የኦዲት ግኝት ያለባቸው ተቋማት ላይ የሚወሰደው ርምጃ በቂ አይደለም

አዲስ አበባ፦ የኦዲት ግኝት ባለባቸው ተቋማት ላይ የሚወሰደው ርምጃ በቂ አይደለም ሲል የከተማ አስተዳደሩ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት አስታወቀ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ከባለድርሻ አካላትና ከኦዲት ተደራጊ ተቋማት አመራሮች ጋር የመንግሥት ሀብትን ከብክነት እና ምዝበራ መከላከል ላይ ያተኮር ውይይት ትናንት አካሂዷል።

የመሥሪያ ቤቱ ዋና ኦዲተር አመንቴ መቻሉ በወቅቱ እንደገለጹት፤ የኦዲት ግኝት በታየባቸው በተሰብሳቢ እና ተከፋይ ሂሳቦች ላይ ርምጃ እንዲወሰድ የተጠናከረ ግፊት ያለማድረግ፣ ከማን እንደሚሰበሰቡ እና ለማን እንደሚከፈሉ ባልታወቁት ሂሳቦች ላይ ግልጽ የሆነ ውሳኔ ሰጥቶ አፈጻጸሙን የመከታተል ችግር ይስተዋላል:: እንዲሁም ተጠያቂነት አለመጠናከር እና የፋይናንስ መመሪያዎችን ለረጅም ጊዜ አለማሻሻል በኦዲት ወቅት በተቋማት የታዩ ክፍተቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።

የዋና ኦዲት መሥሪያ ቤት የኦዲት ሽፋን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ነው። በዚሁ ልክ ደግሞ የሚወሰደው ርምጃ መጠናከር አለበት ያሉት አቶ አመንቴ፤ ምክንያቱም ግኝቶች ከሥራዎች ብዛትና ጫና ጋር ተያይዞ መጠናቸው እያደገ መምጣቱን አመልክተዋል:: ከዚህ አንፃርም የኦዲት ግኝት ያለባቸው የከተማ አስተዳደሩ ተቋማት ላይ የሚወሰደው ርምጃ በቂ አይደለም ብለዋል።

ሰነዶች ከአስር ዓመት በላይ ከቆዩ ርምጃ የማስወሰድ ኃይላቸውን እንደሚያጡ የጠቀሱት አቶ አመንቴ፤ ተጠያቂ አልሆንም የሚል አካል ካለ ጉዳዩን በሕግ አግባብ ማየት አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል። እንዲሁም ከፋይ የሌላውን መዝገቦች በተመሳሳይ በሕግ አግባብ ማየትና ምላሽ መስጠት ለነገ የማይባል ተግባር ነው ያሉት።

የአዲስ አበባ ሲቪል ምዝገባና ነዋሪዎች አገልግሎት ኤጀንሲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግርማ መኮንን በበኩላቸው፤ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት በከተማ አስተዳደሩ የሚሰበሰበው ገቢ በተቀመጠለት ዓላማ መሠረት ጥቅም ላይ እንዲውል የቁጥጥርና የክትትል ሥራ የሚሠራ ተቋም መሆኑን ገልጸዋል።

ይህም አጠቃላይ የከተማዋን ሀብት ከብክነትና ከምዝበራ ለመከላከል የሚያስችል ነው። ነገር ግን በዚህ ሂደት የሚፈጠሩ የተለያዩ ክፍተቶች መኖራቸውን ገልጸው፤ የተቋማት የውስጥ ኦዲተሮችን አቅም ማሳደግ፣ ከ20 ዓመታት በላይ ሲንከባለሉ ለመጡ የኦዲት ግኝቶች መፍትሔ ማስቀመጥ እና የዲጂታል አሠራሮች ላይ አስፈላጊውን አሠራር መፍጠር ከዋና ኦዲት መሥሪያ ቤት የሚጠበቁ ሥራዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።

ተጠያቂነት ያለው አሠራር በመዘርጋት የመንግሥት በጀት እና ሀብት ከብክነትና ከምዝበራ ማዳን የእያንዳንዱ የመንግሥት ሠራተኛ ኃላፊነት መሆኑን የገለጹት ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የመንግሥት በጀት አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ስንታይተሁ ደስታ፤ በየጊዜው የኦዲት ግኝቶች ክትትል እንዲደረግባቸው ለምክር ቤት አስፈፃሚ አካላት ይሰጣል። በዚህም ግኝቶቹ ለረጅም ጊዜ ሲንከባለሉ የቆዩ በመሆናቸውን መረዳት ተችሏል ነው ያሉት።

አሁን ግን ይህንን ችግር ከስር መሠረቱ ለማስተካከል በዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት አስተባባሪነት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ችግሮቹ እስኪፈቱ ድረስ ምክር ቤቱ በራሱ አሠራርና መመሪያ መሠረት ክትትል እንደሚያደርግ ጠቁመው፤ የተቋማት ኃላፊዎች የተንከባለሉ የኦዲት ግኝቶች ለቀጣይ አመራር እንዳይተላለፉ የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በውይይት መድረኩ በከተማ አስተዳደሩ የሚገኙ የአስፈፃሚ ተቋማት አመራሮችና የ11ዱም ክፍለ ከተማ ምክር ቤት አፈ ጉባኤዎች ተገኝተዋል።

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን ሐሙስ መጋቢት 25 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You