ከፊጣሪ ሃዋሮ እስከ ፍቼ ጫምባላላ

የሲዳማ ሕዝብ ዘንድሮ የዘመን መለወጫውን «ፍቼ ጫምባላላ» በዓልን ባለፈው ሳምንት በሐዋሳ ሶሬሳ ጉዱማሌ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ በተገኘበት በድምቀት አክብሯል። ዋዜማውን ”ፊጣሪ ሃዋሮ” እንዲሁ በተመሳሳይ ድባብ አክብሯል። ከብት የማይታረድበት፤ ዛፍ የማይቆረጥበት፤ ያጠፉ ይቅር የሚባባሉበት በዓል ነው። የሲዳማ የዘመን መለወጫ ፍቼ ጫምባላላ። የሲዳማ አባቶች የጨረቃና የከዋክብትን አቀማመጥ በማጥናት ማሕበረሰቡ የዘመን መለወጫ በዓልን የሚያከብርበትን እለት ይፋ ያደርጋሉ።

የሲዳማ ማሕበረሰብ በተለይ በቄጣላ ባሕላዊ ጭፈራው እጅግ ይታወቃል፡፡ ማሕበረሰቡ አንድነቱን ከሚያሳይባቸው ኪነ-ጥበባዊ ክንውኖች መካከል አንዱ ቄጣላ ነው፡፡ ትከሻ ለትከሻ ሆኖ በጋራ ዜማ የሚከናወነው ጭፈራ፤ በመሪ ዳንሰኞች የሚታየዉ የውዝዋዜ ትወና እና እንቅስቃሴ ተመልካችን ያስደምማል። የማሕበረሰቡ አዋቂዎች እንደሚናገሩት በዳንሱ በዜማው ሠላም፤ አንድነት ይሰበካል፤ አዲሱ ዘመን መልካም ይሆን ዘንድ ምኞት ይገለጽበታል፣ ፈጣሪም ይመሰገንበታል፤ ወቅታዊ ጉዳዮች እና መልዕክቶች ለማሕበረሰቡ ይተላለፉበታል።

የሲዳማ ሕዝብ የዘመን መለወጫ ፍቼ ጫምባላላን ለማክበር ቀደም ብሎ ከፍተኛ ዝግጅትን ያደርጋል። አከባበሩ ከዋዜማ ጀምሮ ይደምቃል፡፡ ጎረቤት ይሰበሰባል፤ ከእንሰት የሚዘጋጀውን ቡርሳሜ ተብሎ የሚጠራ ምግብን ያዘጋጃል፤ በወተት ይመገባል። ስጋ የሚባል ነገር ከቤት ይወጣል። ሲዳማ ከአንድ ዓመት ወደሌላው የሚሸጋገርበት ሂደት ሁሉቃ ይባላል። ሁሉቃ ማለት ከሸምበቆና ከእርጥብ ቅጠል ተሠርቶ የሚቆም ነገር ነው። በዚህ እለት ሰዎች በዚህ በተሰራ በኩል ያልፋሉ። በእለቱ በሲዳማ ከብቶች ሳይቀሩ ደስ ብሏቸዉ እንዲውሉ ይደረጋል፡፡ ቀድም ብሎ በተዘጋጀላቸው ግጦሽ ቦታም ይሰማራሉ፣ በእለቱ እንስሳት አይመቱም፣ አይታረዱም፣ ዛፍ አይቆረጥም፤ ያጠፉም ይቅር የሚባሉበት እለት ነው።

የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን በዓሉን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፤ የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባሕል ተቋም (ዩኔስኮ) በቅርስነት የመዘገበው የሲዳማ ዘመን መለወጫ ፍቼ ጫምባላላ ክብረ በዓል መቼ እንደሚውል የሲዳማ ሽማግሌዎች ማለትም አያንቶች በኮከብ ቆጠራ እለቱን አውቀው በአያንቱዎች አዋጅ መሰረት በዓሉ በየዓመቱ የሚከበርበት ቀን ይቆረጣል። ቀኑ የሚገለጸው በላላዋ ነው። ላላዋ በሲዳማ የመረጃ መለዋወጫ ስልት ነው። ጫምባላላ ከመድረሱ አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ የዘመን መለወጫው እለት በዚህ ቀን ይውላል የሚለው መረጃ በየገበያው ይገለጻል፡፡ ጫምባላላ መከበር የጀመረው መቼ እንዲሆን እስካሁን በጥናት የተገለፀ ነገር ባይኖርም፤ ፍቼ ጫምባላላ የሲዳማ ጥንታዊ በዓል ነው ይለናል።

