የለውጡ ሰባት ዓመታት፣ በሰባት ማሳያዎች

እንደ መግቢያ

ተግባር ከቃል ይወለዳል፤ የቃል መነሻው ደግሞ የውስጥ ሃሳብና ስሜት ነው። እናም ከውስጥ ያለው እውነተኛ ስሜት በሃሳብ ጎልብቶ ወደ ቃል፤ ቃልም ተለውጦ ተግባር ይሆናል። ይሄ ግን በሁሉም መስክ፤ በሁሉም ዘንድ እውን የሚሆን አይደለም። ምክንያቱም፣ ሃሳብ ከልብ ካልሆነ፤ ቃልም ከልብ መነሳሳት በሚገለጥ ተግባር ካልታገዘ፤ ተግባር በበኩሉ ከአንድ ወቅት የወረት ጉዞ የተሻገረ ልምምድና ባሕል ካልሆነ፤ ሃሳብ ከምኞት፣ ቃልም ከወሬ የተሻገረ ፍሬ አይኖራቸውም።

ያለፉት ሰባት የለውጥ ዓመታት ጉዞም ከዚህ አኳያ ሲታይ፣ በልብ የኖረ ሃሳብ ወደ ቃል የተቀየረበት፤ በአፍ የተነገረውም ቃል በተግባር የተገለጠበት፤ ተግባሩም ልምምድ፣ ልምምዱም ባሕል የሆነበትን እውነት ያስመለከተ ነው። ለዚህ ደግሞ የለውጡ እርሾ ከተቀመጠበት የመጋቢት 24/2010 ዓ.ም የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመጀመሪያ ቀን የፓርላማ ንግግር ጀምሮ፣ በቅርቡ ቃል እስከ ባሕል መዝለቁ የተገለጠበትን የብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ ግኝቶች ያሉ እውነታዎችን መመልከት ይቻላል።

ዛሬም፣ የለውጡን ሰባተኛ ዓመት በምናስብበት እለት ሆነን፣ እነዚህን እውነታዎች ገጽ በገጽ ዘርዝረን ለመመልከት ባንችልም፤ ይሄንን ሊያስረዱ ይችላሉ ያልኳቸውን ቅንጭብ ነጥቦች፤ በተለይም የለውጡ ሰባት ዓመታትን ለመመልከት እድል ይሳጣሉ፣ የለውጡ መገለጫም ውስን አስረጅ ይሆናሉ ያልኳቸውን ሰባት (በሀሳብ ልዕልና፣ በማረም ጎዳና፣ በአልቆ ፈጻሚነት፣ በሰው ተኮርነት፣ በተግባር ተሻጋሪነት፣ በስኬታማ ዲፕሎማሲ እና በሁለንተናዊ ብልጽግና) ጉዳዮች በማንጸሪያነት በማንሳት ከወፍ በረር ባነሰ እይታ ለመጠቃቀስ እሞክራለሁ።

የአስተሳሰብ ልዕልና

በመግቢያዬ ለመጠቆም እንደሞከርኩት፣ ተግባር ጥንስሱ የልብ መሻትና ሃሳብ ነው፤ ሃሳብ ወደ ቃል አድርጎ ይወለዳል፤ በተግባር ስጋ ለብሶም ይገለጣል። የለውጡ የመጀመሪያ ዓመታትም በዚህ በኩል የሚገለጥ በርካታ ጉዳዮችን አስተናግደዋል። ምክንያቱም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመጀመሪያው የምክር ቤት ንግግራቸው የሕዝቡን ስሜት ከማስከን እና ለጥያቄዎቻቸው መልስ የማግኘት ተስፋን ከመስጠታቸው ባሻገር፤ የሕዝብን ጥያቄ ከማዳመጥ፤ በልኩ ከመገንዘብ እና እንደየጥያቄው ባህሪ መልስ ከመስጠት አኳያ በርካታ ሥራዎች ተሰርተዋል።

