አዲሱ የአሜሪካና የኢራን ፍጥጫ

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን በኑክሌር መሣሪያዋ ጉዳይ ከአሜሪካ ጋር በቀጥታ የመነጋገር ፍላጎት አላት ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል። ፕሬዚዳንቱ ሰሞኑን ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ፣ ‹‹ኢራን በሦስተኛ ወገን አደራዳሪ በኩል መነጋገር ፈልጋ ነበር፤ አሁን ግን አቋማን የቀረች ይመስለኛል›› ብለዋል። ዋሺንግተን ከቴህራን ጋር የፊት ለፊት ንግግር ታደርጋለች የሚል ተስፋ እንዳላቸውም ገልፀዋል።

‹‹በቀጥታ ብንነጋገር የተሻለ ይሆናል ብዬ አስባለሁ። በቀጥታ መነጋገር ለውይይት የሚቀርበውን አካል በተሻለ ሁኔታ ለመረዳት ያስችላል።እነሱ ሦስተኛ ወገን አደራዳሪዎችን መጠቀም ፈልገው ነበር ። አሁን ግን ያ ፍላጎት ያለ አይመስለኝም›› ብለዋል።ፕሬዚዳንት ትራምፕ በኢራን የኑክሌር መርሃ ግብር ላይ ለመነጋገር ፍላጎት እንዳላቸው የሚገልፅ ደብዳቤ ባለፈው ወር ለኢራን ባለሥልጣናት መላካቸው ተገልጿል።

ትራምፕ ይህን ቢሉም ኢራን ግን ቀደም ብላ ይፋ ባደረገችው መግለጫ፣ ከአሜሪካ ጋር በቀጥታ መነጋገር እንደማትፈልግ አሳውቃለች።ከሳምንት በፊት የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት መሱድ ፔዥሽኪያን ሀገራቸው በሦስተኛ ወገን አደራዳሪዎች በኩል ካልሆነ ከአሜሪካ ጋር በቀጥታ ለመነጋገር ፍላጎት እንደሌላት ገልፀዋል።

ፕሬዚዳንቱ ለካቢኔ አባላት በሰጡት ማብራሪያ ‹‹ከአሜሪካ ፕሬዚዳንት ለተላከልን ደብዳቤ በኦማን በኩል ምላሽ ሰጥተናል። ቀጥተኛ ንግግርን እንደማንቀበልና በሦስተኛ ወገን በኩል ለሚደረግ ውይይት ግን ዝግጁ መሆናችንን አሳውቀናል›› ነው ያሉት። ከዚህ በተጨማሪም ኢራን በመርህ ደረጃ ድርድርን የምትቀበል ቢሆንም አሜሪካ ከዚህ ቀደም በኢራን ላይ ያደረገቻቸውን ተገቢ ያልሆኑ ድርጊቶችን ማረምና መተማመንን መገንባት እንደሚገባት ፕሬዚዳንት ፔዥሽኪያን ገልጸዋል።

በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ለኢራኑ መንፈሳዊ መሪ አያቶላህ ኻሜኒ በጻፉት ደብዳቤ፣ ኢራን ከአሜሪካ ጋር ለመነጋገር ፍላጎት ካላሳየች ኢኮኖሚያዊና ወታደራዊ ርምጃዎች እንደሚወሰዱባት አስጠንቅቀውም ነበር።ኻሜኒ በበኩላቸው ‹‹ኢራንን ማስፈራራት ምንም ለውጥ እንደማያመጣ አሜሪካ ማወቅ አለባት።አሜሪካም ሆኑ ሌሎች አካላት ኢራንን የሚጎዳ ተግባር ከፈፀሙ አደገኛ ቅጣት እንደሚጠብቃቸው ሊያውቁ ይገባል›› በማለት ለትራምፕ ዛቻ ምላሽ ሰጥተዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ኢራን ሚሳኤል ለማስቀመጥ ከምድር በታች የገነባቻቸውን ምሥጢራዊ ማቆያዎች በቅርቡ ይፋ አድርጋለች። ከእስራኤልና አሜሪካ የሚቃጣ ጥቃትን ለመመከት እንደምትጠቀምባቸውም አስታውቃለች።

