“…ዝቅ ማለትን ታሪክ ያደረግንበት…”

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠበትንና ለፍጻሜ የበቃበትን ምክንያት በማድረግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባስተላለፉት መልዕክት፦ “ሕዳሴ ግድብ ዝቅ ማለትን ታሪክ ያደረግንበት ፕሮጀክታችን ነው” ብለዋል።

አዎ ዓባይ እንደ ስሙ ግዙፍ ስለነበር እሱን ከፍ አድርገን የሀገርንና የሕዝብን አቅም ስናኮሰምን ስናሳንስና ዝቅ ስናደርግ ኖረናል። ዓባይን ለመገደብ በራሳችን ላይ ሀብት የለንም፤ አቅም የለንም፤ ወኔው የለንም የሚል ሟርትና መርገም ስናውጅ ኖረናል።

ዛሬ ግን ይሄን የመርገም ጨርቅ ቀዳደን ጥለናል። ታሪክን ቀይረናል። “ሕዳሴ ግድብ ዝቅ ማለትን ታሪክ ያደረግንበት ፕሮጀክታችን ነው።” የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የግድቡ ግንባታ የተጀመረበት 13ኛ ዓመት “በኅብረት ችለናል” በሚል መሪ ቃል እየተከበረ ነው። ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ ባለፈው ማክሰኞ መጋቢት 24 ቀን 13ኛ ዓመቱን ደፍኗል። የግድቡ ግንባታ ከዛሬ 13 ዓመታት በፊት መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ/ም ነበር በይፋ የተጀመረው።

በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊም ኢትዮጵያ በታላቁ የዓባይ ወንዝ ላይ ከአፍሪካ ቀዳሚ ከዓለም ደግሞ ተጠቃሽ የሆነ ግዙፍ ግድብ መገንባት መጀመሯን በማብሰር በይፋ የመሠረት ድንጋዩን አኑረዋል። ከዚያም ወዲህ ግድቡ በበርካታ ውጣ ውረዶች ውስጥ አልፏል። የነበሩበትን እንደመርግ የከበዱ ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎች ተሻግሮ አሁን ላይ ወደ ፍጻሜው እየተንደረደረ ይገኛል።

ኢትዮጵያውያን ራሳቸው መሐንዲስም የፋይናንስ ምንጭም ሆነው ይገነቡታል የተባለለት ግድቡ 5 ዓመታትን እንደሚፈጅ ነበር በወቅቱ የተገለጸው። ሆኖም በግንባታው መጓተት በተለይም የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) በኃላፊነት ወስዷቸው በነበሩ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራዎች መጓተት ምክንያት በተያዘለት እቅድ መሠረት መጠናቀቅ ሳይችል ቀርቷል።

ለዚህም በግንባታ ፕሮጀክቱ የተስተዋሉ የአስተዳደር እና የብልሹ አሠራር እንከኖች በምክንያትነት ተጠቅሰዋል። ከዚህ ጋር በተያያዘ የፕሮጀክቱን ዋና ሥራ አስኪያጅ የኢንጂነር ስመኘውን ሕይወት እስከመንጠቅ የደረሱ ሁነቶች አጋጥመው እንደነበርም ይታወሳል።

የመንግሥት ለውጥ ከመጣ ከ2010 ዓ.ም ወዲህም በግድቡ የግንባታ ፕሮጀክት ተስተውለዋል የተባሉ ህጸጾች ተነቅሰውና የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራዎች ተቋራጩን እስከመቀየር እንዲሁም የተርባይኖቹን ቁጥር ከ16 ወደ 13 እስከመቀነስ የደረሱ እርምጃዎች ተወስደው ግንባታው ቀጥሎ አሁን አጠቃላይ የግንባታ ሥራው 95 በመቶ ደርሷል። የግድቡ አጠቃላይ የሲቪል ሥራው ግንባታ የደረሰበት ደረጃ 98 ነጥብ 9 በመቶ ተጠናቋል የተባለ ሲሆን የኤሌክትሮ መካኒካል ሥራውም በመፋጠን ላይ እንደሆነም ተገልጿል፡፡

