
ከመገናኛ ወደ ሜክሲኮ የሚሄድ ታክሲ ውስጥ ነኝ፥ ሁለት ወጣት ወንዶች ድምጻቸውን ጎላ አድርገው ጨዋታ ይዘዋል። ጥሎብኝ ጆሮዬ አያርፍም፥ ድምጽ ከወጣበት አቅጣጫ ሁሉ ይቃርማል። ታዲያ አሁንም እንዲያው ሆነና ጆሮዬ በእነዚህ ሁለት ወጣቶች ጨዋታ ውስጥ ጣልቃ ገባ።
ጨዋታቸው ስቦኝ፥ መንገድ ላይ ካለው የመኪና ጡሩምባ ድምጽ፣ የኮሪደር ልማቱን ከሚያሳልጡ ግዙፍ መሣሪያዎች ጋጋታ፣ ከታክሲው ረዳት ጥሪ፣ መኪናው ውስጥ ከተከፈተው ራዲዮ አልፎ ሥራዬ ብሎ ጆሮዬ ለጨዋታቸው ትኩረት የሰጠው ሴቶች አደባባይ ስንደርስ ነው።
መነሻ ጉዳያቸው አቧሬ አካባቢ በሚገኘው በሴቶች አደባባይ ላይ የተገነባውና ይህን ወግ በማወጋችሁ ሰዓት ገና ተመርቆ ለዕይታ ያልበቃው ሐውልት ነው። ሐውልቱ የማን ይሆን የሚል ጥያቄ ከአንደኛው ተነሳና በጉዳዩ ላይ ሁለቱም የየራሳቸውን መላ ምት ሰጡ። አንደኛው ሁለት ታዋቂ፣ ዝነኛ እና ጀግና ሴቶችን ጠቀሰ። ሌላኛው ደግሞ ሐውልቱ የሁለቱም ሴቶች ላይሆን የሚችልበትን ምክንያት በሳቅ በታጀበ አኳኋን ገለጸ።
በበኩሌ እነዚህ ሁለት ወጣቶች የጠቀሷቸውንና በሀገራችን በጀግንነታቸው የሚነሱ ሴቶችን ስም እዚህ አልጠቅስም። ምክንያቱም ከጠቀስሁ አብሬ ልጆቹ የእነዚያን ሴቶች ጀግንነት ያሳነሱበትንም ነጥብና ምክንያት ልጠቅስ ነው። እመኑኝ! ያነሱት ምክንያት ደግሞ በፍጹም ውሃ አያነሳምና፥ ‘ከሰደበኝ መልሶ የነገረኝ’ እንዲሉ እንዳይሆንብኝ እነርሱ የተናገሩትን ጭራሽ በጽሑፍ አልደግመውም።
እዚህ ላይ ይቆየንና፥ እኔን እንድትታዘቡኝ እድል ልስጣችሁ። እነዚህ ወጣቶች ይህን ጉዳይ ሲያወሩ ስናደድ፣ ስገረም፣ ስደነቅ፣ ሳዝን፣ ‘ሆ…ይ’ ስል ብቆይም ምንም የቃል ምላሽ አልሰጠሁም። ለነገሩ ገጽታዬና የፊቴ ሁኔታ ዝም ያለ አይመስለኝም፥ ሆኖም ቃል አልተናገርኹም። ደፈር ማለት ስለሚጎድለኝ ነው መሰለኝ። ወይም ክርክር ስለማልወድ ነው፥ ካልሆነም ጎበዝ ተናጋሪ አይደለሁም። በእርግጥ ከእነዚህ ምክንያቶች ውጭ፥ ልጆቹ በጉዳዩ ላይ ያላቸውን ሃሳብ በሙሉ አሟጥጠው እንዲናገሩና ትዝብቴን ይዤ እኔም ወዲህ መምጣትን አስቤም ነው። የሀገሩን ጀግና ሴቶች ማስታወስና ማወቅ የማይችል የሀገሬ ልጅ ምን እንደሚያስብ ለማወቅ ጓጉቼ።
እናማ! ስሞችን አከታትለው መጥራት ጀመሩ፥ አከታትለው ስላችሁ ግን ሦስት ሴቶች ብቻ ነው መጥቀስ የቻሉት። ግራ ገባቸው፥ “እኛ ሀገር ጀግና ሴት ማን አለች?” ተባባሉ። አብረው ተጠበቡ፣ አሰላሰሉ፥ ‘አላገኙም’። በኋላ፥ አንዱ ከሌላኛው ትንሽ ሻል ይላል መሰለኝ፥ “እኛ ስላማናውቃቸው ይሆናል” አለ፥ ‘አስቦ አስቦ’ ጀግና ሴት በማጣቱ። ሌላው ትንሽ ባስ ያለበት ሳይሆን አልቀረም፥ “እንዴ! ቢኖሩማ ልናውቃቸው ይገባ ነበር።” አለ፥ ቆፍጠን ብሎ።
እነርሱ የጨዋታቸው ርዕስ ተቀይሮ፥ የሴቶች አደባባይን አልፈን ወደ ብሔራዊ አካባቢ ስንደርስ፥ እኔ በሃሳቤ ጀግኖቼን እየዘረዘርሁ ነበር። እገሊትን እንዴት አያውቋትም፣ እገሊትን እንዴት እንደጀግና አላስታወሷትም፣ እገሊትስ ብትሆን ጀግኒት አይደለች እንዴ?