አሜሪካ ባለፈው ሳምንት ቦምብ የጫኑ ስድስት ተጨማሪ የጦር አውሮፕላኖችን በኢራንና የመን አቅራቢያ ወደሚገኙ ወታደራዊ ጣቢያዎች ማስጠጋቷን የሀገሪቱ ባለሥልጣን ለሮይተርስ ጠቁመዋል። ኢራን ለዚህ በምላሹ ‹‹አሜሪካ በቀጣናው ያላት ወታደራዊ እንቅስቃሴ የመስታወት ቤት ውስጥ ተቀምጦ ሌሎች ላይ ድንጋይ የመወርወር ያህል ነው›› በማለት አስጠንቅቃለች።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ እስላማዊቷን ሪፐብሊክ አጥብቀው በመኮነን ይታወቃሉ። በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው የኢኮኖሚ ማዕቀቦችን ጨምሮ በኢራን ላይ የተለያዩ ርምጃዎችን ወስደዋል። ለአብነት ያህል ሀገራትና ትልልቅ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ከኢራን ነዳጅ እንዳይገዙ አስጠንቅቀዋል፤ የኢራንን አብዮታዊ ዘብ ከአሸባሪዎች መዝገብ አስፍረውታል፤ ከባድ የጦር መሣሪዎችን ኢራን ወደምትገኝበት ቀጣና ልከው አሠማርተዋል፤ አሜሪካን እ.አ.አ በ2015 በኢራንና በስድስቱ የዓለማችን ኃያላን ሀገራት (አሜሪካ፣ ቻይና፣ ሩሲያ፣ ጀርመን፣ ብሪታኒያ እና ፈረንሳይ) መካከል ከተፈረመው የኢራን የኑክሌር ስምምነት (Iran Nuclear Deal) አስወጥተዋታል።

በኢራንና በስድስቱ የዓለማችን ኃያላን ሀገራት (አሜሪካ፣ ቻይና፣ ሩስያ፣ ጀርመን፣ ብሪታኒያ እና ፈረንሳይ) መካከል የተፈረመውን የኢራን የኑክሌር ስምምነት ኢራን የኑክሌር ጦር መሣሪያ ግንባታዋን እንድታቆምና በምላሹም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ በአውሮፓ ኅብረትና በአሜሪካ የተጣሉባት ማዕቀቦች እንዲነሱላት ይደነግጋል። ኢራን ስምምነቱን የማታከብር ከሆነም ቀደም ባሉት ጊዜያት ከተጣሉባት ማዕቀቦች የከፋ ፖለቲካዊና ምጣኔ ሀብታዊ ተፅዕኖ ያላቸው ማዕቀቦች እንደሚጣሉባት፤ ከዚያም አልፎ ጉዳዩ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት እንደሚቀርብ በስምምነቱ ውስጥ ከተካተቱት ድንጋጌዎች መካከል ይጠቀሳል።

ከስምምነቱ መፈረም በኋላም ኢራን የስምምነቱን ድንጋጌዎች ተቀብላ አንዳንድ ርምጃዎችን ወስዳ ነበር። ከእነዚህም መካከል በናታንዝ እና ፎርዶ ጣቢያዎች የሚገኙ ግብዓቶች እንዲወገዱ መደረጉ፤ በብዙ ቶን የሚቆጠር ዩራኒየም ወደ ሩሲያ መወሰዱ እና የዓለም አቀፉ አቶሚክ ኃይል ተቆጣጣሪ ድርጅት ባለሙያዎች የኢራንን የኑክሌር መሣሪያ ግንባታ በየጣቢያዎቹ ተገኝተው መመልከታቸው ይጠቀሳሉ።

ስምምነቱ ሲፈረም አሜሪካን ሲያስተዳድሩ የነበሩት የወቅቱ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ስምምነቱ እንደትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ድል ተቆጥሮላቸዋል።ኦባማን ተክተው ወደ ነጩ ቤት የመጡት ቢሊየነሩ ዶናልድ ትራምፕ ግን ስምምነቱን መቀበል ይቅርና ስለስምምነቱ መስማት አይፈልጉም። ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ‹‹የምንጊዜውም መጥፎው ስምምነት›› እያሉ የሚያብጠለጥሉትን ይህን ስምምነት እንደሚሰርዙት ያስታወቁት ገና በፕሬዚዳንታዊ የምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ነው።