ለምሳሌ፣ ለውጡ እንዲወለድ ምክንያት ከሆኑ ጉዳዮች መካለል የፖለቲካ ምሕዳሩ ላይ የተፈጠረው ብልሽት ነው። በዚህም ሰዎች በፖለቲካ አመለካከታቸው ምክንያት ይታሰሩ፤ ይሰደዱ እና በአሸባሪነት መዝገብ ተይዘውም ለከፋ ችግር ተጋልጠው ነበር። የለውጡ የመጀመሪያ ወራትም እነዚህ ፖለቲካው የገፋቸው፣ ያሳደዳቸው፣ ያሰራቸውና ያዋከባቸው ኃይሎች በይቅርታም፣ በምሕረትም፣ ከአሸባሪነት መዝገብ በመሰረዝም ለሀገራቸው በቅተዋል፤ ከእስር ተፈትተዋል፤ ከጫካ ወደ ከተማ ገብተዋል።

ቀድሞ ፖለቲካውንም፣ ዴሞክራሲውንም፣ ኢኮኖሚውንም፣ ማኅበራዊ ሁነቱንም እግር ከወርች አስረው የያዙ የሕግና አሰራር ክፍተቶችን በመለየትም፤ አዳዲስ ሕጎች ወጡ፤ አንዳንዶችም ተሻሻሉ። ተቋማትም ከፖለቲካ እና ከፓርቲ አገልጋይነት መንፈስ እንዲላቀቁ የሚያስችል የሪፎርም ሥራ ተከናውኖ፤ ምርጫ ቦርድን፣ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንን የመሳሰሉ የዲሞክራሲ ተቋማት በልካቸው እንዲገለጡ ተደረገ።

የመከላከያ እና የደኅንነት ተቋማትም በዚሁ አግባብ በተሰራላቸው ሪፎርም ዛሬ ላይ ላሉበት ክብርና ደረጃ፤ ለሀገር አለኝታና ለጠላት ራስ ምታት ለመሆን ችለዋል። ሌላው፣ የፓርቲ ጉዳይ ሲሆን፤ በአጋር እና እኅት ስሌት ዜጎች የእኩልም፣ የፍትሃዊነትም ውክልና የተነፈጉበትን አካሄድ የሻረ፤ የአንድ ሀገራዊ ፓርቲ ምስረታን እውን በማድረግ ብልጽግና ፓርቲ እንዲወለድ የተደረገበት አካሄድ ከለውጡ ፍሬዎች መካከል ከፍ ብሎ የሚገለጥ ነው።

ከመገፋፋትና ከመጠፋፋት አካሄድ ይልቅ በሀሳብ የበላይነት ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ምሕዳር ከመፍጠር አኳያም፤ ፓርቲዎች ወደሰላማዊ መድረክ እንዲመጡ ተደርጓል። ዛሬ ላይ በምርጫ የተሸነፉ ፓርቲ አመራሮች በየደረጃው የመንግሥት የካቢኔ አባላት የመሆን እድል ተሰጥቷቸዋል። ከራስ አልፎ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ሰላማዊ ግንኙነትን ለመፍጠር በተሰራው ሥራም እንደ ሀገርም እንደ መሪም የሰላም የኖቬል ሽልማትን መቀዳጀት ተችሏል።

በዚህ መልኩ የለውጡ የመጀመሪያ ወራት እና ዓመታት ላይ የተከናወኑ በርካታ የሪፎርም ተግባራት ታዲያ፤ የለውጡ ኃይል የሀሳብ ከፍታን፤ የለውጡን ጉዞ የሃሳብ ተገዢነትን የሚያመላክቱ፤ የለውጡን ኃይልና መሪዎች የሃሳብን ልዕልና ለማንገስ ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚናገሩ ናቸው። ይሄም የለውጡ ኃይል በሕዝቡ ውስጥ እንዲገባ፤ መንግሥትም የሕዝብ አጋርነት እንዲኖረው፤ በምርጫ ሂደትም ከፍተኛ ድምጽ አግኝቶ የቀጣይ ጉዞውን በስኬት እንዲመራ አቅም የሆኑ ነበሩ።

