
አዲስ አበባ፡– ከለውጡ ወዲህ የተተገበረው አካታችነት የፖለቲካ ምህዳሩን እንዳሰፋው በተግባር ታይቷል ሲሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ገለጹ።
በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አዝመራ እንደሞ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት፤ ባለፉት ጥቂት የለውጥ ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ አካታችነት መተግበር በመቻሉ የፖለቲካ ሥነ-ምህዳሩን በማስፋት ተጨባጭ ውጤት ተመዝግቧል።
ቀደም ሲል በነበረው ገዥ ፓርቲ ዋና እና አጋር የሚባሉ የፖለቲካ ድርጅቶች እንደነበሩ አስታውሰው፤ ብልፅግና ፓርቲ ወደ ሥልጣን በመጣ ጥቂት ዓመታት አካታችነትን በመከተሉ አጋር ድርጅት የሚባሉት ጠፍተው ሁሉም እኩል መብትና የጋራ እሳቤ እንዲኖራቸው ተደርጓል። በኢትዮጵያ ጉዳይ እኩል ተሳትፎ እንዲኖራቸው መደረጉም የፖለቲካ ምህዳሩን ካሰፉ ጉዳዮች አንዱ ነው ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ከ50 በላይ ሀገራዊ እና ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች መኖራቸው የፖለቲካው ምህዳር ለመስፋቱ ሌላ ማሳያ እንደሆነም ጠቅሰዋል።
ፓርቲዎቹ መኖራቸው ብቻ ሳይሆን በምርጫ ውስጥ ገብተው መሳተፋቸው ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ማቋቋማቸው፤ በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ በጋራ መምከራቸውና ህጸጾችን እያወጡና ማስተካከያ እየሰጡ መሄዳቸው፤ የፖለቲካ ምህዳሩ እየሰፋ መሄዱን የሚያመላክቱ ለውጦች ስለመሆናቸው አስረድተዋል።
በኢትዮጵያ ሕገ -መንግሥትም ፤ በፖለቲካ ፓርቲ ሕገ- ደንብም ፤ አሸናፊው ፓርቲ የሕግ አውጭውንም፤ ሕግ አስፈፃሚውንም ቦታ የሚይዝ መሆኑን የጠቆሙት አቶ አዝመራው፤ ነገር ግን ተፎካካሪ ፓርቲዎች ምርጫ ባያሸንፉም ብልፅግና ባሸነፈበት አስፈፃሚ ሆነው ተቋማትን እንዲመሩ መደረጉን አመልክተዋል። በዚህም
መሠረት የተወሰኑ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች በተፎካካሪ ፓርቲዎች የሚመሩ መሆኑን አስረድተዋል።
አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በየተቋማት፤ በየክልሎችም የሚገኙ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ባያሸንፉም ተቋማትን እየመሩ ስለመገኘታቸው ገልጸዋል።
ይህ አዲስ የፖለቲካ ባህል ኢትዮጵያ ውስጥ ምን ያህል የፖለቲካ ምህዳሩ እየሰፋ እንደሄደ ማሳያ ነው ብለዋል።
ተፎካካሪ ፓርቲዎች በምርጫ ተሸንፈውም ቢሆን በሥራ አስፈጻሚው ገብተው እንዲሠሩ ማድረግን የዛሬ 20 ዓመት ብንጀምረው ኖሮ አሁን የሚታየው ግርግር አይኖርም ነበር ሲሉ አስረድተዋል።
እንዲህ አይነቱ የፖለቲካ ባህል ኢትዮጵያን በጋራ ለመገንባት፣ ብሄራዊ መግባባትን ለመፍጠር እና የወል ትርክትን ለመገንባት የራሱ ድርሻ እንዳለውም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያን ማሳደግ የሚቻለው የሆነ ቡድን በሆነ አምስት ዓመት ውስጥ በሚይዘው ሥልጣን ሳይሆን በዚህ መልኩ እንደሆነም አስረድተዋል። እንዲህ ዓይነቱ አካታች ልምምድ ለሥልጣን የሚኖርን አተያይ የሚቀንስ ስለመሆኑም ተናግረዋል።
በእነዚህ የለውጥ ዓመታት የፖለቲካ ምህዳሩ ሙሉ ለሙሉ መጨረሻው ደረጃ ላይ ደርሷል ባይባልም፤ እየሰፋ ስለመሄዱ ግን ጥርጥር የለንም ሲሉ ምክትል ሰብሳቢው አስረግጠዋል።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን መጋቢት 28 ቀን 2017 ዓ.ም