ነባሩን ለውጥ የተካው አዲስ ለውጥ

የ2010ሩ ለውጥ ከኢትዮጵያ ሁለተኛው ዘመናዊ የፖለቲካ ዘመን (የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ዘመናዊ የፖለቲከ ለውጥ ከቀዳማዊ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ እስከ 1966 አብዮት ያለው ነው) ለውጦች በአንድ መሠረታዊ ነገር ይለያል። የ66ቱ ትውልድ ባልሆነ አዲስ ትውልድ የመጣ ለውጥ በመሆኑ።

ከ1966 ጀምሮ ኢትዮጵያ ውስጥ ሁለት ዋና ዋና የለውጥ ሙከራዎች እና ሁለት ዋና ዋና ለውጦች ነበሩ። ከሁለቱ የለውጥ ሙከራዎች አንዱ በ66ቱ ትውልድ ወታደራዊ መሪዎች ሲሞከር፣ ሁለተኛው በ66ቱ ትውልድ የፖለቲካ መሪዎች ተሞክሯል።

የመጀመሪያው የለውጥ ሙከራ የደርግን መንግሥት ለመለወጥ በግንቦት 8 ቀን 1981 የተደረገው መፈንቅለ መንግሥት ነው። ይሄም መፈንቅለ መንግሥት በዋናነት በ66ቱ ትውልድ ወታደራዊ መሪዎች የተቀናበረ ነበር። ዋነኛው መሪ የነበሩት ኤታማዦር ሹሙ ጄኔራል መርዕድ ንጉሤ የነገሌው ጦር በ1966 ሲያምጽ ከጀርባ የነበሩ የጦር መኮንን ነበሩ። ደርግ ሲቋቋምም የደርጉ ሥራ አስፈጻሚ አባል ሆኑ። ልጅ ኢያሱ በተቀየሩበት፣ ንግሥት ዘውዲቱ በተገደሉበት፣ በኋላም ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ከሥልጣን በተወገዱበት መንገድ ነው መፈንቅለ መንግሥቱም የተመራው። የጊዜ እንጂ የእሳቤ ለውጥ የለውም።

ሁለተኛው የኢሕአዴግ መንግሥት በሰላማዊ ትግል በምርጫ ካርድ ለመለወጥ በ1997 የተካሄደው ሙከራ ነው። ይሄም በዋናነት በ66ቱ ትውልድ የፖለቲካ መሪዎች የተከናወነ ነው። ያም ቢሆን ግን መሪዎቹ ከ66ቱ የተለየ ሰላማዊ መንገድ ለመከተል ሞክረው ነበር። በውስጣቸው ግን ከ66ቱ ትውልድ ሤራና ሸፍጥን የወረሱ፣ በጥሎ ማለፍ የተካኑ ስለነበሩበት፣ ከሌሎች ፈተናዎች ጋር ተደምሮ ሳይሳካ ቀረ።

የመጀመሪያው የተሳካ ለውጥ የ1966ቱ አብዮት ነው። ይህ የኢትዮጵያን ነባር ሥርዓተ መንግሥት የቀየረ ሥር ነቀል አብዮት፣ በሁለቱ የ66ቱ ትውልድ ጥምረት የተካሄደ ነው። በፖለቲካዊና በወታደራዊ የ66ቱ ትውልድ። ሁለቱም በየራሳቸው መንገድ ተሰልፈው ንጉሣዊውን ሥርዓት ቢጥሉም፣ ሁለቱ አብረው ለመቀጠል ግን አልቻሉም። ንጉሡን በጋራ ከጣሉ በኋላ እርስ በርሳቸው ተጋደሉ። በኋላም ወታደራዊ መሪዎች ፖለቲካዊ መሪዎችን በጠመንጃ አሸነፉ።

በ66ቱ ወታደራዊ መሪዎች የተሸነፉት፣ የ66ቱ የፖለቲካ መሪዎች፣ ለአራት ተከፈሉ። ጥቂቶች ከደርግ ጋር ተግባብተው ቀጠሉ። ሌሎች ወደ ውጭ ተሰደዱ። ሌሎች ደግሞ አንድም ተገደሉ ወይም ታሠሩ። የቀሩት ግን ነፍጥ አንሥተው ወደ ጫካ ገቡ።