የማረም ጎዳና

የሀሳብ ልዕልናን በማስረጽ የተጀመረው ጉዞ፤ ቀጣይ ማረፊያው ሕዝቡን ቀርቦ በማነጋገር፤ ችግር ብሎ የሚያነሳቸውን የማዳመጥ፤ እንዲታረሙ እና እንዲጎለብቱ የሚሻቸውን የመለየት፤ በዚሁ አግባብ ተገቢውን ሥራ በመስራት የተሻለ ነገር እውን ወደማድረግ ተሸጋገረ። በዚህ ረገድ ቀድሞ ሲሰራ የተበላሸውን ማስተካከል፤ በሕዝቦች መካከል የመከፋፈልና የመጠፋፋት እሳቤን ማረም፤ የትብብርና የአብሮነት እሴትን በመትከልም የይቅርታ መድረክ መድረሻ ድልድይን መገንባት ተጀመረ።

ይሄ ደግሞ በሀገር ውስጥ የነበሩ ጠብና ቁርሾዎችን በሚያክም በሕዝብ ለሕዝብ ውይይቶች አንድ ብሎ ተጀመረ። በሶማሌ፣ በኦሮሚያ፣ በትግራይ፣ በአማራ፣ በጋምቤላ፣ በደቡብ፣ በሐረሪ፣… በሁሉም አካባቢዎች የተናጠልም፤ የጋራም ውይይትና ምክክር ተደረገ። ከሀገር ውጪም በአሜሪካም፣ በአውሮፓም ምድር ሳይቀር የጥላቻን ግንብ ያፈረሰ፤ የእርቅና አንድነትን ድልድይ የገነባ ጉብኝትና ውይይት ተካሄደ።

እነዚህ ውይይቶች ታዲያ በሀሳብም፣ በምግባርም ይገለጡ የነበሩ ሕጸጾችን ማረም አስችለዋል። ለምሳሌ፣ የሰላም ችግሮችን ለማረም ከንግግር ባለፈ የእርቀ ሰላም ኮሚሽን እስከ ማቋቋም ተደረሰ። ከአፈጻጸም ጋር የተገናኙ ክፍቶችንም በጥናት ጭምር ተደግፎ በመለየት የማረም ሥራ ተከናወነ። በዚህ መልኩም አያሌ ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸው ፕሮጀክቶችን ማረምና ማቅናት ተችሏል።

የዚህ አንዱና ዐቢይ አብነት ደግሞ የዓባይ ግድብ ነው። የዓባይ ግድብ የዘመኑ ትውልድ ዓድዋ፤ የማድረግ አቅም መከሰቻ፤ የአንድነትና ሉዓላዊነት ማንጸሪያ ሕያው ፕሮጀክት ነው። ይሁን እንጂ ይህ ፕሮጀክት ቀድሞ በነበረው ሥርዓት ከመኖር ወደ አለመኖር እንዲሸጋገር የሚያደርጉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች እንዲፈተን ተደርጎ ቆይቷል።

ከለውጡ ማግስት ታዲያ ታርመው ሕልውናቸው እንዲመለስ ከተደረጉ በርካታ ግዙፍ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ መሆን ችሏል። በዚህም የዓባይ ግድብ የዚህ ዘመን ትውልድ ዳግማዊ ዓድዋ፤ የኢትዮጵያውያንም የኢኮኖሚ ነጻነትና ሉዓላዊነት ማጽኛ አንድ አቅም ሆኖ እንዲገለጥ፤ ዛሬ ላይ ሊጠናቀቅ የወራት እድሜ የተቆረጠለት መሆን ችሏል።

የማረም ጎዳናው፣ ከዚህ ያለፉ ሌሎች በርካታ የእርምት እርምጃዎችም የተከናወኑበት ነው። በተለይ ከለውጡ ማግስት በነበረው የሕዝብ ስሜትን ተገንዝቦ፣ ፍላጎቱንም ተረድቶ በልኩ ለመመለስ በሚደረገው ፈጣን ግስጋሴ ውስጥ እንደ ፓርቲም፣ እንደ ግለሰብም እግር የሚጎትቱ፤ ሁለት ቦታ ሆነው ጊዜ የሚጠባበቁ፤ በሚፈጠረው የለውጥና የሪፎርም ቀዳዳ ሁሉ የራስና የቡድን ፍላጎትን ለማሳካት የሚደረጉ ያልተገቡ ተግባራት ውስጥ የተሰማሩ አካላትን የመለየት እና የእርምት እርምጃ የመውሰድ ከፍ ያለ ሥራ የተሰራበት ነበር።

