
አዲስ አበባ፣ መንግሥት ለሕዝብ ጤና እና ደኅንነት በተሰጠው ልዩ ትኩረት በኢትዮጵያ የትምባሆ አጫሾች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ተገለፀ።
የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን፣ ከኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ ከዓለም የጤና ድርጅትና ሌሎችም አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን እድሜያቸው ከ15 ዓመት በላይ በሆናቸው ሰዎች ላይ ያካሄደው የትምባሆ አጠቃቀም ጥናት ውጤት ትናንት ይፋ ሆኗል።
በመድረኩ ላይ የጤና ሚኒስቴር ዴኤታው ዶክተር ደረጄ ዱጉማ እንደገለፁት፣ በአሁን ወቅት በኢትዮጵያ ከተላላፊ በሽታዎች በተጨማሪ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መጋለጥ ዋነኛ ምክንያት የሆነው ሲጋራ ማጫስና ሌሎች የትምባሆ ምርቶችን መጠቀም ነው። ትምባሆም ካንሰር፣ ሳንባና ልብን ጨምሮ ለተለያዩ ከፍተኛ የጤና ቀውሶች ከፍ ሲልም ለሞት የሚዳርግ ነው።
መንግሥት በዓለም አቀፍ ደረጃ በፍጥነት እየተዛመተና በሰው ልጆች ጤና ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እያስከተለ ያለውን የትምባሆ ተጠቃሚዎች ቁጥር ለመግታትና በዜጎች ላይ ከሚያስከትላቸው መጠነ ሰፊ ችግሮች ለመጠበቅ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል ብለዋል።
በጠንካራ የሕግ ማሕቀፍና በቅንጅታዊ የቁጥጥር ሥራዎች በኢትዮጵያ የትምባሆ አጫሾች መጠንን በመቀነስ ረገድ ተጨባጭ ለውጦች እያስመዘገበች መምጣቷን ያስገነዘቡት ዶክተር ደረጄ፤ ይሁንና አሁንም ቢሆን ከችግሩ ስፋት አንፃር ከዚህም በላይ መሥራት የግድ መሆኑን ተናግረዋል።
የትምባሆ ተጠቃሚና ዋነኛ ተጎጂዎች ወጣቶችና ዋነኛ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሾች እንደመሆናቸው የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራዎችን በቀጣይም በቅንጅትና በትኩረት መሥራት የግድ ስለመሆኑ ያስገነዘቡት ዶክተር ደረጄ፣ በተለይ በመንግሥት ተቋማት፣ በሕዝብ ትራንስፖርትና ሌሎችም የሕዝብ መሰብሰቢያ አካባቢዎች ሕጉን ከማስከበርና ከማክበር አንፃር እንዲሁም የኅብረተሰብ ግንዛቤን ከማጎልበት አንፃር በትኩረት መሥራት እንደሚያስፈልግም አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሄራን ገርባ በበኩላቸው፣ መንግሥት ለሕዝብ ጤናና ደኅንነት በተሰጠው ልዩ ትኩረት ኢትዮጵያ ዝቅተኛ ሲጋራ የማጨስ ምጣኔ ካለባቸው ሀገራት አንዷ ሆና እንድትቀጥል ማድረግ መቻሉንም አስረድተዋል።
በ2016 ዓ.ም በተጠና ጥናት በኢትዮጵያ በአጠቃላይ የትምባሆ ተጠቃሚዎች ቁጥር 5 በመቶ እንደነበር ያስታወሱት ዋና ዳይሬክተሯ፤ በተከናወኑ ዘርፉ ብዙ የትምባሆ ቁጥጥር ሥራዎች ይህን አኃዝ ከመጨመር ይልቅ አሁን ላይ ወደ 4 ነጥብ 6 በመቶ መቀነሱንም ጠቁመዋል።
ሰዎች በሚሠሩባቸው የሥራ ቦታዎች የነበረው ለትምባሆ ሁለተኛ ወገን አጫሽነት የመጋለጥ ምጣኔ ከ29 ነጥብ 3 በመቶ አሁን ላይ ወደ 19 ነጥብ 8 መቀነሱንም የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሯ፣ የሴት አጫሾች ቁጥርም በ 2016 ከነበረው ከ አንድ ነጥብ 2 በመቶ በከፍተኛ መጠን ቀንሶ ወደ 0 ነጥብ 5 በመቶ ወርዷል›› ብለዋል።
ከዚህ ቀደም መንግሥት ከዚህ ኢንዱስትሪ ውስጥ ዋነኛ የሼር ባለቤት፣ የትንባሆ ኢንዱስትሪውም ከፍተኛ ግብር ከፋይ እንደነበር ያስታወሱት ዋና ዳይሬክተሯ፣ ‹‹አሁን ላይ መንግሥት በዚህ መልኩ የሚመጣን ጥቅም ወደ ጎን በመተው ሙሉ በሙሉ ከኢንዱስትሪው ወጥቷል፣ ከዚህ ባለፈ ሌሎች ኢንዱስትሪዎች እንዳይስፋፉ ጫና በማድረግ ችግሩን ለመከላከል ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር እያስመሰከረ ይገኛልም፣ ለዚህም እውቅና ሊቸረው ይገባል›› ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ኃይሉ በበኩላቸው፣ የትምባሆ አጫሾችን ቁጥር በመቀነስ ረገድ ጥንካሬውን ማስቀጠል ድክመቶች ላይ ይበልጥ መሥራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
መረጃዎች እንደሚያመላክቱ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ በዓመት 8 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በትምባሆ ምክንያት ለኅልፈት ይዳረጋሉ። ከዚህ ውስጥ 1ነጥብ 2 ሚሊዮን ቀጥተኛ አጫሽ ሳይሆን ለጭሱ ተጋላጭ በመሆን ብቻ ለሞት ይዳረጋሉ።
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ዓርብ መጋቢት 26 ቀን 2017 ዓ.ም