
አዲስ አበባ:- የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፌዴራል መንግሥት በክልል ጣልቃ የሚገባበትን ሥርዓት ለመደንገግ የወጣውን ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 1373/2017 በሁለት ድምፀ ተዓቅቦና በአብላጫ ድምፅ አፀደቀ፡፡
ምክር ቤቱ ትናንት ባካሄደው 22ኛ መደበኛ ስብሰባው የፌዴራል መንግሥት በክልል ጣልቃ የሚገባበትን ሥርዓት ለመደንገግ የወጣው አዋጅ ቁጥር 395/2003 በአተገባበር የታዩ ክፍተቶችን ለመሙላትና በቀጣይ የአዋጁን አፈፃፀም ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ እንዲሻሻል መወሰኑ ተመልክቷል፡፡
የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) አዋጁን ማሻሻል ያስፈለገው በአተገባበር የታዩ ክፍተቶችን ለመሙላትና የአዋጁን አፈፃፀም ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በምክር ቤት ተገኝተው ስለማሻሻያው ማብራሪያ የሰጡት የፍትሕ ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሐና አርዓያሥላሴ በበኩላቸው፣ ማሻሻያው ባለፉት ዓመታት በትግበራ ላይ ያጋጠሙ ችግሮችን ለመፍታት እንደቀረበ አመልክተዋል፡፡
በትግራይ ክልል ያለውን ጊዜያዊ አስተዳደር የቆይታ ጊዜ በማስቀጠል ለዘላቂ ሰላም፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩ በሚሰጠው የሥራ ኃላፊነት መሠረት እንዲሠራ የሚያስችል እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
የውሳኔውን መተላለፍ ተከትሎ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ሕገመንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለውን ሁኔታ በማስተካከል ወደ መደበኛ ምርጫ ለመግባት የሚያስችል ሥራ ለመሥራት እንደሚያስችልም ጠቁመዋል፡፡
አዋጁ በሚሰጠው ኃላፊነት መሠረት ጊዜያዊ አስተዳደሩ ወደ መደበኛ አስተዳደር ለመግባት አስፈላጊ ርምጃዎችን እንዲፈጽም ተጨማሪ ትዕዛዝ ሊሰጠው እንደሚችልም ጠቁመዋል፡፡
ማሻሻያው የጊዜያዊ አስተዳደር የቆይታ ጊዜን በክልሉ ካለው ነባራዊ የፀጥታና የፖለቲካ ሁኔታ አኳያ መዝኖ በማራዘም ዘላቂ ሰላም ለማስገኘት እና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለማስጠበቅ ጥሩ መደላድልን እንደሚያስቀምጥም ነው ወይዘሮ ሐና የጠቀሱት፡፡
ተስፋዬ (ዶ/ር) ሕገ መንግሥቱን ለመጠበቅና ለመከላከል በሕገ መንግሥት በተሰጠ ሥልጣንና ኃላፊነት መሠረት ከክልል አቅም በላይ የሆነ የፀጥታ መደፍረስ ሲያጋጥም፣ በክልሉ መስተዳድር ጥያቄ ሲቀርብ፣ ሰብዓዊ መብቶች ሲጣሱና ክልሉ ድርጊቱን ማቆም ሳይችል ሲቀር ጣልቃ ሊገባ እንደሚችል በሕገ መንግሥቱ መደንገጉን አመልክተዋል፡፡
ማንኛውም ክልል ሕገ መንግሥቱን በመጣስ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ እንደሆነም በፌደሬሽን ምክር ቤት ትዕዛዝ የፌደራል መንግሥቱ በክልሎች ጣልቃ ሊገባ እንደሚችል መቀመጡንም ተናግረዋል፡፡
ድንጋጌዎቹን መነሻ በማድረግም የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ ገብነት የሚመራበት ሥርዓት ለመደንገግ አዋጅ ቁጥር 395/2003 ወጥቶ ሥራ ላይ መዋሉን አስታውሰዋል፡፡
አዋጁ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ አደጋ ላይ በመውደቁ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ትዕዛዝ ፌደራል መንግሥቱ የክልል ምክር ቤት እና የሕግ አስፈጻሚን በማገድ ጊዜያዊ የክልል አስተዳደር እንዲቋቋም ሊወስን የሚችልበትን ሥርዓት ማስቀመጡንም ነው ያመለከቱት፡፡
የጊዜያዊ አስተዳደር ቆይታን ለማራዘም ውሳኔ የሚሰጠው የፌዴሬሽን ምክር ቤት በዓመት ሁለት ጊዜ ብቻ የሚሰበሰብ መሆኑ እንደ ክፍተት ተለይቷልም ብለዋል፡፡
የአዋጁን ትግበራ አስፈላጊ የሚያደርጉ እጅግ ውስብስብ የፀጥታና የፖለቲካ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስፈልገው ጊዜ እንደ ጉዳዩ ክብደት መለያየቱም ተግዳሮት መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ዘላለም ግዛው
አዲስ ዘመን ሐሙስ መጋቢት 25 ቀን 2017 ዓ.ም