤት ውስጥ ረጅም ጊዜ ስለምትቀመጥ ቢዝነሱን በሚፈለገው ደረጃ አታንቀሳቅሰውም፡፡ ስለዚህም ኪሳራ ይገጥመናል በሚል ሁሌም የቤት እመቤት ሆና እንድትቆይ ይፈረድባታል፡፡ ነገር ግን እየታየ ያለው ተቃራኒ መሆኑን መገንዘብ የቻሉት ጥቂቶች ናቸው፡፡ ማለትም ሴት በሥራ ቆራጥ ነች፡፡

ገና ባልጠነከረ አቅሟ ሳይቀር ሀቋን ላለመተው ትሰራለች፡፡ ብድርን የልጆቼ እዳ ሊሆን አይገባም በማለትም የማትቆፍረው ድንጋይ የለም፡፡ ነጻነቷን አውጃ ለልጆቼ የምትለው ቅርስ በማስቀመጥም ማንም አያክላትም። ሆኖም የተዛባው አመለካከት ግን ዛሬም ከችግሯ ሊያላቅቃት አልቻለም። በዚህም ነው የሴቶች ለውጥ በፖሊሲ ብቻ መምጣት አይችልም ባህል በማድረግም እንጂ የሚባለውም ሲሉ ያብራራሉ፡፡

ወይዘሮ ዮሐናን ሌላው የሴቶች ጉዳይ ባህል ሆኖ እንዳይቀጥል ያደረገው የማኅበረሰቡ ጫና እንደሆነ ያነሳሉ፡፡ ሴት ልጅ ከፍ ብላ ስትሄድ ለወንድ አትታዘዝም፤ የቤቱን ነገር ትተወዋለች፤ አላግባብ ትንጠራራለችና መሰል ነገሮች ትባላለች። ይህ ደግሞ በገቢ ብቻ ሳይሆን በትምህርት እንኳን እንዳትሻሻል የሚገድባት ነው፡፡ የተሻለች ሴትን ወንዶች ይፈሯታል። በዚህም ትዳር ጭምር ለመያዝ ትቸገራለች፡ ምክንያቱ ደግሞ ብዙ ጊዜ በገንዘብ ትጫነኛለች፤ ውጪ ውጪ ስለምትል ቤቱን መምራት አትችልም የሚል ስጋት ስለሚያድርባቸው ነው፡፡ ከዚያ ባሻገርም ቤተሰብ ሳይቀር አግብታ እንኳን ቢሆን ትቅርብህ ይባላል። እናም በእነዚህና መሰል ምክንያቶች ሳቢያ ሁሌ አንዲት ሴት ከፍ ማለት አትችልም፡፡ ዝቅ ካለች ግን ትክክለኛ ቦታ ላይ እንዳለች ይነገራታል፡፡

ሴት ልጅ ለከፍተኛ ስልጣን ስትታጭ እና ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሳ መስራት ስትፈልግ አትችልም፤ ልጆቹን ማን ያሳድጋቸዋል፤ ቤተሰቧን በትና ለምን ትሄዳለችና መሰል ነገሮች ትባላለች፡፡ ወንድ ግን የትም ቢሆን ተዘዋውሮ እንዲሰራ ይፈቀድለታል፡፡ ይህ በማኅበረሰቡ ዘንድ ያለው የተዛባ አመለካከት አንዱ ሴትን ልጅ የገደባት ችግር መሆኑን ያነሳሉ፡፡

በወይዘሮ ዩሐና እሳቤ፤ ተፈጥሮ ሁለቱንም ጾታ ይለያቸዋል፡፡ ሴት ትወልዳለች በዚህም ድካም ይኖርባታል። እንደ ወንድ ጉልበታም ሆና ነገሮችን ማከናወን አትችልም፡፡ ወንድ ደግሞ ብልሃት የለውም። ነገሮችን ፊት ለፊት ተጋፍጦ በጉልበቱ ጭምር ማከናወንን ይመርጣል፡፡ ስለዚህም የሁለቱ ልዩነት ሥራን በአግባቡ ከመወጣት አንጻር ሳይሆን መታየት ያለበት ተፈጥሮ አንዱን ከአንዱ በምን ለይታዋለች በሚለው መሆን ይገበዋል፡፡ ከዚያ ውጪ ያሉ ነገሮች ሁለቱም በእኩል የሚከውኗቸውና እኩል ቢሰጣቸው የሚያስፈጽሟቸው ናቸው፡፡ እንደ ሀገር የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት ከሕግና መመሪያ ባሻገር ባህል ሆኖ ይተግበር የሚባለውም በሁለቱ መካከል ያለውን ክፍተት ለመሙላት ነው።

