
ሐረር፡- የጀጎል ቅርስ እድሳት ለ‹‹ሹዋል ኢድ›› በዓል ልዩ ድምቀት እንደሚሰጥ የሐረሪ ክልል ባህል፣ ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ፡፡
የሐረሪ ክልል ባህል፣ ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ተወለዳ አብዱሽ፤ የሐረር ከተማን የልማት ሥራዎች እየጎበኙ ላሉ ጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ፤ ነገ ቅዳሜ የሹዋል ኢድ በዓል ‹‹የቅርስ ሀብቶቻችን ለቱሪዝም እድገታችን›› በሚል መሪ ሃሳብ በታላቅ ድምቀት ይከበራል፡፡ የጀጎል ቅርስ እድሳት ለሹዋል ኢድ በዓል ትልቅ ድምቀት ይሰጣል፤ የሹዋል ኢድን በዓል በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብም በጀጎል ቅርስ ላይ የተደረገው እድሳት አዎንታዊ አስተዋፅዖ ይኖረዋል ብለዋል፡፡
ሐረር ትናንት ከነበራት የቱሪስት ፍሰት አሁን ላይ ያላት እየተሻሻለ መጥቷል ያሉት አቶ ተወለዳ፤ ለዚህም አንዱ ምክንያት ሹዋል ኢድ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡
ሹዋል ኢድ በመላው ዓለም ያሉ ዲያስፖራዎች እና የሀገሬው ነዋሪዎች የሚሳተፉበት ደማቅ በዓል እንደሆነ ጠቅሰው፤ የጀጎል ቅርስ እድሳትና በከተማዋ እየተከናወነ ያለው የኮሪዶር ልማት የጎብኚዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲጨምር የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡
እድሜ ጠገቡ የጀጎል ቅርስ ከዚህ በፊት ደኅንነቱና ንጽሕናው ተጠብቆ በእንክብካቤ አልተያዘም ነበር ያሉት ኃላፊው፤ በዚህም የተነሳ ለነዋሪዎችም ይሁን ለጎብኚዎች ምቹ አልነበረም ብለዋል፡፡
የክልሉ ፕሬዚዳንት በሰጠቱ የሥራ አቅጣጫ መሠረት ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ ቅርሱን የማልማት ሥራ ሲሠራ መቆየቱን አውስተው፤ በዚሁ መሠረት በመጀመሪያው ዙር ለጀጎል የግንብ አጥር አደጋ የሆኑና ከግንቡ ጋር ተያይዘው የተሠሩ ግንባታዎችን፣ ሕገ-ወጥ ንግዶችን እና አጥሮችን በማንሳት በግንቡ ዙሪያ ከ6 ሺህ ስኴየር ሜትር በላይ የአረንጓዴ ሥፍራ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት፡፡
በሁለተኛው ዙር የልማት ሥራም ከ7 ኪሎ ሜትር በላይ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች እንዲለሙ መደረጉን አመልክተው፤ በእድሳት ሥራው ወጣቶች የነዋሪውን ባህላዊ እሴት የሚያሳዩ የቅርጻቅርጽና የፈጠራ ስዕሎችን በመሥራት አስተዋፅዖ ማበርከታቸውን ተናግረዋል፡፡ በዚህም ለበርካቶች የሥራ ዕድል መፈጠሩን ጠቅሰዋል፡፡
በአሁኑ ገዜ በጀጎል መልሶ ማልማት ሦስተኛው ዙር መርሐ-ግብር እያንዳንዱ ሴክተር የሥራ ክፍፍል አድርጎ 5 ነጥብ 1 ኪሎ ሜትር የመንገድና የግንብ እድሳት ሥራዎችን እያከናወነ ስለመሆኑም ገልጸዋል፡፡
ሥራው ምንም አይነት የመንግሥት በጀት ያልተበጀተለት ነው ያሉት ኃላፊው፤ በዲያስፖራዎች፣ በከተማውና በገጠሩ ማኅበረሰብ እንዲሁም በሴክተር መሥሪያ ቤቶች ድጋፍ አድራጊነት እየተሠራ ያለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የኮሪዶር ልማቱን ከቱሪስት መዳረሻዎች ጋር አስተሳስሮ በማልማት ጎብኚዎች የበለጠ ሐረርን እንዲያውቋት፣ እንዲወዷትና እየተመላለሱ እንዲጎበኟት እየተሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡
ነገ ቅዳሜ በሚከበረው ‹‹ሹዋል ኢድ›› የአጎራባች ሕዝቦች ወንድሞችና እህቶች ሐረር ከተማ ላይ ይከትማሉም ብለዋል፡፡ ከክብረ በዓሉ በተጓዳኝ የፓናል ውይይት፣ የጀጎል ሓዋርድ ሥነ-ሥርዓት እና ሹዋል ኢድን የተመለከቱ የጎዳና ላይ ትርዒቶች የሚከናወኑ እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡
በመጨረሻም ኅብረተሰቡ ቅርሶችን ለመንከባከብና ሐረር ከተማን ለማዘመን እያደረገ ያለውን አስተዋፅዖ አመስግነው፤ በሩቅም በቅርብም ያሉ ሰዎች በሕዝቡ ተሳትፎ የለማችውን የሐረር ከተማ እየመጡ እንዲጎበኙ እና በሹዋል ኢድ በዓል ላይ እንዲሳተፉ አቶ ተወለዳ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ዓርብ መጋቢት 26 ቀን 2017 ዓ.ም