ከወጪ ንግድ ስድስት ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት በትኩረት እየተሠራ ነው

– አዲሱ የንግድ ፖሊሲ ተወዳዳሪነትን ያሳድጋል

አዲስ አበባ:– ዘንድሮ በዓመቱ መጨረሻ የወጪ ንግድ ገቢን ስድስት ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ እንደሚገኝ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሣሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለጹ። አዲሱ የንግድ ፖሊሲም ተወዳዳሪነትን የሚያሳድግ መሆኑ ተጠቁሟል።

ካሣሁን ጎፌ (ዶ/ር) ሚኒስቴሩ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ረቂቅ የኢትዮጵያ የንግድ ፖሊሲ የማጠቃለያ ግብዓት ማሰባሠቢያ መድረክ ትናንት ሲያካሄድ እንዳሉት፤ ባለፉት ስምንት ወራት ከወጪ ንግድ አራት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል። በቀሪ ጊዜ ገቢውን በማሳደግ ስድስት ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ ትኩረት ተሰጥቷል ብለዋል።

በ2010 ዓ.ም ከወጪ ንግድ የገባው ሁለት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ዶላር እንደበር አስታውሰው፣ በ2017 በጀት ዓመት መጨረሻ የወጪ ንግድ ግኝትን ከስድስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ለማድረስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል። መንግሥት የንግዱን ዘርፍ ተወዳዳሪ እና ተገማች ለማድረግ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱንም ካሣሁን (ዶ/ር) አመልክተዋል።

ተቋሙ ከተመሠረተ ጀምሮ በተለያዩ ስያሜዎች እየተጠራ 117 ዓመታት ማሳለፉንና እስካሁን የንግድ ፖሊሲ እንዳልነበረውም ገልጸው፤ እየተረቀቀ ያለው ፖሊሲ ከነባራዊ ሁኔታ ጋር የተዛመደ፣ የወደፊት አቅጣጫን መሠረት ያደረገ መሆኑንም አመልክተዋል። ቶሎ ፀድቆ ወደ ተግባር እንዲገባ ይደረጋልም ብለዋል።

ተገማች የገበያ ዕድሎችን በማስፋት ጥራት ያላቸውን ምርቶችን በማቅረብ ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያስችል ሥራ መሥራት ተገቢ መሆኑን በማመን እንቅስቃሴ መጀመሩን አስገንዝበዋል።

የወጪና ገቢ ንግድ ተወዳዳሪ መሆን የሚቻለው ጥራትን ማዕከል ሲያደርግ መሆኑን የጠቆሙት ካሣሁን (ዶ/ር)፣ ይህንን በመገንዘብ ስምንት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር ወጪ ተደርጎ የተገነባው የጥራት መንደር ተመርቆ አገልግሎት መጀመሩ ለተግባሩ በበጎነት እንደሚጠቀስ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ባካሄደችው 5ኛውን የዓለም ንግድ ድርጅት የሥራ ቡድን ስብሰባ ኢትዮጵያ የድርጅቱ አባል መሆን እንደምትችል ተጨባጭ ተስፋ የታየበት እና በስኬት የተጠናቀቀ ድርድር መካሄዱን ተናግረዋል። ቀሪ ሥራዎችን ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የእሁድ ገበያዎችን በማስፋፋት ሸማቹ በተመጣጣኝ ዋጋ ምርትና አገልግሎት ማግኘት የሚያስችለውን ሥራ መሠራቱን አመልክተዋል። የንግድ ፍቃድ ለማውጣት ይፈጅ የነበረውን ጊዜ በመቀነስ አሠራሩን ምቹ ለማድረግ መቻሉንም ተናግረዋል።

የተዘጋጀውን ረቂቅ የኢትዮጵያ የንግድ ፖሊሲ ሰነዱን ያቀረቡት የኢትዮጵያ ነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ደስታው መኳንንት (ዶ/ር)፣ ፖሊሲው ላይ ከተቀመጡት አቅጣጫዎች መካከል ከፍተኛ የወጪ ምርት የሚመረትባቸው አካባቢዎች ላይ መሠረተ ልማት እንዲሟላ፣ የኮሪዶር ልማት እንዲተገበር እንደሚደረግ አመልክተዋል።

ቀጣናዊ ትስስርና ውሕደትን ለማጠናከር እንዲሁም ሀገራዊ ተወዳዳሪነትን ለማሻሻል እንዲቻል የመንገድ፣ የባቡር መሠረተ ልማት እና ዲጂታል ትስስርን ጨምሮ ቀጣናዊ የልማት ትብብሮች ላይ ሀገርን የሚመጥን ተሳትፎ ለማድረግ አቅጣጫ መቀመጡን አመልክተዋል።

ድንበር ተሻጋሪ ንግድን ቀላል እና ቀልጣፋ ለማድረግ የተቀናጀና ዘመናዊ መሠረተ ልማት ግንባታና የተቀናጀ የአሠራር ሥርዓት መዘርጋትን የፖሊሲ ሰነዱ ማመልከቱንም ነው ደስታው (ዶ/ር) የተናገሩት።

ዘላለም ግዛው

አዲስ ዘመን ዓርብ መጋቢት 26 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You