ፍቼ ጫምባላላ የአብሮነት፣ የሰላም፣ የፍቅርና የመረዳዳት እሴቶች ጎልቶ የሚታዩበትም ነው፡፡ በዓሉ የሲዳማ ሕዝብ ዘመን መለወጫ በዓል ብቻም ሳይሆን የነበረ ቂምና ቁርሾ ተወግዶ ይቅርታ የሚሰፍንበት የእርቅና የሰላም ባሕላዊ ትውፊት ነው። በመሆኑም ፍቼ ጫምባላላ የሰላም፣ የእርቅና የይቅርታ ተምሳሌት የሆነ ቅርሳችን ነው፡፡

የሲዳማ ሕዝብ የራሱ የሆነ የቀን አቆጣጠር ያለው ሲሆን ቀናትን፣ ሳምንታትንና ወራትን በራሱ ባሕላዊ የአቆጣጠር ዘዴ ተከትሎ ይጠቀማል፡፡ በበዓሉ ከሰው እስከ እንስሳት እንዲሁም ለዕፅዋትና አራዊቶች መልካም ምኞት የሚንጸባረቅበት ትውፊት ነው፡፡ በመሆኑም በዓሉ የቀደምት አባቶችን የዕውቀት ከፍታ ማሳያ፣ የሕዝቡን የጥበብ ጥግ ታሪክ ባለቤትነት መገለጫም ጭምር ነው፡፡

በዓሉ የሲዳማን ሕዝብ ማንነትና ባሕል ከማስተዋወቅ ባለፈም የክልሉን የቱሪዝም ልማትና ዕድገት በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ አዎንታዊ ሚና ይኖረዋል፡፡ በተጨማሪም ፍቼ ጫምባላላን የእርቅ፣ የሰላም፣ የአብሮነት እና የወንድማማችነት እሴቶች ከማጎልበቱም ባሻገር ለሀገር ግንባታና የወል ትርክትን ለመገንባት የሚኖረው ሚና ጉልህ ነው፡፡ ስለ በዓሉ ይሄን ካልሁ በቅጡ በወጉ ስላልተጠቀምንበት በመባከኑ ሁል ጊዜ እንደ እግር እሳት ስለሚያንገበግበኝ ባሕላዊ ወረታችን ላስታውሳችሁ ወደድሁ።

ባሕላዊ ንብረት (cultural capital) የሚለው ሀረግ ፔሬ ቦርዴው በተባለ በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ማብቂያ ላይ የተነሳ የስነ ሕብረተሰብ ተመራማሪ እንደተፈጠረ የተለያዩ የዘርፉ ድርሳናት ያትታሉ ። ባሕላዊ ንብረት በማሕበረሰብ ውስጥ ያለን ተቀባይነት ቦታ ከፍ ለማድረግ እውቀትን፣ ፀባይና ክሕሎትን የማሳደግ የማካበት ሂደት ነው። ባሕላዊ ንብረት በግለሰብ፣ በማሕበረሰብ ከፍ ሲልም በሕዝብ በሀገር ይሰላል። የበለፀገ ባሕላዊ ንብረት ያካበተ ግለሰብ በማሕበረሰቡ ዘንድ ያለውን ተቀባይነት ከፍ እንደሚያደርገው ሁሉ ያደገ የለማ ባሕላዊ ንብረት ያለው ማሕበረሰብ ሕዝብ በተመሳሳይ ሁኔታ ከፍ ያለ ተቀባይነት ይኖረዋል።

ባሕል ማለትም የሕብረተሰብ የአኗኗር ዘዴ፣ ወግ፣ ልማድ፣ እምነት፣ ወዘተ . በሂደት በእውቀትና በክሕሎት እየበለፀገ፣ እየዳበረ ሲሄድ ለሀገር ሰላም፣ አንድነት ከፍ ሲልም እድገት የላቀ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። በተቃራኒው ባሕል በእውቀት፣ በክሕሎት ካልበለፀገ አይደለም ለሀገር ሰላምና ዕድገት መዋል ይቅርና የማሕበረሰቡን እሴቶች ጠብቆ ማቆየት ካለማስቻሉ ባሻገር የእለት ተእለት ችግሮችን እንኳ መፍታት የሚሳነው ይሆናል። ባሕላዊ ንብረት እንደ ኢኮኖሚያዊ ንብረት ማለትም ገንዘብ በአግባቡ ኢንቨስት ተደርጎ ሰላምን፣ ፍቅርን፣ እርቅን፣ መነጋገርን ፣ መቀባበልን፣ መከባበርን ፣ መተባበርን ፣ አንድነትን ፣ ወዘተ . እውን ማድረግ ካልቻል እንደባከነ እንደከሰረ ሊቆጠር ይችላል።

