
የግንባታው መሠረት ድንጋይ መጋቢት 24/2003 ዓ.ም የተጣለውና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ ጉባ ወረዳ ላይ ግንባታው እየተጠናቀቀ የሚገኘው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከትልልቅ የሀገሪቱ ብሔራዊ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱና ግዙፉ መሆኑ ይታወቃል።
ይህ የባንዲራ ግድባችን የመሠረት ድንጋዩ ከተቀመጠባት እለት ጀምሮ የክርክር፣ ውዝግብ፣ ንትርክና ጭቅጭቅ ማእከል በመሆን እስከ አሁኗ፤ እስከ ዛሬዋ፣ የሪቫን መቁረጫ ዋዜማ ድረስ የዘለቀ ልዩና የመስዋእትነት ውጤት ሪቫኑ ሊቆረጥ አፋፍ ላይ ደርሷል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በኢትዮጵያውያን አንጡራ ሀብት፤ በኢትዮጵያውያን ላብ፣ በኢትዮጵያውያን ጉልበትና እልህ አስጨራሽ ተጋድሎ የተገነባ ሲሆን፤ በተለይም ታሪካዊቷ ጠላታችን ግብፅ እስከ መጨረሻዋ የደም ጠብታ ድረስ የተወራጨችበትና እያፈረች የተመለሰችበት ባንዲራ ፕሮጀክታችን ስለ መሆኑ ዓለም ሁሉ ያውቃል።
ለዝናቡ ጌታ ውሃ ከለከሉት እንዲሉ፣ ነገረ ሥራዋ ሁሉ ካፈርኩ አይመልሰኝ የሆነችው ግብፅ (በተለይ እሷ) ይሉኝታ ይሉ ነገር ላመል እንኳን ያልፈጠረባት እንደ መሆኗ መጠን ግድቡ ገና በፅንሰቱ ይቀር ዘንድ ያልበጠሰችው ቅጠል፤ ያልቆፈረችው ጉድጓድ፤ ያልነጨችው ሳር የለም።
ከተፀነሰም በኋላ ይጨነግፍ ዘንድ ያልገዛችው ባንዳ፣ ያልረገጠችው ኤምባሲ፣ ያልዳኸችባቸው ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ እጅ ያልነሳቻቸው ሹማምንት (ለምሳሌ 150ሺህ ዶላር የተቀበለውን አሜሪካዊ ባለሥልጣን ያስታውሷል) ካሉ ምናልባት በሕይወት የሌሉት ብቻ ናቸው።
ይሁን እንጂ “ሁሉ ነገር ከንቱ” እንዳለው ጠቢቡ ሁሉም ነገር ከንቱ ሆኖባት ከየሄደችበት ሁሉ ባዶ እጇን ስትመለስ ኢትዮጵያውያን ሪቫን ሊቆርጡ ዋዜማው ላይ ይገኛሉ።
አንገት የተፈጠረው አዙሮ ለማየት መሆኑን ካለመገንዘብ እንጂ፣ የ1929 እና 1959 የቅኝ ግዛት ስምምነትን እንደ ዋስትና በመቁጠር ለዓመታት ዓባይን በብቸኝነት መጠቀም “ተፈጥሯዊና ታሪካዊ መብቴ ነው” ማለት በእውነት አለመታደል እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም። የዲፕሎማሲን ሀ፣ ሁ፣ ሂ… ካለማወቅ፤ ክፍለ ዘመኑ 21ኛው መሆኑን ካለመረዳትና መቀንጨር የመጣ እንጂ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል?
