ለዓይነ ሥውራን ብርሃን

ዓይናማ ነች። ሩቅ ያሉትን አቅርባ መመልከት የምትወድ። በሥራ ውጤቶቿ ሌሎችም የምትተርፍ። ሃሳብን ወደ ትግባር ለመለወጥ የማትደክም። በእርሷ የእጅ ጥበቦች ሌሎች ሲያምሩና ሲዋቡ ይበልጥ የምትደሰት፤ ለበለጠ ሥራ የምትተጋ፤ መድከምና መሰልቸትን ከአጠገቧ ያራቃች፣ አካል ጉዳተኟነቷ ያልበገራት ሴት ናት ሜሮን ተስፋዬ። ሜሮን አካል ጉዳተኛ በመሆኗ የደረሰባትን እንግልትና ስቃይ ሌሎች አካል ጉዳተኞች እንዲኖሩት አትፈቅድም። ይህን አስተሳሰቧን ደግሞ በወሬ ሳይሆን በተግባር አስመስክራለች።

ሜሮን አካል ጉዳተኝነት ያገኛት ገና በልጅነቷ ነው። የነርቭ ችግር ነውና ዛሬ ድረስ ችግሩ አብሯት አለ። መሻሻሎች ቢኖሩትም አሁንም መናገር ያዳግታታል። እግሮቿም ቆመው ይራመዱ እንጂ እንደ ጤነኛ ሰው እንደ ልብ አያንቀሳቅሷትም። እጆቿም እንዲሁ እንደፈለጋት አታዛቸውም። በተለይም ቶሎ ቶሎ ለመጻፍ ያስቸግሯታል። በዚህም ምክንያት በርካታ ፈተናዎችን ለማለፍ ተገድዳለች። በተለይም ከትምህርት ጋር በተያያዘ በብዙ ተፈትናለች። ችግሯ የሚጀምረው የመጀመሪያ ደረጃ ማጠቃለያ ፈተና (ሚንስትሪ) ስትፈተን ነበር።

ለመጻፍ ያስቸግራታል። ስለዚህም ለፈተናው ተጨማሪ ሰዓት ከሌለ በስተቀር ሁሉንም አጥቁራ መጨረስ አትችልም። ሰዓት መጨመር ደግሞ በምንም መልኩ አይቻልም። እናም ሌላ አማራጮች መሻት የግድ ይላታል። በመሆኑም ሜሮን የመልስ መስጫ ሳጥኖችን ለማጥቆር የሚረዳትን ሰው ፍለጋ ገባች። አግኝታም ፈተናውን በመውሰድ 98 ነጥብ አግኝታ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ተሸጋገረች።

የሜሮን ሌላኛው ችግር ሀገር አቀፍ የ10ኛ ክፍል ፈተና ላይ የገጠማት ነበር። እዚህ እንዳለፈው የሚንስትሪ ፈተና የመልስ አጥቋሪ ረዳት ሰው ይዞ መግባት አይቻልም። በራስ አቅም ካልተፈተኑ በስተቀር ነገን ለማየት አይፈቅድላትም። ስለዚህ እችላለሁ ብላ ፈተናውን እንደምንም ሠርታ አጠናቃዋለች። ነገር ግን የትናንቱን እድሏን አላገኘችውም። ሁለት ነጥብ በማምጣቷ የመሰናዶ ትምህርትን መቀላቀልም አልቻለችም። ግን በሆነው ነገር አልተቆጨችም። ምክንያቱም የተሻለውን እንደምታገኝ ታምናለች። የምትፈልገውን እንደምትማርም እርግጠኛ ነች።

የሜሮን ቤተሰቦች ሜሮንን ሲያሳድጓት ሁሌም እችላለሁ ብላ ወደፊት እንድትጓዝ በማድረግ ነው። አካል ጉዳቷን በምንም መልኩ እያየች እንድትሸማቀቅ አላደረጓትም። ይልቁንም ሌሎች ልጆች የሚያደርጉትን ሁሉ እያከናወነች እንድታድግ አጠንክረዋታል። ይህ ደግሞ ጠንካራና ብርቱ ሴት አድርጓታል። በነገሮች ቶሎ ተስፋ የምትቆርጥ እንዳትሆንም አግዟታል። ከጉዳት አልባዎች እኩል ተራምዳ ሕይወቷን የምትመራ ሴትም እንድትሆን ረድቷታል። ዛሬ ላይ ቤተሰብ መስርታ ሁለት ልጆችን አፍርታ በተለያዩ ዘርፎች ላይ ተሰማርታ ደስተኛ የሆነ ኑሮን እንድትመራ የሆነችውም ከዚህ አንጻር ነው።

