አፍሪካን ያደመቀ ዳግማዊ ድል

በአፍሪካ ቀንድ በስተምሥራቅ አቅጣጫ ከሚመስሏት ሀገራት መሐል ስሟ በተለየ ቀለም ይጻፋል። የማንነቷ ልክ በ‹‹አትንኩኝ›› ባይነትና በድል አድራጊነት ሲወሳ ኖሯል። ይህች ድንቅ ሀገር በነፃነቷ ድርድርን አታውቅም። ሁሌም ከማንነቷ ጀርባ የሚነሳው ድል አድራጊነት ስሟን በክብር አስጠብቃ እንድትኖር መገለጫዋ ሆኗል። ‹‹ኢትዮጵያ›› የአፍሪካ ቀንድ ፀሐይ፣ የጥቁር ሕዝቦች መመኪያ።

‹‹ኢትዮጵያ›› ይሏት ሀገር ታሪኳ በብዙ ምስጢራት ይመዘዛል። የብርቱ ሕዝቦቿ የጀግንነት ገድል የነፃነት አክሊልን ደፍታ በክብር እንድትዘልቅ ምክንያቷ ነው። ይህ እውነት ደግሞ ያለምክንያት አልሆነም። የደምና አጥንት ታሪክ ተጽፎበታል። የሕይወት መስዋዕትነት ታትሞበታል። በድፍረት ዳር ድንበሯን የረገጡ፣ ክብሯን የተዳፈሩ ሁሉ ካሻቸው ሳይደርሱ ድል ተነስተው ተባረዋል።

ይህ የማይፋቅ ሐቅ ነጠላ ታሪክ አይደለም። የዚህች ሀገር ክቡር ስም ብቻውን ቆሞ አያውቅም። ለመላው ጥቁር ሕዝብ ደማቅ ዓርማ ሆኖ ነፃነትን አሸልሟል። ባርነትን ፍቆ ነባር ስምን ቀይሯል። ዛሬም የኢትዮጵያ ድል አድራጊነት በአሸናፊነት ብቻ አይገለጽም። ይህች ሀገር ሌላውን የታሪክ ድንቅ መገለጫ ማኖር ከያዘች ሰነባብታለች።

ኢትዮጵያ አሁን ‹‹ድህነት›› ይሉትን ቀንደኛ ጠላት ታግላ በአዲስ ምዕራፍ ለመሻገር አሸናፊነቷን ለመላው ዓለም እያሳየች ነው። ለዚህ ድንቅ ዓላማዋ ስኬት ብርቱ ክንዶቿ ዝለው አያውቁም። ሌት ተቀን እረፍት የለሽ ልጆቿ የማይፈዝ ታሪክን ለመድገም ዕንቅልፍ አልባ ከሆኑ ቆይተዋል።

የኢትዮጵያ ድል አድራጊነት ዳግም በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ዕውን መሆን ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል። ኢትዮጵያ እንደቀድሞ ታሪኳ ሁሉ ‹‹አይሆንም፣ አይሞከርም›› የተባለውን መስመር ደፍራ ዛሬም በጀግንነት ቆማለች። ይህ እውነታም ዳግመኛ ለድል ሊያበቃት ነጋሪቱን እየጎሰመ ብሥራቱን እያሰማ ነው።

የዛሬ አስራ አራት ዓመት። መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም። የታላቁን የሕዳሴ ግድብ መሠረት ለመጣል የኢትዮጵያውያን እጆች በአንድ ተጣመሩ ። ቆራጥ ልቦች በእኩል መከሩ። ጠንካራው ዓላማ በዋዛ አልተወጠነም። በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ልቦና ጥብቅ መሠረት ሊያኖር ኃያል መንፈስን አሰረጸ። አንዱ እንደ ብዙ፣ ብዙው እንደ አንድ የሆነበት አጋጣሚ ኅብረ-ብሔራዊነቱ ደመቀ። ሁሉም ከትርፉ ሳይሆን ከባዶ እጁ አንስቶ ለሕዳሴው እውንነት ይሁንታውን አሳየ።

