‹‹ግድቡን በተመለከተ ግብፅ አጀማመሯ የተለሳለሰ ቢሆንም በኋላ ብዙ ጣጣ አምጥታ ነበር›› -አቶ ፈቅአህመድ ነጋሽ

-አቶ ፈቅአህመድ ነጋሽ የዓባይ ጂ ኦ ፖለቲካ ተንታኝ እና ተደራዳሪ

በዓባይ ውሃ አጠቃቀም በተለይም በዓባይ ግድብ ዙሪያ እልህ አስጨራሹን ድርድር በድል ከተወጡ የኢትዮጵያ ባለውለታዎች መካከል አንዱ ናቸው። በኢትዮጵያ፣ በግብፅ እና በሱዳን መካከል በተከታታይ ለቀናት በተለያዩ ጊዜያት ዓመታትን የፈጁ ድርድሮች ሲያካሄዱ፤ ዋነኛ ተሳታፊ የነበሩት የዓባይ ጂ ኦ ፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ እና ተደራ ዳሪው አቶ ፈቅአህመድ የግድቡ ከጫፍ መድረስ ልዩ ስሜት ፈጥሮባቸዋል።

የደስታቸው ምክንያት አንደኛው ልፋታቸው ለፍሬ መብቃቱ ሲሆን፤ ሌላኛው የግድቡ በሙሉ አቅም ሃይል ማመንጨት ያሉት ትሩፋቶች እጅግ ብዙ በመሆናቸው ነው። የዓባይ ግድብ በሙሉ አቅም ሃይል የማመንጨት በዋናነት መታየት ያለበት በሚመነጨው የሃይል መጠን ወይም ሃይሉ ተሽጦ በሚገኘው ገቢ ብቻ ሳይሆን፤ ሰፋ ተደርጎ በደንብ መታየት አለበትም ይላሉ።

ሃይል ከጤና፣ ከትምህርት እና ከአገልግሎት ጋር ይያያዛል። “በጤና ማዕከላት ሃይል የሚኖረው ሚና የሚናቅ አይደለም” የሚሉት ተደራ ዳሪው አቶ ፈቅአህመድ፤ ለኢንዱስትሪ መስፋፋት የሃይል መጠን በቂ መሆን የሚኖረው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው። በቂ ሃይል መገኘቱ ኢንዱስትሪውን እንደሚያነቃቃ እና ለሥራ ዕድል ፈጠራም ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ይናገራሉ።

ለግብርና ዘርፍም የሚኖረው ጠቀሜታ ትልቅ እንደሆነ አመልክተው ፤ ውሃን በመግፋት የመስኖ ልማትን ማስፋፋት ይቻላል። ይህ ደግሞ ከምግብ ዋስትና ጋር የተያያዘ ነው ብለዋል። በተጨማሪ ሆቴሎች እና ሌሎችም የቱሪስት ማዕከሎች ሃይል ይፈልጋሉ። አሁንም ወደ 60 ሚሊዮን ሕዝባችን ጨለማ ውስጥ እየኖረ መሆኑን በማስታወስ፤ በዓባይ ግድብ መጠናቀቅ ምክንያት አብዛኛው ሕዝብ ከጨለማ ሊወጣ እንደሚችል ጠቁመዋል። ይህ ሁሉ ሲሰላ የዓባይ ግድብ በሙሉ አቅሙ ሃይል ማመንጨቱ ትሩፋት እንደሚሆን አሳውቀዋል።

በዓባይ ግድብ መጠናቀቅ ዙሪያ በማተኮር የድርድሩ አካሄድ እና ፈታኝ ሁኔታዎች እንዲሁም በቀጣይ ኢትዮጵያ በውሃ ሀብት አጠቃቀም ዙሪያ መሥራት ያለባት ሥራዎች ላይ አተኩረን የዓባይ ጂ ኦ ፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ እና ተደራ ዳሪው አቶ ፈቅአህመድን የዕለቱ የልዩ እትም እንግዳ አድርገን አቅርበንላችኋል።

አዲስ ዘመን፡- እንደኢትዮጵያዊ ብቻ ሳይሆን እንደ አንድ የዓባይ ውሃ ተደራ ዳሪ ግድቡ ሊጠናቀቅ ጫፍ መድረሱ የፈጠረብዎት ስሜት ምን ይመስላል ?