ለዚህም፣ ብልጽግና እንደ ፓርቲም፣ እንደ መንግሥትም ጎታች እሳቤን፤ ጎታች ግለሰብን፤ ጎታች የአሰራር ሂደትን፤ ጎታች የሕግና ተያያዥ ጉዳዮችን እየለየ አርሟል። መታረም ያልቻለውንም ቆርጦ ጥሏል። ይሄን ማድረግ መቻሉም፣ የለውጡ ማግስት መንገዱ እንዲቀና፣ እንዲፈጥን፣ ዛሬ ለታየው ከፍ ያለ ስኬትም የተናበበ እና የተደመረ አቅም እንዲጨብጥ አድርጎታል።

አልቆ ፈጻሚነት

ሌላው የለውጡ ዘመን ጉዞ፣ አልቆ የመፈጸም አቅም የመገንባት ነው። በዚህ በኩል የነበሩ ችግሮችን ከመለየት እና ከማረም ጎን ለጎን፤ የነበሩትን የማላቅ፣ አዳዲሶችንም ከፍ ባለ ደረጃ ጀምሮ የመፈጸም አብነታዊ ተግባራት ተከናውነዋል። የነበሩትን ከማረምና ከማላቅ አኳያ፤ የገበታ ለሸገር፣ የገበታ ለሀገር እንዲሁም የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶችን መመልከት ይቻላል።

እነዚህ ፕሮጀክቶች አዲስ ታስበው የተወለዱ አይደሉም። ይልቁንም የሚመለከት ዐይን፣ የሚያስተውል ልብ እና አርቆ የሚያስብ አዕምሮ ብቻ የሚፈልጉ ነበሩ። የአንድነት ፓርክ፣ የወዳጅነት አደባባይ፣ የእንጦጦ ፓርክ፣ የታላቁ ቤተ መንግሥት እድሳት፣ የጎርጎራ እና ሌሎችም፤ ቀድመው የነበሩ ግን መኖራቸው እንኳን የማይገለጥ፤ በተሰራው ሥራ ግን ችግሮቻቸው ተወግደው ልቀው የተገለጡ ናቸው።

ከፍ ያሉ አዳዲስ ሥራዎችን አስቦና አቅዶ ከመፈጸም አኳያም፤ የሳይንስ ሙዝዬም፣ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዝዬም፣ የአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬክሽን ማዕከል እና በርካታ ደረጃቸውን የጠበቁ ሎጆችና ሪዞርቶችን መጥቀስ ይቻላል። እነዚህም የለውጡን ማግስት ጉዞ በልዩነት እንዲታይ ከሚያደርጉት አያሌ የአልቆ መፈጸም እሴቱ ማንጸሪያዎች ናቸው።

ሰው ተኮርነት

ያለፉት ሰባት ዓመታት የማረምም ሆነ የማላቅ ተግባራት ማዕከላቸው ሰው ነው። ሰውን መሰረት አድርገው ይታረማሉ፤ ሰውን መሰረት አድርገው ይታቀዱና ከፍ ባለ አቅም ይፈጸማሉ። በዚህ በኩል በገበታ ፕሮጀክቶች የተከናወኑ ተግባራት፤ በዐረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ የተሰሩና እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች፤ የሌማት ትሩፋት ውጤታማ እንቅስቃሴዎች፤ የቤት ልማት መርሃ ግብሮች፤ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶችና እንቅስቃሴዎች፤ የግብርናው፣ የማሕበራዊውና ሌሎችም ዘርፎች ላይ የሚከናወኑ ተግባራት ተጠቃሽ ናቸው።

