
ዓለም ወደ አንድ መንደርነት እየተለወጠች ባለችበት፤ በሁሉም ዘርፍ ተወዳዳሪነት ዓለም አቀፋዊ መርሕ እየሆነ በመጣበት ሁኔታ ውስጥ ራስን እንደቀደሙት ዘመናት ከተቀረው ዓለም ነጥሎ መኖር የሚቻልበት አማራጭ የሚታሰብ አይሆንም። ከዚህ ይልቅ ራስን ለዓለም አቀፍ ሁኔታዎች በማዘጋጀት ተጽዕኖዎችን መቋቋም የሚያስችል አቅም መገንባት ለነገ የማይባል የቤት ሥራ ከሆነ ውሎ አድሯል።
በተለይም በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት፤ የጀመሩትን ዕድገት በማስቀጠል የሕዝባቸውን ፍላጎት በተሻለ መንገድ ለማሟላት፤ በውስጥም በውጪም የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶች አሸንፈው ለመውጣት፤ አሁናዊ ዓለም አቀፍ ሁኔታዎችን በአግባቡ በመረዳት ለዛ የሚሆን ሁለንተናዊ ዝግጁነት መፍጠር ይኖርባቸዋል። የማይቀረውን ፈተና ተጋፍጠው መሻገር የሚያስችላቸውን ቁርጠኝነት መፍጠር ይጠበቅባቸዋል።
በእነዚህ ሀገራት የሚፈጠሩ የትኛውም ዓይነት የለውጥ እሳቤዎች በአንድም ይሁን በሌላ እነዚህን አይቀሪ የለውጥ ፈተናዎች መቋቋም የሚያስችል አቅም መገንባት ይኖርበታል። ይህን ማድረግ ካልቻሉ ፤ የለውጥ አስተሳሰቦቹ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ተጨማሪ የችግር ምንጭ ሆነው መዝለቃቸው የማይቀር ነው። ሊፈጥሩ የሚችሉትም ቀውስ በለውጡ ተስፋ ያደረገውን ሕዝብ ዛሬን ብቻ ሳይሆን ነገንም መናጠቃቸው የማይቀር ነው።
ለውጥ በመርሕ ደረጃ ተስፈኛ እሳቤዎች የሚንጸባረቁበት ብቻ ሳይሆን ፤ ተስፋን እውን ለማድረግ በይቻላል መንፈስ ረጅም ርቀት መሄድ የሚያስችሉ ዋጋ መክፈሎችን አምኖና ተቀብሎ መራመድን ፤ በዛሬ የመስዋዕትነት ፍሬ ነገን በብዙ የተስፋ ጣር አምጦ መውለድን የሚጠይቅ፤ ከዲስኩር እና ዲስኩር ከሚወልደው ተስፈኝነት ያለፈ ነው።
ትናንቶችን እስከ ስጋቶቻቸው በይቻላል መንፈስ፤ በጠንካራ ዲሲፕሊን ተቋቁሞ ማለፍ የሚያስችል የተለወጠ ማንነት፤ ራስን ከትናንት እስረኝነት በጠራ ዕውቀት ነጻ ማውጣትን፤ ነጻነትን አውቆ እና ተቀብሎ ማስተዳደር የሚያስችል የአእምሮ እና የመንፈስ ዝግጁነትን የሚጠይቅ ፤ የማንነት ግንባታ ፍሬ ውጤት ጭምር ነው።
ዘመንን መርምሮ ዘመንን በሚዋጅ የአስተሳሰብ መሠረት ላይ መቆም፤ ትውልዱ የራሱን ዕድል በራሱ እንዲወስን የሚያስችል ራስን የመሆን መነቃቃትን መፍጠር ፤ የተፈጠሩ መነቃቃቶች በመርህ እና በዲሲፕሊን እንዲመሩ የሚያስችል ሥርዓት ማበጀት ፤ ከሁሉም በላይ ሀገር እና ሕዝብን ከትናንት ቅርቃር ውስጥ አስፈንጥሮ ማውጣት የሚያስችል ሁለንተናዊ ዝግጁነት የሚጠይቅ ነው።
በሀገራችን የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴም ቢሆን ከዚህ የተለየ እውነታ አይደለም። ለውጡ ከሁሉም በላይ ከትናንት ተስፈንጥሮ የመውጣት ራዕይ ያነገበ ነው። ትናንትን እንደ ትናንት ተቀብሎ ፤ ደካማ እና ጠንካራ ጎኖቹን መርምሮ ደካማዎቹን ማረም፤ ጠንካራዎቹን አስፍቶ ማስቀጠል የሚያስችል ተለውጦ የመለወጥ ጉዞ ነው።
