ግድቡ ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ባሻገር የሀገራትን ትስስር የሚያጠናክር ነው

አዲስ አበባ፤- በኢትዮጵያውያን የተባበረ ክንድ ተገንብቶ ፍጻሜውን ሊያገኝ ከጫፍ የደረሰው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ባለፈ የሀገራትን ግንኙነት በማጠናከር ረገድ ጉልህ ድርሻ እንዳለው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክ አሶሴሽን ተመራማሪ ሞላ ዓለማየሁ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ሞላ ዓለማየሁ (ዶ/ር) ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያውያን በይቻላል መንፈስ እንዲሁም ከድህነት ለመውጣት ባላቸው ከፍተኛ ቁጭት አስበውበት የገነቡት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከሚኖረው ኢኮኖሚያዊ አበርክቶ ባለፈ የሀገራትን ሕዝባዊ ግንኙነት በማጠናከር ረገድ ጉልህ አስተዋፅዖ አለው፡፡ ግድቡ በዋናነት የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጭ በመሆኑ በዋነኛነት በሀገሪቱ ያለውን የኃይል አቅርቦትና ፍላጎት በማጣጣም የሀገሪቷን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ያሳልጣል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ጉልህ አስተዋፅዖ እንደሚኖረው የተገለጸው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦቱ በቀዳሚነት የሚጠቀስ  ነው፡፡ ያሉት ሞላ ዓለማየሁ (ዶ/ር)፤ ኢነርጂ ወይንም ኃይል ለኢንዱስትሪ፣ ለግብርና ለአገልግሎት ዘርፎች ዋና ግብዓት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ይህ ኃይል ለኢኮኖሚያዊ ዕድገት ወሳኝ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ለሚመረቱ ምርቶችም ሆነ አገልግሎት ለሚሰጡ ተቋማት ለማንኛውም ሴክተር ዋና ግብዓት የሆነው ኢነርጂ ወይንም ኃይልን በአስተማማኝ ሁኔታ ማቅረብ መቻል ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ጠቅሰው፤ ለአብነትም አምራች ድርጅቶች በሙሉ አቅማቸው ማምረት የሚያስችላቸውን ትልቅ አቅም የሚያጎናጽፋቸው  ከመሆኑም በላይ ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር ኢኮኖሚው ላይ በጎ ተፅዕኖ እንደሚፈጥር አመልክተዋል፡፡

‹‹ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሚያመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል የሀገሪቱን የኃይል አቅርቦት በከፍተኛ መጠን በመጨመር ኢኮኖሚያዊ እድገት ያመጣል›› ያሉት ሞላ ዓለማየሁ (ዶ/ር)፤ ይህም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች የኃይል አቅርቦት እንዲያገኙ ያደርጋል፡፡ የኃይል አቅርቦት የሚያገኙ ዜጎችም ሥራቸው የተሳካ እንዲሆን በብዙ ያግዛል፡፡ ለአብነትም በቤተሰብ ደረጃ የኃይል አቅርቦት በተሟላ ሁኔታ የሚያገኝ አንድ ግለሰብ ሥራውን በአጭር ጊዜና በቀላሉ ማጠናቀቅ ከቻለ ቀሪ ጊዜውን በአግባቡ በመጠቀም አምራች መሆን ይችላል ብለዋል፡፡

በተለይም ከሀገር ውስጥ ፍጆታ የተረፈውን የኤሌክትሪክ ኃይል ወደ ውጭ ሀገራት ኤክስፖርት በማድረግ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ከፍ ማድረግ ይቻላል ያሉት ሞላ ዓለማየሁ (ዶ/ር)፤ ግድቡ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ጉልህ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ኤክስፖርት በማድረግ ከምታገኘው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ባሻገር የኤሌክትሪክ ኃይልን ከኢትዮጵያ ከሚገዙ ሀገራት ጋር የተሻለ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ግንኙነት መፍጠር እንደሚያስችላትም አስረድተዋል፡፡

‹‹በአሁን ወቅት ኢነርጂ ለአብዛኞቹ ሀገራት ዋና ግብዓት ሆኖ እያገለገለ ይገኛል›› ያሉት ሞላ ዓለማየሁ (ዶ/ር)፤ ይህንኑ የኃይል ፍላጎት ለሟሟላት የሚፈልጉ በርካታ ሀገራትም ወደ ተለያዩ ሀገራት እያማተሩ እንደሆነና ለዚህም ኢትዮጵያ ተመራጭ እንደሆነች ገልጸዋል፡፡

የኤሌክትሪክ ኃይልን ከሀገር ውስጥ ፍጆታ ባለፈ ለውጭ ገበያ ማቅረብ የሚስችላትን ግድብ በራሷ አቅም መገንባት የቻለችው ኢትዮጵያ በአሁን ወቅት የኤሌክትሪክ ኃይልን ለተለያዩ ሀገራት በማቅረብ ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ባለፈ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን የምታገኝ እንደሆነና በብዙ እንደምታተርፍ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ ከምታገኘው ገቢ በተጨማሪ የኤሌክትሪክ ኃይል ከምታቀርብላቸው ሀገራት ጋር የተጠናከረ ሕዝባዊ ግንኙነት የመፍጠር ዕድል እንዳላት የገለጹት ሞላ ዓለማየሁ (ዶ/ር)፤ በሁለቱ ሀገራት በሚኖሩ ሕዝቦች መካከል የሚፈጠረው የወንድማማችነት ስሜትም ጠንካራና ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ነው የተናገሩት፡፡

የግድቡ ቀሪ ሥራዎች በፍጥነት ተጠናቅቀው ወደ ሥራ መግባት እንዲቻል መንግሥትን ጨምሮ ሕዝቡና ባለሃብቱ ያለመታከት ከፍተኛ ጥረት ሊያደርጉ እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን ሐሙስ መጋቢት 25 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You