ትራምፕ ስምምነቱ ኢራንን ለተወሰኑ ጊዜያት ብቻ ከኑክሌር ማበልጸግ ተግባሯ የሚገታ እንጂ ረጅም ርቀት ተወንጫፊ ባሊስቲክ ሚሳይሎችን ከማምረት የሚያግዳት አይደለም ብለው ያምናሉ።እንዲያውም ስምምነቱ ኢራን በውጭ ሀገራት ባንኮች ያላትንና እንዳይንቀሳቀስ ታግዶባት የነበረው በመቶ ቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ እንዲለቀቅላት ስላደረገ ኢራን ገንዘቡን ሽብርተኞችን ለመደገፍ፣ የጦር መሣሪያ ለመግዛት እንዲሁም አክራሪነትን ለማስፋፋት ተጠቅማበታለች ሲሉ ይከራከራሉ።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ የኢራን የኑክሌር ስምምነትን የማይቀበሉባቸው ምክንያቶች ብዙ እንደሆኑ በተንታኞች ዘንድ ይገለፃል።ሰውየው የአሜሪካ ጠንካራ አጋርና ወዳጅ የሆነችውን እስራኤልን ለማጥፋት እቅድ አላት የምትባለው ኢራን የኑክሌር መሣሪያ ታጥቃ ማየት አይፈልጉም። በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው የልጃቸው ኢቫንካ ትራምፕ ባለቤት የሆኑት አይሁዳዊው ጃሬድ ኩሽነር የፕሬዚዳንቱ ከፍተኛ አማካሪ መሆን ደግሞ ሰውየው ለኢራን ያላቸውን ጥላቻ አባብሶታል ብለው የሚናገሩም አሉ፡፡

የስምምነቱ ፈራሚ የሆኑ የአውሮፓ ሀገራት (ብሪታኒያ፣ ጀርመንና ፈረንሳይ) ግን ኢራን የኑክሌር ጦር መሣሪያ ባለቤት እንዳትሆን ለማድረግ ስምምነቱን አክብሮ ከመቀጠል የተሻለ ሌላ አማራጭ እንደሌለ ደጋግመው ገልፀዋል፡፡

በጆርጅ ዋሺንግተን ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ጉዳዮች መምህር ባርባራ ስላቪን፣ ትራምፕ ከቀድሞው ስምምነት አሜሪካን በማስወጣታቸው ኢራን በአሜሪካ ላይ ያላት እምነት ዝቅተኛ ቢሆን የሚያስገርም እንዳልሆነ ይልፃሉ።የኢራን ኢኮኖሚ በአሜሪካ ማዕቀቦች ክፉኛ ስለመጎዳቱን የሚገልፁት ስላቪን፣ ‹‹ከፊዚካል ጥቃቱ ይልቅ የኢኮኖሚ ቀውሱ ኢራናውያንን የበለጠ ያስጨንቃቸዋል። አሜሪካ ተጨማሪ የጦር መሣሪዎችን ወደ አካባቢው ልካለች። ይህ ደግሞ የዲፕሎማሲ ጥረቶች ካልተሳኩ ወታደራዊ ርምጃዎች ሊወሰዱ እንደሚችሉ አመላካች ነው›› ይላሉ።

በኢራን ላይ ሊወሰድ የሚችል ወታደራዊ ርምጃ ጉዳይ የፈረንሳይም ስጋት ነው።የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዦኖል ባሮ ለሀገሪቱ ፓርላማ ባደረጉት ንግግር፣ ሰላማዊ ድርድሮች ካልተሳኩ ወታደራዊ ርምጃዎች መታየታቸው እንደማይቀር ስጋታቸውን ገልፀዋል። “ኢራን ፈፅሞ የኑክሌር ጦር መሣሪያ ባለቤት መሆን የለባትም›› ያሉት ሚኒስትሩ፣ ከኢራን ጋር የሚደረጉ የዲፕሎማሲ አማራጮች የመሳካታቸው እድል ጠባብ ሆኖ መቆየቱንም ጠቅሰዋል።

ምዕራባውያን ኢራን የኑክሌር ጦር መሣሪያ ባለቤት እንዳትሆን ተደጋጋሚ ጫናዎችን ሲያደርጉባት ቆይተዋል። ኢራን በበኩሏ የኑክሌር ግንባታዋን ለሰላማዊ የኃይል ማመንጫ እንጂ ለጦርነት የማዋል ፍላጎት እንደሌላት ደጋግማ ትገልፃለች።

አንተነህ ቸሬ

አዲስ ዘመን መጋቢት 28 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You