ሜሮንና ትምህርት ሲነሱ ሌላው ገጠመኙዋና የፈተናት ነገር መማር የምትሻው ትምህርት የጤና ትምህርት ቢሆንም እስከ መጨረሻው ልታሳካው የምትችልበት እድሎች አለማግኘቷ ነው። በርካታ ትምህርት ቤቶችን ብትጠይቅም አካል ጉዳተኛ በመሆኗ ሊቀበሏት አልቻሉም ነበር። በስንት ልፋትና ጥረት አንዱ ትምህርት ቤት ቢቀበላትም በዚያም እስከ ሦስት ወር ድረስ ብቻ ነው የተማረችው። አካል ጉዳተኛ መሆኗ ሲታወቅ ከትምህርት ክፍሉ እንድትባረር ተደረገች።

በወቅቱ እጅጉ ተከፍታ ነበር፤ ግን አልተሰበረችም። ይልቁንም ስንቋን እችላለሁ አድርጋ ወደፊት ተራመደች። ‹‹እልፍ ሲሉ እልፍ ይገኛል›› እንዲሉ ሆነና እንደ እርሷ ላሉ ብዙዎች ብርሃን ለመሆን የምትችልበትን የትምህርት መስክም መረጠች። ይህም የልዩ ፍላጎት ትምህርት ነበር። ከተወለደችበት ኤርትራ ከአደገችበት አክሱም ወጥታ ዓድዋ ላይ በመክተምም የዲፕሎማ ትምህርቷን አጠናቀቀች።

ሜሮን በማንም ጫንቃ ላይ ተደግፎ ነገሮችን ማከናወን አትፈልግም። ዘወትር ራሷን የምታወጣበትን መንገድ ትቀይሳለች። በትጋቷ የምታጣው ነገር እንደሌለም ታምናለች። እናም ዲፕሎማዋን እየተማረች ጎን ለጎን ለሁለት ዓመት ያህል አማካሪ በመሆን ሠርታለች። ጥንካሬ፤ ብርታትና ሁልጊዜ ወደፊት መጓዝን የምትመርጠው ሜሮን የመማር ጥማቷን ለማርካት ዲፕሎማዋን ይዛ በቀጥታ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ነበር ያመራችው። ዩኒቨርሲቲው ፈቃደኛ ይሁን አይሁን ሳታውቅ ‹‹ትምህርት እድል ልትሰጡኝ ይገባል›› በማለት ይመለከታቸዋል ያለቻቸውን ሁሉ ጠየቀች። ለማሳመንም መግባት ያለባት ሰው ጋር ሁሉ እየገባች በራቸውን አንኳኳች:: ግን በቀላሉ ሊቀበላት አልቻሉም። ረዘም ላለ ወራት ተመላለሰች።

በእርሷ ዘንድ ተስፋ መቁረጥ ቦታ የለውም። ስድብና አትችይም መባልም እንዲሁ ትኩረት አይሰጣቸውም። ምክንያቱም ያደገችው ትችያለሽ ተብላ ነው። እርሷም በኑሮዋ አልችልም ብላ የተወችውና ያላሳካችው ነገር የለም። ስለዚህም በተስፋ ከብዙ ጥረትና ወጣ ውረድ በኋላ የትምህርት እድሏን ራሳቸው አስመዝግበውና ሁኔታዎችን አመቻችተው ጠርተዋታል። ተምራም በከፍተኛ ውጤት ተመርቃለች።

ሜሮን ሁሌ እንደምታደርገው ማንንም ሳታስቸግር ትምህርቷን ለመከታተል ስትል ከትምህርቷ በተጓዳኝ ሶስቱንም ዓመታት በዚያው በዩኒቨርሲቲው ሥርዓተ ጾታ ቢሮ ውስጥ በአማካሪነት አገልግላለች። የምስራች በሚሰኝ ትምህርት ቤትም በብሬል ጽሑፍ ለአንድ ዓመት አስተምራለች።

