ብር ቢያብር ድህነትን ይሽር

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የትውልዶች የዘመናት ቁጭት እና እልኽ ውጤት ነው። የትውልዶች የዘመናት ጥያቄ የተመለሰበት የዐባይ ግድብ ዘንድሮ 98 በመቶ መድረሱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሰሞኑን አብስረውናል፡፡

የዘመናት የሕዝብ ብሶት ቁጭት የተመለሰበት ዐባይ የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነቱን ወንድማማችነቱ ያሳየበት ነው። ግድቡን በመገደብ ታሪካዊ ሥራ ሠርቶ ዐቢይ ሐውልት ያቆመበት የልማት ውጥኖች ያለብድር በሕዝብ ትብብር መጨረስ እንደሚቻል ያስመሰከረበት ብር ቢያብር ድህነት ይሽር ብለን የምናወጋበት እና የምንተርትበት ኅብር ውጤት ነው፡፡

በብሂላችን ‹‹ድር ቢያብር አንበሳ ያስር›› እንደሚባለው ሁሉ እኛም የታላቁ ሕዳሴ ግድብ አመርቂ ሥራን ብር ቢያብር ድህነት ይሽር ብዩዋለሁ። ትልቁ ጠላታችን ድህነት ነው። ኢትዮጵያ ባሸለበችባቸው የቀደሙት ዘመናት፤ የዐባይ ወንዝ የግጭት መዘዝ፣ የድህነት ሰበዝ ሆኖብን ነበር። ያው አገራችን ከግጭት አዙሪትና ከድህነት ቁልቁለት ጎዳና ያልወጣችው ዐባይ ይገደብብናል ባሉ የቅርብ እና የሩቅ ጠላቶቻችን ግጭት እየፈለፈሉብን ስለነበር ነው። አሁን ግን ከግጭት ተራርቀን ብራችን አስተባብረን ድህነት ለመሻር እየተረባረብን ነው።

ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድህን በእሳት አበባ የግጥም መጽሐፋቸው ዐባይ መኩሪያ መሆኑን ገልጸው ነበር። ግጥሙን በጻፉበት ዘመን የዐባይ ከኢትዮጵያ እየፈሰሰ ለም አፈር እየሸረሸረ ወደ ሱዳንን ግብጽ ከመሄድ ውጪ ለሀገራችን አበርክቶ አልባ ነበር። ዘንድሮ ግን ታሪክ ተቀይሮ የምድረ ኩሽ መኩሪያ ሆኖልናል። አበርክቶውን እያሳየን ነው። ግጥሙም የሚናገረው ከቀድሞው የበለጠ የዘመናችንና መጪው ትውልድ በወንዙ እንደምንኮራ ማሳያ ነው።

‹‹ …ዓባይ የምድረ ኩሽ መኩሪያ

በቅድመ ታሪክሽ መጥረጊያ

ከደም-ቢያ እስከ ኑቢያ

ከሜምፊስ እስከ ሜሮኤ

ለሥልጣኔሽ ትንሳኤ

ከዴልታሽ እስከ ዴር ሡልጣን

ከኡመራህ እስከ አሙ-ዱሩማን

ዓባይ የአቴንስ የጡቶች ግት

የዓለም የስልጣኔ እምብርት

ጥቁር ዓባይ ጥቁር ምንጭ

የካም የሥልጣኔ ፍንጭ…››

ንጉሥ ኃይለሥላሴ ዓባይንለመገደብ ብዙ ጥረት አድርገዋል። የውጭ ሀገራትን የጥናት ባለሙያዎች በመጋበዝ ጥናትም አስጠንተው ነበር። በወቅቱ ንጉሡ እንደተናገሩት ‹‹እኛ ዓባይንእንገድብ ብንል አቅም የለንም። የውጭ ሀገራት ደግሞ ዓባይንለመገደብ እርዱን ብንል ግብጥን (ግብፅን) ላለማስቀየም ፈቃደኛ አይሆኑም። ቀጣዩ ትውልድ ግን ወደፊት በራሱ ንዋይ (ገንዘብ) ይገነባዋል። ጥናቱ በክብር ይቀመጥ›› ብለዋል። ንጉሡ የጥናት ሰነዱ ላይ እንደተናገሩት ቀጣዩ ትውልድ በራሱ ንዋይ ይገነባዋል ሲሉ ትንቢት ቀመስ ነገር በመናገር ለቀጣዩ ትውልድ የቤት ሥራ ሰጥተው አልፈዋል። ይኸው ቀጣዩ ትውልድ ደግሞ የሠጡት ብሔራዊ ኃላፊነት በመወጣት ግድቡዋን ለፍጻሜ እያበቃት ነው።

በየዐመቱ መጋቢት 24 ቀን ሲመጣ የሕዳሴ ግድብ ጅማሮ ይታወሰናል። የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መሠረተ ድንጋዩ የተጣለው መጋቢት 24 ቀን 2003 ዐ.ም በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ነበር። ይኸው ዛሬ ላይ ሆነን ግንባታው ከ98 በመቶ በላይ የሆነውን ታላቁ ሕዳሴ ግድብ ስናስበው እና መጪው ዐመት የ14 ዐመት ግንባታ ውጤት ከድህነት የምንወጣበት ፋታና እፎይታ ይሆነናል። ግድቡ የኢትዮጵያን የኤሌክትሪክ የማመንጨት ዐቅም በእጥፍ ለመጨመር የሚያስችል ነው። 74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ መገደብ የሚችለው ሕዳሴ የግድቡ ሲቪል ግንባታ ከባሕር ጠለል በላይ 645 ሜትር ለማሳደግ ታቅዶ የተገነባ ነው።

ዐባይ ከሀገራችን 19 ገባር ወንዞችን አጠራቅሞ የኢትዮጵያም ለም አፈር ጭኖ ሱዳን ካርቱም ላይ ከነጭ ዐባይ ተገናኝቶ ወደ ግብጽ ይፈሳል። ኢትዮጵያ የዐባይ ግድብ የማያልቅላት የማያዛልቃትን የመሰላት ግብጽም ኢትዮጵያ ግድቡን ጨርሳ አየችው። የማያዛልቃት ያልኩት ያው ግብጽ ግንባታው ሲጀመር ኢትዮጵያ ዐቅም ስለሌላት አትጨርሰውም አበዳሪ አካላት እና ሀገራትም እንዳያበድሩ አደርጋለሁ በሚል አሳቤ ውስጥ ስለነበረች ነው።

የግድቡ ግንባታ መጠናቀቅ መጪው ዘመን ብሩህ ነው ብለን ከመናቆርና ከመቃቃር ርቀን በትብብር ድህነትን መዋጋት እንዳለብን የሚያሳየን ነው። ስትራቦ የተባለ ጥንታዊ ግሪካዊ ፈላስፋ ‹‹ ኢትዮጵያውያን በውጊያ ጀግንነታቸውና ብቃታቸው የሚታወቁ ተዋጊዎች ናቸው ›› ይል የነበረውን አሁን በልማትም ጀግኖች መሆናችንን ግድቡን በመገንባት የተጨማሪ ታሪክ ባለቤት መሆናችንን በተግባር ያስመሰከርንበት ነው።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ፤ የግድቡ ሙሉ ተርባይኖች ኤሌክትሪክ ማመንጨት ሲጀምሩ 65 በመቶ በጨለማ የሚኖረው ዜጋ ብርሃን ያገኛል። ግድቡ ለዜጎች የኤሌክትሪክ ብርሃን የምናዳርስበት ብቻ ሳይሆን ከወዲሁ ለጎረቤት ሀገራትም ኤሌክትሪክ በመሸጥ የውጭ ምንዛሪ የምናመነጭበት ነው። ብልጽግናን በተግባር ልናየው ነው።

ግድቡ ሲጀመር ግብጾች ኢትዮጵያውያን ‹‹የማይወጡት ዳገት የማይወርዱት ቁልቁለት›› ይሆንባቸዋል በሚል ንቀት ዐይተውት ነበር። ግድቡ ሲጀመር በተደጋጋሚ መገደብ አይችሉም በሚል አቤቱታ አቅርበው ነበር። ለተመድ ብቻ 12 ጊዜ ክስ አቅርበው በኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች ተረተዋል። ‹‹የፈሩት ይደርሳል›› እንደሚባለው ኢትዮጵያ ዓባይንትገድብብናለች ብለው ፈርተው ከመንግሥት ጋር ለሚጋጩ ሁሉ ብር እየረጩ ጦር በማስታጠቅ ሀገርን ለማስተላለቅ ጥረዋል።

የሕዳሴ ግድብ ድህነትን የምንገድብበት እና የምንዋጋት ነው የምንለው ‹‹የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ›› እንደሚባለው ብሂል ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ እየወሰዱ ያሉ ሀገሮችን ማሳያዎች ናቸው። ኢትዮጵያ ላለፉት ዐመታት ለሱዳን፣ ኬንያና ጅቡቲ፣ ለደቡብ ሱዳን የኤሌክትሪክ ኃይል ስትሸጥ የቆየች ሲሆን፤ 400 ኪሎ ዋት የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመር ባጠናቀቀችው ኬንያ በኩል፣ ኢትዮጵያ ለታንዛኒያ የኤሌክትሪክ ኃይል እንደምታቀርብ ይጠበቃል።

የምሥራቅ አፍሪካ 11 ሀገራትን የኤሌክትሪክ ኃይሎቻቸውን ለማገናኘት ለተቋቋመው ለምሥራቅ አፍሪካ ፓወር ፑል (ኢኤፒፒ) የሕዳሴው ግድብ መጠናቀቅ ሠርግና ምላሽ የሚሆን ነው። የኤሌክትሪክ ኃይሎቻቸውን ለማገናኘት የተቋቋመው የምስራቅ አፍሪካ ፓወር ፑል አባል 11 ሀገራት ብሩንዲ፣ የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ፣ ግብፅ፣ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ሱዳን፣ ታንዛኒያ፣ ሊቢያ፣ ጅቡቲና ኡጋንዳ ናቸው። ይህም ከሕዳሴው ግድብ ለግብጽ ጭምር ኤሌክትሪክ ለመሸጥ እንደሚቻል ያሳየናል።

ደራሲ ጌታቸው ወልዩ የዐባይ መዘዝ በሚል በ1998 ባሳተሙት መጽሐፋቸው፤ የግብጽ ሕዝብና መንግሥት ዓባይንእንዴት እየተጠቀመበት እንደሆነ ሲጠቅሱ ‹‹… ከግብጽ ሕዝብ በርካታ የዐባይ ሸለቆ ተከትሎ የሚኖር ነው። በዐባይ በመታገዝም ጥጥ፣ ሩዝ፣ ባቄላ፣ ስንዴ፣ በቆሎ፣ ፍራፍሬ የጓሮ አትክልቶች ያመርታል። ምርቶቹ ያለ ዐባይ የማይታሰቡ ናቸው። ግብርናን ለዓለም ቀድማ ያስተዋወቀችው ዓባይንተጠቅማ ነው። የጥጥ ምርት በዓለም አራተኛ ደረጃ እንድትይዝ አድርጓታል።

‹‹ከ90 ሺህ በላይ ትራክተሮች በእርሻ ተሰማርተዋል። ዓባይንማዕከል አድርጎ እኤአ በ1971 የተሠራው የአስዋን ግድብ ለሀገሪቱና ለሕዝቧ ሥጋና አጥንት ሆኖ ያገለግላል። ግብጽ በዐባይ ታግዛ እኤአ 2001 75 ነጥብ 23 ቢሊዮን በዐመት ኪሎዋት አምርታለች። በእህል ምርት ከአፍሪካ የመጀመሪያ ነች። የአፍሪካ ቀዳሚ አይብ አምራችም ነች። እኤአ በ1998 እንኳ 402 ሺህ ቶን አይብ አምርታለች። ከአገሪቱ የቆዳ ስፋት ለእርሻ ተስማሚው 2 በመቶው የሚሆነው ብቻ ይሁን እንጂ ዓባይንበመጠቀም 29 በመቶው በእርሻ ሥራ ተሰማርቷል። …››

እኛም ከአሸለብንበት ልንነቃ ለልማት ልንነሳሳ ይገባናል። በሕዳሴ ግድቡ ዐሳ አርብተው የሚጠቀሙም ይኖራሉ። ግድቡ አካባቢ የሚገኙ ዜጎች ዐሳ በማርባት በመብላት ለራሳቸው ከመጠቀም አልፈው በመሸጥ የገቢ ምንጭ ይሆናቸዋል። ከሰው ሠራሽ ሐይቁና ከዐባይ ወንዝ በመስኖ የሚያመርቱም ሰዎች እንጠብቃለን። የሕዳሴ ግድብ የተፈጥሮ ሀይቁ በራሱ የቱሩስቶች ምንጭ ይሆናል። ግድቡ በግንባታ ላይ እያለ እንኳ ብዙ የሀገር ውስጥ ዜጎች ከየመሥሪያ ቤቱ በመሔድ ግድቡንና ግንባታውን ጎብኝተውታል። ለራሳቸውም በግንባታው ላይ እንኳን ብዙ የሀገር ውስጥ ዜጎች እንዲሁም ዐናት የሚበሳውን ሙቀት በማየት ሙቀቱን ችለው ግድቡን የሚገነቡትን ሰዎች አድንቀዋል።

የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ እየተገነባ በቦታው ታድሞ ለማየት ችሏል። ከባልደረቦቼ ጋር ግንባታውን እያደነቅን ሙቀቱን እየተሳቀቅን እንደገና ደግሞ እኛ ቆመን ዞር ዞር ብለን ያየነውን ግንባታ የሚሠሩ ሠራተኞች ሙቀቱን እንዴት ችለው ነው? የሚሠሩት ጀግኖች ናቸው በማለት መነጋገራችንን አሁንም በመደመም ጭምር አስታውሳለሁ። ዐባይ የሀገር አድባር የሀገር ሲሳይ (ምግብ) የሚለውን ዘፈን በግድቡ አምርተን በተግባር ማሳየት አለብን። የማነቃቂያ ሥራ መሥራት ይጠበቅባቸዋል። አሁን የግድቡ መጠናቀቅ እውን ነው። የእኛ ኢትዮጵያውያን ሕልም ግን ግድቡን ከማጠናቀቅም ያለፈና የተሻገረ ነው። ከቀደመው የስልጣኔ ማማ ላይ የመቀመጥ፤ ድህነትን ታሪክ አድርጎ መጪውን ትውልድ ባለራዕይ የማድረግ ግብ አለን። ይህንን ለዓለም ሕዝብ ማስተጋባት፣ አንድነታችንን ማሳየት ይጠበቅብናል። ሰላም!!

ኃይለማርያም ወንድሙ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 27 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You