ከ”ግድቡን አፈርሰዋለሁ”፤ “በአንድ በተን (የኮምፒውተር ቁልፍ) አመድ አደርገዋለሁ” እና ሌሎችም አስፀያፊ ዛቻዎች ጀምሮ ከአፍሪካ ህብረት እስከ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት እና መሰል ተቋማት ድረስ ያላንኳኳችው በር የለም። ሺህ ጊዜ ታንኳኳ እንጂ ኢትዮጵያውያን ሪቫኑን ለመቁረጥ የመጨረሻው መም ላይ ይገኛሉ።
ግብፅ ቃሏን ሺህ ጊዜ እያጠፈች (ኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን በመጋቢት ወር 2007 ዓ.ም ላይ የመርሆዎች ስምምነት ላይ ፊርማቸውን ማኖራቸው ይታወሳል) ግድቡን ለማስቆም ደፋ ቀና ብትልም፤ ሕገ መንግሥቷን በማሻሻልና አንቀፅ 44ን በማከል ዓባይን የነካ ወዮለት ብትልም ግድባችንን ዛሬ የደረሰበት ደረጃ ከመድረስ፤ ሪቫኑ ወደ መቆረጫው ከመቃረብ ያገደው አንዳችም ነገር የለም።
በወቅቱ ከግድቡ ባለቤት (ኢትዮጵያውያን) አልፎ አልፎ ምላሽ ሲሰጥ የነበረ ሲሆን፤ ግብፆች በአስዋን ግድብ ምክንያት የሚያገኙትን ከዚህ በመለስ ያልተባለ ጥቅም ከዘረዘሩ በኋላ “እነሱ ይህን ሁሉ ትሩፋት ከዓባይ ወንዝ አግኝተው 70 ፐርሰንት በጨለማ ለሚማቅቀው እና በኩበት ጪስ ለሚጨናበሰው (ያውም የውሃው ባለቤት ሆኖ፣ ያውም የማይጎዳቸው መሆኑ እየተነገራቸው) ለኢትዮጵያ ሕዝብ ቅንጣት ታህል ርህራሄ አለማሳየታቸው ይቀፋል።” በማለት አስተያየታቸውን አስፍረው የነበሩትን ቬሪኒካ የተባሉ ፀሀፊ ተጠቃሽ ናቸው።
“በ1950ዎቹ በእንግሊዙ መሃንዲስ ሃሮልድ ኤድዊን ውሃው የበረሃው ሙቀት ከሚበላው ኢትዮጵያ መቆየቱ ጠቃሚ እንደሆነ፤ የሕዳሴው ግድብ በናስር ሃይቅ እና በናይል ወንዝ የሚከማቸውን ደለል ለመቀነስ እጅግ ጠቃሚ” መሆኑ ለግብፆች ቢነገርም ጉዳዩ ካፈርኩ አይመልሰኝ በመሆኑ ጩኸቱ ዘላለማዊ ሆኖ እስከ ሪቫን ቆረጣው ዋዜማ ድረስ ዘልቆ አሁንም እየተሰማ ሲሆን፤ ጉዳዩ ውሾቹ ይጮሃሉ፤ ግመሉ ይሄዳል ነውና የዛሬ ስድስት ወር ሪቫኑ ይቆረጣል።
ስሜነህ የተባሉ ፀሀፊ እንደሚናገሩት በአዓለማችን ከ300 በላይ የሚሆኑ ወንዞች ድንበር ተሻጋሪ ሲሆኑ በህንድና በባንግላዴሽ መካከል ብቻ 54 ወንዞች ድንበር ተሻግረው ይፈሳሉ፡፡ በ1978 በዓለማችን 214 ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች እንደነበሩ የሚጠቁሙ መረጃዎች በ2002፤ ደግሞ 263 መድረሳቸውን ያመለክታሉ፡፡
ከእነዚህ ውስጥ 145 ሀገራት ድንበራቸውን የከለሉት በድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ነው፡፡ ላለፉት 50 ዓመታት 1831 ያህል ስምምነቶችና ግጭቶች በእነዚህ ወንዞች ዙሪያ መከሰታቸውና ከሁለት መቶ በላይ የትብብር ስምምነቶች መፈረማቸውም በታሪክ መዝገብ ላይ የሰፈረ የዓለማችን እውነት ነው፡፡
ወደ ግብፅ አካባቢ ይህንን ታሪክ ባለማወቅ ይሁን አውቆ በመተኛት ለትብብር ስምምነት እጅ መስጠት ነውር ሆኖ ዛሬም ድረስ ካፈርኩ አይመልሰኝ አካሄድ ይታያል። ይታይ እንጂ ውሾቹም ከመጮህ፣ ግመሉም ከመሄድ ሳያቋርጡ ሪቫኑ ይቆረጣል።