የመጀመሪያው (የ66ቱ) ለውጥ፣ በሀሳብ ቢጀመርም የተደመደመው በነፍጥ ነበር። በኋላም ወንበሩን የያዙትን የ66ቱን ልጆች፣ ሌሎቹ የ66ቱ ልጆች ተመልሰው መጥተው በነፍጥ አሸነፏቸው። 66ቱ በ66ቱ ተሸነፉ። 1983 ማለት ይሄ ነው።

አዙሪቱ ቀጠለ።

ሁለተኛው ዙር የ66ቱ ትውልድ በነፍጥ ወንበሩን ሲይዝ፣ ሌሎቹ የ66ቱ ትውልድ ደግሞ በከፊል ተመሳሳይ ዕጣ ገጠማቸው። የተወሰኑት ወደ ወህኒ ተወረወሩ፤ ሌሎች ተሰደዱ፤ ጥቂቶች ከኢሕአዴግ ጋር አብረው መሥራት ቀጠሉ፤ ጥቂቶችም በተቃዋሚዎች ጎራ ተሰልፈው ፓርቲ መሠረቱ። ቀሪዎቹ ወደ ትጥቅ ትግል ገቡ። ይሄ ግማሽ ምዕት ዓመት የወሰደ የፖለቲካ አዙሪት ነው።

የ2010 ለውጥ ይሄንን የአዙሪት ቀንበር የሰበረው ነው።

የ2010 ለውጥ በዋናነት ከ66ቱ ትውልድ ውጭ በሆነ አስኳል አመራር የመጣ ለውጥ ነው። ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ከ66ቱ ጥንተ አብሶ (የቆየ መርገም) መላቀቋን ያየችበት ለውጥ ነው። አንዱ የለውጡ ፈተናም ይሄው ነው። እስከ የ2010ሩ ለውጥ የኢትዮጵያ ፖለቲካ በ66ቱ ተጽዕኖ ውስጥ ይኖር ነበር። ፖሊት ቢሮ፣ ማዕከላዊ ኮሚቴ፣ መሠረታዊ ድርጅት፣ ሕዋስ፣ ነጻ አውጪ፣ ታጋይ፣ ወዘተ. የሚሉ አደረጃጀቶች በገዥውም፤ በተቃዋሚውም፤ በታጣቂውም ፓርቲዎች ውስጥ ነበሩ። ርዕዮተ ዓለሙ ከኮሙኒዝም እሳቤ አይወጣም። ጠላትና ወዳጅ፣ የሚመታና የሚታቀፍ፣ የሚለው ፍረጃ የፖለቲካ ባሕሉ ነጭ የደም ሴል ነው።

የ2010ሩ ለውጥ ከ66ቱ ትውልድ በተግባርም በአስተሳሰብም በተነጠለ አዲስ ትውልድ የመጣ ለውጥ በመሆኑ፣ አብዮት የሚለውን ነባር ሾተላይ አስቀርቷል። ኢትዮጵያ ውስጥ ነባሩን እየጠራረጉና እየደመሰሱ አዲስ ነገር ለመሥራት የመሞከር አባዜ ሀገራችንን ዋጋ አስከፍሏታል። ከሦስት ሺ ዘመን በላይ የነጻነት ታሪክ ያላትን ሀገር በየሃያ እና በየሠላሳ ዓመቱ እንደ አዲስ ጀማሪ አድርጓታል። ስለዚህም ነባሩን ነቅሎ አዲስ ተክሎ ከሚሄድ ከአብዮትም ሆነ በቀርፋፋነቱ ተስፋ አስቆራጭ ከሆነ ከዘገምተኛ ለውጥ ይልቅ በሪፎርም መንገድ መጓዙ የተሻለ ነው ብሎ የለውጡ አመራር አመነ። ያልተሞከረውን እንሞክረው የሚል እሳቤ መጣ። በተመሳሳይ መንገድ ሄዶ፣ የተለየ ውጤት መጠበቅ ቀረ።