አሁን ላይ ግድቡ የያዘው የውሃ መጠን 42 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ሲሆን ግድቡ ሲጠናቀቅ የሚይዘው አጠቃላይ የውሃ መጠን ወደ 74 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ከፍ ይላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ከ13 ዓመት በፊት የተጀመረው ታላቁ የሕዳሴው ግድብ ሁለት ተርባይኖች ኃይል በማመንጨት ላይ ናቸው። የካቲት ወር 2014 ዓ.ም ግድቡ ካሉት ተርባይኖች ውስጥ አንዱ የሆነው እና ዩኒት 10 የሚል መጠሪያ ያለው ተርባይን 270 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት መጀመሩ ይታወሳል።

በነሐሴ ወር 2014 ላይ ደግሞ ዩኒት 9 የሚል መጠሪያ ያለው ተርባይን 270 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት መጀመሩ ይታወሳል። ይህን ተከትሎም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የዛሬውን ጨምሮ በአጠቃላይ 540 ሜጋዋት የኤሌክትሪክ ኃይል እያመነጨም ይገኛል። ፕሮጀክቱ በቀጣይ ተጠናቆ የሚጠበቅበትን 5 ሺህ 150 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት ይጀምራል።

ይህም የኢትዮጵያን አጠቃላይ ኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅም በእጥፍ የሚያሳድግ ነው። የፋይናንስ ምንጭ ሆነው ግድቡን እንደሚገነቡ የተነገረላቸው ኢትዮጵያውያንም ዐይነተ ብዙ የገንዘብና የዓይነት ድጋፎችን እያደረጉ ነው። እስካሁንም በአጠቃላይ ባለፉት 13 ዓመታት ከሕዝቡ 20 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ ማሰባሰብ መቻሉ ተገልጿል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚደረገውን ሕዝባዊ ድጋፍ ለማስቀጠልም 13ኛ የግንባታ ዓመቱን ታሳቢ ባደረገ የገቢ ማሰባሰቢያ እስከ 300 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱን ለማወቅ ተችሏል።

ከዚህ በኋላ ትውልድ እስከ ምፅአት ዓይኑን “ከፍ የማለት ምሳሌ፤” ከሆነው ዓባይም ሆነ ከታላቁ የሕዳሴ ግድብ አያነሳም። ከዚህ በፊት እንዳልሁት ስለ ዓባይና ስለ ሕዳሴው ግድብ ለመስማት ጆሮውን አቁሞና አዘንብሎ በንቃት ይጠባበቃል። ታላቁ መጽሐፍ እንደሚለው ከመናገር ይልቅ ለመስማት ይፈጥናልና። ለዚህ ደግሞ የማያቋርጥ የተፈተገ፣ ታጥቦ የተቀሸረ፣ የታሸና በኪን የተዋዛ ቋሚ የመረጃ ቋትና አቅርቦት ያስፈልጋል።

ሥርዓተ ትምህርቱም ከዚህ አንጻር እንደገና መቃኘት ይኖርበታል። ከዚህ በኋላ ትውልድ ሲቀባበለው የሚኖር አጀንዳ፣ የዱላ ቅብብል ነውና። ይህ እስኪሆን ግን እጅን አጣጥፎ መቀመጥ አይገባም። ስለ ዓባይ በልኩ ሳያሰልሱ መጻፍ፣ መናገር፣ መሟገትና ማንሰላሰል ግድ ይላል። ስለ ዓባይ ሙዓዘ ጥበባት ዳንኤል ክብረት እንደሚለው፣ የብዕር ዘገሬን ነቅንቄ ፣ የቀለሜን ጦር ሰብቄ ተነስቻለሁ። እፅፋለሁ። እሰናዘራለሁ። ለዛሬ ኢ/ር ወንድሙ ተክሌ ሲጎ (ፒ ኤች ዲ) በአንድ ወቅት በሄራልድ ላይ፤ “An Egyptian Illusion of Control over the Nile River “ በሚል ለንባብ ያበቁትን ማለፊያ ጽሑፍ ወደ አማርኛ አዋድጄ በመመለስ በሁለት ክፍሎች አቀርባለሁ።የዓባይ ተፋሰስ የአፍሪካን አሕጉር አንድ አስረኛ ይሸፍናል። በዓለማችን ከምንጩ እስከ ሜዲትራኒያን ባሕር ድረስ 6ሺህ 700 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ረዥሙ ወንዝ ነው።