ሀገርን ሕዝብን ከግጭት ፣ ከቀውስ ፣ ከመፈናቀል፣ ከመጠራጠር ፣ ከጥላቻ ፣ ከበቀል ፣ ወዘተ . መታደግ አልቻለም። እስኪ ለአንድ አፍታ ባሕሎቻችንን እምነቶቻችንን ወይም ባሕላዊ ንብረቶቻችንን ከዚህ አኳይ እንመዝናቸው። ባክነዋል ወይስ በአግባቡ ሥራ ላይ ውለዋል ! ? አሁን ከምንገኝበት ሀገራዊ ቁመና አንጻር ባክነዋል ቢባል የሚያስኬድ ይሆናል። ታዲያ እነዚህን ባሕላዊ ንብረቶቻችንን እንደ ጦር እቃ ለብሶ እንደ ጥሩር ደፍቶ መውጣት መግባት፣ መመላለስ ለምን ተሳነን ? መልሱ ቀላል ነው። ላይ ላዩን እንከውናቸዋለን እንጅ አንኖራቸውም። በቃል እናነበንባቸዋለን እንጂ በልባችን አላተምናቸውም።

ባልንጀራህን፣ ጎረቤትህን እንደ ራስህ ውደድ የሚሉ አብርሃማዊ እምነቶችን ማለትም ክርስትናን፣ እስልምናንና አይሁድን እየተከተልን እንዴት በጥል ግድግዳ ተለያየን!? በአንድ አምላክ በዋቄ ፈና እያመን ኢ ሬቻን በየዓመቱ እያከበርን እየከወን ይቅር መባባል ለምን ተሳነን? መልሱን ለማግኘት ሚስጥሩን ለማወቅ ሞራ ማስገለጥ ወይም ኮከብ ማስቆጠር አያሻም። መልሱ ቀላል ነው። እሱም ባሕላዊ ንብረቶቻችንን በካዝና ቆልፈን አስቀመጥን እንጂ ሥራ ላይ ስላላዋልናቸው (ኢንቨስት) ስላላደረግናቸው ነው። ሀገራዊ ሰላምና አንድነት እውን ለማድረግ የተቆለፈባቸውን ባሕላዊ ንብረቶች ከካዝና አውጥቶ በእያንዳንዱ ዜጋ ላይ በፍጥነት ማፍሰስ ኢንቨስት ማድረግ ይጠይቃል።

በኢኮኖሚክስ አስተምህሮ ባሕል ከተፈጥሮ፣ ከሰውና ከአካላዊ ፣ ቁስ አካላዊ (physical) ቀጥሎ 4ኛው ንብረት ሆኖ መጠናት ፣ መተንተን ከጀመረ ከራርሟል። በአግባቡ ጥቅም ላይ ከዋለ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ለሀገር እድገትና ለዘላቂ ሰላም አስተዋጽኦ ያበረክታል። ሰላም በሌለበት ኢኮኖሚያዊ እድገትም ሆነ ብልፅግና ሊታሰብ አይችልምና። የመደመር ሶስቱን “ምሠሦዎች” መሰብሰብ ፣ ማከማቸትና ማካበትን እውን ማድረግ አይታሰብም።

ለሀገር ግንባታ በአዎንታዊም ሆነ በአሉታዊ ወሳኝ ሚና ከሚጫወተው ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ሥርዓት በተጨማሪ ለዘመናት እንደ ሕዝብ ፣ እንደሀገር አጋምዶ ያቆየን ባሕላዊ ንብረታችን ነው። ሁነቱን፣ ክዋኔውን፣ መንፈሱን ጠብቆ ተንከባክቦና አልምቶ ከትውልድ ወደ ትውልድ ማስተላለፍ ፣ ማስቀጠል፣ ማክበርና ማስተዋወቅ ትልቅ ኃላፊነትም አደራም ነው። ሆኖም የመጨረሻ ግብ ሆኖ ግን ሊወሰድ አይገባም። ቱባነቱን እንደጠበቀ ማደግ ዘመንና ትውልድ መዋጀት ይጠበቅበታል። አዎ ! የትውልዱንና የዘመኑን ህፀፅ የሚያርም ለምፅ የሚያነጻ ፣ የሚዋጅና የሚቤዥ መሆን አለበት።

