የሴቶች ጤና ክትትል፣ሕክምናና መድሀኒት አገልግሎትን በዲጂታል መንገድ

ቅድስት ተስፋዬ ትባላለች:: በኢትዮጵያ ብትወለድም በሁለት ዓመቷ ከወላጆቹ ጋር ወደ አሜሪካ በመሄድ በዚያው አድጋለች፤ ትምህርቷን በዚያው ተከታትላለች::

ከልጅነቷ ጀምሮ የሕክምና ሙያ በውስጧ ተጸንሶ የኖረው ቅድስት፣ ይሄው ፍላጎቷ ተፈጽሞም በሕክምና ዘርፍ መሥራት የሚያስችላትን ትምህርት ቀስማለች::

መንግሥት ዲያስፖራው ወደ ሀገሩ ገብቶ መሥራት እንዲችል ያቀረበውን ጥሪ መሰረት በማድረግ ወደ ትውልድ ሀገሯ ተመልሳ በሕክምናው ዘርፍ በጳውሎስ ሆስፒታል ለስድስት ወራት አገልግላለች:: የሆስፒታሉ ቆይታዋ በጤናው ዘርፍ ያሉ ችግሮችን በተለይ ከሴቶች ጋር ተያይዘው የሚስተዋሉ ችግሮችን ለይታ ለማወቅና ለመገንዘብ ጥሩ ዕድል ፈጥሮላታል::

ቅድስት ‹‹ጳውሎስ ሆስፒታል በሰራሁበት አጋጣሚ በጤናው ዘርፍ ብዙ ነገሮች እንደሚቀሩ ለማየት ችያለሁ፤ ከዚያ ወደ አሜሪካ ተመልሼ በሄድኩበት ጊዜ ለእዚህ የሚያስፈልጉኝን ትምህርቶች ተከታትያለሁ›› ስትል ገልጻ፣ በአሜሪካ ብዙ የሥራ እድሎች እንዳሉ ብትረዳም እሷ ግን ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት የጤናውን ዘርፍ በማሻሻል ረገድ የራሷን አስተዋጽኦ ማድረግ አንዳለባት ወስናም ተመልሳለች::

ይሁንና ኮቪድ 19 ወረርሽኝ በመከሰቱ ያሰበችውን መከወን አልቻለችም:: እንዲያውም እጇን አጣጥፋ አልተቀመጠችም:: በተለያዩ ዘርፎች የሚያማክር ድርጅት ከፍታ ለሦስት ዓመታት ያህል ሰርታለች:: ይህም በጤና ዘርፍ በመንግሥትም ሆነ በግል ዘርፉ በተለይም በሴቶች ጤና ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን መመልከት አስቻላት:: ይህም ወደ ሀገሯ የተመለሰችበት ዓላማና የነብሷ ጥሪ መሆኑን ተረድታ፣ በሴቶች ጤና ላይ ያስተዋለቻቸውን ችግሮች ለመፍታት የዳሳሰ ጥናት አካሂደች::

ባደረገችው ጥናት መሰረትም ለሴቶች ጤና ዲጂታል መፍትሔ ይሰጣል ያለችውን “የኔ ኸልዝ “ዲጂታል መተግበሪያን በመሥራት፤ “ የኔ ኼልዝ” የተባለ ድርጅት አቋቋመች:: የድርጅቱ መስራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ቅድስት ተስፋዬ ከጥናቱ በበለጠ ለሥራው ሴትነቷ እንዳገዛት ትናገራለች::

‹‹ያደረግኩት ጥናት ብቻ ሳይሆን በራሴ በሴትነት ያየኋቸው ተግዳሮቶች በሴቶች ጤና ላይ አተኩሬ እንድሰራ አድርጎኛል:: በጳውሎስ ሆስፒታል ያየሁትም ችግሩን በደንብ ስላሳወቀኝ ቀጣዩ ሥራ መፍትሔ መምጣት ነው ብዬ ማመኔ ወደ የኔ ኼልዝ እንድመጣ አድርጎኛል›› ስትል ታብራራለች:: በጤናው ዘርፍ ላይ ለውጥ ለማምጣት አልማ በመነሳቷ ሌሎች ሰዎች በሀሳቡ እንዲስማሙ ማድረግ ላይም አልተቸገረችም::