ይሄ ደግሞ ለውጡ የሰዎች ከፍ ያለ መሻት ያዋለደው እንደመሆኑ፤ የለውጡ ማግስት ጉዞም ይሄንኑ የሰው ፍላጎት የወለደውን እሳቤ ማዕከል ያደረገ ለመሆኑ ማረጋገጫ ነው። ብልጽግናም እንደ ፓርቲ ራሱን ሪፎርም ሲያደርግ ይሄንኑ የዜጎችን ፍላጎት ማዕከል አድርጎ እንደመሆኑም፤ የመንግሥትነት ሥራዎቹም ሰው ሰው የሚሸቱ፤ ሰውን ያቀፉ፣ የሰውን እድገትና መለወጥ የሚናገሩ፤ ፍትሃዊነትን የሚሰብኩ ናቸው።

ተሻጋሪነት

ከላይ የተጠቃቀሱት የለውጡ ማግስት ተግባራት ሌላው መገለጫ የሃሳብም ሆነ የተግባር ተሻጋሪነት ነው። የሚታሰበው ከዛሬ ባለፈ ስለ ነገ ነው፤ የሚታቀደው ከአሁን የተሻገረ የቀጣዩን አማክሎ ነው፤ የሚፈጸመውም ከእለት ጥቅም እልፍ ላለው ዘላቂ ተጠቃሚነት ነው። ይሄ ደግሞ ሀገር የአንድ ዘመን ትውልድ ሥራ ብቻ አለመሆኗን፤ የተግባር ተሻጋሪነትና ተሰናስሎ የግድ መሆንን የሚያረጋግጥ ሁነት ነው።

ትናንት የነበሩትን አልቆ በመፈጸም ሂደትም፤ አዳዲስ የሚፈጸሙት ከፍ ያሉ ተግባራትም ሰውን ማዕከል እንዲያደርጉ ሲደረግም፤ ዛሬን ብቻ ታሳቢ ያደረጉ አይደሉም። የነገውን ትውልድ የተሻለ የኑሮ ዘዬ እንዲያጎናጽፉ ዘመን ተሻጋሪነታቸው ከግምት ውስጥ ገብቶ ነው።

ትርክቶች ቢቀረጹ፤ የሰላም መንገዶች ቢተለሙ፤ የልማት ሥራዎች ቢከናወኑ፤ የፖለቲካ ውሳኔዎች ቢወሰኑ፤ የማኅበራዊ መሰረተ ልማቶች ቢዘረጉ፤ የሕግና አሰራር ማሻሻያዎች ቢደረጉ፤… የዛሬን ችግር ለማለፊያ ብቻ አይደለም። የነገን አብሮነት ማጽናት እንዲችሉ ጭምር ነው።

የባሕር በር ጉዳይ ዛሬ ላይ ቢቀነቀንና መንገዱ ቢጀመር፤ የዓባይ ግድብን አጠናቅቆ የማዳበሪያ ፋብሪካ ስለመገንባት ቢወራ፤ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ኢንዱስትሪዎች እንዲስፋፉ ቢደረግ፤ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ቢሊዬን ችግኞች በየዓመቱ ቢተከሉ፤ የሀገራዊ ምክክር ተቋቁሞ ዜጎች ችግሮቻቸውን በምክክር ፈትተው የጋራ ነጋቸውን አብረው እንዲተልሙ ሥራ ቢጀመር፤… ሁሉም ከዛሬ ባሻገር ብሩን ነገር በማለም ተወጥነው እየተፈጸሙ ያሉ ናቸው።

ስኬታማ ዴፕሎማሲ

የለውጡ ማግስት ሰባት ዓመታት በሀገር ውስጥ እንደታየው ዘርፈ ብዙ ውጤት ሁሉ፤ በዲፕሎማሲው መስክም ከፍ ያለ ውጤት የተመዘገበበት ነበር። ምክንያቱም፣ ለውጡ ከሰጠው እድል አንዱ፣ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ማሻሻያ ማድረግ መቻሉ ነው። በዚህ ፖሊሲ የዜጎችን ክብር ከማስጠበቅ ጀምሮ፤ እንደ ሀገር የሚደረጉ የዲፕሎማሲ እና የውጭ ግንኙነት ተግባራት ሁሉ የሀገርን ጥቅምና ፍላጎት ያስጠበቁ፤ የጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረቱ እንዲሆኑ አስችሏል።