አቶ ፈቅአህመድ፡- የግድቡ መጠናቀቅ ተራ ጉዳይ ሳይሆን እጅግ በጣም ትልቅ ነገር ነው። ለእኔም ሆነ ለማንኛውም ኢትዮጵያዊ እጅግ አስደሳች ነው። ምክንያቱ ደግሞ በሀገሪቱ ወደ ፊት ለሚሠሩ ሥራዎች ትልቅ ግብዓት ስለሚሆን የግድቡ መጠናቀቅ ልዩ ስሜት መፍጠሩ አይቀርም።

በዘርፉ ላይ እንዳለ ባለሙያ እና እንደተደራዳሪ ሳየው ደግሞ ፤ በቅድሚያ ግድቡ ይጠናቀቃል ብለን ያሰብነው በሰባት ዓመት ጊዜ ውስጥ ነበር። አሁን ግን አስራ አራተኛ ዓመታትን አልፎ ወደ አስራ አምስት እየተሻገረ ነው። ይህ በራሱ ችግር ነው። በእርግጥ ቀድሞም ቢሆን በሰባት ዓመት ይጠናቀቃል ቢባልም አሥር ዓመት መፍጀቱ አይቀርም ነበር። በአሥር ዓመት ቢያልቅ ኖሮ ደስታዬ ከዚህ በላይ እጥፍ ድርብ ይሆን እንደነበር መሸሸግ አልችልም።

ትልቁ ነገር አሁንም ቢሆን ይኽኛው በሰላም እየተጠናቀቀ ነው። በቀጣይ ለሚሠሩት ግድቦች ደግሞ ቀድሞ መዘጋጀት ያስፈልጋል። ያለፈው ጊዜ ግን በጣም አስቸጋሪ ሁኔታዎች ነበሩበት። ያ ሁሉ አልፎ ማጠናቀቃችን ለሁላችንም ትልቅ ስኬት ነው የሚል እምነት አለኝ።

አዲስ ዘመን፡የድርድሩን ሒደት በማንሳት ምን ያህል ፈታኝ እንደነበር ያብራሩልን?

አቶ ፈቅአህመድ፡ መጀመሪያ የዓባይ ግድብ ግንባታ ሲጀመር ግብፆች የገቡት ተለሳልሰው ነው። በዋናነት ግድቡ እንደተጀመረ ስጋት ነበረባቸው። ስጋት ለምን ኖረባቸው ማለት አይቻልም። ማንኛውም የታችኛው ተፋሰስ ሀገር የላይኛው ተፋሰስ ሀገር አካባቢ ግድብ ቀርቶ ትንሽ እንቅስቃሴ ካለ ስጋት ይኖርበታል።

ግድቡ እንደተጀመረ ስጋት አለብን ብለው መጡ። መረጃ ይሰጠን ብለው ሲጠይቁ፤ ኢትዮጵያ መረጃ አልሰጥም ትላለች የሚል ፍራቻ ነበረባቸው። ምክንያቱም እ.አ.አ በ1960 ወይም በኢትዮጵያ በ1952 ዓ.ም እነርሱ የዓስዋንን ግድብ ሲጀምሩ፤ ኢትዮጵያ መረጃ ይሰጠኝ ግድብ እየሠራችሁ ነው ስትል፤ ‹‹አያገባሽም፤ መረጃ አንሰጥም›› የሚል አሉታዊ ምላሽ ሰጥተው ነበር። በእዛ ጊዜ የግብፅ መንግሥት ቀና ምላሽ ስላልሰጠ፤ በመንግሥት ደረጃ ቢመጡ ‹‹ተመሳሳይ አሉታዊ ምላሽ እናገኛለን ፤ የኢትዮጵያ ምላሽ አሉታዊ ከሆነ ወደፊት እንቸገራለን›› ብለው በመስጋታቸው መረጃውን በቀጥታ መንግሥታቸው የኢትዮጵያን መንግሥት አልጠየቀም።

የዓባይ ግድብ እንደተጀመረ ግብፆች 36 ዓባላትን የያዘ ሕዝባዊ የዲፕሎማሲ ቡድን ላኩ። መጀመሪያ ቡድኑ ወደ ዑጋንዳ ሔዶ ፕሬዚዳንት ሙሴቪኒን ከጎናቸው ለማሰለፍ ሞክሮ ነበር። ሆኖም የዑጋንዳ ፕሬዚዳንትን ለመያዝ አልተሳካላቸውም። ስለዚህ በቀጥታ ወደ አዲስ አበባ መጥተው የተለያዩ የማህበረሰብ አካላትን በማነጋገር፤ መረጃ ለማግኘት ሞከሩ።