“የኔ ኼልዝ” በሴቶች ጤና ላይ የሚሰራ ስታርትአፕ ድርጅት ነው:: የቴክኖሎጂ ድርጅት እንደመሆኑ የኔ ኼልዝ የሞባይል መተግበሪያ በመስራት ተደራሽ እየሆነ ይገኛል:: የድርጅቱ ዋና ዓላማ ሴቶች ጤናቸውን በቀላሉ መጠበቅ እንዲችሉ በማድረግ ተደራሽ መሆን ነው::

ዋና ሥራው ማስተማር ሲሆን፣ ስነተዋልዶ ጤና፣ ስለመድኃኒት አወሳሰድ፤ የስኳር፣ የልብና የመሳሳሉትን በሽታዎች በተመለከተ ትምህርት መስጠት ነው:: በተጨማሪም ስለየበሽታዎቹ አይነትና ስለመድሃኒት አጠቃቀማቸው፣ የወር አበባ፣ እርግዝናና የመሳሰሉትን በተመለከተ ሴቶች ማወቅ ስላለባቸው ነገሮች በሚገባቸው ቋንቋ በቀላል ዘዴ ትምህርት እንዲያገኙ ይደረጋል::

የኔ ኼልዝ የሞባይል መተግበሪያ በውስጡ ብዙ ነገሮች በአንድ ላይ ጠቅልሎ ይዟል:: በአማርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋ አገልግሎት ይሰጣል:: በኦንላይንም ሴቶች በጤና ዙሪያ ማግኘት ያለባቸው ትምህርት እንዲያገኙ ያስችላል:: በተጨማሪም የኦንላይን ፋርማሲ አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን፣ በኦንላይን ፋርማሲ እንደራይድ አይነት የመድኃኒት አገልግሎት ይሰጣል:: አንድ ሰው ቤቱም ሆነ የትም ቦታ ላይ ሆኖ ባለበት ቦታ ድረስ መድኃኒት እንዲያገኝ ማድረግ የሚያስችል አሰራር አለው::

የአገልግሎቱ ፈላጊዎች ክፍያውን በቴሌ ብር ከፈጸሙ በኋላ መድኃኒቱ በአስቸኳይ እንዲደርሳቸው ይደረጋል። መድኃኒት ፍለጋ ላይ ብዙ ሰው እንደሚጉላላ ጠቅሳ፣ መድኃኒት ፈላጊዎች የሚፈልጉት መድኃኒት አገልግሎት ካዘዙ በታማኝነት ባሉበት የማድረስ ኃላፊነቱን ይወጣል::

ድርጅቱ ቴሌኼልዝ የተሰኘ አገልግሎትም ይሰጣል:: ቴሌኼልዝ የሕክምና አገልግሎትን በስልክ መስጠት ማለት ነው:: ይህም ልክ የራይድ አገልግሎት ፈላጊ ራይድ እንደሚጠራ ሁሉ ቴሌኼልዝ አገልግሎት ፈላጊም ወደ የኔ ኼልዝ መተግበሪያ በመግባት ቴሌኼልዝ የሚለውን አገልግሎት በመንካት ሀኪም በማነጋገር ክፍያውን ወዲያውኑ ፈጽሞ በስልክ የሕክምና አገልግሎት ማግኘት ይችላል::

በዚህም በቪዲዮ፣ በኦዲዮ እና በስልክ የሚያስፈልገውን አገልግሎት እንዲያገኝ ይደረጋል:: ዋጋውም ቢሆን በጣም ተመጣጣኝ ወይም ርካሽ የሚባል ነው:: በተለይ የቴሌኼልዝ ካርድ ከማውጣት ጀምሮ እስከ ሕክምና ድረስ ታማሚዎች የሚደርስባቸውን ወረፋ ከመጠበቅ አንስቶ ያለውን እንግልት ከማስቀረት በላይ አገልግሎቱ በአጭር ጊዜ እንዲያገኙም ያስችልላቸዋል:: መተግበሪያውን ተጠቅመው ባሉበት ሆነው ሕክምና ወዲያወኑ በማግኘት የሚታዘዘላቸው መድኃኒትም በፍጥነት እንዲያገኙ ያስችላል። በተጨማሪም ስለ ጤናቸው ትምህርት የሚያገኙበት መሆኑን ታስረዳለች::

