
ከልጅነታቸው ጀምሮ የሕይወት ውጣውረዶችን አሳልፈዋል፤ በብዙ ተፈትነዋል። ሆኖም በችግሮች ከመሸነፍ ይልቅ አሸናፊ በሚያደርጋቸው ጉዳዩች ላይ አተኩረው ውጣውረዶችን በክንዳቸው ደቁሰው አንቱታን ያተረፉላቸውን ተግባራት መከወን ችለዋል። ከትንሿ የገጠር ቀበሌ ተነስተው ሀገር አቀፍ ብሎም ዓለም አቀፍ የቁራን ተወዳዳሪና አሸናፊ ለመሆን በቅተዋል:: ገና የሰባተኛ ክፍል ተማሪ ሳሉም ዓለም አቀፍ የቁርዓን ውድድር ላይ ተሳትፈው የደረጃ ባለቤት መሆን ችለዋል፤ ሀገራቸውን አስጠርተዋል ኑረዲን ቃሲም (ዶ/ር)።
ኑረዲን (ዶ/ር) ለሀገራቸው ልዩ ፍቅርና አክብሮት አላቸው፤ በተለያዩ ጉዳዮች ዓለም አቀፍ እውቅናና ተፈላጊነት እንዲኖራትም የተቻላቸውን ሁሉ ያደርጋሉ:: በዚህም ውጤታማ የሆኑባቸው ማሳያዎች አሏቸው:: በሀገር ደረጃ ታስቦ የማያውቀውን ዓለም አቀፍ የቁርዓንና አዛን ውድድሮች በሀገር ውስጥ እንዲጀመር ማድረግ ነው:: ቀደም ባሉት ጊዜያት ጀምሮ ዓለም ኢትዮጵያን በበጎ ነገር አያነሳትም፤ ሁልጊዜም ረሃብና ጦርነት የሰፈነባት የክርስትና እምነት ተከታይ ብቻ ሀገር አድርጎ ይስሏታል:: ይህንን መሰል የተዛቡ ምልከታዎችን ለማስተካከል ሁለት ጊዜ ዓለም አቀፍ የቁርዓንና አዛን ውድድሮች በሀገራችን ደረጃ እንዲደረግ አስችለዋል::
በመጀመሪያ ዙር ከ56 ሀገራት በሁለተኛው ዙር ደግሞ ከ60 ሀገራት የተለያዩ ተሳታፊዎችን እንዲመጡ በማድረግም የሀገር ገጽታ ግንባታ ላይ ዐሻራቸውን አሳርፈዋል:: በእርሳቸው ጥሪ የመጡ አንዳንድ ሀገራትም በሰላምና ጸጥታ እንዲሁም በኢንቨስትመንቱ ዘርፍ አልፎ ተርፎም በሃይማኖታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለመሥራትም የተለያዩ ስምምነቶችን እያደረጉ መሆናቸውን ይናገራሉ::
በግል ጥረታቸው ራሳቸውን አብቅተው ዓለም አቀፋዊ የቁርዓን ዳኛ መሆን የቻሉት ኑረዲን (ዶ/ር)፤ ሀገራቸውን እያገለገሉ ያሉት በሃይማኖታዊ ትምህርት ብቻ ሳይሆን በዘመናዊው ትምህርትም ወደፊት ተራምደው ነው:: በተለይም በጤናው ዘርፍ ላይ ትልቅ አበርክቶ ነበራቸው:: ዜጎች በሥነ ምግባር ተቀርጸው ለሀገራቸው የተሻለ ትውልድ እንዲሆኑም «የዘይድ ኢብን ሳቢት የቁርዓን ማህበር»ን መስርተው እየሠሩ ይገኛሉ:: በቢዝነሱ ዓለምም በበርካታ ተግባራት ተሰማርተዋል:: ከዚህና መሰል ተሞክሯቸው አንጻርም ለብዙዎች የሚተርፍ ተሞክሮ አላቸውና የዛሬው ‹‹የሕይወት ገጽታ›› ዓምድ እንግዳችን አድርገናቸዋል::
የፈጣሪ ልጅ
ውልደትና እድገታቸው የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በዓለም አደባባይ ከፍ ያደረጉና ያስጠሩ አትሌቶች ከፈለቁባት አርሲ ውስጥ ነው:: ልዩ ቦታዋ አርባጉጉ እርኤ አንባ ትባላለች:: እንደ ማንኛውም የገጠር ልጆች በወላጆቻቸው ልዩ እንክብካቤ እየተደረገላቸው አድገዋል:: ቤተሰቡ የሚተዳደረው በግብርና ቢሆንም እንደ ገጠር ልጅ በእርሻ ሥራ ላይ ተሰማርተው አያውቁም:: ከዚያ ይልቅ ከእንስሳት ጋር ልዩ ቅርበት ኖሯቸው ነው ልጅነታቸውን ያሳለፉት:: ከብት በማደለብ፤ አጥር በማጠርና እንጨት በመልቀም ቤተሰቦቻቸውን አግዘዋል::
