
ኢትዮጵያ ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ያለማንም ድጋፍ ብቻዋን በመገንባት ታሪክ ሠርታለች። ግድቡን በብድር፣ በድጋፍ አሊያም በአጋርነት የደገፈ አንድም ሀገር የለው። ምንም የውጭ ገንዘብ ጥቅም ላይ ሳይውል ግንባታ የተደረገበት ሜጋ ፕሮጀክት የሕዳሴው ግድብ ሲሆን የመላው ኢትዮጵያውያን ሕልም እውን ሆኖ በቅርብ ጊዜ ውስጥ በይፋ መጠናቀቁና ሙሉ ለሙሉ ኃይል ማመንጨት መጀመሩ ይፋ ይሆናል። የዚህ ታላቅ ሕልምን የሰነቀ ግድብ መጠናቀቅ የኢትዮጵያውያንን አንድነትና ጥንካሬ ማሳያ ግዙፍ የልማት ሐውልት ነው።
አሁን ኢትዮጵያውያን ሌላ ትልቅ ግብና ሕልም አለን። እርሱም ላለፉት ግማሽ ክፍለ ዘመን ለሚጠጋ ዓመታት ተነፍገን የቆየነውን የባሕር መዳረሻ መልሶ ማግኘት ነው። የባሕር በርና በብቸኝነት የምናስተዳድረው ወደብ ለኢትዮጵያ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ቁልፍ ነው። በዚህ ምክንያት በዛሬው ርዕሰ ጉዳዬ ላይ የኢትዮጵያ የባሕር መዳረሻ የማግኘት እቅድ ለምን ሕጋዊ መብት እንደሆነ፣ ታሪካዊ ዳራው እና የሰላም መንገድ በመከተል እንዴት እውን አንደምናደርገው እዳስሳለሁ።
ዓለም ያወቀው ፀሐይ የሞቀው አንድ ሐቅ ሁሌም እኛን ኢትዮጵያውያንን ያብሰከስከናል። እርሱም ኢትዮጵያ ከረጅም ጊዜ በፊት የባሕር መዳረሻ ነበራት። ይህ እውነታ ላለፉት ጥቂት የማይባሉ አስርተ ዓመታት ታሪክ ሆኖ ቆይቷል። ለዘመናት አያት ቅደመ አያቶቻችን ሉዓላዊ በሆነው የቀይ ባሕር ዳርቻዎቻችን ከዓለም ጋር ይገናኙ ነበር። ንግድ፣ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትና የባሕር ኃይል የነበረን ሕዝቦች ነን። ይህንን የኃያልነት መገለጫ ምልክታችንን እንደ ቀልድ እንደ አውሮፓውያኑ ዘመን አቆጣጠር በ1993 ኤርትራ ነፃ ስትሆን አብሮ አንደ ጉም መትነኑ እና ዝግ ሀገር መሆናችን የሚያስቆጭ ሐቅ ነው። በዚህ ምክንያት ኢትዮጵያ በግፍ እና ታሪካዊ ስህተትን በሠሩ ግለሰቦች የባሕር ጠረፍዋን አጥታለች፤ ዛሬ ወደብ አልባ ነን።
ኢትዮጵያ ውስጥ ከ120 ሚሊዮን በላይ ሰዎች እንኖራለን። በአፍሪካ ሁለተኛዋ በሕዝብ ብዛት ቀዳሚ ሀገር ነች። ሆኖም እንደ ጅቡቲ ባሉ ጎረቤቶች ላይ የተመካ የንግድ ማቀላጠፊያ ወደቦች ላይ ጥገኞች ነን። ይህ በፍፁም ተቀባይነት የሌለው የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና ብሔራዊ ጥቅም የሚጎዳ መታረም ያለበት ስህተት ነው። በጣም ውድ በሆነ የውጪ ምንዛሪ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ ንግድ በጅቡቲ በኩል ያልፋል። ከፍተኛ የወደብ ክፍያዎች የዜጎችን ኑሮ ሰማይ ሰቅሎታል፣ የሀገሪቱን እድገት ወደኋላ ጎትቶታል።
ኢትዮጵያን የባሕር መዳረሻ የማግኘት ሕጋዊ መብት አላት። ዓለም አቀፍ ሕግ የባሕር በር የሌላቸው አገሮች በሰላም ወደቦች እንዲያገኙ ይፈቅዳል። ኢትዮጵያ ደግሞ ከሕጋዊ መብትም የተሻገረ ታሪካዊ እና የሞራል መብት ጭምር አላት። ኢትዮጵያ የምትፈልገው ፍትሐዊ ስምምነት እንጂ ግጭት አይደለም። ይህንኑ ሃሳብ በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ‹‹የባሕር በር ለኢትዮጵያ የሕልውና ጉዳይ ነው›› በማለት በግልፅ አስፍረውታል። የኢትዮጵያ ታሪክ እና እያደገ የመጣው ሕዝብና ኢኮኖሚ ይህንን መብት ያረጋግጣሉ።
የኢትዮጵያ የባሕር በርና ወደብ ማግኘት ሁሉንም ነገር ይለውጣል። ዜጎች በርካሽ ሸቀጦችን የማግኘት ዕድላቸው ከፍ ይላል። እንደ መንገድ እና ባቡር ያሉ መሠረተ ልማቶች በዝቅተኛ የውጪ ምንዛሪ እንዲስፋፉ ያደርጋል። አሁን ካለው በላይ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በፍጥነት ያድጋል። እንደሚታወቀው የሕዳሴው ግድብ በድል መጠናቀቅ ኢትዮጵያ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን እንደምታሳካ ምስክር ነው። ግድቡ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ዜጎች የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ከማድረሱም ባሻገርና ኢንዱስትሪን ያሳድጋል። በወደብ ልማትና በባሕር በር መዳረሻዎችም ይህንኑ ድል መድገም ይቻላል።
ኢትዮጵያ ከጎረቤቶች ጋር ሰላም ትፈልጋለች። ለቀጣናው ሰላምም ለዘመናት በፍፁም ቅንነት ሠርታለች። አሁንም ምሥራቅ አፍሪካንና መላው አፍሪካን ሰላም ለመጠበቅ ከኅብረቱ ጋር እየሠራች ነው። የልማት ፍላጎቶቿንም በሰላማዊ መንገድ የመፈፀም ፍላጎት አላት። የሕዳሴው ግድብ ግንባታ ሲከናወን በነበረበት ወቅት ወደ ግጭት ሊያስገቡ የሚችሉ ትንኮሳዎች ሲገጥሟት ከግብፅ እና ከሱዳን ጋር የሦስትዮሽ ድርድር በማድረግ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ጥራለች። ዛሬም የሰላም በሮችን ሳትዘጋ የግድቡን ግንባታ እውን አድርጋለች። ሁሉ ኢትዮጵያዊ የባሕር ይገባኛል ጥያቄውን በዚህ መንፈስ ነው የሚያደርገው፤ ታሪካዊና ሕጋዊ መብታችንን በፍትሐዊነት ለማግኘት ድርድር ምርጫ የሌለው መፍትሔ ነው። ለዚህ ነው በተደጋጋሚ የኢትዮጵያ የባሕር በር ይገባኛል ጥያቄ የትኛውም ሀገር እንደማይጎዳ እየገለፅን የምንገኘው።
የሕዳሴው ግድብ (GERD) ጠቃሚ ትምህርቶችን ሰጥቶናል። ግድቡን ለማጠናቀቅ እጅግ በርካታ ጫናዎች ቢደርሱብንም የሀገር ውስጥ አቅምን፣ ገንዘብን እና መሐንዲሶችን ተጠቅመን ዳር አድርሰነዋል። የማያግባቡ ችግሮችን ለመፍታት ከግብፅ እና ከሱዳን ጋር በተደጋጋሚ ተደራድረናል። ይህ አካሄድ ለባሕር በር ፍላጎታችን መሳካት ምሳሌ ሊሆን ይችላል። ከዚህ መነሻ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2024 ከኤርትራ፣ ሶማሊያ እና ጅቡቲ ጋር ድርድር ለማድረግ ብዙ ጥረቶች ተደርገዋል። በውይይቶቹ እና ይፋዊ ጥያቄዎቹ በግልፅ እንደተቀመጠው ኢትዮጵያ የምትፈልገው አጋርነት እንጂ ተቀናቃኝ የጎረቤት ጠላትነትን አይደለም።
የኢትዮጵያ ወጣቶች ይህንን ራዕይ እና ግብ ጠንቅቀው ያውቃሉ። ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን ከ25 ዓመት በታች ናቸው። የሕዳሴው ግድብ ግንባታን እድገት እያዩ ነው ያደጉት። ይህ ማለት ኢትዮጵያ ማንኛውንም ነገር ማሳካት እንደምትችል እነርሱን የዚህ አካል መሆናቸውን አይጠራጠሩም፤ ምክንያቱም ጠንክሮ በትብብር መሥራትን እንጂ ድህነትን አልወረሱም። የባሕር በር ለኢትዮጵያ የማኅበራዊ ሚዲያ ጫጫታ ብቻ አለመሆኑን ይገነዘባሉ። ለዚህ ነው የኢትዮጵያ የልማት ሕልሞች አሸዋ ላይ የተገነባ እንዳልሆኑ ሁሉም ሊያውቅ የሚገባው።
አንዳንዶች የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ በቀጣናው ግጭት ሊፈጥር ይችላል ብለው ይፈራሉ። ኢትዮጵያ ግን ጦርነትም ሆነ ግጭት ጠማቂ አይደለችም። ለዚህ ምስክር የሕዳሴው ግድብ ነው። ግድቡን በፍፁም ወንድማዊ ውይይቶችና ዲፕሎማሲያዊ ድርድሮች ሰላማዊ መፍትሔዎች በማስቀመጥ ሠርተን አጠናቀናል።
የሕዝብ እንደራሴዎች ፊት ቀርበው በባሕር በር ጥያቄና የኢትዮጵያ የልማት ሕልሞች ዙሪያ ያብራሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ማንንም አናስገድድም አንወረርም ሲሉ ሀገሪቱ ሰላም ምርጫዋ እንደሆነ በግልፅ ተናግረዋል። ኢትዮጵያ የጎረቤት ሀገሮችን ሉዓላዊነት ታከብራለች። ሁሉን ተጠቃሚ የሚያደርግ ስምምነቶችን ትፈልጋለች። በመሆኑም የባሕር በር ጥያቄ ከዚህ የተለየ አካሄድና ፍላጎት የለውም።
የኢትዮጵያ ሕዳሴው ግድብ ተጠናቋል። የመጨረሻዎቹ ተርባይኖች በቅርቡ ኃይል ማመንጨት ይጀምራሉ። ይህ ስኬት በትውልዱ ላይ በራስ መተማመንን ይጨምራል ዓለም የኢትዮጵያን ቁርጠኝነት ይመለከታል። የባሕር መዳረሻ ቀጣዩ ሕልማችን መሆኑን ይገነዘባል። በዚህ ታሪካዊ ጥያቄ ላይ ኢትዮጵያ ብቻዋን አይደለችም። እንደ ቦሊቪያ ወይም ካዛክስታን ያሉ ብዙ ወደብ የሌላቸው ሀገሮች የባሕር በር የማግኘት መብቶችን ይደግፋሉ። የኢትዮጵያ ጥያቄ ደግሞ በታሪካዊ መብቶቿ ጭምር የሚደገፍ ነው። ለዚህ ነው የኢትዮጵያ የባሕር በር መዳረሻ ጥያቄ ስለ ፍትሕ እና ሕልውና መሆኑን ደጋግመን የምንናገረው።
ሰው መሆን
አዲስ ዘመን ሐሙስ መጋቢት 25 ቀን 2017 ዓ.ም