በሴቶች ጤና ላይ በተለይ ከስነ-ተዋልዶ ጤና፣ እርግዝናና ጋር የተያያዙ በርካታ ችግሮች እንዳሉም ጠቅሳ፣ በዚህ ትኩረት ሰጥተን የምንሰራውም ለዚህ ነው ስትል ቅድስት ትናገራለች::

መተግበሪያው የወር አበባን በኢትዮጵያ የጊዜ አቆጣጣር/በካላንደር/ መሠረት መከታተል የሚያስችል ፕላትፎርም እንዳለው ተናግሯል፣ ይህም ሴቶች የወር አበባቸው መቼ እንደሚመጣ ለማወቅና ለመቆጣጣር እንደሚያስችላቸው አስታውቃለች::

እሷ እንዳለችው፤ የወር አበባ የመጣበት ቀን ሲስተም ላይ ገብታ ትመዘገባለች፤ መጥቶ የሄደበትንም ቀን እንዲሁ ትመዘግባለች:: ከዚያም ሲስተሙ የሰጠችውን ዳታ ተጠቅሞ በሚቀጥለው ጊዜ የወር አበባ የሚመጣበትን ጊዜ አስቀድሞ ያሳውቃታል::

የወር አበባ መዛባት ከጤና ጋር ተያያዥ በሆኑ ምክንያቶችም የሚከሰት መሆኑን ገልጻ፣ በጊዜ መስተካከል ካልቻለ ሕክምና ሳይገኝ ቀርቶ ችግር ሊፈጠር እንደሚችል አስገንዝባ፣ ሲስቱሙ በየወሩ ለመከታተል ለመቆጣጣር እንደሚያስችል ጠቁማለች:: ከሕክምናው በተጨማሪም የወር አበባው በሚቀጥለው ጊዜ የሚመጣበት ቀን መታወቁ በራሱ የተስተካከለ ሕይወት ለመኖር እንደሚያስችል ቅድስት አብራርታለች::

ለእርጉዞችም እርግዝናቸውን የሚከታተሉበትና ትምህርት የሚሰጥ ፕላትፎርም እንዳለውም ተናግራ፣ ወደ መተግበሪያ ገብታ እርጉዝ መሆኗን ያሳወቀች ሴት ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የእርግዝናውን ሂደት ለመከታተል ያስችላታል:: ከአንድ ሳምንት ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ወር ድረስ በየሳምንቱ ያላትን ለውጥና የጽንሱን /ልጇን/ ጤንነት ሳይቀር እየተከታተለ በየጊዜው የተረጋገጠ መረጃ ይሰጣታል::

የጽንሱን ጤንነት በመንገርም ማድረግ ያለባትን እያስተማረ የመውለጃዋን ጊዜና የሕክምና ተቋም መቼ መሄድ እንዳለባትም እየነገረ ያሳውቃታል:: ይህንን መረጃ ለማግኘት የግድ ሕክምና ተቋማት መሄድ ሳያስፈልጋት በቀላሉ መረጃዎችን በመከታተል ማወቅ የምትችልበት ነው::

የኔ ኼልዝ ዓላማ በተለይ ከ15 እስከ 49 ዓመት ላሉ ሴቶች የሥነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎትን በቀላሉ ተደራሽ ማድረግን ያለመ ነው የምትለው ቅድስት፤ ሴቶች ስለጤና ለማወቅ ለመማር እንዲሁም የሕክምና ባለሙያ ለማማከር: ከሀኪም ጋር ውይይት ለማድረግ የሚያስችል እና አስፈላጊውን አገልግሎት ባሉበት ቦታ ሆነው በቀላሉ እንዲያገኙ ዓላማ አድርጎ እየሰራ መሆኑን አብራርታለች:: መተግበሪያውን ያለምንም ክፍያ በነጻ አውርዶ መጠቀም እንደሚቻልም ጠቁማለች::

