‹‹ባለፉት ሰባት ዓመታት ለዘመናት ሊመነዘር የሚችል ውጤት ተመዝግቧል›› – ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር

አዲስ አበባ፡- መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም የለውጡ አመራር ወደ ኃላፊነት ከመምጣቱ ወዲህ ባለፉት ሰባት ዓመታት ለዘመናት ሊመነዘሩ የሚችሉ ውጤቶች መመዝገባቸውን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር “ትናንት፣ ዛሬና ነገን ለኢትዮጵያ ልዕልና” በሚል መሪ ሀሳብ ባለፉት ሰባት ዓመታት በተመዘገቡ ስኬቶችና በቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ ትናንት የውይይት መድረክ ሲካሄድ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ ባለፉት ሰባት ዓመታት ለዘመናት ሊመነዘሩ የሚችሉ ሁለንተናዊ ለውጦች ተመዝግበዋል፡፡ ይህ ለውጥ ሊመዘገብ የቻለው ደግሞ ኢትዮጵያ ሃሳብ ያለውና ሃሳቡን ወደ ተግባር መቀየር የሚችል መሪ ስላገኘች ነው ብለዋል፡፡

በገበታ ለሀገርና በገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች የተሠሩት የቱሪዝም መዳረሻዎች፣ የስንዴ ልማት፣ ለዘመናት ታፍኖ የቆየው የባሕር በር ጥያቄ አጀንዳ ማድረግን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን አመላክተው፤ የመጠፋፋት ፖለቲካ ተወግዶ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር በማድረግ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ሲመኙት የነበረው ሕልም እውን መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

የሕዝቦች ተጠቃሚነት የተረጋገጠበት ዘመን ተሻጋሪ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ያነሱት ሚኒስትሩ፤ በትክክለኛ አቅጣጫ የሚመራና ሃሳብን ከተግባር፣ አካታችነትን ከፍትሐዊነት ጋር በማዋሓድ የሚመራ መሪ መኖር ለውጤቱ መገኘት ምክንያት ሆኗል ብለዋል፡፡

ሃሳብ ያለውን ጉልበት ለመመልከት አዲስ አበባ ዛሬ ያላትን መልክ መመልከት ሕያው ምስክር መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ልጆቻችን ከእኛ የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩ ዋጋ መክፈል አለብን ያሉት ሚኒስትሩ፤ አመራር ሲቀየር የማይቀየር፣ ለልጆቻችን የተሻለ እና የዘመነ ተቋም ብሎም ሀገር ለማውረስ ተግተን ልንሠራ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ባለፉት ሰባት የለውጥ ዓመታት ስኬት ያስመዘገበችው ያጋጠሙ ፈተናዎችን እያሸነፈች መሆኑን ጠቁመው፤ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በማኅበራዊና በዲፕሎማሲ ዘርፎች ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ ችላለች ነው ያሉት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሰጡት በሳልና አሻጋሪ አመራር ኢትዮጵያ ፈተናዎችን እያሸነፈች ትልልቅ ስኬቶችን እንድታስመዘግብ ማድረጉን አመልክተው፤ ይህን ስኬት ለማስቀጠል ሁላችንም በየተሠማራንበት ቦታ ኃላፊነታችንን በአግባቡ ልንወጣ ይገባል ብለዋል፡፡

ባለፉት ሰባት ዓመታት በትራንስፖርት ዘርፉ አስደናቂ ውጤት መመዝገቡንም ያስታወቁት ሚኒስትሩ፤ በቀጣይነትም የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማረጋገጥ የትራንስፖርት ሚኒስቴርን ጨምሮ የተጠሪ ተቋማት አመራሮችና ሠራተኞች ይበልጥ መትጋት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ሥልጣን ተረክበው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቃለ መሐላ መፈጸማቸው ይታወሳል፡፡

ፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን ሐሙስ መጋቢት 25 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You