ለነገሩ ጀግንነት ራሱ ምንድን ነው? በልምዳችን ጀግና የምናውቀው በጦር ሜዳ ወይም ብዙዎች በሚያዩት አደባባይ ገድል የሠራ ሆኖ እንጂ፥ በየጓዳው፣ በየመጋረጃው ጀርባ ቢታይ ሀገራችን የጀግኖች መናኽሪያ በተባለች ነበር። ደግሞም ጀግንነት በምስክሮች ቃል የሚጸናና የሚረጋገጥ ሳይሆን በተግባር የሚገለጥ ነው። አንድ የጀግንነት ሥራን የሠራ ሰው፥ ሰዎች ስላላወቁት ጀግና አይደለም ማለት አይደለም። ሰዎች ባያውቁትም፣ እስኪያውቁትም፥ ጀግና ያው ጀግና ነው፥ ጀግኒትም ያው ጀግኒት ናት። ከዛ ግን ምስክር ከተገኘ እሰየው፥ ፈለግ ለመከተል ላሰበ መንገዱ ተጠረገለት ማለት ነው። ብዙ ጊዜም ከጀግና በላይ ጀግናውን የሚያውቅ ነው ተጠቃሚ አይደለ?
እና ጀግንነትን በጦር ሜዳ ብቻ ለሚያስብ፥ ወራሪን ድል ከማድረግ ጋር ብቻ ለሚያነጻጽር በሰላም ዘመን ጀግናውን ማግኘት፣ አርአያውን ማየትና ለትውልድ ምሳሌን መፍጠር ይቸገራል። ለዛ ይመስለኛል በውጭ ሀገራት አንዳንድ አስደናቂና ለሰው ልጅ የሚጠቅም ተግባር የፈጸሙ ‘ውሾች’ን ሳይቀር “ሂሮ” የሚሏቸው፥ የጀግና ስም የሚሰጧቸው።
ወደ ቢሮዬ የሚያደርሰውን የእግር መንገድ እየሄድሁ፥ ታክሲ ውስጥ የገጠሙኝ ወጣቶች ጀግና ሴቶችን ማስታወስ ያቃታቸው በሦስት ምክንያት ሊሆን ይችላል ብዬ እያሰብሁ ነበር። አንደኛው የመረጃ ክፍተት ሊሆን ይችላል። ሰው እንኳንና ጀግናውን የሀገሩን ብሔራዊ መዝሙር ለማወቅም ጊዜ መስጠት፣ መጠየቅና ለማወቅ መፈለግ ይጠበቅበታልኮ!