እንደ ቅድስት ማብራሪያ፡ ከሴቶች በተጨማሪ ማንኛውም ሰው መተግበሪያውን ከአፕስቶርና ከፕሌይስቶር ላይ አውርዶ መጠቀም ይችላል:: ዌብ ሳይት ያለው ሁሉም ሰው ገብቶ መጎብኘት ይችላል::

ዋና ዓላማው ሴቶች በራሳቸው ስለጤናቸው በደንብ አውቀውና ተረድተው በኃላፊነት ስሜት ጤናቸውን መጠበቅ እንዲችሉ ያደርጋል:: አሁን በአብዛኛው በመተግበሪያ ላይ የምንናገኛቸው ተጨማሪ ልጅ መውለድ የማይፈልጉ፣ የአባላዘር በሽታ ያለባቸው እና የሚፈልጉትን አገልግሎት በስልክ ብቻ በግልጽ በማውራት የሚፈልጉ ናቸው ሲሉ ጠቅሰው፣ አገልግሎቱም ያለባቸውን ሕክምና እንዲያገኙ ያስችላል ብላለች:: ሴቷ ይህንን ማድረጓ የራሷንም፣ የልጇንና የቤተሰቧንም ጤና መጠበቅ እንድትችል ያደረጋል::

በሌላ በኩል ደግሞ የጤና ዘርፍ የኦንላይን መተግበሪያ ሥርዓትም አብሮ የተዘረጋለት ነው:: ይህም የሕክምና ተቋማት፣ ክኒሊኮች፣ ፋርማሲዎች እና አጠቃላይ በጤና ዘርፉ ላይ የሚሰሩ ማዕከላት የኔ ኼልዝ አባል እንዲሆኑ ይደረጋል:: በመቀጠልም በ‹‹ሆል ሴል›› ወይም በመድኃኒት ማከፋፈል ሥራም የሚሰራበት ነው::

ሴቶች የኦንላይን አገልግሎቱን እንዲያገኙ እያደረግን መድኃኒት የማናቀርብ ከሆነ ዞሮ ዞሮ ከችግር ማላቀቅ አይቻልም ስትል አመልክታለች፣ መድኃኒት ለማቅረብ የሚያስችል አሰራር እንዳለውም አመልክታለች:: በሌላ በኩል ፋርማሲዎችም ሆኑ ሀኪም ቤቶች መድኃኒት ለማከፋፈል መጋዘን ለማስቀመጥ የገንዘብ እጥረት ሊገጥማቸው እንደሚችል ጠቁማለች፤ ሕጋዊ ፋርማሲዎች አባል እንዲሆኑ በማድረግ መድኃኒቱን ከአምራቾችና ከአስመጪዎች በቀጥታ እንዲገዙ የብድር አቅርቦት በማመቻቸት ይሰራል::

በሲስተሙ እየተጠቀሙ ተበድረው መድኃኒት በሚገዙበት ወቅት የመድኃኒት አቅርቦት እጥረት እንዳያጋጥምና ሁሌም መድኃኒት እንዲኖር በማድረግ ተጠቃሚው አገልግሎቱን እንዲያገኝ ይደረጋል:: ይህ ሥራ ከተጀመረ ሦስት ወራትን ብቻ ቢያስቆጥርም፣ ውጤታማ ሥራ እየሰራ መሆኑን ትናግራለች:: መድኃኒት ለመያዝና ለማከፋፈልም እንደሰራ ትገልፃለች።