እናት መቀነቷን ፈታች። አባወራው ከላብ ከድካሙ ስለሀገሩ ‹‹እነሆኝ›› አለ። ባለሀብቶች ስለነገው መልካምነት የዛሬ ሲሳያቸውን አሳልፈው ሰጡ ። ተማሪዎች፣ ሕጻናት፣ የጉልት እናቶች በታላቅ ደስታ ለታላቁ ህዳሴ በረከታቸውን ለገሱ። ይህ የኢትዮጵያዊነት ግማድ ዘርን ከሃይማኖት፣ ዕድሜን ከፆታ ሳይለይ በአንድ ቋንቋ ስለሕዳሴው መቆም በኅብር ዘመረ። የመጋቢት ወር የመጨረሻ ሳምንት በጽናት ተሞሽራ መሠረቷን በጥብቅ አጸናች።

ይህ ያልታሰበ አንድነት ዕውን በሆነ ማግስት ከአዕምሮ በላይ የሆነ ፈተና አላጣውም። ገና ከጅማሬው የኢትዮጵያን ተስፋ ለማጨለም የፈጠኑ ኃይሎች ቁጥራቸው በረከተ። እነዚህ ወገኖች አቅማችን ነው ባሉት አጋጣሚ ሁሉ የታላቋን ሀገር ዓላማ ለማደናቀፍ ሌት ተቀን ማሰኑ።

ያለምንም የውጭ ድጋፍና እገዛ በሕዝቡ አንድነት ብቻ መታየት የጀመረው ፀጋ እውነት ባይመስላቸው የግድቡን ሥራ ለማጨለም ዕንቅልፍ ይሉት ከዓይናቸው ራቀ። ባገኙት የመገናኛ ብዙኃን ብቅ እያሉ ራሳቸውን እንደበደለኛ፣ ኢትዮጵያን እንደ ወንጀለኛ ፈርጀው መላውን ዓለም ‹‹ፍረዱን›› ሲሉ ጮኹ።

ከግላዊ ጥቅም ይልቅ የአንድነት ገበታን ያስቀደመችው ሀገር ጥያቄያቸውን በአሳማኝ መልስ እያስቀመጠች ቀዝቃዛውን ጦርነት በጽናት ተጋፈጠች። ኢትዮጵያ ግድቡን ከጀመረች አንስቶ በእሾህ መሐል የበቀለች አበባ እስክትመስል ጦር ሲመዘዝባት፣ ዛቻ ሲመላለስባት ቆይቷል።

እስከዛሬ በዚህች ሀገር የዘመናት ታሪክ የዓባይ ጉዳይ ከዜማና እንጉርጉሮ አልፎ አያውቅም። ታላቁ ወንዝ ለዓመታት በሕዝቡ ሲወቀስና ሲታዘንበት ኖሯል። ግንድ አዝሎ መዞሩ፣ ለሌሎች ለም አፈር ማቀበሉ ተጠያቂነቱን እንዳገዘፈው ከትውልድ ተሻግሯል።

የሰው ሀገር ሲሳይነቱ በደሉን ቢያበዛ፣ ብሶቱን ቢያሰፋ ግጥም ከዜማ ተጣምረው ሲዘልፉት፣ ሲተክዙበት ኖረዋል።

ከወንዙ ፍሰት ጋር ዕልፍ የኃዘን ግጥሞች፣ በርካታ የወቀሳ ዜማዎች በጆሮ ተመላልሰዋል። ዓባይ የትካዜ፣ ዓባይ የእንጉርጉሮና ብሶት ማመላለሻ ሆኖ ዘመናት አልፈዋል።

ዛሬ ግን ይህ አንደበት እንደትናንቱ አልቀጠለም። የአሁኑ ግጥምና ዜማ ቅኝቱን ቀይሯል። በዓባይ ወንዝ ላይ ታላቁን ግድብ የሚያንጽ ትውልድ ክንዱ ፈርጥሞ ተግባሩን ጀምሯል። በኢትዮጵያ ምድር ድህነት ተንሰራፍቶ ሕዝቦች ሲፈተኑ፣ ረሀብና ድርቅ እንዳሻው ሲስፋፋ የዓባይ ትሩፋት ለግብፅና ሱዳን ሕዝቦች ሞልቶ ሲትረፈረፍ ነበር።