በጊዜው ጥያቄያቸው ኢትዮጵያ በቅርቡ የፀደቀው የናይል የትብብር ማሕቀፍን ለማፅደቅ ሥራ ጀምራ ነበር። ስለግድቡ መረጃ ብቻ ሳይሆን የትብብር ማሕቀፉም እንዲዘገይላቸው ነው። በኢትዮጵያ በኩል የተሰጣቸው ምላሽ እንደስጋታቸው አሉታዊ አልነበረም። ለሁለቱም ጥያቄዎቻቸው በጎ ምላሽ ተሰጥቷቸዋል።

መንግሥት ጥያቄያቸውን መቀበል ብቻ ሳይሆን፤ ይሁንልን ያሉትን ተግባራዊ አድርጓል። መጀመሪያ መረጃ ይሠጠን አሉ። ከዛ በኋላ መረጃ ለመስጠት የሶስቱ ሀገራት ባለሙያዎች አንድ ላይ ግድቡን ይመርምሩ የሚል ጥያቄ አቀረቡ። የኢትዮጵያ መንግሥት እንደገና እሺታውን ገለፀ። ‹‹እሺ›› በተባሉ ቁጥር የእነርሱ ጥያቄ ማባሪያ አልነበረውም። እንደገና የውጪ ባለሙያዎች ይግቡበት የሚል ጥያቄ ሲያቀርቡ፤ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ‹‹አይሆንም›› አልተባሉም። እንደገና እሺታን የሚገልፅ በጎ ምላሽ ተሰጣቸው።

አራት የውጪ ባለሙያዎች ተካተው፤ ብዙ ምርምር እና ጥናቶች ከተካሔዱ በኋላ በዓመቱ ውጤቱ ወጣ። ሶስቱም ሀገራት እና ባለሙያዎቹ የሚፈርሙበት ሪፖርት ተዘጋጀ። በዚህ ጊዜ ሱዳን አምናበት ከዛ በኋላ ከፍተኛ መለሳለስ አሳይታለች። እንደውም ለግድቡ ያላትን ትልቅ ድጋፍ አሳይታለች። ሆኖም ግብፆች ግን ሪፖርቱ እንደደረሳቸው ተሰብስበው የወቅቱን መንግሥት ከሚቃወሙ ጋር ሆነው፤ ኢትዮጵያ ላይ ዶለቱ።

ግድቡን እንዴት እንደሚያወድሙ እና እንደሚደበድቡ እንዲሁም ኢትዮጵያ ውስጥ እንዴት ረብሻ እንደሚያስነሱ፤ እንዴት ጉቦ ሰጥተው ባለሙያ እንደሚያነሆልሉ ሲመክሩ እንደነበር ታወቀ። ሴራቸውም በቀጥታ በመረጃ ብቻ ሳይሆን በማስረጃ ተደግፎ በቴሌቪዥን ሲተላለፍ ዓለም ሰማቸው። የመጀመሪያ ምላሽ የሠጡት በዚህ መልኩ ነው። ያ ማለት ግን የዓለም አቀፍ ባለሙያዎች የድርድር ጉዞ በዛ ጊዜ ቀላል ነበር ማለት አይደለም። ትልቅ ጭቅጭቅ የነበረበት፤ አንዳንዴም ግብፆች ረግጠው እየወጡ ተለምነው እየገቡ ንግግር የሚካሔድበት ሁኔታ ነበር።

አንዴ ጥናት ከተካሔደ በኋላ ግን፤ ሁኔታዎች የበለጠ አስቸጋሪ መሆናቸውን ቀጠሉ። ግብፆች በድጋሚ ጥናት ይካሔድ የሚል ጥያቄ አቅርበው እንደገና የተወሰኑ ጥናቶችን አማካሪ ተቀጥሮ ገንዘብ ተከፍሎ መሠራት ሲጀምር፤ መሃል ላይ ይህም እንደማያዋጣቸው ሲያውቁ ውድቅ አደረጉት። በኋላም በራሳቸው በተዳራዳሪዎች ጥናት ይካሄድ ተባለ። እርሱንም የራሳቸው ተመራማሪዎች ሳይቀሩ የተሳተፉበትን አጥንተው ሲጨርሱ፤ እንደገና ውድቅ አድርገው አሜሪካ እና ዓለም ባንክ እንዲገቡ ጠየቁ።