እሷ እንዳለችው፤ ከአምስት ሺ በላይ የጤና ባለሙያዎች (ሀኪሞች፣ ነርሶችና ፋርማሲስቶች) በሲስተሙ ውስጥ ገብተዋል:: እነዚህን ባለሙያዎች በደንብ በማሰልጠንና ቴክኖሎጂን በማስተማር በቴሌኼልዝ ሲስተም ላይ ገብተው ሕክምና እንዲሰጡ እየተደረገ ይገኛል:: ይህም ለብዙ የጤና ባለሙያዎች የሥራ እድል እንዲፈጥሩ ያደረጋል:: በአጠቃላይ የኔኼልዝ ከሴቶች ጀምሮ እስከ አገልግሎት ሰጪዎች ድረስ ያሉትን በአንድ ፕላትፎርም በማገናኘት የተሳለጠ የጤና አገልግሎት ተቋም ሆኖ እየሰራ ነው::

ቅድስት እንደምትለው፤ የኔ ኼልዝ ወደ ሥራ ከገባ ሦስት ዓመታት ሆኖውታል:: የመጀመሪያው ሁለተኛው ዓመታት በጥናት ጊዜ ተሰቶት የተሰራበት ነው:: በተለይ በሁለተኛ ዓመት ቴክኖሎጂው ላይ በትኩረት ተሰርቷል::

የየኔ ኼልዝ መተግበሪያ ይፋ ከተደረገ 10 ወራት ጊዜ ብቻ ቢሆንም ከ30ሺ በላይ ሰዎች አውርደውታል:: አሁን ላይ በየትምህርት ቤቱ ፕሮግራሞች እየተዘጋጁ መተግበሪያውን እየተዋወቀ ነው:: ከአዲስ አበባና ጅማ ዩኒቨርሲቲ ጋር ፕሮግራም በማዘጋጀት ተማሪዎቹን በማሰልጠን መተግበሪያውን ተማሪዎች እንዲጠቀሙት እየተደረገ ይገኛል::

ድርጅቱ ከብዙ ድርጅቶች ጋር በአጋርነት ይሰራል፤ ከጤና ባለሙያዎች ጋር ይሰራል:: ለአብነትም ቴሌኼልዝ በኦንላይን አገልግሎት በአንድ ሀኪም ብዙ ታካሚዎች ማከም ይችላል:: አንድ ሀኪም በቀን 30 ሰዎች ማየት ከቻለ 10 ሀኪም ቢኖረን አስሩም እያንዳንዳቸው በቀን ሰላሳ ሰዎች ማየት ከቻሉ መረጃውንም ተደራሽ ማድረግ ይችላሉ ማለት ነው:: ከሕክምና ተቋማት፣ ክሊኒክ፣ ፋርማሲዎች ችግር በደንብ በመፍታት አብሮ እየሰራ በመሆን የኔ ኼልዝ ተደራሽነቱ እየሰፋና እያደገ እንዲሄድ አድርጎታል::

ድርጅቱ ለ26 ያህል ሰዎች በቋሚነት የሥራ እድል የፈጠረ ሲሆን፤ ሰፋ ያሉ ሥራዎች ባሉበት ወቅት ደግሞ ብዙ ጊዜያዊ ሠራተኞች ይቀጠራሉ:: በተዘዋዋሪም ለብዙ የጤና ባለሙያዎች የሥራ እድል መፍጠር ችሏል:: ከድርጅቱ ጋር የሚሰሩ የሕክምና ተቋማት የጤና ባለሙያዎች ለመቅጠር ሲፈልጉ በፕላትፎርሙ ከተመዘገቡ ባለሙያዎች እንዲቀጠሩ የሚደረግበት አሠራር አለው::

ድርጅቱ በጤናው ዘርፍ የሚሠራቸውን ሥራዎች አስፋፍቶና ሰዎችን አሳምኖ ለመጓዝ ብዙ ጥረት ማድረግን ይጠይቀዋል:: ብዙ የሚቀረው ነገር ቢኖርም፣ እየታየ ያለው ለውጥም ቀላል የሚባል አይደለም የምትለው ቅድስት፤ እንደ ጀማሪ መንገዱን እየጠረግን ስለምንሄድ በቀጣይ ጥሩ አሰራር እንዲዘረጋ እያደረግን ነው ብላለች::

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ማክሰኞ መጋቢት 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You