
ከዓመታት በፊት ከፍትሕ መጽሔት ላይ ያነበብኩት ገጠመኝ ነው። ፀሐፊው የጻፈው ለጥናት ጽሑፍ መጠይቅ ወደ ገጠር ሄዶ የገጠመውን የጓደኛውን ገጠመኝ ነው። ገጠመኙን በአጭሩ ልግለጽላችሁ።
አንድ ምሑር በሃይማኖቶች መካከል ስላለው ግንኙነት ጥናት ሊሠራ ወደ ገጠሩ የሀገራችን ክፍል ይሄዳል። ሙስሊም እና ክርስቲያን በሚኖርበት አካባቢ ሄዶ ጥያቄ ይጠይቃቸዋል። ጥያቄውም በሙስሊም እና ክርስቲያን መካከል ግጭት እንዳይነሳ ምን አይነት ጥንቃቄ እንደሚያደርጉ የሚጠይቅ ነው። ተጠያቂዎቹ ግራ ገባቸው። ራሱን ጠያቂውን ጠየቁት። ‹‹የምን ግጭት ነው? ለምንድነው የምንጋጨው? ማነው ተጋጭተዋል ያለህ?›› የሚሉ ጥያቄዎችን ነበር የጠየቁት። አንዳንዶችም ደፈር ብለው ‹‹እናንተ የተማራችሁ የምትባሉ ሰዎች ናችሁ ስለግጭት የምታወሩት›› ብለው እንደነገሩት ገጠመኙን ሰፋ አድርጎ ጽፏል።
ከዓመታት በፊት አቶ አዲሱ አረጋ (የኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን እያሉ) በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ የጻፉት አንድ ገለጻ ልጨምርና ወደ ራሴ ትዝብት ልሂድ። ኦሮሚያ ክልል ውስጥ በሚገኝ አንድ አካባቢ ሁለት ግለሰቦች ተጋጭተው እስከመገዳደል ደረሱ። ገዳይ እና ሟች የአማራና የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች ናቸው። የማኅበራዊ ሚዲያ እና የፖለቲካ አራጋቢዎች ነገሩን የብሔር መልክ አስይዘው እገሌ እገሌን ገደለ በሚል አናፈሱት። ይህኔ ‹‹እውነታውን ማሳወቅ›› በሚል አቶ አዲሱ አረጋ ትክክለኛውን ምክንያት አጣርተው ጻፉ። ግለሰቦቹ የተጣሉት በዱቤ ብድር ከገንዘብ ጋር በተያያዘ ጉዳይ ነበር።
እንዲህ አይነት አጋጣሚ የትም ያለ ነው። የአንድ አካባቢ ተወላጅ የሆኑ፤ ይባስ ብሎ ዘመድ የሆኑ ሁሉ ሳይቀር ይገዳደላሉ። ወደ እንዲህ አይነት ሰይጣናዊ ድርጊት የሚገቡት ብሔሩን ወይም ሃይማኖቱን አስበው ሳይሆን በመከዳዳት ወይም በሌላ ቂም ነው። ይህ በግለሰቦች ባሕሪ የሚወሰን ነው። ችግሩ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ የግለሰብን ባሕሪ መለየት የማይቻል እየሆነ ነው፤ የሚታሰበው በቡድን ብቻ ነው። አንድ ግለሰብ በግልፍተኛ ባሕሪው ያደረገውን ነገር ለግለሰቡ ብሔር ወይም ሃይማኖት ተጋሪዎች መስጠት የተለመደ ሆኗል። ይህ ሲሆን፤ የዚያ ግለሰብ ብሔር ወይም ሃይማኖት ተጋሪዎች ግን በንፁህ ልባቸው ምንም የሚያውቁት ነገር የለም፤ ዳሩ ግን በግድ የዕዳው ተካፋይ እንዲሆኑ ይደረጋል። ከመሰደብና ከመወቀስ አልፈው ይባስ ብሎ የጥቃቱ ሰለባ ሊሆኑ ሁሉ ይችላሉ።
ይህ ወር በኢትዮጵያ የረጅም ዘመን የአብሮነት ታሪክ ያላቸው የሙስሊምና ክርስቲያን ጾም በአንድነት የሚጾምበት ነው። ሰሞኑንም የኢፍጣር ሥነ ሥርዓት በመስቀል አደባባይ እና በተለያዩ ተቋማትና መድረኮች እየተካሄደ ነው። በሕዝቡ ዘንድ ያለው አንድነትና አብሮነት እንዲህ በተቋማት ደረጃም መለመድ አለበት፤ የተማረ ነው በሚባለው የኅብረተሰብ ክፍልም መለመድ አለበት።
የሙስሊምና ክርስቲያን አብሮነት በማንም ስብከት ሳይሆን በራሱ በሕዝቡ ልባዊ ፍቅር ሲጋመድ የኖረ ነው። ደስታቸውንም፣ መከራቸውንም ሲካፈሉ የኖሩ ናቸው። አንተ ትብስ፣ አንተ ትብስ ሲባባሉ የኖሩ ናቸው።
ፖለቲከኛው አቶ ጃዋር መሐመድ ‹‹አልፀፀትም›› በሚል ርዕስ በጻፈው መጽሐፍ ያነበብኩት አንድ ታሪክ በእጅጉ አስገርሞኛል። እኔና ጃዋር ያደግንበት አካባቢ የተራራቀ ነው። የጻፈው ጽሑፍ ግን በቀጥታ የእኛ ሰፈር አባቶች ሲያደርጉት ያየሁትን ነው። በዚያ ልክ መመሳሰሉ ገርሞኛል። ነገሩ እንዲህ ነው።
