ቋሚ ኮሚቴው በወርቅ የተገኘውን እመርታ በሌሎች ማዕድናት መድገም እንደሚገባ አሳሰበ

አዲስ አበባ፡- በበጀት ዓመቱ ባለፉት ስምንት ወራት በወርቅ ምርት የተገኘውን እመርታ በሌሎች ማዕድናት በመድገም የዘርፉን የሥራ ዕድል ፈጠራ ማሳደግ እንደሚገባ የኢንዱስትሪና የማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢንዱስትሪና የማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የማዕድን ሚኒስቴርን የስምንት ወራት የሥራ አፈፃፀም ሪፖርት ገምግሟል፡፡

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በስምንት ወራት ውስጥ ስድስት ቶን ወርቅ አምርቶ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ አቅዶ 22 ነጥብ አምስት ቶን ወርቅ ለውጭ ገበያ ማቅረቡ ከፍተኛ ውጤት የተገኘበት መሆኑን ቋሚ ኮሚቴው ተናግሯል፡፡

ኢንዱስትሪና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ፍቃዱ መንግሥቱ (ዶ/ር) በዕለቱ እንደገለጹት፤ በማዕድን ዘርፉ እየተፈጠረ ያለው የሥራ ዕድል አነስተኛ ነው፡፡

የማዕድን ዘርፍ እንደ ሀገር ለኢኮኖሚ ሁለንተናዊ ግንባታ ትልቅ ግምት ከተሰጣቸው አምስት ዋና ዋና ዘርፎች መካከል ነው ያሉት ምክትል ሰብሳቢው፤ ይህንንም ታሳቢ በማድረግ በዘርፉ ለዜጎች የሚፈጠረው የሥራ ዕድል ማሳደግ ይገባል ብለዋል፡፡

በተለይ ከወርቅ ወጪ ንግድ አንጻር የተገኘው አበረታች ውጤት ማስቀጠልና ሀገሪቱ በጌጣጌጥ ማዕድናት ላይ ከፍተኛ አቅም ያላት በመሆኑ ባለው ልክ ተጠቃሚ ለማድረግ መሥራት ያስፈልጋል ሲሉ አሳስበዋል፡፡

እንደ ፈቃዱ (ዶ/ር) ገለጻ፤ ሀገርን ባለው ልክ ተጠቃሚ ለማድረግ በዘርፉ ያሉ የአሠራር ክፍተቶች መሙላትና በሕገ-ወጥ መንገድ የተሰገሰጉ ተዋናዮች ላይ ርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል፡፡ በተጨማሪም ብልሹ አሠራሮችን ማስወገድና ዘመኑን የዋጁ አዳዲስ አሠራሮችን መዘርጋት ወሳኝ ነው፡፡

ከሥራ ዕድል ፈጠራ አኳያ በቂ ባለመሆኑ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ይበልጥ ትኩረት ሊያደርግበት እንደሚገባ ጠቅሰው፤ በሌሎች ማዕድናት ላይ እንደሀገር ያለውን ዕድል አሟጦ መጠቀም ተገቢ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ተኪ ምርትን ለማሳደግ የሕግ ማሕቀፍ የማወጣት፤ ያለውን የገበያ ትስስር ችግርን ለመፍታት በጥናት የተለየ ሥራ መሥራት ይገባል ሲሉ ገልጸዋል። በተጨማሪም የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የአፈር አሲዳማነትን ማከም ይገባልም ብለዋል፡፡

በቋሚ ኮሚቴው የማዕድን ዘርፍ ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ደስታዬ ጥላሁን በበኩላቸው በስምንት ወሩ ከወጪ ንግድ የተገኘው አንድ ነጥብ 88 ቢሊዮን ዶላር ከፍተኛ ውጤት ቢሆንም ከወርቅ ውጪ በሁሉም ዘርፍ እቅዱን ማሳካት ቢቻል ለሀገር ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት የሚቻልበት ነው ብለዋል፡፡

ከቅንጅታዊ አሠራር አኳያ ያሉ ክፍተቶች በመሙላት ከዘርፉ ተዋናዮች ጋር ጥብቅ ቁርኝት በመፍጠር መሥራት ወሳኝ መሆኑንም ነው ወይዘሮ ደስታዬ የተናገሩት፡፡

የሥራ ዕድል ፈጠራ ውስንነት የመጣው ማዕድን የማምረት ሂደቱ በማሽን በመደገፉ ነው ያሉት ደግሞ የማዕድን ሚኒስትር ኢንጅነር ሀብታሙ ተገኝ ፤ ማዕድናት በሚገኙባቸው አካባቢዎች ያሉ ኅብረተሰብ ለማስጠቀምና ይበልጥ የሥራ ዕድል እንዲፈጥር ለማስቻል ከማኅበረሰቡ እንዲሁም ከየአካባቢው አስተዳደሮች ጋር ሲሠራ መቆየቱን ጠቅሰዋል፡፡ ወደፊትም ይህ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው ዘርፉ የተሻለ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እንዲኖረው የተቀናጀ አሠራርን እየተከተለ መሆኑን ጠቁመው፤ አነስተኛ የወርቅ አምራች ኢንተርፕራይዞች ለኩባንያዎች ምርታቸውን እንዲያቀርቡ በማድረግ ተጠቃሚነታቸውን እንዲያድግ እየተደረገ ነው፤ በዘርፉም የሚጠበቀውንም የሥራ ዕድል ለመፍጠር በትኩረት ይሠራል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ልጅዓለም ፍቅሬ

አዲስ ዘመን ዓርብ መጋቢት 26 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You