በ2010 ከዚህ ባሕል የወጣ አዲስ አመራር ሲመጣ፣ በነባሩ የፖለቲካ ልሂቅ ዘንድ ሦስት ዓይነት ስሜት ተፈጠረ።

የመጀመሪያው እፎይታ ነው። ካለፈው ሥሪት ለመላቀቅ የሚፈልጉ ነባር የፖለቲካ ልሂቃን እፎይታ ተሰምቷቸዋል። እነዚህ የ66ቱ ትውልድ በሠራው ስሕተት የሚጸጸቱና አዲስ መንገድ የሚፈልጉ ናቸው። ግን በቁጥር እጅግ ጥቂቶች ነበሩ። ሁለተኛዎቹ ደነገጡ። እነርሱ ጥርስ ያልነቀሉበት አዲስ የፖለቲካ መንገድ መምጣቱን አልወደዱትም። ከፖለቲካ ጨዋታ ውጭ የሚሆኑ መሰላቸው። ስለዚህም በጥርጣሬና በሥጋት ተመለከቱት። ሦስተኛዎቹ በተዛባ ደስታ ተቀበሉት። የደስታው መነሻ ሁለት ነው። አንደኛው የለውጡን አስኳል አመራር ዝቅ አድርጎ (አሳንሶ) ከመገመት የመጣ ነው። ለእነዚህ የፖለቲካ መለኪያቸው የ66ቱ መንገድ ነው። በ66ቱ ጠበል ያልተጠመቀውን ሁሉ የፖለቲካ ሀሁ እንዳልገባው አድርገው ይቆጥሩታል። ስለዚህ በቀላሉ በእነርሱ ቁጥጥር ሥር ሊያውሉት እንደሚችሉ አመኑ። “የተዛባ ደስታ” የተባለውም ለዚህ ነው።

ሁለተኛዎቹ ለውጡን በየራሳቸው መንገድ በመውሰዳቸው የተነሣ ነው። የተዛባው ደስታ የመጣውም አንዱ ከዚህ ነው። ቀዳሚዎቹ ከለውጡ ጋር ተጓዙ። ሁለተኛዎቹ ምንሽርም ግርግርም አነሡ። ሦስተኛዎቹ ወደራሳቸው መንገድ ለውጡን ሊለውጡት ታገሉ።

ለውጡን ለመለወጥ ከታገሉት አንደኛዎቹ ለውጡን በየራሳቸው መንገድ የተረጎሙት ናቸው። አንዳንዶች የእገሌ አካባቢን ወይም ማሕበረሰብን ጥቅም ብቻ ለማስከበር የመጣ ለውጥ አድርገው ወሰዱት። ሌሎቹ ደግሞ የሆነን አካባቢ እሳቤ ለማሳካት እንደመጣ ቆጠሩት። ሁሉም እንደ ሚስት ለውጡን የየራሳቸው ብቻ አድርገው ሊነጥቁት ከጀሉ።

ሌሎቹ ደግሞ የእነርሱን ነባር የፖለቲከኛነትና የታጋይነት ክህሎት ተጠቅመው የለውጡን አስኳል አመራር ወደፈለጉበት መንገድ ሊዘውሩት እንደሚችሉ ገመቱ። ፍኖተ ካርታና ካልኩሌተር አዘጋጅ አድርገው ራሳቸውን ሾሙ። “እባብ ግደል:: እባቡንም በትሩንም ወደ ገደል” እንደሚባለው የለውጡ አስኳል አመራር ወያኔን ታግሎ ካስወገደላቸው፤ እነርሱ ደግሞ የለውጡን አመራር በቀላሉ መዘወር ወይም መቀየር እንደሚቻላቸው አድርገው ከልክ በላይ ተማመኑ።

እነዚህ ለውጡን ለመለወጥ የተነሡ ኃይሎች፣ መጀመሪያ አንድም አድፍጠው በዝምታ፤ አንድም ተባባሪ መስለው በይሁንታ “ከለውጡ አመራር ጋር” ነበሩ። በኋላ ግን ሁለት ነገሮችን ተረዱ። ቀዳሚው ለውጡ አዲስ መንገድ የሚከተል አንጂ የእነርሱን መንገድ ብቻ የሚከተል አለመሆኑን ነው። ሁለተኛው ደግሞ የለውጡን አመራር አብረውት መሥራት እንጂ እንደ ክራር ወደ ፈለጉት ዜማ ሊቃኙት እንደማይችሉ መገንዘባቸው ነው።

እነዚህ ሁለቱም የለውጡን አስኳል አመራር አቅምና አቋም በሂደት ተረዱ። ማንም በፈለገው መንገድ የሚዘውረው የመኪና ጎማ አልሆነላቸውም። በዚህ ጊዜ እነዚህ ወገኖች፣ ሀገርንም ለውጡንም እየጣሉ ሄዱ። የለውጡ አመራር የራሱ አቋም ያለው እንጂ የእገሌ ወእገሌን ለውጥ አራማጅ አልሆነላቸውም። ለኢትዮጵያ የሚያዋጣውን መንገድ እንጂ፣ የነ እገሌን አጀንዳ፣ የነ እገሌን ሐሳብ ወይም የነ እንቶኔን ፍላጎት ብቻ ለማርካት አልመጣም። ይሄንን ሲያውቁ ሁሉም ወደለመዱት የ66ቱ የሸፍጥ እና የሤራ ጎሬ ገቡ።

አሁን የለውጡ ትግል በሁለት አካላት መካከል የሚደረግ ትግል ነው። በ66ቱ የሥጋና የመንፈስ ልጆች እና በዘመናዊቷ ኢትዮጵያ የትንሣኤ ልጆች። የ66ቱ የሥጋና የመንፈስ ልጆች ባለፉት 50 ዓመታት ሤራውን ተክነውበታል። ኔት ወርኩን ዘርግተውታል። ፕሮፓጋንዳውን ቆልተው በልተውታል። ስድብና ጥላቻውን፣ ተንኮልና ክፋቱን ሠልጥነውበታል። በዚህ የተነሣ አየሩን የመያዝ ዕድሉ ነበራቸው። እነዚህ የ66ቱ የሥጋና የመንፈስ ልጆች አራት ቦታ ላይ ይገኛሉ።

  1. የኢትዮጵያን ሾተላያዊ የፖለቲካ ጉዞ ገምግመው፣ አዲስ መንገድ ይሻለናል ብለው፣ በአዲስ መንገድ የሚጓዙ አሉ። እነዚህ የመጀመሪያዎቹ ናቸው።
  2. ከነፍጥ ውጭ ሌላ አማራጭ ሀሳብ የማይገባቸው ደግሞ ጫካውን መርጠዋል። አዲሱ አመራር ጫካውን ለአረንጓዴ ዐሻራነት ይተክላል። የ66ቱ የሥጋና የመንፈስ ልጆች ደግሞ ጫካውን ለመግደልና ለመድፈር ይፈልጉታል።
  3. ሌሎቹ ደግሞ በተለያዩ የውጭ ሀገራት እየኖሩ ተምኔታዊ ዓለም ፈጥረዋል። እነርሱ ታግለው፣ እነርሱ አሸንፈው፣ እነርሱ ተሹመው፣ እነርሱ የሚመሩበት ተምኔታዊ ዓለም። ለዚህ ተምኔታዊ ዓለም ይሰበሰባሉ፤ ገንዘብ ያዋጣሉ፣ ሚዲያ ይከፍታሉ፣ ዕቅድ ያወጣሉ፣ ይመራረጣሉ፣ መልሰው ደግሞ በተምኔት ሥልጣን ይጣላሉ።
  4. ቀሪዎቹ ደግሞ አድፋጭ አልማጭ ናቸው። ዕድልና ጊዜ የሚጠብቁ፤ በየመዋቅሩ የተሠገሠጉ ናቸው። ዋናው ድርጅታቸው “ሽነድ” ይባላል። ሽብር ነዥ ድርጅት ማለት ነው። በየሆቴሉ፣ በየመሥሪያ ቤቱ፣ በየታክሲው፣ በየአውቶቡሱ፣ በየልቅሶው ቤት፣ በየቡናው ላይ የምኞትና የሤራ ወሬ ሲያወሩ ይውላሉ። መጡ፣ ደረሱ፣ ገቡ፣ አለቀ፣ ደቀቀ፣ ሲሉ የሚኖሩ ናቸው። ነጩን ሲያጠቁሩ፣ ማሩን ሲያመሩ፣ ሰማዩን ሲሰብሩ ይኖራሉ። ዓላማቸው ሕዝብን ማሸበርና ሰላም መንሣት ነው። ሥራን በማደናቀፍ፣ ቢሮክራሲን በማርዘም፣ ሕዝብን በማማረር፣ ሲያለምጡ የሚኖሩ ናቸው። ምኞታቸው እንደ እልዋሪቆን አልደርስ ብሏቸው ይጨነቃሉ።

ግን አንድ እውነት አለ። የ66ቱ ትውልድ አይተካም። እያለቀ እንጂ እየጨመረ አይሄድም። ተጽዕኖው ሰፊ የሆነ ትውልድ ነበረ። እንዳይቀጥል የሚያደርጉ ሦስት ምክንያቶች ገጥመውታል።

