
አዲስ አበባ:- ሀገራዊ ብልፅግናን ለማስፈን ብሔራዊ ትርክትን ማፅናት፣ የሕዝብን ተጠቃሚነት እና የተጀመረውን ሁለንተናዊ ልማትንም ማስቀጠል እንደሚገባ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ፡፡
“ትናንት፣ ዛሬና ነገን ለኢትዮጵያ ልዕልና” በሚል መሪ ሃሳብ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አመራርና አባላት ለውጥ የተካሄደበትን 7ኛ ዓመት አክብረዋል።
በውይይቱ የተገኙት አፈጉባኤ አገኘሁ፤ በአንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋሉ ችግሮችን በመቋቋም ለውጡን ማፅናት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። ለውጡን ለማስቀጠል ብሔራዊ ትርክትን ማፅናት፣ የሕዝብን ተጠቃሚነትና የተጀመረውን ሁለንተናዊ ልማት ማስፈን እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡
ሰላምና ደኅንነትን ለማስፈን ለንግግር እና ለውይይት ዝግጁ መሆን እንደሚያስፈልግም አመልክተው፤ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት በትኩረት መሥራት እንደሚገባም ጠቁመዋል
ሥራ አጥነትን፣ የኑሮ ውድነትን፣ የዋጋ ንረት ለመከላከልና የኢኮኖሚ ስብራቱን ለመጠገን የኢኮኖሚ ማሻሻያ መደረጉን በመጠቆምም፤ አረንጓዴ ዐሻራ፣ የሌማት ትሩፋትና ሌሎችም የልማት ሥራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።
ከለውጡ በፊት ኢትዮጵያ መስቀለኛ መንገድ ላይ ነበረች፣ ለውጡ ተጋርጦ የነበረውን የመፍረስ አደጋ የታደገ እና ለዓለም ተምሳሌት የሆነ ተግባር የተከናወነበት መሆኑንም አመልክተዋል፡፡
ለውጡም በመላው ኢትዮጵያውያን ተሳትፎ የመጣ፤ ሕዝባዊ፣ ድርጅታዊና ሕገመንግሥታዊ ሥርዓትን የተከተለና ባለፉት ሥርዓተ መንግሥታት ውስጥ ከተካሄዱ የለውጥ ሙከራዎች የተለየ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ውስብስብ ችግሮችን አልፎ እውን የሆነ ኢትዮጵያውያን የሕይወት መስዋዕትነት ከፍለውበት የተሳካ መሆኑንም አስታውስተው፤ ለውጡ በተገቢው መንገድ እንዲመራ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ ከማመንጨት ጀምሮ ሮድ ማፕ በማዘጋጀትና ለውጡን በመምራት ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያደረጉበት መሆኑንም አመልክተዋል፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈጉባኤ ሎሚ በዶ በበኩላቸው፤ ለውጡ መጠነ ሰፊና ውስብስብ ችግሮችን በመጋፈጥ አኩሪ ድሎችን እንደተመዘገበበት ጠቁመዋል፡፡
ምክትል አፈ ጉባኤ ሎሚ በዶ፤ ለውጡ ኢትዮጵያውያን ከጫፍ እስከ ጫፍ የተረባረቡበት፣ መጋቢት 24 የሕዳሴ ግድብ የመሠረት ድንጋይ የተጣለበት እና የፖለቲካ ለውጥ ተካሂዶ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ቃለ መሐላ የፈጸሙበት ዕለት መሆኑን አስታውሰዋል፡፡
መጋቢት 24 በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሂደት መጠን ሰፊና ውስብስብ ችግሮችን በመጋፈጥ በሁሉም መስክ አኩሪ ድል የተመዘገበበት ፈተናዎችን ወደ ዕድል መቀየር የተቻለበት መሆኑንም አንስተዋል፡፡ የሕዝብን ተጠቃሚነት እና የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር የሚያስችሉ ሥራዎች መከናወናቸውንም ተናግረዋል።
የፍትሕ ዘርፉን በማዘመን፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው ሥርዓት ማስፈን መቻሉን ጠቁመዋል፡፡ ፍትሕና ርትዕ ያለው ሥርዓት እንዲሰፍን እና አሳሪ የነበሩ ሕጎች እንዲሻሻሉ የተደረገበት ሥራ የተከናወነበት እንደሆነም አመልክተዋል፡፡ የተሻለች ኢትዮጵያን ለመፍጠር የሚያስችል ምዕራፍ ላይ መደረሱንም ነው ምክትል አፈ ጉባኤ ሎሚ የጠቆሙት፡፡
የዴሞክራሲ ሥርዓትን ለማጽናት ዘርፈ ብዙ ሥራዎች መተግበራቸውን፣ ያደሩ ችግሮችን ለመፍታት ጥረት የተደረገበት፣ የዴሞክራሲ ተቋማት ነፃ፣ ገለልተኛ እና ጠንካራ እንዲሆኑ መሠረት የተጣለበት ሂደት እንደሆነም አስታውሰዋል፡፡
ለውጡ ኢትዮጵያውያን ያለልዩነት በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች እንዲሳተፉ ማስቻሉንም አመልክተው፤ ውስጣዊ እና ውጫዊ ጫናዎችን በመቋቋም ተፈጥሯዊ ሀብቷን በአግባቡ እንድትጠቀም ያስቻለ ተግባር መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
አካታችነትንና አቃፊነትን ለማስፈን የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አባላት የተሻለ የመሪነት ሚና ኖሯቸው አስተዋፅዖ እንዲያደርጉ ዕድል መፈጠሩንም ጠቁመዋል።
በ50 ከተሞች እየተከናወነ የሚገኘው የኮሪዶር ልማት ለኑሮ ምቹ ማድረግን ዓላማ ያደረገና የከተማና የገጠር ማኅበረሰብ አብሮ እንዲያድግ ያስቻለ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ዘላለም ግዛው
አዲስ ዘመን ሐሙስ መጋቢት 25 ቀን 2017 ዓ.ም