ለዘመናት ያለ አንዳች ከልካይ ከኢትዮጵያ ምድር ሲጓጓዝ የኖረው የተፈጥሮ ፀጋ ሀገራችንን አደህይቶ፣ ምድሯን ያለጥሪት አራቁቷል። በተቃራኒው እጃቸውን አጣጥፈው መና ለሚጠብቁት ባዕዳን ታላቅ በረከት ሆኖ ተዝቆ የማያልቅ ሀብት አላብሷል።

ሀገር በሻማ ጭላንጭል፣ በኩራዝ ጭስ ስትደናበር፣ የእጇን በረከት የሚሻሙ ሌሎች ፀጋዋን ተላብሰው ሲዛበቱባት ኖረዋል። ለም አፈሯን፣ አንጡራ ሀብቷን ነጥቀው ራሳቸውን በእጅጉ አልምተዋል። ይህ እውነት ከቁጭትና ንዴት በላይ ነው። ይህ ሐቅ ከትዝብትና ከእይታ ይልቃል። ጉዳዩ ሁሉ ‹‹ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር…›› የሆነባት ኢትዮጵያ የቁርጧ ቀን እስክትደርስ ‹‹ሙያ በልብ›› ስትል ቆይታለች።

ታላቁ የሕዳሴ ግድብ በኢትዮጵያውያን ጥረት፣ ላብና ወዝ የተገነባ ድንቅ ታሪክ ነው። ይህ ታሪክ ዕውን ሲሆን ድህነትን ‹‹ነበር›› የሚያስብል አዲስ ቀን ይወለዳል። በዚህ ቀን እልፍ ትሩፋቶች፣ ታላላቅ በረከቶች ሁሉ የኢትዮጵያውያን ይሆናሉ። እስከዛሬ የእሷን ፀጋ ጭምር ለብቻቸው ሲያጋብሱ፣ የቆዩት በዚህ ድንቅ ርምጃ ቢደናገጡም ይህች ሀገር ‹‹ሁሉን ለብቻዬ›› ይሉት ዓላማ የላትም። ከትሩፋቱ፣ ከሚገኘው ፀጋ ለሌሎች ሀገራት ጭምር የማካፈል ውጥን አላት።

እስከዛሬ በገዛ ቤቷ ‹‹የበይ ተመልካች›› ሆና የኖረችው ኢትዮጵያ አሁን ዳር ሆና የምትመለከትበት ጊዜ አብቅቷል። ታላቁ የሕዳሴ ጉዞ ከመሠረቱ አንስቶ በፈተናዎች ውስጥ ቢመላለስም ጣፋጩን ፍሬ የማጣጣሚያ ጊዜው አሁን ነው። ይህ አፍሪካዊ ግዙፍ ግድብ ዛሬም እንደትናንቱ ድል በብቸኝነት ነግሶ ታሪክ ሊመዘግብ ከጫፍ ደርሷል።

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለመላው ዓለም ‹‹ይድረስ›› ባሉት መልዕክት የሕዳሴ ግድብ ማለት ለመላው አፍሪካ መቻልን ያሳየንበት፤ ስህተትን ያረምንበት ነው ሲሉ ገልጸውታል። 74 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ ይዘንበታል ባሉት በዚህ ግዙፍ ግድብ አፍሪካውያን ብድር ቢከለክሉ የራሳቸውን ሀብት በገዛ ዜጎቻቸው ማልማትና መቀየር እንደሚችሉ ማሳያ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ከዓመታት ልፋትና ድካም በኋላ ዕውን የሚሆንበት ጊዜ ተቃርቧል። ይህ እውነትም ኢትዮጵያ ዳግም በራሷ ማንነት ጸንታ የቆመችበትን ዳግማዊ ድል የሚያሳይ ድንቅ ታሪክ ሆኖ በወርቃማ መዝገብ በድምቀት ይጻፋል።

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 24 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You