ወንድም ሆነ ሴት የየራሳቸው አቅም አላቸው። እኩልነታቸው ይረጋገጥ ሲባልም ሴት ላይ እስከዛሬ ከሚደርስባት ጫና አንጻር በተገቢው ሁኔታ ተሳታፊም ተጠቃሚም ስላልሆነች ነው፡፡ ይህ ግን በብዙዎች ዘንድ ሴቶች ሁሌ አንገታቸውን ደፍተው እንዲቀመጡ ነው የሚታሰበው፡፡ ታሳዝናለች እየተባለች እንድትቀጥል ብዙ ሰው ይፈልጋል፡፡ ስለሴቶች ሲነገርም ተቃውሞ በሚመስል መልኩ ‹‹ የሴቶች አቀንቃኝ›› የሚል ስያሜ ይሰጥና ስለ እነርሱ መናገራችንን እንድናቆም እንሆናለን። ‹‹ሴቷ መብቴ ነው›› ስትል በአሉታዊ አመለካከት እንድትሰበር በማድረግ መብቷን እንዳታስከብርና አቅሟን እንዳታሳይ ያደርጓታልም፡ በዚህ ምክንያትም ነው ዛሬ ላይ ብዙ ሴቶችን ወደፊት መጥተው የማናያቸው፡፡ እናም ባህል ይሁን ሲባል እነዚህን የተዛቡ ምልከታዎችን ለመፍታትም እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች፣ ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የሴቶች ተሳትፎ ማብቃትና ተጠቃሚነት ዳይሬክተር ወይዘሮ ስፍራሽ አልማውም በዚህ ጉዳይ ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ይሰጣሉ፡፡ እንደእርሳቸው ገለጻ፤ ሴቶችን በማብቃትና በማሳተፍ ዙሪያ ሀገር ብዙ እየሰራች ትገኛለች፡፡ ሆኖም ባህል አድርጎ መቀጠሉ ላይ ክፍተቶች ይታያሉ፡፡ አንዱ ችግር የሴቶች ሥራ ሰፊ መሆኑ ነው፡፡ ማለትም የውጪውን ሥራዋን አከናውና ብትገባም ቤት ውስጥ የሚጠብቃት ተጨማሪው ሥራ በርካታ ነው፡፡ ወንዶች የቤት ውስጥ ሥራን መጋራት አይፈልጉም። ከእነርሱ እኩል ብትገባም የቤቱ ሥራ የእርሷ ብቻ እንደሆነ ያስባሉ፡፡ እናም በድካም ላይ ድካም እየሆነባት ነገሮችን እንድታከናውን ትገደዳለች። ይህ ደግሞ ተስፋ አስቆራጭ ነገሮች እንዲያጋጥሟት ሊያደርጋት ይችላል፡ እናም የግንዛቤው ችግር በሀገር ውስጥ ያለውን የሴቶች ተጠቃሚነትና ተሳትፎ ባህል አድርጎ ለመቀጠል እንዳይቻል ገድቦታል።

ሌላው ለሴት ልጅ የሚሰጠው ማኅበራዊ ኃላፊነት በቤት ውስጥ ሥራ ተጠምዳ የቢሮ ሥራና የግል ሥራዋን እንዳታሳልጥ ማድረጉ ነው። ተፈላጊውን ሥራ በሚፈለገው ቀን እንዳታደርስ ይገድባታል። በዚህም ሴቶች አይችሉም የሚለው እሳቤ እንዲሰፋ ያደርገዋል። በተጨማሪም የፋይናንስ ሁኔታቸው የተገደበ ነው። ብድር ለመበደር እንኳን ንብረት ማስያዝ ግድ ይላቸዋል። እንደ ሀገር ያለው የንብረት ባለቤትነት ደግሞ በአብዛኛው በወንዶች እጅ በመሆኑ ፈቃድ የማግኘቱ ሁኔታ አዳጋች በመሆኑ የሚፈልጉት ላይ እንዳይደርሱ እንቅፋት ይሆንባቸዋል፡፡