ዘረኝነትን ፣ ጥላቻን ፣ ቂም በቀልን ፣ ደባን ፣ መከፋፈልን ፣ ወዘተ . መቤዥ ፣ መዋጀት አለበት። ባሕላዊ ንብረታችንን ይበልጥ በማጎልበት ፣ በማልማትና በማስፋት ለመጻኢ እድላችን ፣ ለነገ ተስፋችን፣ ለእርቅ፣ ለሰላም ፣ ለአንድነት፣ ለሁለንተናዊ ብልፅግና፣ ለመደመር ወዘተ. ልናውለው ይገባል። ስኬቶቻችንን የምናወድስበት፣ ፈተናዎቻችንን የምንሻገርበት ነገአችንን የምንተልምበት ጭምር አድርጎ ስለመጠቀም አበክረን ማሰብ ያስፈልጋል።

የፍቅር ፣ የእርቅ ፣ የሰላም ፣ የአብሮነት ፣ የማካፈል፣ የመተባበር ፣ የመተጋገዝ ፣ የመረዳዳት ፣ የምስጋና ፣ ወዘተ . ባሕሎች ፣ ልማዶች ፣ እምነቶች፣ ሃይማኖቶች ከፍ ሲልም ድምር ባሕላዊ ንብረቶች ባለቤት እንዲሁም የጥንታዊት ሀገር ባለቤት ሆነን አንድነትን በመከፋፈል ከሰዋን ፣ ፍቅር ከጎደለን ፣ እርቅ ከገፋን ፣ ሰላም ከራቀን፣ አብሮነትን በቀዬአዊት ከተካን፣ ማካፈልን በስስት ከቀየርን ፣ መተባበርን በመለያየት ከለወጥን ፣ ምስጋናን በእርግማን ከተካን፣ ወዘተ . ምኑን ሙሉኡ ሆነው? ባለፉት ስድስትና ሰባት ዓመታት ያለፍንባቸው ሀገራዊ ውጣ ውረዶች፣ አሳፋሪ ድርጊቶች እውነት የእነዚህ ሁሉ መንፈሳዊና ባሕላዊ ፀጋዎች ባለቤት ስለመሆናችን የሚመሰክሩ ናቸው? እስኪ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የሚከበሩ መንፈሳዊና ባሕላዊ ሁነቶች የተሸከሙትን ግዙፍ መልዕክቶችና አንድምታዎች አለፍ አለፍ ብለን እየተመልከትን ሂሳብ እናወራርድ።

ፍቼ ጫምባላላ ፣ ቡሔ ፣ ሻደይ ፣ አሸንዳ፣ ሶለል አይነ ዋሬ ፣ እንቁጣጣሽ ፣ መስቀል ፣ መስቀላዮ፣ አጋመ ፣ ጊፋታ፣ ኢ ሬቻን ፣ ጋሮ ፣ ቺሜሪ ፣ ወዘተ በአንድም በሌላ በኩል በተለያዩ የሀገራችን ማሕበረሰቦች የሚከበሩ ሃይማኖታዊ ወይም ባሕላዊ ክዋኔዎች ናቸው። ሁሉም ማለት ይቻላል ተስፋን ፣ ፍቅርን ፣ ነፃነትን ፣ አብሮነትን፣ ምስጋናን ፣ እርቅን ፣ ይቅርታን ፣ ወዘተ . የሚያውጁ ፣ የሚለፍፉ ናቸው። ግን በነቂስ ወጥተን ለዘመናት በየዓመቱ በአደባባይ የምናከብራቸው የምንዘክራቸውን ያህል በዕለት ተዕለት ኑሮአችን አንኖራቸውም። አንለማመዳቸውም። ከገጠሙን ቀውሶች ፣ ፈተናዎች መውጣት ማገገምና ማንሰራራት የቻልነው በቀሩን ሽርፍራፌ እንጥፍጣፌ በባሕላዊ ንብረቶቻችን ነው። ባለፉት 34 ዓመታት ቀን ከሌት እንደ ተሰበከው ልዩነት ፣ ጥላቻና ዘርኝነት ቢሆን ኑሮ እርስ በእርስ ተበላልተናል። ተጨራርሰናል። ለዚህ ነው መዳኛችን ፣ ማገገሚያችንና ማንሰራሪያችን የሆነውን ባሕላዊ ንብረት ወደሙላቱ መመለስ ለነገ የሚባል ጉዳይ የማይሆነው።

