
ዜና ሐተታ
ከዛሬ ሰባት ዓመታት በፊት ወጣቶች በሀገራቸው ላይ ሊያይዋቸው የሚፈልጓቸውን ለውጦች ለመንግሥት በተለያዩ መንገዶች ቢያቀርቡም መንግሥት ፈጣን ምላሽ ሊሰጣቸው አልቻለም:: በዚህ የተነሳም የወጣቶቹ የዘመናት ጥያቄዎች ቁጣን አዋልደው በርካቶችን መስዋዕት እንዲሆኑ አድርጓል::
ወጣቶቹም ለጥያቄያቸው መልስ ሲጠብቁ በኃይል ጥያቄን ለማስቆም የሞከረው መንግሥት ወጣቶቹን ለበለጠ ትግል አነሳስቶ ግንባራቸውን ለጥይት ሰጥተው እንዲታገሉት አድርጓቸዋል:: ይህ ሕዝባዊ ዕንቢተኝነትም ለመንግሥት ለውጥ መነሻ ሆኗል:: ይህንንም ተከትሎ የመጣው የለውጡ መንግሥት በመላ ሀገሪቱ ከጫፍ እስከ ጫፍ ሕዝቡ በአንድነት በመሆን ደግፎታል:: ሕዝቡ በወቅቱ በተደረገው የድጋፍ ሰልፍ ላይ በመገኘት ብቻ ሳይሆን በምርጫም መሪውን ሹሟል::
የለውጡ መንግሥትም ሀገርን በለውጥ መርከብ ላይ ካሳፈረ ሰባት ዓመታት ተቆጥረዋል:: ይህን በማስመልከትም በትላናንትናው ዕለት ባለፉት ሰባት ዓመታት የነበረበትን የጉዞ ሂደት ለማስታወስ “ትናንት፣ ዛሬና ነገን ለኢትዮጵያ ልዕልና” በሚል ቃል ከተማ አቀፍ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።
በመድረኩም የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ አባ ገዳዎች እና ሀደ ሲንቄዎች፣ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች፣ የተፎካካሪ ፓርቲ ተወካዮች፤ ምሑራን፣ የስፖርት እና የንግዱ ማኅበረሰብ ተወካዮች እና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል::
በእለቱም ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ ብልፅግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ የለውጡ መንግሥት ከአብዮት ይልቅ ሪፎርምን የተከተለ መሆኑን ገልጸዋል:: ትርክቱ ወንድማማችነት እና ብሔራዊ አንድነት የሆነ፤ አዲስ አበባን እንደስሟ ውብ አበባ ለማድረግ የሠራ፤ ሰው ተኮር በመሆን የልማት ሥራዎችን የሚሠራ፤ ሀገርን ለማበልፀግ የሚተጋ መሆኑንም ተናግረዋል::
እንደ አቶ ሞገስ ገለጻ፤ ፓርቲው ከፈተናዎች ይልቅ ዕድሎችን የሚያይ ነው:: የሚጋረጡበትን ችግሮችንም በድል የሚወጣ ነው:: ባስመዘገባቸው የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ እና ማኅበራዊ ለውጦች የማይዘናጋ፤ ሁሌም ለተሻለ እድገት የሚሠራ ነው:: የለውጡ መንግሥት እና ፓርቲው ያለፉት ሰባት ዓመታት በፖለቲካው ዘርፍ መገለልን ያስወገደ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም እንዲኖር የተጋም ነው::
ባለፉት የለውጥ ጉዞ ዓመታትም በባህል፤ በስፖርት፤ በጤና እና በሁሉም ዘርፎችም ከፍተኛ ለውጦች መመዝገባቸውን የሚናገሩት የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ፤ እንደ ኮቪድ 19፤ አንበጣ፤ የተፈጥሮ አደጋ እና ግጭቶች ቢኖሩም በእነዚህ ሁሉ ፈተናዎች ውስጥ ሆኖ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ስኬቶችን ማስመዝገቡን ይገልጻሉ::
የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ጃንጥራር ዓባይ በበኩላቸው የለውጡ ዓመታት አያሌ ስኬቶች የተመዘገቡበት እና መሠረታዊ የለውጥ አቅጣጫ የታየበት መሆኑን ተናግረዋል::
ኢትዮጵያ ባለፉት ሰባት ዓመታት ሀገራዊ ለውጥ ያሳየችበትና ለብልፅግና ጉዞዋ መሠረት የጣለችበት ጊዜ እንደነበረም አስታውሰዋል። ከለውጡ በፊት የነበሩትን ጠንካራና ደካማ ጎኖችን በመለየት አካታች የፖለቲካ አመራር መርሕን በመከተል ስኬቶች መመዝገባቸውንም ጠቁመዋል::
እንደ ምክትል ከንቲባው ገለጻ፣ በተፈጥሮ አደጋዎች የሚፈጠሩ ጉዳቶችን ለመቅረፍ ሀገሪቱ በአረንጓዴ ልማት ፕሮጀክት ጠንካራ ሥራ በመሥራት የአየር ንብረት ለውጥ አደጋ መቀነስ ተችሏል:: በዲፕሎማቲክ ጉዳዮችም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፅዕኖ ፈጣሪ መሆን ተችሏል:: ሀገሪቷን በዲጂታላይዜሽን እና በቴክኖሎጂ የላቀች ለማድረግ ከፍተኛ ሥራ ተሠርቷል::
አዲስ አበባ በዓለም መድረኮች ደምቃ እንድትታይ ሁለንተናዊ ለውጥ ተደርጎላታል:: በመሠረተ ልማት፤ በትምህርት፤ በጤና እና የቱሪዝም መዳረሻዎቿን በማስፋት የዲፕሎማቲክ ከተማነቷን የሚመጥኑ ሥራዎች መሠራታቸውንም አቶ ጃጥራር ገልጸዋል::
ለምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ምሳሌ በመሆን እና ልምድን በማካፈል በርካታ ሥራ መሠራቱንም ጠቁመዋል:: እስካሁን የተሠሩ ሥራዎች ለብልፅግና ጉዞ መስፈንጠሪያ መሆናቸውን እና በቀጣይም የተያዘውን በጎ ጅምር ለማስቀጠል መንግሥት በትጋት እንደሚሠራም ተናግረዋል::
መክሊት ወንድወሰን
አዲስ ዘመን ሐሙስ መጋቢት 25 ቀን 2017 ዓ.ም