ሁለተኛ ዲግሪዋን በዲላ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት መስኳን ሳትቀይር ተምራለች። ሜሮን፤ የብዙ አካል ጉዳተኛ ሴቶች የጥንካሬ ተምሳሌት ነች። ምክንያቱም ትምህርቷን በተግባር ያዋለች ለብዙዎች ብርሃንን የፈጠረች ሴት ነች። ሜሮን ለሥራዋ መነሻ የምታደርጋቸው ነገሮች የምትመለከታቸው ተግባራት ናቸው። ዓይኖቿ ሁሌ በሥራ ይጠመዳሉ። ያየችውን ደግሞ እጆቿ ይሠራሉ። ለዚህም የፈጠራ ውጤቶቿ ምስክር ናቸው።

የመጀመሪያው በትግራይ ውስጥ እያለች የሠራችው የፈጠራ ሥራ የዓይነ ሥውራን ጭንቀትና ኑሮን ለማሸነፍ የሚያደርጉትን ትግል በአየችበት ወቅት የሠራችው ነው። ነገሩ እንዲህ ነው። አንድ ዓይነ ሥውር በሆቴል ውስጥ አገልግሎት ለማግኘት ይገባል። ምግብ ማዘዝ ፈልጎ አስተናጋጅዋን ጠርቶ ያለውን ምግብ ምንነትና ዋጋ እንድታስረዳው ይጠይቃታል። እርሷ ግን በሥራ ብዛት ባትላ ነበርና ምላሽ አልሰጥህ አለችው። በዚህም አዕምሮው ያቀበለውን ምግብ አዝዞ ተመገበ። ሂሳቡን ለመክፈል ሲጠይቅ ግን ሂሳቡ ኪሱን የሚደፍር አልነበረም። የተጠየቀውን ገንዘብ በኪሱ አልያዘም። ስለዚህም አማራጩ ሞባይሉን አሲይዞ መውጣት ነበርና ይህንኑ አደረገ። ይህንን ያየችው ሜሮንም ወዲያውኑ አዕምሮዋ ውስጥ አንድ ነገር አስቀመጠች። ዓይነ ሥውራን በብሬል የምግብ ዝርዝሩ ቢዘጋጅ ኪሳቸው ያለውን ገንዘብ አውቀው ያዛሉ። ለምን ይህንን ማድረግ ተሳነን? በማለትም ለሥራው ተፋጠነች። ሜኑውንም በማዘጋጀት ለአካባቢው ዓይነ ሥውራን ደረሰች።

አዲስ አበባ ከመጣች በኋላ ደግሞ ይህ ሥራዋ ምን ያህል እንዳለ ለማወቅ አሰሳ አደረገች። ማንም አያውቀውም፤ አልተጠቀመበትምም። በጣም አዘነች። ምክንያቱም የአፍሪካ መዲና ዓለም አቀፍ መድረኮች የሚካሄዱባት ከተማ ሆና ሳለች አካል ጉዳተኛን ያመከለ ሥራ ግን ከትንሹ እንኳን አልታየባትም። እናም ሆቴሎቹን በማሳመን ከ11 በላይ ለሆኑ ትልልቅ ለሚባሉ ሆቴሉች ሜኑዋቸውን በብሬል አዘጋጀች። ይህ ደግሞ ለዓይነ ሥውራኑ ጥቅም ብቻ ሳይሆን ለሆቴሎቹ ደንበኞቻቸውን በአግባቡ ከመያዝ አልፎ የውጪ እንግዶችን በሀገር ውስጥ በማቆየት ከፍተኛ ገቢ እንዲያገኙ እንደሚያስችላቸውም ታምናለች።

