የአሸናፊው የፈጠራ ሃሳብ ባለቤት

ዜና ሐተታ

ሉሊት ሰሙንጉሥ ትባላለች፡፡ የብሩህ እናት የሥራ ፈጠራ ውድድር አሸናፊና የ500 ሺህ ብር ተሸላሚ ናት። ልጇ የለውዝ ቂቤ እንደሚወድ የምትገልፀው ሉሊት፤ ሆኖም ልጁ የለውዝ ቂቤ አላርጂክ ስላለበት ሲመገብ ሰውነቱ እንደሚቆሳስል ትገልፃለች፡፡

በዚህም ምክንያት ለውዝን የሚተካ ነገር ለማግኘት ማንበብ ስትጀምር ሰሊጥን ማግኘቷን ታስረዳለች። ሰሊጥን ለማቆየት የሚረዱ ዘዴዎችን ለማወቅ ጥረት ስታደርግም ታሂኒ የሚባል ምርት መኖሩን ማወቋን ነው የነገረችን፡፡

ዓለም ላይ ታሂኒ እንዴት እንደሚመረት፣ ሰሊጡ ከየት እንደሚገኝ የመሳሰሉትን ስታነብ ደግሞ ሰሊጥ ከኢትዮጵያ እንደሚሄድ በማወቋ የፈጠረባት ቁጭት ለፈጠራ ሥራው ተጨማሪ መነሻ እንደሆናት ታስረዳለች። የሰሊጥ ቅቤ በኢትዮጵያ ውስጥ ማምረቱ የማህበረሰቡን ችግር ከመፍታት ባሻገር የሀገርንም የውጭ ምንዛሬ ግኝት የማሳደግ ሚና እንዳለው ትጠቁማለች፡፡

ከቤቷ ስትወጣ ጀምሮ በፈጠራ ሥራዋ አሸንፋለሁ ማለቷን የምትገልጸው ሉሊት፤ የሆነ ህልም ይዘሽ ስትነሺ የሆነ ጥግ እንደሚደርስ መገመትሽ አይቀርም ትላለች፡፡ ወደ ገበያ ለመግባት ዝግጅት መጀመሯን ገልፃ፤ የድርጅቷ ስም አዲናይን እንደሚባል ትጠቁማለች፡፡ በፈጠራ ሥራ ላይ ለተሠማሩ ሴቶችም ተስፋ አትቁረጡ፤ አንድ ቀን መሳካቱ አይቀርም የሚል መልእክቷን ታስተላልፋለች፡፡

በብሩህ እናት የፈጠራ ሥራ ውድድር ማጠናቀቂያ መርሀ ግብር ላይ የተገኙት የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰለሞን ሶካ በበኩላቸው፤ ብሩህ የሚለው ስያሜ ድምቀትንና ጉልህ ሆኖ መታየትን ያመለክታል። ተወዳዳሪዎቹም ጎልተውና ደምቀው በመውጣታቸው ለዚህ መብቃታቸውን ጠቁመዋል፡፡ በቆዩባቸው የውድድር ጊዜያትም የፈጠራ ሃሳባቸውን ወደ ንግድ ሃሳብ መቀየር የሚያስችል ሥልጠና ማግኘታቸውን ገልፀዋል፡፡

ሥልጠናው በውስጣቸው ያለው ብርሃን እንዲደምቅና የበለጠ ጎልቶ በዙሪያቸው ላሉ ሁሉ እንዲያበራ ተጨማሪ ኃይልና ጉልበት የሚጨምር መሆኑንም አስረድተዋል። ከዚህ ባሻገር ቆይታቸው ተሞክሮአቸውን እርስ በርስ ለመለዋወጥና ሥራዎቻቸውን ለማሳደግና ለማሻሻል እድል እንደሰጣቸው ጠቁመዋል፡፡

በውድድሩ ቆይታ ሴት ወጣቶች እድል ካገኙ የፈጠራ ሃሳቦችን ከማፍለቅ ባሻገር ለሀገር የሚጠቅሙ ምጡቅ ሃሳቦችን ማመንጨት እንደሚችሉ ለመረዳት መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡

ሀገሪቱ ለያዘችው ፈጠራንና ኢኖቬሽንን በማሳደግ ብልፅግናዋን ማረጋገጥም ትልም የሴቶች ሚና ከፍተኛ መሆኑን መረዳታቸውን አንስተው፤ እነዚህንና መሰል ሥራዎች ለተሠማሩ ሴቶችን መደገፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልፀዋል፡፡

“መንግሥታዊ ድጋፎች የሚቀጥሉት በሁለት እግራችሁ እስክትቆሙ ነው” ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ እስከዛሬ የመጣችሁበትን የአሸናፊነት፣ የመለወጥና የታታሪነት ፅናት አጠናክራችሁ እንደምትቀጥሉ እምነታችን ነው ብለዋል፡፡

የእናት ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ትዕግስት አባተ በበኩላቸው ባንኩ ባለው የ12 ዓመት ተሞክሮ ከዚህ በፊት የነበረውን የባንክ አሠራር በመቀየር ሁሉን አካታች ሥራዎችን ሲሠራ መቆየቱን ገልፀዋል፡፡ በተለይም ሴቶች ተሳታፊ የሚሆኑበትን እንዲሁም በኢኮኖሚ ራሳቸውን የሚያበቁበትን ፅኑ ራዕይ ይዞ የተለየ የባንክ አሠራር ሲተገብር መቆየቱን አስረድተዋል፡፡

ሴቶች የፈጠራ ችሎታቸውን የሚያወጡበት የራሳቸው የሆነ ማዕከል ያስፈልጋቸዋል በሚል ብሩህ ኢትዮጵያ በተባለ ስያሜ ለአራት ዓመታት ሲካሄድ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡ ይህንንም ከዳር ለማድረስ እንደ እቅድ የያዙት  በትብብር መሥራትን መሆኑን ጠቁመው፤ ሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ላደረገላቸው ድጋፍ አመስግነዋል፡፡

ፈጣሪ ሴቶች ያስፈልጉናል ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቷ፤ ባንኩ ሴቶችን ለማገዝ ኢኖቬቲቭ ሆኖ እየሠራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡ ለሥራ ፈጣሪ ሴቶችም መፍጠር፣ ማብቃትና ሃሳቡን መሬት ለማውረድ ፅኑ እምነት መኖር እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡ ለዚህም ባንኩ ዘላቂ የሆነ የፋይናንስ አገልግሎት እንደሚያቀርብ ጠቁመዋል፡፡

የኢንተርፕሪነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ቦሩ ሻቃ ፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ600 በላይ ሴቶች ተወዳድረው ከእነዚህ ውስጥ ሃምሳው መመረጣቸውን አስታውሰዋል፡፡

ከሃምሳዎቹ ደግሞ አስሩ ማሸነፋቸውን ጠቁመው፤ ለኢንስቲትዩቱ ግን ሁሉም አሸናፊዎች ናቸው ብለዋል። ኢንስቲትዩቱ በቀጣይ ከተሸለሙትም ካልተሸለሙትም ጋር አብሮ እንደሚሠራ ገልፀዋል፡፡

ነፃነት አለሙ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ መጋቢት 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You