ለቤተሰቡ የመጀመሪያ ወንድ ልጅ በመሆናቸው የሚሰጣቸው ትኩረት ከሌሎች ልጆች የላቀ ነው:: የሥራ ጫና ሳይበዛባቸው ከእኩዮቻቸው ጋር እንደልብ ተጫውተዋል:: በተለይም በእግር ኳስ ጨዋታ የሰፈሩ ልጅ ሁሉ የሚመርጧቸው ዓይነት ተጫዋች ናቸው:: አባታቸው በሃይማኖት ትምህርት እንዲገፉ ሲፈልጉ እናታቸው ደግሞ ዘመናዊ ትምህርቱ ላይ እንዲያተኩሩ ይሻሉ:: በዚህም ልጅነታቸውን ያሳለፉት የሁለቱንም ስሜት በመጠበቅ ነው::
ባለታሪካችን ልጅነታቸው ያለፈው በአብዛኛው ጭምትና ቁምነገረኛ ሆኖ ነው:: መጀመሪያ አካባቢ ትንሽ ያስቸግሩ ነበር:: ተደባዳቢና እልኸኛ ነበሩ:: ወደ ሃይማኖታዊ ትምህርቱ ሲገቡ ግን ተደባዳቢነታቸው ቆመ:: ጸባያቸውን ቀይረውም ሃይማኖታዊ ትምህርቱ ላይ ትኩረታቸውን አደረጉ:: በሃይማኖታዊ ትምህርቱ እየገፉ በመምጣታቸው ከሀገር አልፎም የውጭውን ዓለም ወደ ማሰቡ ገቡ፤ በወቅቱ ፓስፖርት ለልጅ ቀርቶ ለአዋቂዎችም ለማውጣት ከባድ በነበረበት ጊዜ በሰባተኛ ክፍል የተማሪነት መታወቂያቸው ፓስፖርት ወጥቶላቸው ዓለም አቀፍ የቁርዓን ውድድር ላይ መሳተፍ ቻሉ:: ኢራን ሀገር በመሄድም ከ40 ሀገራት ከመጡ ተወዳዳሪዎች ጋር ተወዳድረው ከአንድ እስከ ሦስት መውጣት ባይችሉም ከፍተኛ የሚባለውን የደረጃ እርከን በመያዝ ሀገራቸውን አስጠርተው መመለስ ችለዋል::
እንግዳችን ልጅነታቸውን ሲያስታውሱት ቀድሞ ወደ አዕምሯቸው የሚመጣው የማኅበረሰቡ ልዩ እንክብካቤ ነው:: ማንም የማንም ልጅ ይሁን ሳይጠይቅ እኩል ክብር ይሰጠዋል፤ ማንነቱን ሳይሆን የፈጣሪ ልጅ መሆኑን በማመንም የፈለገውን ያገኛል:: ልብስ፤ ምግብና መሰል ነገሮች ከልጅ እኩል ይደረግለታል:: ጎረቤቱ የአካባቢው ልጅ በሙሉ ኃላፊነት አለበት:: ጥፋት ሲያይ ይገስጻል፤ በሥነ ምግባርም ያሳድጋል:: የሃይማኖት ልዩነት ቢኖርም በደስታ በሀዘኑ አብሮ ይሳተፋል:: ልዩነቱን አክብሮ መልካም ነገርን ሁሉ አብሮ ያደርጋልም::
‹‹እኔ በዚህ ማኅበረሰብ ውስጥ ሳድግም የ‹ፈጣሪ ልጅ› እየተባልኩ ነው:: የፈጣሪ ልጅ መሆን መልካም ነገሮችን ከአካባቢውና ከማኅበረሰቡ እየተማረና፤ እየኖረበት ልጅነቱን ማሳለፍ ነው:: የዘርና ሃይማኖት ልዩነት ሳይኖር ተከባብሮ የተሻለውን የሚፈጠርበትም ነው ሁሉም ልጅ በእኔ ልክ አድጓል ብዬ አስባለሁ:: ምክንያቱም ትናንት የተሰጠንን ዛሬ እየኖርን ነው:: እኛ ምን ያህል የተረከብነውን እየሰጠን ነው ጥያቄው›› የሚሉት እንግዳችን፤ አባታቸው አርሶ አደር ብቻ አይደሉም:: የሃይማኖት ሰውና በአካባቢው ተጽዕኖ ፈጣሪ ናቸው:: በዚህም ብዙዎች በቤታቸው ይሰበሰባሉ:: ቁርዓን ይቀራሉ:: ይህ ደግሞ ለእርሳቸው የነገ ሕልማቸውን ያበራላቸው ነበር::
ሻማና መብራት በሌለባት በዚያች ትንሽ የገጠር መንደር ውስጥ አባት ዘወትር ከእምነቱ ሰዎች ጋር ሰብሰብ ብለው በምድጃ እሳት ብርሃን አለያም በኩራዝ ቁርዓንን ይቀራሉ:: ይሰግዳሉ፤ ሃይማኖታዊ ተግባራትን በየደረጃው ይከውናሉ:: ይህ ትጋታቸው ደግሞ ለትንሹ ኑረዲን በየጊዜው ግርምትን ይፈጥርባቸው ነበር:: ቁርዓን መቅራት እንዳለባቸውም የቆረጡት ጭለማ ሳይገድባቸው ፈጣሪያቸውን ሲያመሰግኑ ማየታቸው ነው:: እናም ሞዴል አድርገዋቸው የቁርዓን የቃል ንባቡን መማር ጀመሩ:: አዲስ አበባ ላይ የቁርዓን ውድድር እንዳለ ሲሰሙ በአካባቢያቸው ለመወዳደር ወሰኑ::
በአንድ ምሽት 30 ጁዝ 600 ገጽ በመሸምደድም ለውድድሩ ቀረቡ:: ነገር ግን አዲስ የገቡ በመሆናቸው መወዳደር እፈልጋለሁ ቢሉም በቀላሉ አልተቀበሏቸውም:: ብዙ ከታገሉ በኋላ ነው ውድድሩን እንዲያደርጉ የፈቀዱላቸው:: በዚህም እድላቸውን በአግባቡ ተጠቅመውበታል:: ዓመታት ይፈጅ የነበረውን የቁርዓን ቃል ንባብ በአንድ ምሽት ሸምድደው ስለነበር አንደኛ በመውጣትም ውድድሩን አጠናቀዋል::
በ1984 ዓ.ም ለእርሳቸው ሌላ የመኖር ምስጢር ሆኖላቸው በሰባት ዓመታቸው ቀያቸውን፤ እናት አባታቸውን ትተው አዲስ አበባ ከተሙ:: ምክንያቱም ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ ተወዳዳሪዎችን ተቀላቅለው ‹‹መርከዘል አንሳር የእስላማዊ ትምህርት ተቋም ወይም ማዕከል›› አዳሪ ትምህርታቸውን መከታተል ጀምረዋል::
ታሪክ ቀያሪው ቁርዓን
ኑረዲን (ዶ/ር) የትምህርት ጉዞ ሃይማኖታዊና ዘመናዊ ነው:: ስለዚህም በሁለት በኩል የተሳሉ ሰይፍ ናቸው ቢባል ማጋነን አይሆንም:: አንዱ ለአንዱ ትምህርታቸው መሠረትም ነበር:: የሃይማኖት ትምህርቱን በስፋት በመማራቸው ከአንደኛ ክፍል ደብል መተው አምስተኛ ክፍል እንዲገቡ አስችሏቸዋል::
ሃይማኖታዊ ትምህርቱን የጀመሩት በትውልድ ቀያቸው ባለ ትልቅ መስጊድ ውስጥ ነው:: ጠንካራና በጣም ጎበዝ ተማሪ በመሆናቸው ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ‹‹መርከዘል አንሳር የእስላማዊ ትምህርት ማዕከል›› ውስጥ የአዳሪ ትምህርት ተማሪ ሆነው ለሦስት ዓመት ተኩል ተምረዋል:: በቁርዓን ሄፍዝ (የቁርዓን ቃል ንባብ) ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ሲሆን፤ ጎን ለጎንም በርካታ የእስልምና ትምህርቶችን ተከታትለዋል::
ባለታሪካችን በሃይማኖት ትምህርቱ ሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪ ድረስ የተማሩ ሲሆን፤ በቁርዓን ሳይንስ የትምህርት መስክ ተመርቀዋል:: በዚህ ደግሞ የሃይማኖት መምህር፤ ዓለም አቀፍ ዳኛ ለመሆንም በቅተዋል::
ኑረዲን (ዶ/ር) የዘመናዊ ትምህርት ጉዞም የሚጀምረው እንደ ሃይማኖታዊ ትምህርቱ ከቀያቸው ነው:: እርኤ አንባ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤትም የቀለም ትምህርታቸውን አሀዱ ያሉበት ነው:: በርግጥ ከአንደኛ ክፍል በኋላ በዚያ መማርን አልፈለጉም:: ትምህርት ቤት ሲላኩ ጭምር ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት ውጭ መስክ ላይ ሳር ውስጥ ሲንከባለሉ ነው:: ሳይደግስ አይጣላ እንዲሉ ነውና በሃይማኖታዊ ትምህርቱ ገፍተውበት ዘመናዊ ትምህርቱ ያለውን ዋጋ እንዲረዱ እድል አግኝተዋል::
የአቋረጡትን ትምህርትም ዘነበወርቅ አካባቢ በሚገኘው አህሉል ቤት ወይም ነስር ትምህርት ቤት በመግባት ተከታትለዋል:: እስከ አምስተኛ ክፍል ተከታትለዋል::