ለሜሮን ሌላው ዓይኗ ያደረሳት ፈጠራ ለዓይነ ሥውራን የሚሆን ኮምፒውተር ላይ የሚለጠፍ ኪቦርድ ማዘጋጀት ነው። ይህንን ሥራ እንድታከናውን ያስገደዳት ደግሞ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ዓይነ ሥውራን አሳይመንት ለመሥራት ሲቸገሩ ማየቷ ነው። የዓይነ ሥውራን ችግር በእጅጉ የጸና ነበር። ኢንተርኔት መጠቀም አይችሉም፤ ቤተ መጻሕፍት ገብተው የሚያስፈልጋቸውን መጻፍ ማገላበጥና አንብበው መሥራትም እንዲሁ። ከዚያም የሚብሰው ደግሞ ጥያቄውን እንኳን ለማወቅ ሪከርድ ያደረጉትን ድምጽ ሰምተው ነው። ድምጽ ከፍተው ለማዳመጥ ደግሞ ቤተመጻሕፍት ውስጥ አይቻልም። በጆሮ ማዳመጫ ዘወትር መጠቀሙ ደግሞ ዓይናቸው ነውን ጆሯቸውን በሕመም ምክንያት ሊያሳጣቸው ይችላል። ስለሆነም ለዚህ ችግራቸው መፍትሔ ለመሆን ተነሳች። በኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት እውቅና የተሰጠው የኮምፒዩተር ኪይ ቦርድ ዓይነ ሥውር የሚለየው በብሬል የተዘጋጀ እና ኪቦርድ ላይ የሚለጠፍ ፈጠራ አወጣች።

‹‹ሜሮን አካል ጉዳተኝነት፤ ሴትነት በማህበረሰቡ ግንዛቤ ችግር ይገጥማቸዋል። ግለሰቡ አስተሳሰብ ልኬት ግን ይህንን መፍታት ይችላል። እኔ በርካታ ችግሮችን በሕይወቴ አሳልፋለሁ። ግን ችግር እንዲጥለኝ አልፈቅድለትም፤ አንብቼ መሄድም አልፈልግም። በዚህም ዘወትር ለራሴ አንድ ነገር እነግረዋለሁ። ‹ይህም ይታለፋል፤ ነገ ሌላ ቀን ነው፤ አዲስ ነገር ሠርቼ እስቅበታለሁ› እላለሁ። በዚህም ንዴቴ ከ40 ደቂቃ በላይ እንዲጓዝ አልፈቅድለትም። በሳቄ ለውጬ በደስታ ወደፊት እራመዳለሁ›› ስትልም ችግርን እንዴት መጋፈጥ እንደቻለችና እንዳለፈችው ታወሳለች።

ሜሮን ሴቶች ሁሌም ራሳቸውን ችለው መውጣት አለባቸው። የዚያን ጊዜ ቤተሰብም ሆነ ባለቤቷ ክብር ይሰጣታል፤ መውደድንም ወደራሷ ታመጣለች። በተለይም ባሌ ትቶኝ ሄደ አልሄደ የሚለውን ስጋቷን ለማስቀረት የራስ የሆነ ገቢ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው ትልና፤ ‹‹ እኔ አካል ጉዳተኛ ነኝ፤ ብዙዎች እንደሚያስቡት በባሌ ጫንቃ ላይ የምቀመጥ አይደለሁም። በየጊዜው አዳዲስ ነገሮችን እሞክራለሁ። በቋሚነት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሴቶችና ሕጻናት ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የሕፃናት ክትትልና ድጋፍ ባለሙያ ሆኜ እሠራለሁ። በዚያ ብቻ ታጥሮ መቅረትን አልሻም። ሽፎኖችን ራሴ ዲዛይን አድርጌ ሰፊ ቀጥሬ በተሻለ ጥራትና ዲዛይን አቀርባለሁ። በፈጠራ ሥራዬ ደግሞ ሜኑዎችን ለብዙ ትልልቅ ሆቴሎች ሠርቼአለሁ። አሁንም በኪቦርዴ አማካኝነት የሚሠራ ፕሪንተር ስለገዛሁ ማንኛውንም ጽሑፍ ለዓይነ ሥውራን በሚሆን መልኩ ማዘጋጀት እችላለሁ። በዚህ አጋጣሚ በሁሉም ዘርፍ የተሠማራችሁ አካላት እድሉን ብትሰጡኝ›› ትላለችም።

