በማይናማር ርዕደ መሬት የተረፉ ሰዎችን የማግኘት ዕድል አናሳ መሆኑ ተገለጸ

ከ2ሺ በላይ ሰዎች በሞቱበት የማይናማር ርዕደ መሬት ከአደጋው የተረፉ ሰዎችን ለማግኘት ሙከራው ቢቀጥልም ሰዎችን በሕይወት የማግኘት ተስፋው ግን የተመናመነ መሆኑ ተሰምቷል፡፡ በተለይ ርዕደ መሬቱ ከተነሳ 72 ሰዓታት በማለፉ ተጎጂዎችን በሕይወት የማግኘት ዕድል ጠቧል ተብሏል፡፡

7 ነጥብ 7 ማግኒትዩድ የተለካው ርዕደ መሬት የተነሳበትን ሰዓት ለማስታወስ የሕሊና ፀሎት እንደሚደረግ የተገለጸ ሲሆን ከሞቱት ባለፈ በአደጋው ሳቢያ ከ4ሺ በላይ ሰዎች መጎዳታቸው ታውቋል፡፡

በማይናማር ጎረቤት ታይላንድ በርዕደ መሬቱ ንዝረት 20 ሰዎች መሞታቸውም ተሰምቷል፡፡ በባንኩክ ሕንጻዎች በመሰነጣጠቃቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መኖሪያ ቤታቸውን ጥለው ለመውጣት ተገደዋል፡፡

ለአምስት ቀናት የሀገሪቱ ሰንደቅ ዓላማ ዝቅ ብሎ እንደሚውለበለብ ወታደራዊ መንግሥቱ የገለጸ ሲሆን ዜጎች በያሉበት ሆነው ለተጎጂዎች የሕሊና ጸሎት እንደሚያደርሱም ተገልጿል፡፡ ወታደራዊ መንግሥቱ ሩሲያ፣ ቻይና እና አሜሪካን ጨምሮ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ርዳታ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡

የተራድዖ ድርጅቶችም በቀጣይ የሚኖረው ሥራ ከባድ እንደሚሆን እየገለጹ ይገኛሉ፡፡ የተለያዩ በሽታዎች ሊነሱ የሚችሉ ስለመሆኑም ተገምቷል፡፡ የመሠረተ ልማት ውድመት የርዳታ እንቅስቃሴውን ሊያስተጓጉለው እንደሚችል ተነግሯል፡፡ ቢቢሲ በርሚዝ የተመለከታቸው አካባቢዎች የርዳታ አቅርቦት በሁሉም ስፍራ አለመጀመሩን ገልጿል፡፡ በይፋ የሟቾች ቁጥር ሁለት ሺ ደርሷል ቢባልም ሀገሪቷን እያስተዳደረ ያለው ወታደራዊ መንግሥት የተፈጥሮ አደጋ በሚደርስ ጊዜ የተጎዱ ሰዎችን ቁጥር አሳንሶ መግለጹ ይታወቃል ተብሏል፡፡

በባንኩክ በርካታ የግንባታ ሠራተኞች በሥራ ላይ ሳሉ ርዕደ መሬቱ ስለተነሳ በፍርስራሽ ስር ሲቀበሩ ከአደጋው የተረፉ ሰዎችን ለማግኘት የሚደረገው ጥረት እምብዛም ውጤት አለማምጣቱ ተገልጿል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በበኩሉ፤ ርዕደ መሬቱ በማይናማር ያለውን አስከፊ ሁኔታ የበለጠ ያባባሰ ነበር ሲል ተናግሯል፡፡

ለአራት ዓመታት የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ የምትገኘው ማይናማር ርዕደ መሬቱ ጉዳት እያደረሰ ባለበት ወቅት ወታደራዊ መንግሥቱ ለዲሞክራሲ በሚታገሉ አማጺያን ላይ የአየር ጥቃት እያደረሰ እንደሆነ ተነግሯል፡፡ ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ በጦርነት ውስጥ ለሰነበተች ሀገር እንዲህ ያለ ተፈጥሯዊ አደጋ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ብሂል ያለው ነው፡፡

ርዕደ መሬቱ በተነሳበት ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኘው ሳጋይንግ የሚታየው ሰብዓዊ ቀውስ እጅግ የበረታ እንደሆነም ተመላክቷል፡፡ ሰላም የራቃቸው ዜጎቿ በእንዲህ አይነቱ አደጋ የበለጠ ለጉዳት መዳረጋቸው ብዙዎችን ያሳዘነ ክስተት ነው ተብሏል፡፡ የርዳታ ተቋማት ሰብዓዊ ቀውሱ እየተባባሰ ሊሄድ እንደሚችል ጥቁምታ የሰጡ ሲሆን ክስተቱ ሁኔታዎችን ከበፊቱ የባሰ ውስብስብ ሊያደርግ እንደሚችልም አስጠንቅቀዋል፡፡

በባንኩክ በተደረመሰ ሕንፃ ምክንያት ከሞቱት ሰዎች በተጨማሪ ሰባ ሰዎች እስካሁን የገቡበት እንዳልታወቀ ሲዘገብ ርዕደ መሬቱ ከማይናማር በተጨማሪ ታይላንድ ላይ ጉዳት ያደረሰ ሲሆን በቻይናም ንዝረቱ እንደተሰማ ታውቋል፡፡ የተፈጥሮ አደጋዎች ድንገታዊ ክስተት ስለሆኑ መቼ እና የት እንደሚነሱ ለማወቅ አስቸጋሪ ከመሆናቸውም በላይ አደጋቸው የከፋ ነው፡፡

በእርስ በርስ ጦርነት ስር ያለችው ማይናማር በተፈጥሮ አደጋ መመታቷ ሌላው አሳዛኝ ክስተት ሲሆን ለዚህ አደጋም ሀገራት የሰብዓዊ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡ በተንቀሳቃሽ ምስል የታየው ክስተትም እጅግ አሳዛኝ እና ልብ ሰባሪ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ አደጋው ሦስት ቀናትን በማስቆጠሩ በሕይወት የተረፉ ሰዎችን የማዳን እንቅስቃሴ ተስፋ አስቆራጭ መሆኑ ተገልጿል፡፡ መረጃውን ከቢቢሲ አግኝተናል፡፡

ዘላለም ተሾመ

አዲስ ዘመን ሐሙስ መጋቢት 25 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You