ሴቶች በሥራቸው አካባቢ ጠንካራ ግንኙነት አለመኖራቸውም እንዲሁ ተጠቃሚነታቸውና ተሳትፏቸው ባህል ሆኖ እንዳይቀጥል የሚገድበው ነው፡፡ እንደ ልብ እንደወንዶች ሁሉ በሥራቸው ጉዳይ ዙሪያ ተቀራርበው መነጋገር አይችሉም። ከወንዶች ጋር ተቀምጠው ሲያወሩ በመጥፎ ሴትነት ይፈረጃሉ። አሊያም ጾታዊ ትንኮሳን ያስተናግዳሉ፡፡ ስለዚህም ከማንም ጋር ሳይነጋገሩ ብቻቸውን ወሳኝ፤ ብቻቸውን ሰሪና ለፊ ይሆናሉ። ይህ ደግሞ ውጤታማ ሊያደርጋቸው አይችልም፡፡ የሚያግዟቸው፤ የሚደግፏቸው ሰዎች ስለማይኖሩ ወደ ፊት ለመጓዝም ይከብዳቸዋል ይላሉ፡፡

ሴቶች በራሳቸው አቅማቸውን ያለማሳደግ ችግርም ከፍ ብለው እንዳይወጡና ጉዳያቸው ባህል ሆኖ እንዳይቀጥል ያደረገው እንደሆነ ወይዘሮ ስፍራሽ ጠቅሰው፤ ይህም በትምህርት፤ በሥራ ራሳቸውን ብቁ አድርገው አለመጓዛቸውና እችላለሁ ብሎ አለመቀበላቸው እንደሆነ ያብራራሉ። አክለውም በአመራር ብቃቷ ከወንዶች እሻላለሁ ብላ አለማሰቧ፤ ወንዶችም አትችልም ብለው ጫና ማሳረፋቸው ሴቶች ከፍ ብለው እንዳይወጡ የገደባቸው ነገር እንደሆነም ይገልጻሉ፡፡

እንደ ወይዘሮ ስፍራሽ ሀሳብ፤ ሴቶች ለራሳቸው ጊዜ አለመስጠታቸው፤ አቅም እንዳላቸው አለመቀበላቸውና፤ የሴቶችን እኩልነት አለማመናቸውም ሌላው ፈተና እንደሆነ ያነሳሉ። በተለይ ማኅበረሰቡ መርጧቸው አልችልም ብለው ኃላፊነትን መግፋታቸው የተሻሉ ሰዎች እንዳይወጡና በትልልቅ ኃላፊነቶች ላይ ወንዶች ብቻ እንዲቀመጡ መፍቀዳቸው ተሳትፏቸውና ተጠቃሚነታቸውን ከገደበው መካከል እንደሆነም ያስረዳሉ፡፡

ችግርን እንደ ችግር ተቀብሎ ለማለፍ አለመጣር፤ በቀላሉ ተስፋ መቁረጥና በምሬት ውስጥ መቆየትን መምረጣቸው ሴቶችን ባኅል አድርጎ ወደ ለውጥ ጎዳና ለማራመድ ያልተቻለበት አንዱ ተግዳሮት እንደሆነ የሚገልጹት ዳይሬክተሯ፤ ይህንን ለመፍታት የማበረታቻና የማትጊያ ተግባራት በብዛት መከናወን እንዳለባቸው፤ ተሞክሮዎች በስፋት መቅረብ እንደሚገባቸው፤ ሴት ልጅ ዙሪያ ያሉ የተሳሳቱ ትርክቶችን በመፍታት ዙሪያ የሚሰሩ ተግባራት መስፋት እንደሚያስፈልጋቸው ያነሳሉ። ከሁሉም በላይ ደግሞ ሴቶች ከራሳቸው የጀመሩ ሥራዎችን መስራት፤ ሴቶች የሚመካከሩባቸው መድረኮች ማስፋትና ማኅበረሰቡን በዚህ ዙሪያ ማንቃት እንደሚያስፈልግ ያስገነዝባሉ፡፡

ጽጌረዳ ጫንያለው

አዲስ ዘመን ማክሰኞ መጋቢት 9 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You