ሜሮን ሁልጊዜ ሳቋ ይቀድማታል። የሚያናድድ ነገር ብትሰማ፤ የሚያስከፋት ነገር ቢደርስባት እርሱን እያሰላሰለች ጊዜዋን ማሳለፍ በፍጹም አትፈልግም። ይልቁንም በሁኔታው ስቃበት ታልፋለች። ለደረሰባት ችግርም መፍትሔ ትሻለች። ለአብነት በአንድ ወቅት ፈተና እየተፈተነች ሳለ በአካል ጉዳቷ የተነሳ ጊዜ አነሷት። እናም ሰዓት እንዲጨመርላት ጠየቀች። ምላሹ ግን ብዙዎችን ያሳዘነ ነው፤ ከፍተኛ ሕመምንም ይፈጥራል። ይህም ‹‹ ለምን ጤነኛ አትሆኝም ነበር›› የሚል ነበር። ብዙዎች ቢናደዱም እርሷ ግን ይህንን ባለው ሰው ብዙም አልተከፋችም። ይልቁንም አዘነችለት፤ ነገ ጤነኛ እንደሚሆን አስቦ በማለቱም የአስተሳሰቡ ድክመት እንደሆነም ተረዳችው። በዚህም ንዴቱን ወደ ሳቅ ለውጣ ፈተናዋን ተፈትና ወጣች። ከማንም የተሻለ ውጤትም ማስመዝገቧን ታስታውሳለች።

በዚህ አጋጣሚ አንድ ነገር ለሁሉም ሰው ትመክራለች። ‹‹ማን ጤነኛ ማን ጉዳተኛ እንደሚሆን አይታወቅምና ለማንም ሰው ሀዘን አትሁኑ፤ በንግግራችሁ ነጋችሁን አስቡ፤ ለነጋችሁም ሥሩ›› በማለት። አክላም እያንዳንዱ ነገር በፈለግነው ልክ የሚጓዝ ነው። ይህ እንዲኖረኝ እፈልጋለሁ ካላችሁ በእቅድ ያዙና መቼ ላይ ማሳካት እንደምትፈልጉ ወስኑ። ለውሳኔያችሁም ታመኑና ወደፊት ገስግሱ። ያን ጊዜ ስኬታችሁን ታገኙታላችሁ። በተለይም ሴቶች ጥንካሬ፤ አርቆ አስተዋይነቱና ተፈጥሮ በብዙ መልኩ የሚያዘን ስለሆንን ማድረግ የማንችለው ነገር አለ ብዬ አላስብም ትላለች።

በመጨረሻም ሜሮን ከሥራዎቿ ጋር በተያያዘ የምትለው አላት። ብዙ ጊዜ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ላይ ቀርቤያለሁ። በጋዜጣዎችም በየጊዜው የመቅረብ ዕድሉ ነበረኝ። ነገር ግን ሽልማቴ ሳይቀር በሌሎች ተወስዶብኛል። ሥራዎቼም መልካም ቢሆኑም አይቶ ምላሽ ሊሰጠኝ የቻለ አካል የለም። በአዋሽ ባንክ በኩል የፈጠራ አሸናፊ በሚል ከ300ሺ ብር በላይ ተሸልሜያለሁ። ያለ ምንም ማስያዢያ 5ሚሊዮን ብር ብድር እንደሚሰጠኝም ቃል ተገብቶልኛል። ሆኖም ይህ ነገር ስኬታማ ያደርገኛል ብዬ አላስብም። በተሸለምኩት ብርም የብሬል ወረቀትና ኮምፒውተር ገዝቼበታለሁ።

አሁን የሥራ ፈጠራዬ እውን ሆኖ እንደ ሀገር ጥቅሙ ጎልቶ ዓይነ ሥውራን እንዲጠቀሙበት ኑ በጋራ እንስራ ስል ጥሪ አቀርባለሁ ትላለች።

የዝግጅት ክፍላችንም እንደነዚህ ዓይነት ፈጠራዎች መበረታታት እንዳለባቸው ያምናል። እንተባበር፣ በመተጋገዝ ሀገራችንን እናቅና በማለት ተሰናበትን።

ጽጌረዳ ጫንያለው

አዲስ ዘመን ማክሰኞ መጋቢት 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You