ኢትዮጵያ በየዋህነት ለእዚህም ጥያቄ የሰጠችው ምላሽ ‹‹እሺ›› የሚል ነበር። የእነርሱ አካሔድ ግን ከባድ ነበር። አሜሪካ እና ዓለም ባንክ ገብተው ኢትዮጵያ ወደ ፊት የዓባይን ውሃ እንዳትጠቀም የሚያደርግ ስምምነት ለማስፈረም ብዙ ሞክረው ነበር። በኢትዮጵያ በኩል በተለያየ አቅጣጭ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ሃሳባቸው ውድቅ እንዲሆን ማድረግ ተችሏል።

ግብፅ በብዙ መልኩ አላረፈችም። ለዓለም አቀፍ ሰላም እና መረጋጋት አደጋ ነው በሚል ጉዳዩን ወደ ተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ለመውሰድም ሞክራለች። ሆኖም ፤ እዛም ከደረሰ በኋላ በኢትዮጵያ በኩል ብዙ ጥረቶች ተደርገው ጉዳዩ ወደ አፍሪካ ሕብረት ተመለሰ። ግብፅ የአረብ ሊግ ሀገራትን ተጠቅማ መግለጫ በማሰጠት ለማስፈራራት ሞክራለች። ሆኖም ግብፆች ብዙ ጥረት ቢያደርጉም ምንም ማምጣት አልቻሉም። ግብፅ ግድቡን በተመለከተ አጀማመሯ የተለሳለሰ ቢሆንም፤ በኋላ ብዙ ጣጣ አምጥታ ነበር።

በእኛ በኩል አጀማመሩ ጥሩ ነበር። ግድቡ ይገንባ ብሎ መወሰን በራሱ ትልቅ ጉዳይ ነው። ነገር ግን ፈተና ከግብፅ ወይም ከውጪ ብቻ ሳይሆን ከውስጥም ብዙ ፈተናዎች ነበሩ። በዋናነት የውስጥ ችግር ሲነሳ የብረታ ብረት እና ኢንጂነሪግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) በዓባይ ግድብ ግንባታ ላይ መግባት አልነበረበትም። በሒደት አቅሙን ያደረጃል ቢባልም፤ እንዲገባ ከተፈለገ እንደውም ኤሌክትሮ መካኒካል እና ሃይድሮ መካኒካል ላይ ከሚገባ ግንባታው ላይ ቢገባ ይሻል ነበር። ምክንያቱም የኤሌክትሮ መካኒካል እና የሃይድሮ መካኒካል ሥራው በጣም ውስብስብ ስለነበር፤ መሥራት ባለመቻሉ ሥራው ተጓትቶ ለመዘግየትም ሆነ ለተጨማሪ ወጪ ዳርጎናል።

በሌላ በኩል ሀገር ውስጥ ሰላም እና መረጋጋት የማይኖርበት አጋጣሚ መኖሩም ሥራው ላይ ጫና ፈጥሮ ነበር። በፋይናንስ በኩል የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንደፈተና መወሰድ ያለበት ጉዳይ ነው ፤ በዘገየ ቁጥር ደግሞ አማካሪዎቹም ኮንትራክተሩም ተጨማሪ ክፍያ የሚፈልጉበት ሁኔታ ነበር። ሆኖም ያ ሁሉ አልፎ ለእዚህ መብቃቱ ትልቅ ውጤት ነው።

አዲስ ዘመን፡ከድርድሩ ጋር በተያያዘ ችግሮች ሲያጋጥሙ የምትፈቷቸው እንዴት ነበር?