የዓባይ ወንዝ ሁለት ታላላቅ ገባሮች አሉት። ከቪክቶሪያ ሐይቅ ተፋሰስ የሚነሳው ነጭ ዓባይና ከኢትዮጵያ ተራራማ ቦታዎች የሚመነጨው ጥቁር ዓባይ ነው።

ለናይል ወንዝ 77 ነጥብ 5 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውሃ ማለትም 86 በመቶ ከእነ ለም አፈሩ በመገበር ጥቁር ዓባይ እንደ ስሙ ታላቅ ወንዝ ነው። ለራሱ ለጥቁር ዓባይ ደግሞ 49 ነጥብ 5 ቢሊዮን ሜትር ኩብ በመገበር ዓባይ ትልቁን ድርሻ ሲወስድ፤ ባሮ አኮቦ ወንዝ 17 ቢሊዮን ሜትር ኩብ እና የተከዜ ወንዝ 11 ቢሊዮን ሜትር ኩብ በዓመት ይገብራሉ።

የጥቁር ዓባይ የፍሰት መጠን ከሀገሪቱ አጠቃላይ ፍሰት ግማሽ ከመሆኑ ባሻገር በጠቃሚ ማዕድናትም የበለፀገ ነው። ጥቁርና ነጭ ዓባይ ሱዳን ካርቱም ላይ ይገናኙና ዓባይ /ናይል/ ይሆናሉ። ዳሩ ግን የናይል ወንዝ የስምንት የራስጌ ተፋሰስ ሀገራት ሀብት ጭምር ቢሆንም እስከ ዛሬ በብቸኝነት እየተጠቀሙ ያሉት ግን የግርጌ ተፋሰስ ሀገራት የሆኑት ሱዳንና ግብፅ ናቸው። የጋራ የውሃ ሀብት ቢሆንም የራስጌ ተፋሰስ ሀገራት እኤአ በ1929 በሱዳንና በግብፅ በቅኝ ግዛት ዘመን በተፈረመ አግላይ ስምምነት የተነሳ መጠቀም አልቻሉም።

በእንግሊዝ አይዟችሁ ባይነት በተፈረመው ኢ-ፍትሐዊ ውል መሠረት ለሱዳን 4 ቢሊዮን ሜትር ኩብ፤ የተቀረውን ማለትም 48 ነጥብ 5 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ለግብፅ ጀባ ብሏል።

የሚገርመው ከጥር እስከ ሐምሌ ያለውን ፍሰት ያካትታል። ይህ የቅኝ ግዛት ዘመን ውርዴ የሆነ ስምምነት ሱዳንና ግብፅ የራስጌ የተፋሰሱ ሀገራትን በድጋሚ በማግለል በራቸውን ዘግተው እኤአ እስከ ተፈራረሙበት 1959 ድረስ የቀጠለ ሲሆን፤ በእብሪት የተወጠረው ይህ ስምምነት፣ “ከግብፅ መንግሥት ፈቃድ ውጭ የውሃ መጠኑን ሊቀንስ የሚችል የመስኖም ሆነ የኃይል ማመንጫ ሥራዎችን በዓባይ ገባሮችና ሐይቆች ላይ መገንባት አይቻልም። ይህ ግብዝነትንና እብሪትን የሚያሳይ ስምምነት ታዋቂው የግሪክ የታሪክ ሊቅ ሔሮዶተስ “ግብፅ የዓባይ ስጦታ ናት።” የሚለውን ይትበሀል የዘነጋ ነው።