ሁለተኛ እነዚህ ልጆች ጀግንነትን የተረጎሙበት መንገድ ይሆናል። የጀግና መጸነሻና ማደሪያዎች ፖለቲካና የጦር ሜዳ ብቻ ከሆኑ፥ ሰው ጀግና ለመሆንና ለመባል እንግዲህ ትውልድ ሁሉ ጠብ ሊጭር፥ መሣሪያ አተኳኮስ ሊሠለጥን ነው።
ሦስተኛውና ሌላው ምክንያት ደግሞ ሲመስለኝ፥ የሴቶች ታሪክ አሁንም በሚገባ ስላልተጻፈ ነው። አሁን ማን ይሙት፥ ሴት ተዋንያትን ወይም በውበት የተደነቁ ሞዴሎችን ጥቀሱ ብንባል መዘርዘር ይቸግረናል? በፍጹም። ሙያው ውስጥ ጀግንነት ባለመኖሩ ሳይሆን፥ ለዕይታና ለጆሮ ቅርብ የሆኑና ብዙ መረጃ ማግኘት የሚቻልባቸው ጉዳዮች ስለሆኑ ነው። በእርግጥ እንደዛም ሆኖ፥ ሴቷን በሚያየው ነገር እንጂ በተሠራው ሥራ የሚመዝነው በጣት ቁጥር የሚገባ አይደለም።
ያም ሆነ ይህ፥ የሴቶች አደባባይ ላይ የማን ሐውልት ይሆን የተቀመጠው? የትኛዋ ሴት ጀግናችንን ምሳሌ ትሆን ዘንድ ከፍ አደረግናት? እንደው ሁሉም ሰው እድል ቢሰጠው የማንን ሴት ሐውልት ያቆም ይሆን? መቼስ በዓለምም በአፍሪካም “የመጀመሪያ’ የተባሉ ታሪክ ሠሪ ሴቶች ባሉበት ሀገር ይህ ሊቸግረን አይችልም። በሀገራችን አደባባይ ላይ ምልክት ሆና የምትቆመው ጀግኒት፥ በየሐሳባችን እና አስተያየታችን፥ በውስን መረጃ ልትሆን ትችላለች ብለን የምናስባት ልትሆን ትችላለች፥ ላትሆንም ትችላለች። ያላሰብናት ትሆናለች፥ ወይ ጭራሽ ከዚህ የራቀ ሐውልት እናይ ይሆናል። እሱን ጊዜው ሲደርስ የምናይ ይሆናል።
በየልባችን ግን ጀግና ሴት አለች። የቻልን የመሰከርንላት፥ ያልቻልን አንግሠን ያኖርናት። መልኳን የሰጠች እናት፣ ዋጋ የከፈለች እህት፥ ያላትን ከመስጠት ያልሰሰተች ሚስት፣ ከብራን ያስከበረች ልጅ፣ ሥራዋንና ሕልሟን ስለቤተሰቧና ስለልጆቿ ያቆየችይቱ፣ ልጆቿንና ባሏን ያስቀደመችዋ፣ በቤቷም በመሥሪያ ቤቷም ያላጎደለችይቱ፣ የደረሰባትን ጥቃትና ጉዳት በፈገግታዋ ጋርዳ ያሸነፈችይቱ፣ ልጆቿን ለብቻዋ ለከፍታ ለማድረስ የተጋችይቱ፣ እንደሰው ፍትሕን ፍለጋ የምትጣራዋ፣ ሴትነቷን ለጥቅም የማትመዝዘዋ፣ …ብዙ ጀግና በየልባችን ላይ አለች።
የእናንተ ጀግና፥ በሀገር አደባባይ ሐውልት ይሠራላት የምትሏት ከእነዚህ ሁሉ መካከል ላትሆን ትችላለች። ከእነዚህ መካከልም አንዷ ልትሆን ትችላለች። ልንስማማባት እንችላለን፥ ልዩነቶች ሊኖሩ ይችላሉ። አንድ በእርግጥ የምናውቀው እውነት ግን፥ የጀግንነት መለኪያ ሚዛናችን ካልተንሻፈፈ በቀር በየአንድ ርምጃው ሊጠቀሱ የሚችሉ በርካታ ቀዳማዊት ሴቶች ያሉን መሆኑ ነው። ለማያውቁ፣ ላልተረዱ፣ ትርጉሙ ላልተገለጠላቸው ደግሞ ‘እኔ ነኝ ባይ ማን ነሽ?” ትባያለሽና፥ እህቴ ወዲህ ብቅ በይ። እኛም እንላለን፥
“…ፍጹም ኢትዮጵያዊት ዓይናማ ደማማይ፣
ወይዘሪት ኢትዮጵያ ቆንጂት እኔ ነኝ ባይ፣
ተራመጅ ወደፊት ውጭ በአደባባይ፣
እንቃወማለን አንቺን በክፉ የሚያይ።”
ይህን ለማስታወስ የሴቶችን ቀን መጠበቅ አይጠበቅብንም፥ በሕይወት እስካለን ድረስ ሁሉም ቀን የእኛ አይደለ? ደህና ቆዩኝ!
ሂላርያ ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 13 ቀን 2017 ዓ.ም