ይህ ብቻም አይደለም፣ በወቅቱ ለጆሮና ለንባብ በቅተው የነበሩ መረጃዎች እንዳመለከቱት፣ ግብፅና ሱዳን ድርድሩ ተካሂዶ ከስምምነት ላይ ከመደረሱ በፊት ኢትዮጵያ ግድቡን በውሃ እንዳትሞላ እና ሥራ እንዳትጀምር ቢወተውቱም ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የውሃ ሙሌት በ2012 ክረም ወራት ላይ አካሂዳለች።
በመስከረም ወር 2013 ዓ.ም የትራምፕ አስተዳደር ኢትዮጵያ ከግብፅና ከሱዳን ጋር ከስምምነት ሳትደርስ ግድቡን መሙላት በመጀመሯ ምክንያት ለሀገሪቱ ከሚሰጠው ርዳታ ላይ ቅነሳ እንደሚያደርግ አስታወቀ። ይህ በወቅቱ ከአሜሪካ መንግሥት ታገኝ የነበረውን የገንዘብ ድጋፍ እንዳታገኝ አደረጋት እንጂ ግድቡን ከመገንባት ወደ ኋላ ሊያደርጋት አልቻለም።
በዚያው ዓመት ሰኔ ወር ላይ ኢትዮጵያ ሁለተኛውን የውሃ ሙሌት ያካሄደች ሲሆን ይህንንም ተከትሎ ግብፅ እና ሱዳን ለፀጥታው ምክር ቤት ያስገቡት ቅሬታ ላይ ምክር ቤቱ ተወያየ።
በኢትዮጵያ፣ በሱዳንና በግብፅ መካከል በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ ለተከሰተው አለመግባባት በተመሳሳይ ጉዳይ ላይ ቀደም ሲል ባልታየ ሁኔታ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ሐምሌ 2013 ዓ.ም ላይ ተሰበሰበ፤ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በተመለከተ የፀጥታው ምክር ቤት መወያየቱን እንደማትቀበለው በማስታወቅ የሕዳሴው ግድብ ግንባታ ምንም ዓይነት የደህንነት ስጋት በሱዳንና በግብፅ ላይ እንደማያስከትል ለምክር ቤቱ አስረዳች።
ምክር ቤቱ በውይይቱ መደምደሚያ ላይም ጉዳዩ ቀደም ሲል በተያዘበት በአፍሪካ ሕብረት በኩል መቋጫ እንዲያገኝ ውሳኔ ሰጠ። በዚህ ሁሉ ጫጫታ መሃል የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ለማይክሮ ሰከንድም ሳይቋረጥ እንደ ቀጠለ ነበር።
በቅኝ ግዛት ወቅት በእንግሊዝ አደራዳሪነት በተደረገ ስምምነት ወንዙን ለመከፋፈል ከስምምነት ላይ ተደርሶ፤ ግብፅ 66 በመቶውን፤ 22 በመቶውን ደግሞ ሱዳን የውሃ ድርሻን እንዲጠቀሙ ተደረገ። 12 በመቶ የሚሆነው በትነት የሚባክን መሆኑ ታሳቢ ሲደረግ ከዚህ ውስጥ ኢትዮጵያ ምንም ድርሻ አልነበራትም ነበር። ይህ ዛሬ ተረት ሆኗል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ያለፈውን ስድስት ወር አፈፃፀም በተመለከተ ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት (መጋቢት 11 ቀን 2017 ዓ.ም) እንደተናገሩት የዛሬ ስድስት ወር ሪቫኑን የኢትዮጵያ ሕዝቦች በጋራ ይቆርጣሉ። “የዓድዋ ድል በጉባ ተደገመ” ይሏል ይህ ነው። “ይቀጥላል …”ም እንደዛው።
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ መጋቢት 23 ቀን 2017 ዓ.ም