እኔ ግን ግብፅ የዓባይ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ስጦታ ናት ብዬ ነው የማምነው። ጥንታዊ ሥልጣኔዋም ሆነ የዛሬ ሕልውናዋ ከዓባይ ጋር የተቆራኘ ሆኖ ሳለ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከራስጌ የተፋሰስ ሀገራት ጋር ተቀራርቦና ተባብሮ መሥራቱ ይቅርና የምታሳየን እብሪት ማንአህሎኝነትና ንቀት ያበግናል። ከግርጌዋ ተፋሰስ ሀገራት ለዛውም ከሱዳን ጋር ስለ ዳግም የውሃ ክፍፍሉ ምክክር ካደረገች ከ15 ዓመታት በላይ እንደሆናት መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህ ፈርዖኖችም ሆኑ የዛሬዎቹ ገዥዎች ምን ያህል ከዘመኑ ጋር የመሄድና መሬት ላይ ያሉ ተጨባጭ ሁኔታዎችን ለመቀበል ፍላጎቱ እንደሌላቸው ያስረዳል። ሆኖም ውሎ አድሮ ሱዳን የፍትሐዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ ማንሳቷ አልቀረም። የ1929ኙ ስምምነት ላይ እንደገና መደራደር እንደምትፈልግ ግብፅን መወትወት ጀመረች።

የ1959ኙ የውሃ ክፍፍል ላይም ጥያቄ ማቅረብ ቀጠለች። የተፋሰሱን ራስጌ ሀገራት ፍትሐዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ አዲስ ስምምነት መፈራረም ካልተቻለ፤ ሱዳንና ግብፅ በአንድ በኩል፣ ኢትዮጵያና ሰባቱ የራስጌ ተፋሰስ ሀገራት በሌላ በኩል ለግጭት የመዳረግ እምቅ አቅም እንዳለው ቀጣናዊ የውሃ ፖለቲካ ልሒቃን ያስጠነቅቃሉ።

የጋራ የሆነውን የውሃ ሀብት በጋራ መጠቀም ሲገባ፤ ግብፅ ግን ከማንኛውም ድርድር በፊት የግርጌም ሆነ የራስጌ ሀገራት የ1959ኙን ስምምነት እንዲቀበሉ ቅድመ ሁኔታ ታስቀምጣለች። ሆኖም ይህ የግብፅ ቁሞ ቀር ቅድመ ሁኔታ በተፋሰሱ ሀገራት ተቀባይነት አላገኘም። ምክንያቱም ስምምነቶቹ የተፋሰስ ሀገራትን በተለይ ሀገራችንን ያላሳተፉ ከመሆኑ ባሻገር ስምምነቶቹ የመንግሥታቱ ድርጅት እኤአ በ1997 ይፋ ካደረገው የፍትሐዊ ተጠቃሚነት ድንጋጌ ጋር ይጣረሳሉ። ሆኖም የተፋሰሱ ሀገራት የጋራ የሆነውን የዓባይ የውሃ ሀብት ለማልማት የግብፅ ፍቃድ አያስፈልጋቸውም። ሱዳንና ግብፅ ዓባይን ለትላልቅ መስኖዎችና የኃይል ማመንጫነት ሲጠቀሙበት በአንጻሩ ሌሎች የራስጌ ተፋሰስ ሀገራት ወንዙን የሚጠቀሙበት ለአነስተኛ ኃይል ማመንጫነት ብቻ ነው። ይህ የሆነበት ምክንያት የጋራ የሆነውን ሀብት በስፋት አልምተው የመጠቀም ፍላጎት ስለሌላቸው ሳይሆን ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት በግብፅ ተፅዕኖ የተነሳ ብድር የመስጠት ፍላጎት ስለሌላቸው ነው። የተፋሰሱ ሀገራት የሕዝብ ብዛት በከፍተኛ ፍጥነት በመጨመር ላይ መሆኑን ተከትሎ የውሃ ፣ የምግብና የኃይል ፍላጎታቸው በእጅጉ እያሻቀበ ነው። የሚያሳዝነው እነዚህ ፍትሐዊ ያልሆኑ የፋይናንስ ተቋማት ለግብፅ ሲሆን እጃቸው ይፈታል።

በዚህም ጭው ባለ በረሃ ግዙፍ መስኖዎችን፣ ሀገሪቱን ሙሉ በሙሉ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ያደረጉ ትላልቅ የውሃ ኃይል ማመንጫዎችን ገንብተዋል። በስተሰሜን የሱዳንና ግብፅ ድንበር ላይ ግብፅ በዓለማችን ረጅሙን የዓባይ ወንዝ በመገደብ በግዙፍነቱ ከዓለም 3ተኛ የሆነውን የአስዋን ግድብ ገንብተዋል። የአስዋን ግድብ 10 ዓመት ከፈጀ ግንባታ በኋላ እአአ በ1970 ተጠናቋል። በ1954 ግብፅ ከዓለም ባንክ ብድር፣ ከአሜሪካ ደግሞ ርዳታ ለማግኘት ጠይቃ ተስፋ ተሰጧት የነበር ቢሆንም ከእሥራኤል ጋር በገባችበት ውዝግብ የተነሳ ሳይሳካ ቀርቷል።

በዚህ የተከፋችው ግብፅ ወዲያውኑ ፊቷን ወደ ሶቪየት ኅብረት በማዞር ባገኘችው ብድር ግንባታውን ማካሄድ ችላለች። ግድቡ 90ሺህ ሱዳናውያን ከማፈናቀሉ ባሻገር በቅርስነት ተከልለው የነበሩ ቦታዎችም በውሃ ተውጠዋል። እነዚህ ተፈናቃዮች ከቀዬአቸው 600 ኪሎ ሜትር ርቀው እንዲሰፍሩ ሲደረግ፤ በግድቡ የተነሳ ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ ግብፃውያን ግን 40 ኪሎ ሜትር ብቻ እርቀው እንዲሰፍሩ ተደርጓል።

ግብፅ ይህን ግዙፍ ግድብ ስትገነባ ከሱዳን ውጭ ሌሎች ሀገራትን ማማከር አይደለም እወቁልኝ እንኳ አላለችም። ሱዳንንም ያማከረቻት አስባላት ሳይሆን በዜጎቿ ላይ የምትፈፅመውን ግፍ እንድታውቀው ይመስላል። የአስዋን ግድብ 2ሺህ 100 ሜጋ ዋት በማመንጨት ማለትም ግማሹን የሀገሪቱን የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት ያሟላ ሲሆን፣ ለከፍተኛ መስኖ ልማትም ውሏል።

ግብፅ እምቅ የኃይል አማራጭ ቢኖራትም ከውኃ የኃይል ማመንጫዎች ውጭ የመጠቀም ፍላጎት የላትም። አንዳንድ ምንጮች እንደሚጠቁሙት 4 ነጥብ 4 ቢሊዮን በርሜል የነዳጅ ድፍድፍ ክምችት በምድሯ ቢኖርም በቀን እያመረተች ያለው ከ640ሺህ በርሜል በታች ነው። የተፈጥሮ ጋዝ ክምችቷ ወደ 2 ነጥብ 2 ትሪሊዮን ኩም የሚጠጋ ሲሆን፣ እያመረተች ያለው ግን ወደ 60 ቢሊዮን ኩም የሚጠጋ ብቻ ነው።

እንዲሁም 547ሺህ 500 በርሜል በቀን የተጣራ ነዳጅ ታመርታለች። ሰፊ የከርሰ ምድር ውሃ እንዳላትም ጥናቶች ያመለክታሉ። ይህ ሁሉ አማራጭ የኃይልም ሆነ የመስኖ ሀብት እያላት መላው ስስቷና ቀልቧ ዓባይ ላይ ነው። እሷ የተሻለ አማራጭ ያላት መሆኑን ዓይኔን ግንባር ያድርገው ብላ በየአደባባዩ እየማለች፣ እየተገዘተችና እየካደች፤ ኢትዮጵያ ዝናብን ጨምሮ በርካታ አማራጭ የውሃ ሀብት እያላት ጥቁር ዓባይ ላይ ግድብ የምትገነባው ግብፅን ለማንበርከክና ጂኦፖለቲካዊ ሚዛኗን ለመጨመር ነው ስትል በየመድረኩ የአዞ ዕንባዋን እየረጨች ነው።

ግብፅ ዕያነባች ወደምትወርደው እስክስታ ስንመለስ፤ ግብፅ የዓባይን የተፈጥሮ ፍሰት በመቀየር በረሃውን ለማልማት 30ሺህ 300 ኪሎ ሜትር የመስኖ ቦዮችን ገንብታለች። ከአስዋን ግድብ 300 ኪሎ ሜትር ርቀት ያህል ውሃ በመሳብ ቶሽካ የተባለውን ሰው ሠራሽ ሐይቅ በመገንባት በረሃውን እያለማች ትገኛለች። በአሁኑ ሰዓት ግብፅ 3 ነጥብ 76 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በመስኖ ታለማለች። ከአስዋን ግድብና ከዓባይ ወንዝ ያልተገባ አጠቃቀም ጋር ተያይዞ የሚነሱ በርካታ ችግሮች እንዳሉ ሆኖ። በትነትና በስርገት የተነሳ በየዓመቱ ከ12 እስከ 14 በመቶ የሚደርስ ውሃ ከግድቡና ከመስኖ ቦዮች ይባክናል።

ለመስኖ ከሚያስፈልገው ውሃ በላይ በመጠቀም ማባከንና ጥራት የሌለው የፍሳሽ መውረጃ በግድቡ ላይ ከሚስተዋሉ ዋና ዋና ችግሮች ይጠቀሳሉ። ከአሜሪካው የካምፕ ዴቪድ ስምምነት በኋላ የግብፅና የእስራኤል ግንኙነት በመሻሻሉ፤ የወቅቱ የግብፅ ፕሬዚዳንት አንዋር ሳዳት የፍልስጤምና የእየሩሳሌም ችግር የሚፈታ ከሆነ ከዓባይ ወንዝ 365 ሚሊዮን ሜትር ኩብ ውሃ በየዓመቱ ለእሥራኤል ለመስጠት ቃል ገብተው ነበር። ይህ የጂኦ ፖለቲካ የአሰላለፍ ለውጥ በራስጌ የተፋሰስ ሀገራት ላይ ውስብስብ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩ አልቀረም። ሌላዋ የግርጌ ተፋሰስና ጎረቤት ሀገር ሱዳን ግድቦችን ገንብታለች። እአአ በ1926 ሴናርን ለመስኖ፣ በ1936 ጀበል አውሊያ ለኃይል ማመንጫና ለመስኖ ገንብታለች።

በ1950 3ኛውንና 420ሺህ ሄክታር መሬት መስኖ የማልማት አቅም ያለው የሮሴሪስ ግድብን እንዲሁም ከእዚህ በተጨማሪ ሌሎች ግድቦችን ገንብታለች። በዚህም በመስኖ መልማት ከሚችለው 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬቷ 1ነጥብ 9 ሚሊዮን ሄክታሩን ማልማት ችላለች። በግብፅና በሱዳን በመስኖ እየለማ ያለ መሬት የዓባይን 86 በመቶ ከምታበረክተው ሀገራችን ጋር ስናስተያየው እዚህ ግባ የሚባል አለመሆኑ ሊያስቆጨን ይገባል። እንግዲህ ከፍ ብሎ እንደተመለከትነው በዓባይ የውሃ ሀብት ላይ በብቸኝነት እየተጠቀሙ ያሉት ሁለቱ የግርጌ ተፋሰስ ሀገራት በተለይ ግብፅ ናት።