አቶ ፈቅአህመድ፡ ልክ ግድቡ እንደተጀመረ በእኛ በኩል የብሔራዊ የባለሙያዎች /የኤክስፐርቶች ፓናል ተቋቋመ። ይሄ የብሔራዊ የኤክስፐርቶች ፓናል ሀገሪቷ ውስጥ ካሉ ከተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማት እና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት፣ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተውጣጡ 20 የሚደርሱ በተለያየ ዘርፍ ላይ ትልቅ ልምድ እና ተሞክሮ የነበራቸው ባለሙያዎች የተወከሉበት ነው ። ሁሉንም ሥራ የሚሠሩት እነርሱ ነበሩ። ይህ የኢትዮጵያ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ ብሔራዊ የኤክስፐርቶች ፓናል ለዘጠኝ ዓመት ያህል ከግድቡ ጋር ተጉዟል።

በግድቡ ላይ እያንዳንዱን ጉዳይ ይከታተሉ ነበር። ከባድ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ ብሔራዊ የኤክስፐርቶች ፓናል ለሶስት እና አራት ቀናት ከከተማ ወጥተው ቀኑን ሙሉ በመሥራት ሪፖርት ያደርጋሉ። በተጨማሪ በየሳምንቱ ከቀኑ 11 ሰዓት እስከ ምሽት 4 ሰዓት ተሰብስበው አስፈላጊ ጉዳዮች ላይ ይወያያሉ። በተለይ በሙያ ዘርፍ ከፍተኛ ድጋፍ ይሰጡ ነበር።

ሌላኛው በተለያዩ ተቋማት መካከል ያለው ጥምረት ነው። በተለይ በውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት እና በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር የቴክኒክ ሥራው ከፖለቲካ ሥራው ጋር ተቀናጅቶ እንዲሔድ ያደረጉበት ሁኔታ በጣም በመልካም ጎን መታየት ያለበት ጉዳይ ነው። እንዲሁም ከላይ በመንግሥት በከፍተኛ ደረጃ ክትትል ይደረግበት ነበር። የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ሃይል ቦርድም በቅርበት ሲከታተል ነበር። ከሁሉም በላይ ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ከግድቡ ኋላ ቆሞ ነበር። ያ ደግሞ ለሚደራደሩት አካላት ትልቅ ግብዓት ነበር።

የሚደራደሩት አካላት የሀገራቸውን ጥቅም ለማስከበር ውጪ ሔደው ተደራድረው ሲመጡ፤ የሕዝብ ድጋፍ እንደሚኖር ስለሚያውቁ ምንም ስጋት አይኖርባቸውም። ሕዝቡ በራሱ ትልቅ አቅም ስለነበር ግድቡ ለዚህ መብቃት ችሏል። ይሔ ማለት ስህተቶች አልነበሩም፤ ችግር አልተፈጠረም ማለት አይደለም። ስህተቶች ይኖራሉ። ስህተቶች ሲያጋጥሙ ወዲያው የመፍትሔ ርምጃዎች እየተወሰዱ፤ ይህ ውጤት መጥቷል። ወደፊት የነበረው ሁኔታ ተቀምሮ ለወደፊት መማሪያ መሆን አለበት።

አዲስ ዘመን፡ከብዙ ፈተና በኋላም ቢሆን የዓባይ ግድብ እውን የሚሆንበት ደረጃ ላይ ደርሷል፤ በራሱ የግድቡ መጠናቅ ትርጉሙ ምንድን ነው?

አቶ ፈቅአህመድ፡ግድቡ የመጀመሪያም የመጨረሻም አይደለም። ከአሁን በፊት የተሠሩ ግድቦች ነበሩ። ወደፊትም የሚሠሩ በርካታ ግድቦች ይኖራሉ። የግድቡ መጠናቀቅ መንግሥት በቀጣይነት ትልልቅ ግድቦችን ለመገንባት ለሚሰጠው ውሳኔ ትልቅ ግብዓት የሚሆን ነው። የታላቁን ሕዳሴ ግድብ ለመገንባት ውሳኔ ላይ ሲደረስ መንግሥት እጁ ላይ ምንም አልነበረም። ከጎኑ የነበረውና የተማመነው ሕዝብን ብቻ ነበር። በሕዝቡ ተመክቶ፤ ‹‹በጋራ እንገነባዋለን›› የሚል እምነት ይዞ ተንቀሳቅሷል።

በዚያ ጊዜ የኢትዮጵያ መንግሥት ዓለም አቀፋዊ ድጋፍ አልነበረውም። በቂ ፋይናንስም ሆነ አሁን ላይ ያለው አቅም በዛ ጊዜ አልነበረም። ትልቅ የመወሰን አቅም ስለነበር ውሳኔ ላይ ተደረሰ። በቀጣይም ትልቅ ተሞክሮ ስላለ የተሻለ ዕድል ይፈጠራል።

