ጎበዝ መምህር ለምን ብርቅ ሆነብን?

ሰሞኑን በማህበራዊ ትስስር ገጾች አንድ የፊዚክስ መምህር ተማሪዎችን ያስተማረበት መንገድ ለየት ያለ እና ለተማሪዎች ግልጽ የሚሆን ነው በሚል ብዙዎች አድናቆታቸውን ሲቸሩ አይተናል። በሌላ በኩል ደግሞ በአነስተኛ ደሞዝ እንዲህ ከልቡ የሚያስተምር፣ ከራሱ በላይ ለትውልድ የሚያስብ መሆኑ ሊያስመሰግነው ይገባል ያሉ ብዙዎች ናቸው። በተለይም የሚያስተምርበትን ቀለል ያለ ዘዴ እና አካባቢያዊ ምሳሌ ብዙዎች ወደውለታል። በተለምዶ የፊዚክስ ትምህርት ‹‹ከባድ ነው›› ተብሎ እንደ ትርክት ተይዟል። ፊዚክስን ግልጽ በሆነ መንገድ ማስተማሩ እንደ አንድ ልዩ ጉብዝና ተይዟል፡፡

የእኔ ትዝብት በግለሰብ ደረጃ መምህሩ ላይ አይደለም። መምህሩ መነሻ ሃሳቤ ነው፤ በግሌ የወደድኩለትም ያልወደድኩለትም ነገሮች አሉ። ትዝብቴ መምህሩን መገምገም ስላልሆነ ወደ ጠቅላላ ሁኔታዎች ልሂድ፡፡

ጎበዝ መምህር ለምን እንዲህ ብርቅ ሆነ?

እዚህ ላይ አንድ በድፍረት መነገር ያለበት ነገር፤ ብዙ መምህራን የሚያስተምሩት ትምህርት ሳይገባቸው የሚያስተምሩ ናቸው። ‹‹ሳይገባቸው›› የሚለው አካራካሪ ሊሆን ይችላል፤ ምናልባትም ብዙ መምህራንን ቅር ሊያሰኝ ይችላል። ዳሩ ግን እንሸዋወድ ካልተባለ በስተቀር ሳይገባቸው የሚያስተምሩ ብዙዎች ናቸው። እዚህ ላይ መከራከሪያ ሊሆን የሚችለው ነገር፤ በከፍተኛ ውጤት (የቁጥር ውጤት ማለት ነው) በማዕረግ ተመርቀው መምህር የሆኑ ሰዎችን በመጥቀስ ሊሆን ይችላል። እነዚህ መምህራን ከቁጥር ውