
የከበሩ ማዕድናት ከውበታቸው እና ልዩ ባሕሪያቸው የተነሳ በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ለዘመናት ተወዳጅ ሆነው ዘልቀዋል፤ ባለንበት ዘመንም ተፈላጊነታቸው ከፍተኛ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይጠቁማሉ።
የማዕድናቱ ቀለማት፣ ውበትና ማራኪነት የሰውን ቀልብ የሚስብ ከመሆኑም በላይ በተለያዩ መልኩ ተሠርተው በውድ ስጦታነት ሲበረከቱም ለሰጪም ለተቀባይም ትልቅ እርካታን በማላበስም ይታወቃሉ። በተለይ በውጭው ዓለም በደንብ የሚታወቁ ከመሆናቸውም በላይ፣ በክብር ከሚቀመጡ ውድ እቃዎች መካከል ይጠቀሳሉ።
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ የከበሩ ማዕድናትና ጌጣጌጦች ግብይት በዓለም አቀፍ ደረጃም ይታወቃል። በዓለም አቀፍ ደረጃ በከበሩ ማዕድናትና ጌጣጌጥ ዘርፍ በዓመት ከ250 እስከ 300 ቢሊዮን ዶላር ይንቀሳቀሳል። በግብይቱም አንዳንድ የሩቅ ምሥራቅ ሀገሮች በከፍተኛ ደረጃ ይታወቃሉ። ሕንድ፣ ሲሪላንካና ቻይና በዚህ በኩል ይጠቀሳሉ።
በኢትዮጵያም በርካታ ዜጎች ማዕድናቱን በማውጣት፣ በማዕድናቱ ላይ እሴት በመጨመርና ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ በማቅረብ ላይ ተሰማርተዋል፤ ሀገሪቱም የውጭ ምንዛሪ ታገኝባቸዋለች፡፡
መረጃዎች እንደሚያመላክቱት፤ ኢትዮጵያ በርካታ የከበሩ ማዕድናት ዓይነቶች በብዙ ክምችት አሏት። ከእነዚህም መካከል ሳፋየር፣ ኤምራልድ፣ ኦፓል፣ ጃስበር፣ ኦብሲዲያን፣ ጋርኔት፣ አሜቲስት እና ሲትሪ፣ ኦፓልን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል።
ለመሆኑ የከበሩ ማዕድናትን የከበሩ ያሰኛቸው ምንድነው? ማዕድናቱ የከበሩ የተሰኙበት ዋንኛ ምክንያት አገኛኘታቸው ነው ሲሉ የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። ከሌሎች ማዕድናት አንጻር ሲታይ እንደልብ በበቂ ሁኔታ የማይገኙ መሆናቸው ‹‹የከበሩ›› የሚል ስያሜ እንዲያገኙ አድርጓል ሲሉም ያብራራሉ፡፡
መረጃዎች እንደጠቆሙት፤ ማዕድናቱ የከበሩና በከፊል የከበሩ በመባልም ይከፈላሉ። በከፊል የከበሩ (semi precisions) ከሚባሉት ማዕድናት መካከል ጃስበር፣ ጥቁር ባልጭ /ኦብሲዲያን/፣ ጋርኔት፣ አሜቲስት፣ ሲትሪንን መጥቀስ ይቻላል። የከበሩ (precisions) የሚባሉት ደግሞ በአንጻራዊነት የመገኘት ዕድላቸው እጅግ አነስተኛ የሆኑ እንደ ሳፋየር፣ ኤምራልድ፣ ኦፓል ያሉት ናቸው።
እነዚህን ማዕድናት ከሌሎች የተለየ የሚያደርጋቸው አንዱ ምክንያት በቀላሉ አለመገኘታቸው ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የተገኙት ማዕድናት ያላቸው የጥራት ደረጃ መለያየቱ ነው።
ከከበሩ ማዕድናት መካከል ኦፓል ስንመለከት የሰሜን ሸዋ እና የደላንታ ኦፓል ተብሎ ይለያል። እነዚህ ሁለቱ የኦፓል አይነቶች በጣም ልዩነት ያላቸው ሲሆን፤ በተለይ የደላንታው ኦፓል በአውስትራሊያ ከሚገኘው ኦፓል እኩል በሚባል ደረጃ ላይ ይገኛል። ጥናቶች እንደሚያሳዩት ደግሞ ይህ ኦፓል ከአውስትራሊያው ኦፓል የበለጠ ጥራት አለው፤ ከፍተኛ ዋጋም ይሰጠዋል ሲሉም የዘርፉ ባለሙያዎች ያመለክታሉ።
በሌሎች አካባቢዎችም የተወሰኑ የኦፓል አይነቶች አሉ። ለአብነትም በአፋር አካባቢ ፋየር ኦፓል የተሰኘ ኦፓል ይገኛል። የኦፓሎቹ በተለያየ አካባቢ መገኘት የጥራት ደረጃቸውን ሲወስንም ይስተዋላል። እንደ ሳፋየር፣ ሩቢ አይነት ማዕድናት ደግሞ ከኦፓል እጅግ ከፍ ያለ ዋጋ ያወጣሉ።
በማዕድን ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የማርብል፣ ግራናይትና ጌጣጌጥ ማዕድናት ዴስክ ኃላፊው አቶ ሰለሞን ዘለቀ በአንድ ወቅት በሰጡን መረጃ እንዳመለከቱት፤ በኢትዮጵያ ከ40 በላይ የከበሩ ማዕድናት ይገኛሉ፡፡
ሀገሪቱ እጅግ በጣም የከበሩ በመባል የሚታወቁት ደግሞ የኮረንድም ፣ የቤሪል ፋሚሊን እንዲሁም ሳፋየር እና ኤመራልድ አይነት የከበሩ ማዕድናት አሏት። በተለይ አሁን ላይ የከበሩ ማዕድናት በማምረት የሚታወቀው ወሎ ሲሆን፤ በዚህ በወሎ ኦፓል ላይ በስፋት እየተሠራበት ነው። እነዚህን ማዕድናት በተለያየ መልኩ ለዓለም ገበያ እየቀረቡ መሆናቸውን አቶ ሰለሞን ጠቅሰው፣ የሚያስገኙት ገቢ ሲታይ ግን በጣም አናሳ መሆኑን አስታውቀዋል።
ዘርፉ በሀገሪቱ በደንብ እየታወቀ የመጣው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መሆኑን አቶ ሰለሞን ገልጸው፤ በሌሎች ሀገሮች ግን ኢኮኖሚን በሰፊው እንደሚያንቀሳቅም አስታውቀዋል። በዓለም ደረጃም ከፍተኛ ሀብት በዘርፉ እንደሚንቀሳቀስ ተናግረው፣ ኢትዮጵያም ሰፊ የከበሩ ማዕድናት ሀብት እንዳላት አመልክተዋል። ዘርፉን በስትራቴጂ መምራት ከተቻለ በዓለም ከሚንቀሳቀሰው የዘርፉ ሀብት ኢትዮጵያም ድርሻ ሊኖራት እንደሚችል ጠቁመዋል።
አቶ ሰለሞን የከበሩ ማዕድናት ዘርፉ እዚህ ደረጃ እንዳይደርስ ካደረጉት ምክንያቶች የተወሰኑትንም አመልክተዋል። የመጀመሪያው ምክንያት ቀደም ሲል ዘርፉ በስትራቴጂ አለመመራቱ መሆኑን ጠቅሰው፣ ሁለተኛው ደግሞ ማዕድናቱ ላይ እሴት ጨምሮ ለገበያ ማቅረብ ላይ እምብዛም አለመሠራቱ ነው ብለዋል።
ዘርፉን ወደፊት ለማምጣት በክልሎች ኮሌጆች በመክፈት የሰው ኃይል ለማሠልጠን የተጀመሩ ጥሩ ሥራዎች እንዳሉ ጠቅሰው፤ ይህን በደንብ አጠናክሮ በማስቀጠል ሀገሪቱ ከዓለም ሀገራት ጋር በከበሩ ማዕድናት ግብይቱ መወዳደር እንድትችል መሥራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል። ተመራጭ የምርምር እንዲሁም የሰርተፊኬሽን ማዕከላት እና የመሳሰሉትን መገንባት እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል፡፡
መንግሥት ዘርፉን ለመምራት የሚያስችል ስትራቴጂ ማዘጋጀቱን ጠቅሰው፣ ስትራቴጂው በከበሩና ጌጣጌጥ ማዕድናት ዘርፍ ለታዩ በርካታ ተግዳሮቶች መፍትሔ የሚያመላክት ከመሆኑ ባሻገር ዘርፉን ለመምራት የሚያስችል ሁኔታ እንደሚፈጥርም አቶ ሰለሞን ተናግረዋል።
በከበሩ ማዕድናት ላይ ያነጋገርናቸው አቶ ዘውዱ አድጎአይቼው በከበሩ ማዕድናት ልማትና ግብይት ላይ የረጅም ጊዜ ልምድ አላቸው። ይህን አስመልክቶም የተለያዩ ሥልጠናዎችን ወስደዋል። የኢትዮ ደላንታ ኦፓልና ሌሎች የከበሩ ማዕድናት ላኪ ድርጅት መሥራችም ናቸው። አቶ ዘውዱ ዘርፉ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መሻሻሎችና አበረታች ለውጦች እየታዩበት መሆኑን ይገልጻሉ።
እሳቸው እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ለእነዚህ ማዕድናት ትኩረት ሳይሰጥ ቆይቷል። የማዕድን ሀብቱን በደንብ ለይቶ በማወቅም ሆነ እሴት ጨምሮ ለገበያ ለማቅረብ ብዙ ርቀት አልተሄደም። ዘርፉን በደንብ የሚያወቅና ማዕድናቱን የሚለይ ባለሙያውም አልነበረም። በዚህ የተነሳም ሀገሪቱ ይህን ሀብቷን በሚገባ ሳትጠቀምበት ኖራለች፡፡
እንደ ሀገር በማዕድናቱ ላይ በስፋት ባይሠራም ኅብረተሰቡ ግን ፋይዳቸውን ከጥንት ጀምሮ የሚውቅ በመሆኑ በተለያየ መልኩ በማውጣት ለጌጣጌጥነትና ለሌሎች አገልግሎቶች ሲጠቀምባቸው መቆየቱን ገልጸዋል። በተለይ በገጠር አካባቢ ማዕድኑ ለተለያየ አገልግሎት ይውል እንደነበር መረጃዎችን ዋቢ አድርገው አቶ ዘውዱ አብራርተዋል።
ማዕድናቱ ከጥንት ጀምሮ በኅብረተሰቡ የሚታወቁ በመሆናቸው ለተለያዩ ጥቅሞች ይውሉ ነበር ሲሉ ጠቅሰው፣ ለአብነትም ‹‹ኦፓል›› እያልን በእንግሊዘኛው መጠሪያው የምንጠራው ማዕድን በአማርኛና በግዕዝ ‹‹መርዕግድ›› ተብሎ ይታወቃል ሲሉ አብራርተዋል። ይህን ማዕድንም በተለያዩ የሀገሪቷ አካባቢዎች ሰዎች ይጠቀሙ እንደነበር የታሪክ ድርሳናትም ጠቅሰው ገልጸዋል።
ማዕድናቱ የተለያየ ጥቅም የሚሰጡ ስለመሆናቸው በውጭ ሀገራት ተመራማሪዎችና አጥኚዎች ብዙ ምርምርና ጥናት መደረጉንም አመልክተዋል። ይህን የሚያመላክቱ ጥናቶች በኢትዮጵያም የተደረጉ ቢሆንም፣ በእዚህ ላይ አሁንም ብዙ መሥራት ያስፈልጋል ሲሉ ጠቁመዋል።
ቀደም ሲል ከነበረው ሁኔታ አንጻር ሲታይ በአሁኑ ወቅት በተለየ መልኩ ኅብረተሰቡ ስለማዕድናቱ እያወቀና ግንዛቤውን እያሰፋ መምጣቱን ጠቅሰው፣ ሁሉም ገዥ /ሸማች/ ነው ባይባልም ስለማዕድናቱ የማወቅ ፍላጎቱ እየጨመረ ነው ሲሉ አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ ያላትን የማዕድናት ሀብት ለገበያ በማዋል ተገቢውን ገቢ ማመንጨት ለምን አቃተ? የሚለው ዋንኛ መታየት ያለበት ጉዳይ መሆኑንም ጠቁመዋል። ለዚህ ዋንኛ ተብለው በምክንያት ከሚጠቀሱት መካከል ስለማዕድን ያለው እውቀት አነስተኛ መሆን አንዱ ነው ይላሉ።
በከበሩ ማዕድናት ላይ ስለሚያጠናው ጂኦሞሎጂ (የአሜሪካ የጂኦሞሎጂ ወይም የከበሩ ማዕድናት ተቋም ነው) በሀገሪቱ እየታወቀ የመጣው በቅርቡ ነው ሲሉም ጠቅሰው፣ ይህም ዘርፉ ቀደም ሲል እምብዛም ትኩረት እንዳልተሰጠው እንደሚያመለክት ተናግረዋል። የዘርፉ ትምህርትም ከሌሎች ትምህርቶች ጋር ተደባልቆ እንደሚሰጥ ገልጸው፣ በዘርፉ ተመርቆ የሚወጣ ብዙ የተማረ የሰው ኃይል አለመኖሩም ሌላኛው ምክንያት መሆኑን አመልክተዋል።
ዘርፉን በደንብ የሚያውቅና ማዕድናቱ ላይ እሴት ጨምሮ ወደ ውጭ ለመላክ የሚያስችል ትምህርት ያለው ባለሙያ የለም ማለት ይቻላል ያሉት አቶ ዘውዱ፤ በአሁኑ ወቅት ሥራ ላይ ያሉትም ቢሆኑ ሥራውን የሚያውቁት በልምድ እንጂ በትምህርት ስለአለመሆኑ ራሳቸው ሲናገሩ ይደመጣል ሲሉም አብራርተዋል፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለዘርፉ ትኩረት መሰጠቱን ተከትሎ የተማረ ሰው ኃይል ለማፍራት ጥረት እየተደረገ መሆኑንና በዚህም ለውጦች እየታዩ መምጣታቸውን አስታውቀዋል። ካለፈው ዓመት ጀምሮም 12 የሚሆኑ የመጀመሪያ ጂኦሞሎጂስቶች መመረቃቸውን ጠቅሰው፣ ይህም ጥሩ ጅማሮ እየታየ መሆኑን እንደሚጠቁም ተናግረዋል።
በዘርፉ ለመሠማራት ፍላጎት ያላቸው ብዙ እንዳልነበሩ ጠቁመው፣ ይህም ማዕድኑ ስለመኖሩ ባለማወቃቸው፣ ቢያውቁም ስለጠቀሜታው በደንብ ባለመረዳታቸው የተከሰተ መሆኑን አብራርተዋል። እያደር ግን በዘርፉ ምርምሮችና ጥናቶች እየተካሄዱ፣ ኅብረተሰቡም የማዕድን ሀብቱን እያወቀ በመምጣቱ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዘርፉ የሚሰማሩ አካላት መታየት መጀመራቸውንም አቶ ዘውዱ ጠቁመዋል።
የከበሩ ማዕድናት በዚህ መልኩ ቀስ በቀስ እየታወቁ ወደ ገበያ እየገቡ መምጣታቸውን ጠቅሰው፤ መጀመሪያ ላይ የታወቀው ‹‹ኦፓል›› እንደሆነም ያመላክታሉ። ይሁን እንጂ አሁንም ድረስ መንግሥትም ሆነ ማኅበረሰቡ ለዚህ ማዕድን የሚገባውን ያህል ትኩረት ሰጥተውታል ተብሎ እንደማይታሰብ ጠቁመዋል።
አቶ ዘውዱ እንዳብራሩት፤ የከበሩት ማዕድናት የከበሩ (precisions) እና በከፊል የከበሩ (semi precisions) በሚል በሁለት ተከፍለው ይታወቃሉ። የከበሩ ማዕድናት በእጅጉ ተፈላጊና ውድም ናቸው፤ የመገኘት ዕድላቸው ግን በጣም አነስተኛ ነው። በከፊል የከበሩ ማዕድናት ማግኘት ግን ከከበሩ ማዕድናት አንጻር ሲታይ ብዙም አስቸጋሪ አይደለም።
የከበሩ ማዕድናት መለየት የሚያስችሉ በርካታ መንገዶች እንዳሉም አቶ ዘውዱ ጠቁመዋል። እነዚህ ዘዴዎች ማዕድናቱ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ እንደሚያስችሉም ይገልጻሉ። የከበረ ማዕድን በዓለም አቀፍ ደረጃ ጥራቱ ተረጋግጦ ገዥ ሊያገኝ የሚችለው እንደ ጂአይኤ ባለ ድርጅት ተረጋግጦ ሰርተፊኬት መለያ ወይም ብራንድ ሲሰጠው መሆኑን ያመለክታሉ።
‹‹በሀገራችንም እንደዚህ አይነት ተቋማት ቢኖሩ ማዕድናቱን የራሳችን ብራንድ ኖሯቸው እንዲሸጡ ማድረግ እንችላለን›› ሲሉም ጠቁመው፣ ይህ እንዲሆን ደግሞ በዘርፉ ላይ የተሠማሩ ሁሉም አካላት ጥረት ሊያደርጉ ይገባል፤ ይህ ሲሆን ውጤታማ መሆን እንችላለን ብዬ አምናለሁ›› ብለዋል።
አቶ ዘውዱ እንደገለጹት፤ በከበሩ ማዕድናት እሴት ጭመራ ላይ ብዙ ሊሠራ ይገባል፤ እሴት መጨመር ጥሬ እቃውን ከማለስለስ ይጀምራል። ጥሬ እቃው ከለሰለሰ በኋላ ደግሞ የተለያየ ቅርጻቅርጽ እንዲወጣለት ይደረጋል፤ በጌጣጌጥ መልክ እንዲታቀፍ በማድረግም ለአንገት፣ ጆሮ፣ እጅ፣ ለራስ፣ ለእግር እና ለመሳሰሉት ጌጥነት እንዲውል ይደረጋል።
ኢትዮጵያ የከበሩ ማዕድናቷን ለዓለም በሚገባ በማስተዋወቅ የራሷን ብራንድ ምርቶች ለዓለም ገበያ ማቅረብ ይጠበቅባታል። በተለይ እሴት ጭምራ ላይ በትኩረት መሥራት አለባት።
የኦንላይን የገበያ ሥርዓት በመዘርጋትም ምርቶቹን በተደጋጋሚ ማስተዋወቅ ያስፈልጋል ሲሉም አስገንዝበው፣ የማዕድን ዘርፉ አካላት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋት እንደሚያስፈልግም ይገልጻሉ።
እንደ አፍሪካ በተለያዩ ሀገራት የኦንላይን የገበያ ሥርዓቶች በመዘርጋት ምርቶችን በኦንላይን ገበያ በማውጣት የማስተዋወቅ ሥራ የሚሠራ ድርጅት እንዳለ ጠቅሰው፤ እንደዚህ አይነት ሥራዎችን የሚሠሩ ድርጅቶች በኢትዮጵያም ቢኖሩ መልካም መሆኑንም ጠቁመዋል። ማዕድን አቅራቢዎችንና ላኪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የማገናኘት ሥራ መሥራት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የከበሩ ማዕድናትን የማውጣቱ ሥራ አሁንም ብዙም ከባሕላዊ መንገድ እንዳልተላቀቀ ጠቅሰው፣ ቴክኖሎጂን የመጠቀም ዕድልን ማስፋት እስካልተቻለ ድረስ ዘርፉን በሚፈለገው ልክ ወደፊት ለማስቀጠል እንደሚያስቸግር ይገልጻሉ። ለከበሩ ማዕድናት ትኩረት በመስጠት ረገድ ለውጦች እንዳሉ ያመለከቱት አቶ ዘውዱ፣ ከዘርፉ የበለጠ ተጠቃሚ ለመሆን መንግሥትም ሆነ በዘርፉ የተሠማሩ አካላት ኃላፊነታቸውን መወጣቸውን ይበልጥ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ዓርብ የካቲት 21 ቀን 2017 ዓ.ም