እንግዳችን እስከ ስምንተኛ ክፍል ባላቸው የትምህርት ጉዞ በሰው ቤት የሰዎቹን ልጆች በማስጠናት ነበር ሲማሩ የቆዩት:: በዚህም ትምህርት ቤታቸው አንድ አካባቢ ላይ የተወሰነ አልነበረም:: ለአብነት የስድስተኛ ክፍል ትምህርታቸውን የተማሩት አውቶብስ ተራ ኳስ ሜዳ አካባቢ በሚገኘው ‹‹ገነሜ›› ትምህርት ቤት ነው:: ሰባተኛ ክፍልን የተከታተሉት ደግሞ አስኮ አካባቢ በሚገኘው ‹‹አወልያ›› ትምህርት ቤት ነው:: እስከ 10ኛ ክፍል ድረስም ይህንን ትምህርት ቤት ሳይለቁ ትምህርታቸውን ተምረዋል::
11ኛና 12ኛ ክፍልን ደግሞ ብዙም ሳይርቁ ጳውሎስ አካባቢ በሚገኘው መድኃኒዓለም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል:: በዚህ የትምህርት ቆይታቸው የተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርት ይስባቸዋል::
በተለይም የባዩሎጂ ትምህርት የሚወዱት ነበር:: ለዚህ ደግሞ መምህሮቻቸው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ነበራቸው:: ስለዚህም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከወሰዱ በኋላ በቀጥታ ጅማ ዩኒቨርሲቲን ሲቀላቀሉ የአካባቢ ጤና አጠባበቅ (environmental health) ትምህርት መስክን መርጠው የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል::
የኑረዲን (ዶ/ር) የልጅነት ህልማቸው የጤና ትምህርትን ማጥናት ነውና ይህንን እንዳሳኩት ይሰማቸዋል:: ምክንያቱም የመጀመሪያ ዲግሪ ብቻ ሳይሆን ሁለተኛና ተጨማሪ ዲግሪዎችን በጤናው መስክ አጥንተዋል:: በመጀመሪያ ዲግሪ በጤና መኮንን ( health officer) ከኪያሚድ ኮሌጅ ተመርቀዋል:: የሥነልቦና ጤና( Health psychology) አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመርቀዋል:: ማህበረሰብ ጤና (public health)ም በሁለተኛ ዲግሪ ሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ መመረቅ የቻሉ ናቸው:: አሁንም በሁለተኛ ዲግሪ ደግሞ የሥነ ምግብ ትምህርት nutration ትምህርት እየተማሩ ይገኛሉ፡: ከጤናው ባሻገርም ማኔጅመንት፤ ቢዝነስ አድሚንስትሬሽን ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ማጠናቀቅ ችለዋል::
የ12 ዓመቱ መምህር
ማዕከሉ የእስልምና ትምህርቱን በአዳሪ ትምህርት ቤት ውስጥ የሚሰጠው በዋናነት የእስልምናው ትምህርት እንዲስፋፋና በሃይማኖቱ የበቁ ትውልዶችን ለመፍጠር ነው:: በዚህም አስተምሮ ያስመረቃቸውን መምህራን ወደ ተለያዩ ቦታዎች የተማሩትን እንዲያካፍሉ ይመድባቸዋል:: እንግዳችንም አንዱ በቁርዓን ቃል ንባብ መምህርነት የተመረቁ በመሆናቸውም እንደሌላው ተማሪ ከቤተሰብ እንዳይርቁ በማሰብ ወደ ትውልድ ቀያቸው እንዲያሰግዱ ተመድበዋል:: ሆኖም አሰላ ላይ ማንም ሊቀበላቸው አልወደደም::
