በሀገር አቀፍ ደረጃ የዓይን መነጽር ጥራትና ደረጃን የሚቆጣጠር አካል የለም

-ዜጎች ጥራቱ የተረጋገጠ መነጽር ስለማያገኙ ለዓይን ጤና ችግር እየተጋለጡ ነው

 

አዲስ አበባ፡- በሀገር አቀፍ ደረጃ የዓይን መነጽር ጥራትና ደረጃን የሚቆጣጠር አካል አለመኖሩን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ህክምና ትምህርት ቤት የዓይን ህክምና ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር እና በዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል የአዋቂና የህፃናት ዓይን ህክምና ልዩ ስፔሻሊስት ሀኪም ዶክተር ሳዲቅ ታጁ አስታወቁ፡፡ ዜጎች ጥራቱ የተረጋገጠ መነጽር ስለማያገኙ ለከፋ የዓይን ጤና ህመም እየተጋለጡ መሆኑን ተጠቁሟል፡፡

ዶክተር ሳዲቅ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ መነጽር በዓይን ጤና ሥራ ውስጥ ልክ እንደ መድኃኒት የሚያገለግል የሕክምና ቁስ ነው። ሆኖም በሀገር አቀፍ ደረጃ እንደ መድኃኒት ሁሉ ጥራቱንና ደረጃውን የሚለይለት አካል የለም፤ ቁጥጥርም አይደረግበትም። በዚህም ምክንያት ዜጎች ጥራቱ የተረጋገጠ ምርት ስለማያገኙ ለተደጋጋሚ ወጪ እና ለተጨማሪ የዓይን ችግር እየተጋለጡ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

የመነጽር ጥራትና ደረጃ ቁጥጥር ባለመኖሩ ሰዎች በትዕዛዝ የተሰጣቸውን መነጽር አውቀው አይገዙም ያሉት ዶክተር ሳዲቅ፤ በዝቅተኛ ዋጋ ያገኙትን እየገዙ ለተጨማሪ የዓይን አደጋ ተጋላጭ እየሆኑ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

የመነጽርን ጥራትና ደረጃ የሚቆጣጠር አካል ባለመኖሩ አሁን ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ መነጽር ቤቶች እና በየመንገዱ መነጽር የሚያዞሩ ከመበራከታቸው ባሻገር እንዳሻቸው ሠርተውና ቆርጠው እንዲሁም ዋጋ ተምነው ለተጠቃሚው የሚያቀርቡ ሆነዋል፡፡ ይህ ደግሞ በርካቶችን ለከፋ የዓይን ጤና ችግር እያጋለጣቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ከዓይን ጤና ችግር ጋር በተያያዘ ብቻ በሀገር አቀፍ ደረጃ እድሜያቸው እስከ 16 የሚደርሱ ልጆች ከ10ሩ አንዱ መነጽር እንደሚያስፈልገው፤ በከተሞች አካባቢም 20 በመቶ የሚሆኑ ልጆች መነጽር የግድ መጠቀም እንዳለባቸው በጥናት መመላከቱን የጠቆሙት ዶክተር ሳዲቅ፤ ማንኛውም እድሜው ከ35 ዓመት በላይ የሆነ ሰው መነጽር መጠቀም እንዳለበት አስታውሰዋል፡፡

በትዕዛዝና በተፈጥሮ የግድ መነጽር መጠቀም ያለባቸው ዜጎች እንደ ሀገር በርካታ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ የመነጽሮች ጥራትና ደረጃን አለመቆጣጠር የዓይን ጤና ችግርን በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር ያደርገዋል። እንደ ሀገር ይህ ጉዳይ ትኩረት ያለማግኘቱ ብዙዎችን ተጎጂ ያደርጋቸዋልና መንግሥት ሊያስብበት እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡

እንደሀገር መነጽር እንዴት መሠራትና መገጣጠም አለበት? የት ቦታ መሠራት አለበት? በምን ያህል የጥራት ደረጃ መሠራት አለበት? በምን አይነት መልኩ መሸጥ አለበት? የሚሉ ጉዳዮችን ለይቶ የሚሠራ አካልን መሰየምም የግድ እንደሚያስፈልግና አፈጻጸሙንም መቆጣጠር እንደሚገባ ዶክተር ሳዲቅ አስረድተዋል፡፡

አሁን ላይ ተጠያቂነት ያለበት አሠራርን በሕግ ማስቀመጥ ካልተቻለ በትንሹ ከ35 ዓመት በላይ ያሉት የማህበረሰብ ክፍሎች ለከባድ የዓይን ጤና ችግር ተጋላጭ እንደሚሆኑ ጠቅሰውም፤ ከአዋቂዎች ይልቅ መነጽር የሚያስፈልጋቸው ልጆች በመሆናቸቸው እነርሱ ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራትም እንደሚገባ ተናግረዋል።

የልጆች ዕይታ ቀድሞ መቀነስ ከአደጉ በኋላ ለመመለስ ያስቸግራል፡፡ በዚህም ልጆች ጥራትና ደህንነታቸው የተጠበቀ መነጽሮችን ተጠቃሚ እንዲሆኑ መንግሥት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ሊሠራ ይገባል ብለዋል።

እንደ ኢትዮጵያ የዓይን ሐኪሞች ማህበር እና እንደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የዓይን ሕክምና ክፍል ከመንግሥት አካላት ጋር ንግግር እየተደረገ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ ምርቱ ከቀረጥ ነጻ ገብቶ በአነስተኛ ዋጋ የሚቀርብበት እድል እንዲፈጠር እየተሠራ ስለመሆኑም አመላክተዋል፡፡

ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ የሚሆነው መንግሥት በቻለው መጠን በመነጽር ሥራና የጥራት ደረጃ ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ሲሠራ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

እንደዓለምአቀፍ ጥናቶች መረጃ እ.አ.አ በ2050 በአነጣጥሮ ማየት ግድፈት ምክንያት ብቻ 50 በመቶ የሚሆነው የዓለማችን ሕዝብ መነጽር ይፈልጋሉ የሚሉት ዶክተር ሳዲቅ፤ ምንም አይነት የዓይን መነጽር የጥራትና የደረጃ ቁጥጥር በማይደረግባት ኢትዮጵያ ደግሞ ይህ ቁጥር የት ላይ ሊደርስ እንደሚችል መገመት አያዳግትም ነው ያሉት፡፡

ጥራትንና ደረጃን ከማስጠበቅ አንጻር ተቆጣጣሪ አካል መመደብ ላይ ትኩረት ማድረግ ከአሁኑ ይበጃል ሲሉም መክረዋል፡፡

ዋጋን ከማረጋጋት አንጻርም መድኃኒትን በሀገር ውስጥ ማምረት እንደተቻለ ሁሉ የዓይን መድሃኒት የሆነውን መነጽርንም በሀገር ውስጥ በመንግሥት አለያም በግል አጋርነት ማምረት ቢቻል መልካም እንደሆነ ዶክተር ሳዲቅ አስገንዝበዋል፡፡

ጽጌረዳ ጫንያለው

አዲስ ዘመን ማክሰኞ መጋቢት 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You