በሌላ በኩል የራስጌ ተፋሰስ ሀገራት ኢትዮጵያን ጨምሮ የከፋ ድህነት ላይ እንደሚገኙ የተባበሩት መንግሥታት የምግብና የግብርና ድርጅት /ፋኦ/ ይፋ ያረገው መረጃ ያመለክታል። ጥቅል የሀገር ውስጥ ምርታቸው እጅግ ዝቅተኛ ከመሆኑ ባሻገር የምግብ ዋስትናቸውን ማረጋገጥ እንዳልቻሉ ፋኦ ያትታል። በተፋሰሱ ሀገራት የሚገኝ አብዛኛው ሕዝብ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ አይደለም ።

አማካኝ የሀገራቱ ኤሌክትሪክ የማዳረስ ፍጥነት ከ30 በመቶ የተሻገረ አይደለም። ከዜጋዋ ከ65 በመቶ የሚልቀው ሕዝቧ ለልጆቹ ማጥኛ፣ ለቤተሰቡ ምግብ ማብሰያና ለምሽቱ ብርሃን የሚያገኝበት የኤሌክትሪክ ኃይል የለውም። ጸሎቱ የማታ እራትና መብራት አታሳጣኝ ቢሆንም አልሰመረለትም። የውኃ ኃይል ማመንጫ በተለይ በራስጌ የተፋሰስ ሀገራት ለምቶ ጥቅም ላይ ባለመዋሉ በእድገታቸውና በልማታቸው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል። ይህ የኃይል እጥረት ዜጎች ፊታቸውን ወደ ከሰልና የማገዶ እንጨት እንዲያዞሩ በማድረጉ ከፍተኛ የደን ጭፍጨፋን ከማስከተሉ ባሻገር የአየር መዛባትንና ብክለትን እያስፋፋ ይገኛል። ለዚህ ነው በተመጣጣኝ ዋጋ ኃይል ማቅረብ የግድ የሆነው።

የራስጌ ሀገራት ግብርና በዋናነት የዝናብ ጥገኛ ቢሆንም በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአየር ፀባይ ለውጥ የተነሳ በየዓመቱ ሊባል በሚችል ሁኔታ ድርቅ ስለሚከሰት የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ፈተና ከሆነ ውሎ አድሯል። ስለዚህ እንደ መስኖ ያለ አማራጭ የውሃ ሀብቶችን በመጠቀም ምርታማነትን ማሳደግ የሕልውና ጉዳይ ነው። የናይልን የውሃ ሀብት በፍትሐዊነትና በኃላፊነት የመጠቀም ጉዳይ ከዓመት ዓመት እየገፋ ከመምጣቱ ባሻገር የተግባር እንቅስቃሴ ተጀምሯል።

ታንዛኒያ ከቪክቶሪያ ሐይቅ 170 ኪሎ ሜትር በተዘረጋ ቧንቧ ውሃ በመውሰድ በሀገሪቱ በከፋ ድህነት የሚታወቀውን ካሃማ የተባለውን አካባቢ በመስኖ ለማልማት እየተንቀሳቀሰች ነው። ሌሎች የራስጌ ተፋሰስ ሀገራትም ከወንዙ ድርሻቸውን በመጠቀም የውሃ ኃይል ማመንጫና የመስኖ ግንባታዎችን በማካሄድ ረሃብንና ድህነትን ለመዋጋት ቆርጠው ተነስተዋል። ለዓባይ ወንዝ ውሃ 86 በመቶውን የምታበረክተው ሀገራችን ኢትዮጵያ ታላቁን የሕዳሴ ግድብ የምትገነባው ከከፋ ድህነት ለመውጣትና የተፈጥሮ ሀብቷን የመጠቀም ሉዓላዊ መብቷን ለማረጋገጥ ነው።ሻሎም ! አሜን ።

በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን) fenote1971@gmail.com

አዲስ ዘመን ዓርብ መጋቢት 26 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You