ትንሽ ልጅ በመሆናቸውም በእድሜም በእውቀትም የሚልቁ ትልልቅ ሰዎች ባሉበትም ይህ መደረጉ አናዷቸው አይቻልምም ብለዋቸዋል:: የዚህ ጊዜ እርሳቸው ያደረጉት ለሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ማሳወቅ ነው:: በርግጥ ወደ አሰላ ሲሄዱ እንደማይቀበሏቸው ያውቃሉ:: በዚያ ላይ ወደ ቀደመ ጨለማና የመማር እድል የሌለበት ሥፍራ መሄድን አልወደዱትም ነበር:: ግን ሃይማኖታዊ ግዴታቸው ነው:: አስተምረዋቸዋልና የማዕከሉን ግዴታ ማክበርም ሳይወዱ በግድ የሚፈጽሙት ነው:: እናም ትዕዛዛቸውን ለመተግበር ሲሉ ወደቦታው አቀኑ:: እንቢ ሲባሉም ጊዜ ሳያጠፉ ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ::
አዲስ አበባ ላይም በሰው ቤት ገብተው ልጆችን እያስጠኑ ሃይማኖታዊና ዘመናዊ ትምህርቶችን መማር ቀጠሉ:: በ1989ዓ.ም የስድስተኛ ክፍል ተማሪ ሳሉ እድሜያቸው 12 ሳይሞላ በሃሺም መስጊድ ውስጥ በቁርዓን መምህርነት ተቀጠሩ:: የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና እስከወሰዱበት ጊዜ ድረስም በማስተማር ሥራው ዘለቁበት:: ከዚያም ባሻገር በየቤቱ እየሄዱም የቁርዓን ቃል ንባብ ትምህርትን ያስጠናሉ:: ይህ ሁኔታ ደግሞ በሁለት መልኩ የተከናወነ ነበር:: አንድ በሰዎች መኖሪያ ቤት ውስጥ ገብተው እዚያው እየኖሩ ልጆችን ያስጠኑበት ሲሆን፤ ሌላኛው ቤት ተከራይተው፤ መስጊድ ውስጥ ሆነው ሲያስጠኑና የራሳቸውን ገቢ እያገኙ ያስተማሩበት ነው::
በሰው ቤት ረጅሙን ጊዜ ያሳለፉ ሲሆን፤ እስከ ስምንተኛ ክፍል የሚኒስትሪ ፈተና ድረስ የዘለቀ እንደነበር ኑረዲን(ዶ/ር) አይረሱትም:: ዘጠነኛ ክፍል መጀመሪያ አካባቢ ደግሞ ሼህወጀሌ መስጊድ የቁርዓን ሄፍዝ መምህር በመሆን ስለተመደቡ ቤት ተሰጥቷቸው የቤት ጉዳይ ሃሳብ ሳይሆንባቸው የአስተማሩበት ጊዜ ነበር:: ከ11 ሰዓት በኋላ በሳምንት ሦስት ቀን ስለሆነ ትምህርቱን የሚሰጡት የተለያዩ መስጊዶች ውስጥ በመምህርነት ያገለግላሉ:: በተጨማሪም ልጆችን የቁርዓን ትምህርት ያስጠናሉ:: በመስጊዱ ውስጥ በአንዴ የሚያስተምሩት በትንሹ 40 ተማሪ ሲሆን፤ በዚህም በርካቶችን አስተምረው ለቁም ነገር ማብቃት ችለዋል:: ወደ 28 ተማሪዎችን ሃፊዝ ለማድረግ በቅተዋል::
በመምህርነትና በአስጠኚነት ሥራቸው ብዙ ሰዎች ልጅ በመሆናቸው ይመርጧቸው ነበር:: የሃይማኖት ትምህርትን ጠንቅቀው ስለተማሩም ምንም እንኳን ልጅነት ቢኖርባቸውም ከፍተኛ ክብርን ከመስጠት ወደኋላ አይሉም:: በሰዎች ቤት ኖሮ መማር በሃይማኖቱ በገጠሩ አካባቢ ‹‹ቀሪኣ›› ይባላል ወይንም ደረሳ ይባላል:: ማኅበረሰቡ የሚፈልገውን እያሟላለት የሃይማኖት ትምህርቱን እንዲከታተል የሚያደርግበት ነው:: እንግዳችንም በዚህ መልኩ በከተማ ቢሆንም እስከ ዘጠነኛ ክፍል ድረስ ባለው ቆይታቸው በሰዎች ቤት እየኖሩ ልጆችን እያስተማሩ፤ መስጊዶች ላይ በቁርዓን ትምህርት እያገለገሉ ዓመታትን አሳልፈዋል::