ኢትዮጵያውያን የምንታወቀው ጦርነት ላይ መረባረብ ነው። ጦርነት ሲኖር ሞራል እንሰጣለን፤ ገንዘብ እናዋጣለን፤ አልፈን ተርፈን እንዘምታለን። ልማት ላይ ግን ብዙም አልነበርንም። አሁን ግን በተለይ የዓባይ ግድብ እንዳሳየን ታሪክ ተቀይሯል። ለልማት ስንረባረብ በዓባይ ግድብ ታይተናል። ይህ መገኘቱ በራሱ ለብቻውን ትልቅ ስኬት ነው።

ከእዚህ ውጪ ግድቡ በሙሉ ሃይሉ ማመንጨት ሲጀምር የሚያመጣው ትሩፋት እጅግ በጣም ብዙ ነው። በዋናነት መታየት ያለበት በሚመነጨው የሃይል መጠን ወይም ሃይሉ ተሽጦ የሚገኘው ገቢ ብቻ አይደለም። ሰፋ ተደርጎ መታየት አለበት። ለምሳሌ የኤሌክትሪክ ሃይል ከጤና፣ ከትምህርት እና ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በሰፊው ይያያዛል።

የጤና ማዕከላት ላይ ሃይል የሚኖረው ሚና የሚናቅ አይደለም። የጤና አገልግሎቱን ለማቀላጠፍም ሆነ በተመቸ ሁኔታ የጤና አገልግሎት ለመስጠት የኤሌክትሪክ ሃይል አስፈላጊ ነው። በሌላ በኩል ለኢንዱስትሪ መስፋፋት የሃይል መጠን በቂ መሆን የሚኖረው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው። በብዛት ማመንጨት ከቻልን ሃይል አጥተው የሚቸገሩ የኢንዱስትሪ ዘርፎች አይኖሩም ማለት ነው። የኢንዱስትሪው መነቃቃት ደግሞ ሥራ አጥነትን ይቀንሳል። ይህ ማለት እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ጋር ትሩፋቱ ይደርሳል።

በተጨማሪ የሚመነጨው ሃይል ለግብርና ዘርፍም ትልቅ ጠቀሜታ አለው። በመስኖ ለማልማት ውሃን ለመግፋት ሃይል ለመጠቀም ኤሌክትሪክ ካለ በግፊት ሃይል የሚንቀሳቀሱ ማሽኖችን መጠቀም ይቻላል። በሌላ በኩል ለመጠጥ ውሃ መዳረስ ሃይል ትልቅ ግብዓት ነው። በሌላ በኩል ውሃ ስለተገኘ ብቻ አይዳረስም። ውሃ የሚገፋው በኤሌክትሪክ ሃይል ነው።

መስኖን ማልማት ደግሞ ከምግብ ዋስትና ጋርም የተያያዘ ነው። በተጨማሪ ሆቴሎች እና ሌሎችም የቱሪስት ማዕከሎች ሃይል ይፈልጋሉ። ለእነዚህ ሁሉ የሚመነጨው ሃይል ጠቃሜታ አለው። አሁንም ወደ 60 ሚሊዮን ሕዝባችን ጨለማ ውስጥ ነው። በዓባይ ግድብ መጠናቀቅ ምክንያት አብዛኛው ሕዝብ ከጨለማ ሊወጣ የሚችልበት ዕድል ሰፊ ነው። ሃይሉን ከመጠቀም አንፃር ስናይ ሌላም የሚፈጥረው ትልቅ አቅም አለ።

ድንበር አካባቢ ላሉ ጎረቤት ሀገራት ሃይል በማቅረብ ቀጣናዊ ትስስር ለመፍጠር ይቻላል። በጣም ሰፊ ጥቅም ይዞ እንደሚመጣ በደንብ መታየት አለበት። ግድቡ በጣም ግዙፍ ነው። ብዙ ተመራማሪዎች ሊመራመሩበት ይችላሉ። የትምህርት ተቋማት እንደትልቅ ምሳሌ ወስደው በዛ ላይ ማስተማር ይችላሉ። በዛ ያለ ጥቅም አለው ፤ ትልቅ ጥቅም ያለው ሥራ የተሠራ በመሆኑ ልንኮራበት ይገባል። ነገር ግን ትልቁ ኩራት የዓባይ የአሁኑ ግድብ ብቻ መሆን የለበትም፤ በዚሁ ላይ ወስነን ሌላ ግድብ ለመገንባት ውሳኔ ላይ መድረስ አለብን ብዬ አምናለሁ።

አዲስ ዘመን፡በቀጣይ የዓባይ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የውሃ ሀብት አጠቃቀማችን ምን መምሰል አለበት ይላሉ?