አንደኛ የዓለም ነባራዊ ሁኔታ ተቀይሯል ኮሚዩኒስትነት የዓለም ፖለቲካ ዋና ግብአት አይደለም። የዓለም ኃያልነት ራሱ በለውጥ ላይ ነው። ገቢር ነበብነት እንጂ በአንድ ርዕዮተ ዓለምና እሳቤ ብቻ መቸከል አዋጪ አልሆነም።

ሁለተኛው የኢትዮጵያም ነባራዊ ሁኔታ መቀየሩ ነው። ኮሚዩኒዝም ኢትዮጵያ ውስጥ “ተተግብሮ” ያመጣውን ጣጣ ሕዝቡ ቀምሶ አይቶታል። እባብ አይቶ በልጥ ደንግጧል። ከነባሩ ፊውዳላዊ እሳቤ ጋር የተዳቀለው ኮሚዩኒስታዊ እሳቤ፣ ሌላ አደገኛ ዝርያ ነው የፈጠረው። ይሄ አደገኛ ዝርያ ደግሞ መግደልን፣ ማስወገድን፣ መደምሰስን እና በመቃብር ላይ መገንባትን እንደ ባሕል ጥሎብን አልፏል። አዲሱ ትውልድ ይሄንን ሊቀበል አልቻለም።

ሦስተኛው ምስጋና ለተፈጥሮ ይሁን የሚያሰኝ ነው። ነባሩ የ66 ትውልድ ተጥሮአዊ ዑደቱን ጨርሶ እየተሰናበተ ነው። የመንፈስ ልጆቹም እየቀነሱ ናቸው። ከላይ ያነሣናቸው ሁለት ምክንያቶች ቁጥራቸው እንዲቀንስ አስገድደዋቸዋል። አንድም ምስጋና ለለውጡ ይሁን። የ66ቱ ትውልድ እንደተበላሸ የድርጅት ሂሳብ፣ አንድ ቦታ ተቆርጧል (Cut off)። የለውጡ ሂሳብ በአዲስ አካውንት ነው የሚመዘገበው። በርግጥ የተቆረጠው ሂሳብ የግማሽ ክፍለ ዘመን ስለሆነ ብዙ መስሎ ይታያል። የለውጡ አካውንት የሰባት ዓመት በመሆኑ ትንሽ ይመስላል። ግን የሚጨምረው ይሄኛው የሂሳብ ቋት ነው። ያኛው አካውንቱ ተዘግቶ ወደ መዝገብ ቤት ተልኳል። በሂደት ሂሳቡ ተጣርቶ ይሠራል።

ለግማሽ ክፍለ ዘመን በውሃ ሲሞላ የቆየ አንድ ኩሬ አለ። አንድ ደግሞ ከምንጭ በመፍለቅ ላይ ያለ አዲስ ጅረት አለ። ኩሬው የግማሽ ምዕት ዓመት ውሃ ስላጠራቀመ ብዙ ነው። ጅረቱ ግን ገና አዲስ እየመነጨ በመሆኑ ጥቂት ነው። ነባሩ ኩሬ አዲስ ውሃ አይጨመርበትም። ከኩሬው እየወሰዱ የሚጠጡ ግን አሉ። በዚህ የተነሣ የኩሬው ውሃ ተበላሽቷል የሚጠጡትንም ያበላሻል። ይሄን እያዩ የሚጠጡት ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ ነው።

የአዲሱ ምንጩን ውሃ ግን ጥቂት ቢሆንም፣ የሚጠጡት ቁጥር እየጨመረ ነው። የምንጩ ውሃ መጀመሪያ ከኩሬው ያንስ ነበር። ቀጥሎ ከኩሬው መስተካል ጀመረ። በመጨረሻም ከኩሬው በለጠ። መብለጥ ብቻ ሳይሆን ፈሳሽ በመሆኑ ሌሎችንም ያዳርሳል። በመንገዱም ከሚመስሉት ጋር እየተደመረ ኃያል ወንዝ ይሆናል። ለውጡ በዚህ መልኩ በመጓዝ ላይ ነው።

እንኳን ለሀገራዊ ለውጡ ሰባተኛ ዓመት አደረሳችሁ።

(ከዳንኤል ክብረት የፌስቡክ ገጽ የተወሰደ)

አዲስ ዘመን ሐሙስ መጋቢት 25 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You