የሃይማኖት ትምህርት ማስተማሩን ጅማ ዩኒቨርሲቲ ሳሉ ሳይቀር የቀጠሉበት ነው:: ይህም በዑመር መስጊድ ውስጥ የቁርዓን ትምህርት ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ያስተምሩ ነበር::
ከሃይማኖት ትምህርት ሥራቸው ባሻገርም በዘመናዊ ትምህርቱም የተለያዩ ቦታዎች ላይ ተመድበው ሀገራቸውን አገልግለዋል:: ከምርቃት በኋላ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ባኮ ጤና ቢሮ ተመድበው ለሁለት ዓመታትም የጤና ባለሙያ በመሆን አገልግለዋል:: ከዚያ ወደ አዲስ አበባ ከተማ መጥተው የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ተቀጥረው በተለያየ የሥራ ዘርፍ አገልግለዋል።
ኑረዲን(ዶ/ር) በባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ እያገለገሉ ባለበት በካቢኔነት ተመርጠው በኮልፌ ቀራኒዮ ወረዳ 16 የጤና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሆነው ሠርተዋል:: ከስድስት ወር በኋላ ደግሞ ወደ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ተመልሰው እስከ 2004 ዓ.ም እንዲሠሩ ተደርገዋል:: ከዚያ በኋላ የቅጥር ሥራ በቃኝ ብለው የራሳቸውን ሥራ ገብተዋል::
ከሥራዎቻቸው መካከል በዋናነት የሚጠቀሰው የቁርዓንና አዛን ትምህርቱ ሲሆን፤ ሕጋዊ እውቅና ባይኖረውም እውቅና ካላቸው ሌሎች ተቋማት ጋር በመቀናጀት የእስልምና እምነት ተከታይ ልጆችን የዓረብኛ ቋንቋ ትምህርትን፤ ቁርዓንን፤ የሥነ ምግባር ትምህርትና የዘመናዊ ትምህርት ማጠናከሪያ ትምህርቶችን በመስጠት የኮረና ቫይረስ በሽታ እስከተከሰተበት ጊዜ ድረስ ሲሠሩ ቆይተዋል:: በ2010 ዓ.ም ደግሞ የ‹‹ዘይድ ኢብን ሳቢት የቁርዓን ማህበር›› በሚል እውቅና ያለው ድርጅት አቋቁመው የቀደመውን ሥራ ሳይለቁ ተጨማሪ ሥራዎችን አስቀጥለዋል::
በድርጅታቸው አማካኝነት የዓለም አቀፍ የቁርዓንና አዛን ውድድሮች ሳይቀሩ እንዲደረጉ እድልን ፈጥረዋል:: ለዚህ መነሻ የሆናቸው ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ የቁርዓን ዳኝነቱን መስፈርት አሟልተው ከመካ ማረጋገጫ በ2009 ዓ.ም ማግኘታቸው ነው:: እውቅናው ሲሰጣቸውና የተለያዩ የዓለም ሀገራት ላይ በመዘዋወር ሲሠሩ በርከት ያሉ ተሞክሮዎችን ቀስመዋል:: ስለዚህም ‹‹ይህ ለሀገሬ መሆን አለበት›› በማለትም እድሉን ወደ ሀገራቸው አምጥተዋል:: ተሳክቶላቸውም ለሁለት ጊዜ ውድድሮችን በኢትዮጵያ ማዘጋጀት ችለዋል::
‹‹በሥራዬ ስኬታማ ነኝ ብዬ ባላምንም ዓለም አቀፍ የቁርዓንና አዛን ውድድሩን ወደ ሀገር ውስጥ ማምጣት መቻሌ ዐሻራዬን በሀገሬ ላይ ማሳረፍ እንደቻልኩ እንዲሰማኝ አድርጎኛል›› የሚሉት ባለታሪካችን፤ ሁለቱ ጊዜ ውድድሮች የኢትዮጵያ ስም በዓለም ላይ እንዲነሳ ሆኗል:: ከባድ ፈተና ውስጥ ሆና ሳይቀር ገጽታ መገንባት እንደምትችል ታይቶበታል:: መልካም ስሟንና ሥራዋ ተገልጦበታል:: ልክ እንደ አትሌቲክሱ ሀገራት ለካ እንዲህ ናት እንዲሉ ያስቻለችበት መድረክ ሆኖም አልፏል:: በተለይም የዓረቡን ዓለም የተሳሳተ ምልከታ በብዙ መልኩ መቀየር የተቻለበትም ነበር:: የኢትዮጵያን አበርክቶ ሁሉም ሀገራት እንዲያዩት ዕድል ፈጥሯል:: እንደ ሞሮኮ ዓይነት ሀገራትም ከሀገራችን ጋር በጥምረት እንዲሠሩ እድል የተፈጠረ ነበር:: ከዚያ ባለፈ ከሃይማኖት ተቋማት ጋርና መሰል መሥሪያ ቤቶች ጋር ለመሥራት ስምምነት ላይ ለመድረስ ንግግር የማድረግ ሁኔታ እንደነበር ይናገራሉ፤
