
በዘመናችን ስፖርት ከመዝናኛና ከውድድርነት ያለፈ ትርጉም እንዳለው ተደጋግሞ ተነግሯል። ስፖርት ከፍተኛ ገንዘብ የሚንቀሳቀስበት፣ ከስፖርተኛው ባለፈ በዙሪያው ያሉ ግለሰቦችን ብሎም የሀገርን ኢኮኖሚ በመደገፍ ረገድ ትልቅ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝም በተግባር ታይቷል። የስፖርት ቱሪዝም በዓለም ላይ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ የመጣ የገቢ ምንጭ፣ የሀገር ገፅታ መገንቢያና የዲፕሎማሲ መሣሪያ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። ይህን ቀድመው የተረዱ ሀገራትም በብዙ እየተጠቀሙም ይገኛሉ።
ስፖርትና ቱሪዝም የማይነጣጠሉና ተመጋጋቢ ጉዳዮች ሲሆኑ የስፖርት ቱሪዝም የምንለውም ስፖርታዊ ክዋኔዎችን ለመታደምና ለመሳተፍ ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሱ ሰዎችን ማዕከል ያደረገ ነው። ለዚህም ነው ያደጉ የሚባሉ ሀገራት ከአነስተኛ የስፖርት ውድድሮች ጀምሮ እስከ ትልቁ የዓለም ዋንጫና የኦሎምፒክ ጨዋታ ድረስ የማዘጋጀት እድሉን ለማግኘት ብርቱ ፉክክር የሚያደርጉት።
በተፈጥሮ ሀብቷ የታደለችው ኢትዮጵያ በቱሪዝም ዘርፍ ካልተጠቀመችበት እምቅ አቅም ዋነኛው የስፖርት ቱሪዝም ነው። ኢትዮጵያ በተለይም በአትሌቲክስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ገናና ስም ቢኖራትም ስፖርቱን ከቱሪዝም ጋር በማቆራኘት በኩል እዚህ ግባ የሚባል ሥራ አልሠራችም። ይህን ቁጭትም በርካቶች በተደጋጋሚ ሲያነሱት ይታያል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ይህን ለመቀየር ትኩረት እየተደረገ ይገኛል። ኢትዮጵያ በ10 ዓመት የልማት እቅዷ ውስጥ ስፖርት ለሀገራዊ፣ ማህበራዊ ልማት እና ብልፅግና እንዲውል ትኩረት ሰጥታለች። ስፖርትን ከባህልና ቱሪዝም ጋር አስተሳስሮ ለሀገር ገጽታ ግንባታ፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ እንዲሁም ለሕዝብ ለሕዝብ ትስስርና አንድነት ያለውን ፋይዳ ከፍ ለማድረግ ታቅዶ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ነው።
በጀግናው አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሤ ተመሥርቶ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ያስቆጠረው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ስፖርትን ከቱሪዝም ጋር በማስተሳሰር ፈር ቀዳጅ ሆኖ ይጠቀሳል። ይህን የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አበረታች ጅምርን የቱሪዝም ሚኒስቴርም ተቀላቅሎ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለያዩ ከተሞች የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድሮችን በማዘጋጀት አብሮ እየሠራ ይገኛል።
