“ሸዋል ኢድ” የቱሪዝም ሴክተሩን ወደ ላቀ የኢኮኖሚ ምንጭነት ለማሸጋገር ያግዛል

የሸዋል ኢድ በዓል በሀረር ከተማ በድምቀት ተከበረ

ሀረር፡- ‹‹ ሸዋል ኢድ›› የቱሪዝም ሴክተሩን ወደ ላቀ የኢኮኖሚ ምንጭነት ለማሸጋገር የሚደረገውን ዘርፈ ብዙ ርብርብ እና ስኬት ያጠናክራል›› ሲሉ የሀረሪ ክልል ፕረዚዳንት አቶ ኦርዲን በድሪ ገጹ።1446ኛውን የኢድ አልፈጥር ተከትሎ በሳምንቱ የሚከበረው የሸዋል ኢድ በዓል በሀረር ከተማ በታላቅ ድምቀት ትናንት ተከብሯል።

በመርሃ-ግብሩ ንግግር ያደረጉት የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ኦርዲን በድሪ ፤ሸዋል ኢድ በዓለም ቅርስነት መመዝገቡ ከሀረሪዎች ባህላዊ ፌስቲቫልነት አልፎ የመላው ኢትዮጵያውያን ብሎም የመላው ዓለም የጋራ እሴት፣ ክንዋኔ፣ ባህልና ልዩ ወጎች የሚያንጸባረቅበት መስታውት ሆኗል ብለዋል።

የቱሪዝም ሴክተሩን ወደ ላቀ የኢኮኖሚ ምንጭነት ለማሽጋገር የሚደረገውን ርብርብ ሸዋል ኢድ የሚያጠ ናክር እንደሆነም አመላክተዋል።

የጀጐል ዓለም አቀፍ ቅርስን ጽዱ፣ውብና አረንጓዴ ማድረግ መቻሉ ለሸዋል ኢድ በዓል የተለየ ድምቀት የሰጠ መሆኑንም አቶ ኦርዲን ገልጸዋል።

ከፍተኛ አመራሩ ከሕዝብ ጋር ተዋህዶ የብልፅግና ሀዲዱን በመጠበቅ የኮሪዶር ልማት ስኬቶችን በሌሎች መስኮችም መድገም ይጠበቅበታል ብለዋል።

በተለይም በመልካም አስተዳደር እና በመንግሥታዊ አገልግሎቶች ስኬቱን መድገም ግድ እንደሚለው አመልክተው፤ በዚህ አግባብም ክልሉ በተለይም የአረንጓዴ ልማት ዘመቻውን የምግብ ዋስትናን በሚያረጋግጥ እና የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖንን መቋቋም በሚያስችል መንገድ አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ተናግረዋል።

ለሕዝቡ አማራጭ የገቢ ምንጮችን እና የሥራ እድሎችን የመፍጠር ጅምሮችንም በልዩ ትኩረት፣ ስፋትና ጥልቀት ለማከናወን መዘጋጀታቸውንም አስረድተዋል።

በክልሉ የተመዘገቡ አነቃቂ ስኬቶችና ውጤቶች የክልሉ ሕዝብና መንግሥት እጅ ለእጅ ተያይዘው ያመጧቸው ለውጦች መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

በኮሪዶር ልማት የተገኙ ውጤቶችም እንደ ሀገር እውቅና የተሰጣቸውና በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አድናቆት የተቸራቸው እንደሆኑ ጠቅሰው፤ እውቅናና አድናቆቱ በክልሉ አመራሮች ላይ የበለጠ አደራና ኃላፊነትን የሰጠ እንደሆነም አንስተዋል።በእስከ አሁኑ ሂደት የነበረው የሕዝቦች የባለቤትነት ስሜትና ተሳትፎ ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ጉዳይ እንደሆነም ጠቁመዋል።

ሀረር ከተማ የምትገለጽበት አንዱ በቀደምት እናቶችና አባቶች መሠረት የጣለው የሸዋል ኢድ የማይዳሰስ ዓለም አቅፍ ቅርስ እንደሆነ ተናግረው፤ በኮሪዶር ልማቱና በቅርሶች እድሳት የተመዘገበውን ለውጥ ወደ ኢኮኖሚ የመለወጡ ሥራ ቀጣይ የቤት ሥራችን ነው ሲሉም አቶ ኦርዲን አመላክተዋል።

በዓሉ በተለያዩ ትርኢቶችና በፓናል ውይይት ተከብሯል።በበዓሉ ላይ ከፍተኛ የፌዴራልና የክልል ባለስልጣናት ተገኝተዋል።ሸዋል ኢድ በዓለም የማይዳሰስ ቅርስ ተብሎ ከጀጎል በመቀጠል ለክልሉ ሁለተኛ ቅርስ ሆኖ የተመዘገበው ሕዳር 2016 ዓ.ም እንደሆነ ይታወቃል።

ኢያሱ መሰለ

 

 

አዲስ ዘመን መጋቢት 28 ቀን 2017 ዓ.ም

 

 

 

Recommended For You