ዓለም አቀፋዊ የቁርዓንና አዛን ውድድሩ በኢትዮጵያ ሲካሄድ ከሌላው ዓለም በተለየ መልኩ ነው:: ኢትዮጵያ መልክም ዘይቤም ያለውና ኢትዮጵያዊ ፍልስፍናን የተከተለ ሆኖ ነው የተዘጋጀው:: በዚህም በርካቶች ልምድ ቀስመውበት የሄዱበት ነው:: በተለይም ልዩነትን አክብሮ በአንድነት የሚኖር ሕዝብ እንደሆነ በሚገባ የተመለከቱበትና እንዲህም ይቻላል ያሉበት ነበርም:: ሌላው በእስልምና ኢትዮጵያ (ሀበሻ) ትልቅ ቦታና ታሪክ ያላት በመሆኗ ይህንን በሚገባ እንዲያዩና እንዲያረጋግጡ የሆኑበት ነው ይላሉ::
ኑረዲን (ዶ/ር) በዚህ ውድድር ብቻ ሳይሆን በሌሎች አዳዲስ ሥራዎችም ሀገራቸውን ከምንግዜውም በላይ ማስተዋወቅ ይፈልጋሉ:: በተለይም ታሪክ ወደ ባለቤቱ እንዲመለስ ለማድረግ በቻሉት ልክ ለመሥራት አቅደዋል:: ይህ ግን በእርሳቸው ብቻ የሚሳካ ስላልሆነ ሁሉም በሙያው እንዲተጋ ይመክራሉ:: በእርሳቸው በኩል የቀጣይ ሥራቸው አዛንን በዩኔስኮ ማስገንዘብ ነው:: ይህንን ለማሳካትም የተለያዩ ጥረቶችን እያደረጉ እንደሆነ ይናገራሉ::
የማይረሳው ገጠመኝ
ሰባተኛ ክፍል ሳሉ ነበር ክስተቱ የተፈጠረው:: በልጅነት ከቤተሰብ ርቆ በሰዎች ቤት መጠለል ይከብዳል:: ሆኖም በእምነቱ ዘንድ ማንኛውም የእምነቱ አዋቂ ቦታው ከፍ ያለ ነውና ትንሽም ቢሆኑ ይከበራሉ:: ልጆቻቸውን ከፍ ያለ ደረጃ ለማድረስም ፈላጊያቸው ብዙ ነው:: ነገር ግን ሠራተኞች ከዋናዎቹ በበለጠ በቤቱ ላይ ሥልጣን ነበራቸውና በብዙ አስቀየሟቸው:: የማይረሳውን ገጠመኝም ሰጧቸው::
ሁነቱ የተፈጠረው የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ሳሉ ነው:: ለሚያስጠኗቸው ልጆች ምንም ሳይሰስቱ እውቀታቸውን ይለግሷቸዋል:: ልጆቹም ጥሩ ተማሪ ነበሩና በሚገባ እውቀቱን ጨብጠዋል:: ግን የቤት ውስጥ ሠራተኛዋ የምታደርገው ነገር በእጅጉ ያሳዘናቸዋል:: በተለይም በምግብ በኩል ስቃያቸውን ያበረታው ነበር:: ብዙ ጊዜ ማንም አያስታወሳቸውምና ጦማቸውን አድረዋል::
በጣሙን የመረራቸው ግን ለሁለት ቀናት ምንም ዓይነት ምግብ ሳይቀርብላቸው መቅረቱ ነው:: ሦስተኛው ምሽት ላይም ጠኔ ሊደፋቸው ሲል ከላይ ትኩስ ከውስጥ ደግሞ ሻጋታ እንጀራ ቀረበላቸው:: ትኩሱን እንደራባቸው ቶሎ ቶሎ በልተው ሲጨርሱና ታችኛው ላይ ሲደርሱ ያዩትን ማመን አቃታቸው:: ለምን አላሉም:: ባይጠግቡም አመስግነው ሻጋታውን መልሰው ሰጡ:: በማግሥቱም ለማንም ምንም ሳይናገሩ ቤቱን ጥለው ወጡ:: በዚህ አጋጣሚም አንድ ነገር ለወላጆች ይመክራሉ:: እኛ ሠራተኞችን ባለመቆጣጠራችን መልካምነታችን ይጠፋል፤ ልጆቻችንም ይጎዳሉ:: ስለሆነም ሁልጊዜ ቤት ውስጥ ያሉ ሰዎችን መከታተልና ምን ጎደለ ማለት ያስፈልጋል:: ሠራተኞችንም መቆጣጠርና ባለቤት እንዳልሆኑ ማስረዳት ተገቢ ነው:: ያን ጊዜ ማንም ሳይጎዳ ኑሮውን ይቀጥላል ይላሉ::