ከዓመት በፊት የብርቅዬ አትሌቶች መፍለቂያ በሆነችው በቆጂ የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድርን በማዘጋጀት የተጀመረው አትሌቲክሱን ከቱሪዝም ጋር የማቆራኘት ጥረት በዚህ ዓመት መዳረሻውን ወደ አራት ከተሞች በማስፋት አበረታች ጅምር ታይቷል። “ልወቅሽ ኢትዮጵያ” በሚል መሪ ሃሳብ ባለፈው የካቲት በሃዋሳ ከተማ የተጀመረው የጎዳና ላይ ውድድር ሰሞኑን ሁለተኛ መዳረሻውን በጅማ ከተማ አድርጎ ተካሂዷል። የ”ልወቅሽ ኢትዮጵያ” የሩጫ ውድድር ከአራት አዘጋጅ ከተሞች አንዷ ለመሆን የበቃችው ጅማ፣ ከታሪካዊ ሥፍራዎቿ፣ ዝነኛ የቡና እና የእንጨት ምርቶቿ በተጨማሪ የሩጫ መዳረሻ ሥፍራ ሆና ከስፖርቱ ቱሪዝም ተጠቃሚ የሚያደርጋትን እድል እንዳገኘች የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ዳግማዊት አማረ ተናግረዋል።
በሁለቱ ውድድሮች በመቶዎች የሚቆጠሩ ከተለያዩ ሀገራት የመጡ የውጭ ሀገር ዜጎች ተሳትፈዋል። በዚህም ኢትዮጵያን በማስተዋወቅ ረገድ ውድድሮቹ ትልቅ ሚና እንደነበራቸው ተሳታፊዎች ከሰጡት አስተያየት መገንዘብ ተችሏል። መሰል ውድድሮችም በቀጣይ ወራት በቆጂና አርባ ምንጭ ላይ ይካሄዳሉ ተብሎ ይጠበቃል። ኢትዮጵያን ለማስተዋወቅና ከስፖርት ቱሪዝም ተጠቃሚ ለመሆን ግን እነዚህ ብቻ በቂ አይደሉም። በቀጣይ በሌሎች ከተሞችም ማስፋት ያስፈልጋል።
ኢትዮጵያውያን አስደናቂ ታሪክ ያስመዘገቡበት አትሌቲክስ ለሀገሪቱ የስፖርት ቱሪዝም ትልቅ ዕድል አለው። የቱሪዝም ሚኒስቴር ተወካይ የሆኑት አቶ ጌትነት ግዛው፣ ኢትዮጵያ እምቅ የቱሪዝም አቅም ቢኖራትም ባለፉት 60 ዓመታት የማህበራዊ ቱሪዝምን ብቻ ስትጠቀም እንደኖረች በማስታወስ ዘርፉን ለማሳደግ ይህን መቀየር እንደሚገባ ያስረዳሉ። ወደ ቱሪዝም ቢዝነስ ለመግባትም ስፖርት ትልቁ መሣሪያ መሆኑን ጠቁመው፣ “ታላቁ ሩጫ በዚህ ረገድ ቀድሞ ነቅቷል” ብለዋል። ቱሪዝም ሚኒስቴርም ይህን የመጠቀም በአዋጅ የተሰጠው ሥልጣን ስላለ ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጋር አብሮ እየሠራ ይገኛል ብለዋል።
አክለውም፣ እድሉን በሚገባ ለመጠቀም አስፈላጊ በመሆኑ በሌዠር ቱሪዝም ላይ ከተመሠረተው የሀገራችን ቱሪዝም በተጓዳኝ የቢዝነስ ቱሪዝምን እንደ አማራጭ ማየት ወቅቱ የሚጠይቀው ጉዳይ እንደሆነ ገልጸዋል። ይህንን በማድረግ ረገድ እንደ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ካሉ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መሥራት የኢትዮጵያን ቱሪዝም ሁለንተናዊ አስተዋፅኦ ሊያሳድግ እንደሚችል ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ እንደ አዲስ እየተጀመሩ ካሉ ኢንሼቲሾች አንዱ የስፖርት ቱሪዝም ሲሆን፣ በዚህ ረገድ ላለፉት ዓመታት ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው። ኢትዮጵያ መልከ ብዙ ቅርሶችና የተፈጥሮ ፀጋ የተቸረች ሀገር እንደመሆኗ ጸጋዎቿን አልምታ የቱሪዝም ገቢዋን ለማሳድረግ የተጀመረው እንቅስቃሴ አበረታች ነው። ያም ሆኖ ከስፖርት ቱሪዝም አንጻር ግን ብዙ ይቀራል። የስፖርት ቱሪዝም ለሀገር እድገትና ገፅታ ግንባታ ያለውን ሚና ለማጎልበት መንግሥት እና የግሉ ዘርፍ በቅንጅት ሊሠሩ ይገባል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 1 ቀን 2017 ዓ.ም