ባሕላዊ ንብረታችን ለበጎ ዓላማ ሲውል ሀገርን ከጥፋት ከእልቂት እሳት እንደሚታደግ ከዓመታት በፊት በጋሞ ሀገር ሽማግሌዎች ተመልክተናል። የጋሞ የሀገር ሽማግሌዎች እሳት ጎርሶ እሳት ለብሶ ለበቀል ተነስቶ የነበረውን የአርባ ምንጭና የአካባቢውን ወጣት ለምለም ሳር ይዘው ተንበርክከው በመለመን ቁጣውን አብርደው መልሰውታል። ይህን የሀገር ሽማግሌዎች ገድል በጥሞና ለተረዳው የአርባ ምንጩን እሳት ብቻ አይደለም ያጠፉት የአርባ ምንጩን ጥፋት ተከትሎ በመላ ሀገሪቱ ሊዛመት የነበረውን የበቀል ሰደድ እሳት ጭምር እንጂ።

ቁጣ አብራጁ ይህ የጋም አባቶች ልመና (ጋሞ ወጋ) እየጠፋ ፣ ትኩረት እየተነፈገው ያለው ባሕላዊ ንብረታችን ተጠብቆ ለትውልድ ሲተላለፍ ሀገርን እንዴት ማዳን እንደሚችል ጥሩ ማሳያ ነው። የጋሞ አባቶች የ2011 ዓ.ም ልዩ የበጎ ሰው ተሸላሚ መሆናቸው በሁሉም ኢትዮጵያዊ ዘንድ ያለ አንዳንች ልዩነት ዳር እስከዳር አድናቆትን ተቀባይነትን ያተረፈው በዚህ እሳቤ ነው።

ሰላምን ፣ ፍቅርን ፣ ይቅርታን ለማነፅ ፣ ለመገንባት ከምንሰጠው ትኩረት ባልተናነሰ በየአካባቢው እንደ ጋሞ ወጋ አይነት የሽምግልና፣ የእርቅ ባሕላዊ ካፒታሎቻችንን ላይም መስራት ይጠበቅብናል። ከዚህ መሳ ለመሳ የአክራሪነት አዝማሚያ ፣ እኩይ አስተሳሰብ እንዲገታ ብሎም ተሸንፎ ከሰላምና ከእርቅ መንገድ ገለል ፣ ዘወር እንዲል ድልብ የሆኑ ባሕላዊ ንብረቶቻችን ጥንስስ ፣ ወረት የማይተካ ሚና አላቸው። ሁሉም ኢትዮጵያውያን የተለያዩ ባሕላዊ ንብረቶች ባለፀጋ ስለሆኑ የየራሳቸውን መዋጮ ማበርከትና ወደ ሥራ መግባት ይጠበቅባቸዋል።

በየአካባቢያችን ፣ በየቀዬአችን የምናንፀው ፣ የምናቀነቅነው ከባቢያዊ ብሔርተኝነት ወደ አክራሪነት፣ ፅንፈኝነት የሚያንደረድር ወደገደል አፋፍ የሚገፋ ስለሆነ እነዚህን ባሕላዊ ወረቶች በመጠቀም መግታት ያስፈልጋል። የዜጎች ማንነት እሴት እንደተከበረ ወደ ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት የሚያደርሰንን ቀና መንገድ በቅንነት መቀላቀል ፣ መያያዝ ይገባል። ይህ ሀገራዊ ብሔርተኝነትም ከገደቡ ፣ ከውሃ ልኩ እንዳያልፍ ጥንቃቄ ማድረጉ እንዳለ ሆኖ ። አይደለም ዘውጌአዊ፣ ወንዜአዊ ብሔርተኝነት ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት በአግባቡ ካልተያዘ ፤ የጎረቤቱን የሚጎመጅ ፣ የሚመኝ፣ የሚመቀኝ ሆኖ የመውጣት አደጋ ስላለው በብልሀት ፣ በማስተዋል ሊቀነቀን ይገባል እላለሁ። እናንተስ ምን ትላላችሁ።

ሻሎም !

አሜን።

ቁምላቸው አበበ(ሞሼ ዳያን)

fenote1971@gmail.com

አዲስ ዘመን ማክሰኞ መጋቢት 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You