የሕይወት ፍልስፍና
ሁሌ ፈተናዎች ቢኖሩም እነርሱን አልፎ አዲስ ነገር ፈጥሮ በመተግበር ሀገርን ማስጠራት ያስፈልጋል:: የሚለው የሁልጊዜ መርሃቸው ነው:: እንደጀመሩትም ይሰማቸዋል:: ትንሽ ነገር መመኘት ትንሽ ያደርጋል የሚል እምነትም አላቸው:: ስለዚህም ሁልጊዜ አርቆ ማሰብ፤ ተጽዕኖ ሊፈጥር የሚችል ሥራ መሥራት ይመቻቸዋል:: አብሮነትና መተሳሰብ የሕይወት መመሪያቸው እንዲሆን ይሻሉም::
መልዕክት ኑረዲን(ዶ/ር)
በሕዝብ ቁጥራችን እንደላቅን ሁሉ በሀገር ወዳድነታችንም ልቀን መውጣት አለብን የሚል መልዕክት አላቸው:: ያለችን ሀገር አንድ በመሆኗ ለእርሷ መሥራት እንጂ በእርሷ ውስጥ ሆነን መተራመስ አይገባንም:: በእርሷ ውስጥ ሆነን እውነቷን፤ ታሪኳን ልንገልጥና ለዓለም ልናሳይ ይገባል:: ሙያችን፤ ባሕላችን፤ ተፈጥሯዊ ችሮታችን ለሁላችንም የሚበቃ ነው:: ተባብረንና ተግባብተን የማንጠቀምበት ከሆነ ግን ሌሎች በእኛ እንዲደሰቱ እንፈቅድላቸዋለን:: ስለሆነም ዛሬ ላይ ነቅተን ተግባብተንና ተረዳድተን ነጋችንን እንሥራ ይላሉ::
ሀገር በምንም ነገር አይለካም፤ መስፈሪያም ወሰንም አይገኝለትም:: ስለሆነም ልጆቻችንን የምንወዳቸው ከሆነ ለዘላለም ደስተኛ የሚሆኑባትን ሀገር ሠርተን እናስረክባቸው:: በሃይማኖት፤ በብሔርና በጥላቻ መንፈስ አንቅረጻቸው:: እኛ መልካሟንና ነፃ የሆነችውን ሀገር እንደተረከብን ሁሉ ባለእዳዎች ነንና በተዘዋዋሪ ቅኝ የምትገዛ ሀገርን ማውረስ የለብንም::
በኢኮኖሚውም፤ በማኅበራዊውም ተጽዕኖ የምትፈጥረውን ሀገር እንስጣቸው:: ለዚህ ነገ ሳይሆን ዛሬ ላይ ቆም ብለን በማሰብ መሥራት ይኖርብናል ሲሉ መልዕክታቸውን ያስተላልፋሉ::
በተለያዩ የሙያ ዘርፍ ላይ ያሉ ምሁራን፤ የሃይማኖት አባቶች፤ በፖለቲካው ዘርፍ ያሉ ሰዎች ሀገርን ከመሥራትና ትውልዱን ከመቅረጽ አኳያ ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው:: ማንኛውንም ፍላጎታቸውን ማሳካት የሚችሉት ሀገር ካለች ብቻ መሆኑን በመገንዘብ ስለ ሀገራቸው ገዷቸው በተለይም ለአብሮነት፤ ለነገ መሻገርና የተሻለ ነገር ሁሌ ሊተጉ ያስፈልጋል:: ትውልዱ በጥላቻ ሳይሆን ብርታትን፤ ሠርቶ መለወጥን መለያው እንዲያደርግ፤ ስለ ሀገሩ ልዕልና እንዲያስብና ዐሻራውን እንዲያሳርፍ ለማድረግም ዘወትር መሪ ሆነው ሊያሳዩት ይገባቸዋል:: የትም ሀገር ልዩነቶች ይኖራሉ:: ግን መስማማትን ማስቀደም ከምንም በላይ መልመድ ይኖርብናል ይላሉ::
አብሮነትና መተጋገዛችን ለኢትዮጵያዊያን ትናንትን ያኖረን፤ ዛሬን ያስተሳሰረን ነገን ደግሞ የሚያሻግረን መርከባችን ነው:: ስለሆነም በዚህ ውስጥ ሆነን ዛሬያችን ላይ መሥራት፤ ነጋችንን ማብራት ይኖርብናል:: ይህንን መርሃችንን በአግባቡ ተጠቅመን ሀገራችንንም ልንገነባ ይገባል ሲሉ መልዕክታቸውን ያስተላልፋሉ::
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን መጋቢት 28 ቀን 2017 ዓ.ም