የሱዳን ጦር ካርቱምን ከተቆጣጠረ ወዲህ ንጹኃን ሰዎች መገደላቸውን ተመድ ገለጸ

የተባበሩት መንግሥታት የሠብዓዊ መብት ኮሚሽን ከፍተኛ ኮሚሽነር የሆኑት ቮልከር ቱርክ የሱዳን ጦር ከሕግ ውጭ ግድያ መፈጸሙን የሚጠቁሙ “አሳማኝ ሪፖርቶች” መኖራቸውን ተናገሩ። በዚህም በጣም ማዘናቸውን ገልጸው፣ ንጹኃን ዜጎች ላይ ግድያው የተፈጸመው የሱዳን ጦር ባለፈው ሳምንት መዲናዋን ከተቆጣጠረ በኋላ መሆኑን ገልጸዋል።

“በርካታ ንጹኃን ዜጎች ላይ የተፈጸሙ ከሕግ ውጭ የሆኑ ግድያዎች እንደነበሩ የሚጠቁሙ ጠንካራ ሪፖርቶች አሉ። በካርቱም የተለያዩ አካባቢዎች ከሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ጋር አብራችኋል በሚል ግድያዎቹ ተፈጽመዋል” ብለዋል ኮሚሽነሩ።

በካርቱም ውስጥና ከካርቱም ውጭም በታጣቂዎች ንጹኃን ሲገደሉ ያሳያሉ የተባሉ ብዙ ቪዲዮዎች በማኅበራዊ ሚዲያ ሲዘዋወሩ ነበር። የመንግሥታቱ ድርጅት የሠብዓዊ መብት ኮሚሽን ቪዲዮዎቹ ተዓማኒነት አላቸው ብሏል።

የሱዳን ጦር ስለቀረበበት ክስ ምላሽ እስከሚሰጥ እየጠበቀ ነው። “የታጠቁ ወንዶች ንጹኃንን በጭካኔ በአደባባይ ሲገድሉ የሚያሳዩ ብዙ አሰቃቂ ቪዲዮዎች አሉ” ብለዋል ኮሚሽነሩ። አንዳንዶቹ ቪዲዮዎች ላይ ጥቃት አድራሾቹ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል (አርኤስኤፍ) ደጋፊዎችን እየቀጡ እንደሆነ ይናገራሉ።

ላለፉት ሁለት ዓመታት የሱዳን ጦርና የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ጦርነት ውስጥ ናቸው። የሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት በዓለም የከፋውን ሠብዓዊ ቀውስ መፍጠሩ ተገልጿል። “የሱዳን ጦር ኮማንደሮች ይሄንን የዘፈቀደ ግድያ በአፋጣኝ እንዲያቆሙ እጠይቃለሁ። በግላቸው ጥቃት የሚሰነዝሩም ይሁን ወታደራዊ ትዕዛዝ የተሰጣቸው በዓለም አቀፍ ሕግ ተጠያቂ መሆን አለባቸው” ሲሉ ኮሚሽነሩ አሳስበዋል።

የሱዳን ጦርና አጋሮቹ በአርኤስኤፍ ሥር የነበሩትን ሳኔር፣ ገዚራ እና የሰሜን ኮርዶፋን የተወሰኑ አካባቢዎችን መልሰው ከተቆጣጠሩ በኋላ የሠብዓዊ መብት ጥሰት በመፈጸም ተከስሰዋል። ከሁለት ወር በፊት ጄነራል አብደል ፈታህ አል-ቡርሃን ኮሚቴ አዋቅረው በገዚራ መዲና ዋድ መዳኒ የተፈጸሙ ጥቃቶች እንዲመረመሩ ቢያደርጉም ግኝቱ ለሕዝብ እስካሁን ይፋ አልተደረገም።

በዋድ መዳኒ ደርሷል የተባለውን ሠብዓዊ መብት ጥሰት ተከትሎ አሜሪካ በአል-ቡርሃን ላይ ማዕቀብ ጥላለች። የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎ መሪ ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎም በጦር ወንጀሎችና በጭካኔ ድርጊት ማዕቀብ ተጥሎባቸዋል።

የአርኤስኤፍ ኃይል ሰዎችን በማሰር፣ በማሰቃየት፣ የሱዳንን ጦር ደግፋችኋል በሚል በመረሸን እና በምዕራብ ዳርፉር ጎሳ ተኮር ግድያ በመፈጸም ተከሷል። ጦሩ ከዚህ ቀደም ግድያ የተፈጸመውና የሠብዓዊ መብት ጥሰት የደረሰው “በተወሰኑ ወታደሮች” ነው ሲል አውግዞ ነበር። መዲናዋ ካርቱም ለሁለት ዓመት ገደማ በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ሥር የቆየች ሲሆን በቅርቡ በሱዳን ጦር ይዞታ ሥር ገብታለች።

ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ውጊያውን ለመቀጠል የዛተ ሲሆን፣ ጦርነቱ በሀገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል በአዳዲስ ግንባሮች ሊቀጥል እንደሚችል ተሰግቷል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።

አዲስ ዘመን መጋቢት 28 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You