በእነዚህ የለውጥ ዓመታት እንደ ሀገር የመጣንበት መንገድ በብዙ ፈተናዎች እና መጎረባበጦች ውስጥ ቢያልፍም ፤ እየተመዘገበ ያለው ውጤት ግን በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ሳይቀር ለለውጥ ቁርጠኝነት ካለ ስኬታማ መሆን እንደሚቻል በተጨባጭ ያሳየ፤ ፈተናዎችን ወደ መልካም ዕድል መለወጥ የሚያስችል የአስተሳሰብ ህዳሴ መፍጠር በራሱ ከትናንት የመሻገሪያ የተሻለ ድልድይ መሆኑን ያመላከተ ነው።
በርግጥ ከለውጡ ዋዜማ ጀምሮ ያጋጠሙን ፈተናዎች ቀለማቸው የበዛ ቢመስልም፤ በመሠረታዊነት ከትናንት የተረከብናቸው ፤ ብዙ ዛሬዎቻችንን ያባከኑብን ናቸው። በዘመናት መካከል የነበሩ የሕዝባችንን የለውጥ መሻቶች ያመከኑ ፤ ባልተለወጠ ማንነት ሀገር እና ሕዝብን ብዙ ዋጋ ያስከፈሉ ፤ ጠባሳዎቻቸውም ገና በአግባቡ ያላገገሙ የትናንትናዎቻችን ጥላዎች ናቸው።
በአንድ በኩል ራስ ወዳድነት ፣ ለሕግ አለመገዛት ፣ ባንዳነት፤ በሌላ በኩል ሥልጣንን ከግለሰብ እና ከቡድን ህልውና ጋር አስተሳስሮ ማየት ፤ ለዚህ ሲባል ሕዝብን ወዳልተገባ መንገድ በመግፋት ተጠቃሚ ለመሆን የሚደረጉ የነውር አካሄዶች፤ “እኔ ከሞትኩ ወዲያ ሰርዶ አይብቀል” አይነት ጸለምተኝነት …ወዘተ በብዙ ፈትነውናል፤ ዛሬም እየፈተኑን ነው።
የሕዝብን የለውጥ መንፈስ የሥልጣን እርካብ አድርጎ ማሰብ፣ በሁከት፣ በግርግር እና በግጭት ውስጥ ሥልጣንን አሻግሮ የማየት አባዜ፣ ያልተቀደሱ የፖለቲካ ጋብቻዎች፣ ምሁራዊ ጽልመተኝነት፣ ዳተኛነት፣ ቡድንተኝነት፣ እልፍ ሲልም ፣ ጽንፈኝነት እና ሽብርተኝነት ለውጡን በብዙ አንገጫግጨውታል። በሕዝቡ ውስጥ የነበረውን የለውጥ መንፈስ አቀዛቅዘውታል።
ከቀደሙት ዘመናት ጀምሮ ለውጥ ፈላጊ ተስፈኛ ትውልዶችን በብዙ ዋጋ እያስከፈሉ ዛሬ ላይ እንደሀገር ፈተና የሆኑብን እነዚህ ትውልድ ተሻጋሪ ችግሮቻችንን ለመሻገር የለውጥ ኃይሉ የሄደባቸው መንገዶች፣ ለውጡ በብዙ መንገጫገጮች እንዳይወድቅ ከማድረግ ባለፈ ፣ ፈተናዎችን ወደ ዕድል መለወጥ የሚያስችል የአስተሳሰብ ሕዳሴ መፍጠር አስችሏል።
“ከይዋጣልን” የፖለቲካ ባህል መውጣት የሚያስችል፤ በንግግር እና በድርድር ላይ የተመሠረተ ሰላማዊ የፖለቲካ አማራጮችን ማስፋት፣ ሀገረ መንግሥቱን ለማጽናት እየተከናወኑ ያሉ የተቋማት ግንባታዎች ፣ በሕዝቦች መካከል መተማመንን እና መከባበርን ፤ ከዚያም ባለፈ ሀገራዊ አንድነትን የሚያጸና የጋራ ትርክት ለመፍጠር እየተደረገ ያለው ጥረት፤ ሀገራዊ አቅሞችን አሰባስቦ ቀጣይነት ያለው ልማት ለማካሄድ ያሉ ጅማሬዎች፤ ሀገሪቱ ታሪኳን እና የነገውን ዓለም ልትመጥን በምትችል መልኩ ለመገንባት የተያዘው ቁርጠኝነት …ወዘተ የአስተሳሰብ ሕዳሴው ትላልቅ ማሳያዎች ናቸው!
አዲስ ዘመን ማክሰኞ መጋቢት 23 ቀን 2017 ዓ.ም