አቶ ፈቅአህመድ፡እንደሀገር መቀበል ያለብን አንድ እውነታ አለ። ብዙ ሕዝብ የሚያምነው ኢትዮጵያ የውሃ ሀብታም ነች ብሎ ነው። ነገር ግን አሁን ባለንበት ደረጃ ኢትዮጵያ በውሃ ሀብታም አይደለችም። እንደውም የውሃ እጥረት ውስጥ ገብተናል። አንድ ሀገር ያለው ውሃ ለሕዝቡ በነፍስ ወከፍ ተከፋፍሎ በዓመት ከአንድ ሺህ ሜትር ኪዩብ በታች ከደረሰ ያ ሀገር የውሃ እጥረት ውስጥ ገብቷል ማለት ነው። በእዚህ የሂሳብ ስሌት መሠረት ኢትዮጵያ ያላት ውሃ 123 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ ነው። ሕዝባችን ወደ 130 ሚሊዮን ተጠግቷል። ብንከፋፈል የሚደርሰን ከአንድ ሺህ በታች ነው።

በተወሰኑ ተፋሰሶች ውስጥ የተሻለ ውሃ ሊኖር ይችላል። ባሮ አኮቦ ፣ ዓባይ እና ኦሞ እንዲሁም ጊቤ አካባቢ የውሃ እጥረት ላይኖር ይችላል። ሆኖም በሌሎቹ አካባቢዎች የውሃ እጥረት ውስጥ ገብተናል። ስለዚህ የውሃ አጠቃቀማችን በጥንቃቄ እና በቁጠባ መሆን አለበት። ተቋሞቻችን ተቀናጅተው መሥራት አለባቸው። ሥራዎቻችን በሙሉ የአካባቢ ጥበቃን መሠረት ያደረጉ፤ የውሃ ምንጮችን በመንከባከብ ላይ መሠረት ያደረጉ እና የተቀናጀ አሠራርን የተከተሉ መሆን አለባቸው። በተለይ የውሃ ልማት ከጊዜ ጋር የሚሔድ እና በፍጥነት መሠራት ያለበት ነው።

ዛሬ አንድ ቦታ ላይ ያለ ውሃ ነገ አይገኝም፤ ካለፈ የታጣ ውሃ ነው። ለምሳሌ ግድቦች ላይ ውሃ ተሞልቶ ሃይል ካላመነጩ ብክነት ነው። በዓባይ ግድብም ውሃ አልፎ ሲሔድ ገንዘብ አልፎ እንደሔደ ማሰብ ያስፈልጋል። የሚገኘው ጥቅም ከፍተኛ እንዲሆን ቶሎ ወደ ሥራ ማስገባት ያስፈልጋል። በቆየ ቁጥር ሃይል እና ሀብት ማጣት ብቻ ሳይሆን ጭቅጭቁም እየቀጠለ ይሔዳል።

ይህ ጉዳይ ትኩረት ተሰጥቶት ቶሎ ወደ ውሳኔ ተገብቶ ዘላቂ የሆነ ልማት በረዥም ጊዜ ዕቅድ በመካከለኛ ጊዜ ፕሮግራም በአጭር ጊዜ ፕሮጀክቶች እየተነደፉ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል። ወደ ሥራ ማስገባት እንዲሁም ሕዝቡ ቀጥተኛ ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል። የበይ ተመልካች ካለ እና ሁሉም የሀገራችን ሕዝብ የትሩፋቱ አካል ካልሆነ በቀጣይም ሕዝባዊ ንቅናቄ ማምጣቱ ላይ ችግር ስለሚፈጥር ከወዲሁ ሊሠራበት ይገባል። በፌዴራል ደረጃ በክልል እንዲሁም በግለሰብ ደረጃ እየተባለ ለእያንዳንዱ ቤተሰብ የውሃ ዋስትና የሚያረጋግጥበት ሁኔታ ከተፈጠረ የተሻለ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ።

አዲስ ዘመን፡ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም እጅግ አመሠግናለሁ።

አቶ ፈቅአህመድ፡እኔም አመሠግናለሁ።

ምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 24 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You