ከዚህም በላይ ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ሂደቱ፣ ዜጎች የሀገራቸው ዲፕሎማትና አምባሳደር የመሆን ከፍታን የሰጣቸው እንደመሆኑ፤ መንግሥት በየሀገሩ ከሚያሰማራው ዲፕሎማት ያልተናነሰ ሥራን ሰርተዋል። ከፍ ያሉ ሀገራዊ ጫናዎችና ፈተናዎችን የመሻገር አቅምን ፈጥረዋል። የበቃ (ኖ ሞር) ንቅናቄ፣ የዓባይ ግድብ ድርድርና ዲፕሎማሲያዊ ሥራዎች፣ የብሪክስ የአባልነት ጥያቄ ምላሽ ማግኘት፣ የባሕር በር ጥያቄ እና የተጀመሩ ሥራዎች፣ የሰላም ማስከበር ተግባራትና ሌሎችም ዘርፈ ብዙ ውጤቶች የለውጡ ማግስት ዓመታት የዲፕሎማሲው መስክ መገለጫዎች ናቸው።

ሁለንተናዊ ብልጽግናን ዓላሚነት

አንድ ሀገር ሙሉ የምትሆነው፤ የተሟላ ሉዓላዊነቷን የምትጎናጸፈውም ሆነ በለጸገች የሚባለው፤ በሁሉም መስክ ስኬት ሲኖራት፤ ሁሉን አቀፍ እድገት፣ ልማትና ብልጽግናን ማምጣት ስትችል ነው። ብልጽግናም እንደ መንግሥት ይሄን አምኖ ብቻ ሳይሆን፤ ከልቡ ይዞ እየሰራ ይገኛል።

ምክንያቱም፣ ሀገራዊ ብልጽግናን የአንድ መስክ ሥራ ብቻውን እውን የሚያደርገው አይደለም። ኢኮኖሚያዊ ብልጽግና ከማኅበራዊ ብልጽግና ጋር መተሳሰር አለበት። የሰው ልጅ በጤናው፣ በአዕምሮው፣ በኢኮኖሚው፣ በአስተሳሰብና ሌሎችም ጉዳዮቹ ምሉዕ መሆንን ይፈልጋል። ይሄ ደግሞ የግለሰብ ብቻ ሳይሆን የሕዝብ እና ሀገርም መሻት ነው። ይሄ መሻት ሙሉ የመሆን፤ በሁሉም መስክ በቅቶ የመገኘት፤ በጥቅሉም የመበልጸግ እሳቤ ነው።

ብልጽግናም እንደ ፓርቲ ከስሙም መረዳት እንደሚቻለው፤ ሁለንተናዊ ብልጽግናን እውን ማድረግ ላይ የተመሰረተ ነው። ለዚህም ነው መደመርን መንገዱ፤ ብልጽግናንም መዳረሻው አድርጎ ላለፉት ዓመታት ሲሰራ የቆየው። በ2018 ከተስፋ ብርሃን ወደሚጨበጥ ብርሃን፣ በ2023 የአፍሪካ ብልጽግና ተምሳሌት፣ እንዲሁም በ2040 ዓለም አቀፍ አርኣያ የሆነች ሀገር እውን ማድረግን ወጥኖ፤ ይሄንኑ ለምርጫ መወዳደሪያ ሀሳብ አድርጎ በማኑፌስቶ ቀርጾ ሲያቀርብም ከዚሁ ሁለንተናዊ ብልጽግናን እውን የማድረግ ሕልሙና ግቡ የመነጨ ነው። የለውጥ ማግስት የሰባት ዓመታት መንገድም ይሄንኑ የሚያረጋግጥ ነው።

በየኔነው ስሻው

አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 24 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You