በአካባቢያችን ክርስቲያን ሠርግ የሚያደርግ ከሆነ ለሙስሊሞች ለብቻ በሬ ወይም ላም ይገዛል። ሙስሊም ሠርግ የሚያደርግ ከሆነ ደግሞ ለክርስቲያኖች ይገዛል። እዚህ ላይ አንድ የሚገርም መተሳሰብ አለ። በእኛ አካባቢ ክርስቲያኖች ይበዛሉ። ክርስቲያን ሠርግ ሲያደርግ በሬ ወይም ላም ይገዛል፤ ለሙስሊሞችም (ጥቂት ሆነው ሳለ) በሬ ወይም ላም ይገዛል። ይህ አግባብ አይደለም ብለው ያመኑ ሙስሊሞች በኋላ አንድ ዘዴ አመጡ።
አንድ የጎረቤታቸው ክርስቲያን ሠርግ ሊያደርግ ቀን ሲቆርጥ፤ አንድ ነገር አስቀድመው ያስጠነቅቁታል። ይሄውም በሬ ወይም ላም እንዳይገዛ ነው፤ ፍየል ብቻ እንደሚበቃ ይነግሩታል። እምቢ ብሎ በይሉኝታ እንዳይገዛ ‹‹ወላሂ በሬ ከገዛህ አናርደውም!›› ብለው ያስጠነቅቁታል። ለጥቂት ሰዎች ብሎ ከፍተኛ ወጪ እንዳያወጣ ነው።
ሙስሊም በሚበዛበት አካባቢም እንደዚሁ በቁጥር ጥቂት የሆኑ ክርስቲያኖች ያስጠነቅቃሉ። ‹‹በሬ ከገዛህ ለእርሻ ፈልገኸው ካልሆነ በስተቀር እኛ አናርደውም፤ ይልቅ ፍየሏን ጭምር እንዳታስቀርብን!›› እያሉ በቀልድ ጭምር ያስጠነቅቁታል። ይህ አይነት ባህልና ሥነ ልቦና በዓይኔ አይቸው፣ በጆሮዬ ሰምቸው ያደኩት ነው። ጃዋር መሐመድ ፖለቲከኛ ስለሆነ ለመቻቻል ሲል የጻፈው ነው ሊባል አይችልም። በፖለቲካ ጉዳዮች የቱንም ያህል ልዩነት ሊኖር ይችላል፤ ይህ የሙስሊምና ክርስቲያን ባህል ግን ምንም ነገር ያልተጨመረበት እውነተኛ ሕይወት ነው።
ታዲያ ይህ የሕዝቡ ባህልና ሥነ ልቦና የተማረ የሚባለው ጋ ሲደርስ ምን ነካው?
አንድ ወፈፌ ክርስቲያን እስልምናን ሲሳደብ ወይም አንድ ወፈፌ ሙስሊም ክርስትናን ሲሳደብ የዚያ ወፈፌ ግለሰብ ባሕሪ ከማድረግ ይልቅ፤ የተማረ የሚባለው ሙስሊም ‹‹ተመልከቱ ክርስቲያኖች ለእስልምና ያላቸውን ጥላቻ!›› ይላል። የተማረ የሚባለው ክርስቲያንም ‹‹ተመልከቱ ሙስሊሞች ለክርስቲያን ያላቸውን ጥላቻ!›› ይላል። ይህን የሚለው ሰውዬ በውስጡ ጥላቻ አለበት ማለት ነው። ያንን ወፈፌ ሰውዬ ምክንያት በማድረግ በዚያች አጋጣሚ ልናገር ብሎ የውስጡን ተናገረ ማለት ነው። ራሱ ጥላቻ ስላለበት አንድን ወፈፌ ግለሰብ ምክንያት ያደርግና የልቡን ይናገራል። ይህ ሰው ፍርሃት ይዞት፣ ወይም ትንሽ ይሉኝታ ነገር አስቸግራው እንጂ ራሱም ጥላቻ ነበረበት ማለት ነው።
በግለሰብ ደረጃ ብዙ አይነት ባሕሪ ያለው ሰው አለ። ያ ሰው በአስተዳደጉም ይሁን ከጊዜ በኋላ በሆነ አጋጣሚ በገነባው የተቃወሰ ሥነ ልቦና አንድን ብሔር ወይም ሃይማኖት ሊሳደብ ይችላል። ሲሳደብ ግን እነማንን ይወክላል? ተብሎ መታሰብ አለበት። አለበለዚያ ሰበብ ፈልጎ የራስን ጥላቻ መናገር የራስን ገመና ማሳየት ነው።
አብሮነት፣ መቻቻል፣ አንዱ ለአንዱ ማሰብ በጥናትና ምርምር የምናመጣው፣ ወይም በመድረክ ስብከት የምናሰርፀው ሳይሆን ለዘመናት ሕዝቡ የኖረበት ከደሙ የተዋሓደ ባህል ነው። አንዳንድ የተማሩ የሚባሉ ወገኖች ይህን ለመሸርሸር የሚያደርጉትን ድርጊት ማክሸፍ ይገባል። በእንዲህ አይነት ልዩ አጋጣሚዎች (የፆም አንድነት) ደግሞ የበለጠ ማሳየት ይገባል። ለዚህ ደግሞ በአብሮነት እየተደረጉ ያሉት የኢፍጣር ሥነ ሥርዓቶች ጥሩ ማሳያዎች ናቸው። የተማረ የሚባለው የኅብረተሰብ ክፍል ልዩነትን የሚፈጥሩ ነገሮችን ከማራገብ ይልቅ እንዲህ አይነት አንድነቶችን ሊያሳይ ይገባል። የኅብረተሰቡን ነባር ባህል እንዲህ በአደባባይ ሊያንፀባርቀው ይገባል።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 10 ቀን 2017 ዓ.ም