
በአማራ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ መድረክ መካሄድ ጀመረ
ባህርዳር ፦ በመሠረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ያለንን የሃሳብ ልዩነት በምክክር ለመፍታት ዝግጁ መሆን ይገባል ሲሉ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ገለጹ፡፡ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአማራ ክልል የሚያካሂደው የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ በትናትናው ዕለት ተጀምሯል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያውያን በአንድ ልብ መክረንና ተግባብተን እንደ አንድ ሕዝብ በተሰለፍንባቸው ጉዳዮች ላይ ታሪካዊ ድሎችን አስመዝግበናል። በአባቶቻችን ጥበብ፣ በእናቶቻችን ሀገር ወዳድነትና ፀሎት፣ በወጣቶች ጥንካሬ ዛሬ ባለሀገር መሆን ችለናል ብለዋል።
በኢትዮጵያ እጅግ መሠረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የሃሳብ ልዩነቶችና አለመግባባቶች ጎልተው ይታያሉ ያሉት ዋና ኮሚሽነሩ፤ እነዚህን መሠረታዊ ልዩነቶች በምክክር ለመፍታት ዝግጁ መሆን እንደሚገባ ተናግረዋል።
በሀገሪቱ የሃሳብ ልዩነቶች የፈጠሩት ችግር ዘርፈ ብዙ እንደሆኑ ጠቁመው፤ ይህንን ልዩነት ለመፍታት የተካሄደው የኃይል አማራጭ መፍትሔ አላመጣም፡፡ ከዚህ መነሻነትም ልዩነቶች ሁሉንም አትራፊና አሸናፊ በሚያደርገው ምክክር ለመፍታት መዘጋጀት እንደሚገባ ገልጸዋል።
የአማራ ሕዝብ በኢትዮጵያ የሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደት እንደ ሌሎች የሀገሪቱ ማህበረሰቦች ሁሉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉን አመልክተው፤ የኢትዮጵያ መገለጫ የሆኑ የቅርስና የታሪክ ምሰሶዎችን ማቆም የቻለ ትልቅ ሕዝብ መሆኑን አንስተዋል።
ይህ ሕዝብ ልዩነቶችን በኃይል አማራጭ ለመፍታት በተደረጉ ጥረቶች ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍሏል፤ እየከፈለም ይገኛል፤ በክልሉ በአሁኑ ጊዜ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህፃናት ከትምህርት ደጃፍ መድረስ አልቻሉም፤ ሴቶችና ህፃናት ለከፋ የጤናና የማህበራዊ አገልግሎት እጦት በመዳረጋቸው በውስብስብ ችግር ውስጥ እንዲያልፉ መገደዳቸውን ተናግረዋል።
ግጭቶች በዘላቂ እንዲፈቱ መግባባት ላይ ከመድረስ ሌላ አማራጭ እንደሌለ ጠቁመው፤ ከዚህ ውጪ ያሉ አካሄዶች በጊዜያዊነት አንዱን አሸናፊ ሌላውን ተሸናፊ በማድረግ ጊዜያዊ መፍትሔ ያስገኙ ይሆናል እንጂ ካሉብን ችግሮች የሚያላቅቁ አለመሆናቸውን ገልፀዋል።
ዛሬ ላይ የበለፀጉ ሀገራት ከግጭት ተላቀው ኢኮኖሚያዊ ዕድገታቸውን ማረጋገጥ የቻሉት አሳታፊ ምክክር በማድረጋቸው ነው ያሉት ፕሮፌሰር መስፍን፤ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን በዚህ የምክክር ሂደት የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ሀገራቸውን ለማሻገር መሥራት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።
የምክክሩ ውጤት ያሉብንን ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ የሚያዋልድ እንዲሆን ኮሚሽኑ በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ አመልክተው፤ በሂደቱ ተሳታፊ ያልሆኑ ታጣቂ ኃይሎች አሁንም ለምክክር በሩ ክፍት በመሆኑ የምክክሩ ተሳታፊ እንዲሆኑ በድጋሚ ጥሪ እናቀርባለን ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንዳሉት፤ ኢትዮጵያውያን ቋንቋና ሃይማኖት ሳይለያቸው በአንድነት በማበር በዓድዋ ድል በመቀዳጀት ለአፍሪካ የነፃነት ተምሳሌት መሆን ችለዋል።
ከዓድዋና ሕዳሴ ቀጥሎ ሶስተኛውን ዓድዋ የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ መሆኑን ጠቁ መው፤ በአማራ ክልል ያለው ግጭት ቆሞ በምክክር መፈታት እንዳለበት ገልጸዋል።
ሀገራዊ ምክክሩ ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠርና በሕዝብ እና በመንግሥት መካከል እምነት ለመፍጠር ያለመ መሆኑን አመልክተው፤ ጥያቄ ሲኖር ነፍጥ አንግቦ ወደ ግጭት ከማምራት ይልቅ በውይይት በማዳበር ለችግሮች መፍትሔ ማበጀት አስፈላጊና
ጠቃሚ መሆኑን ተናግረዋል።
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን መጋቢት 28 ቀን 2017 ዓ.ም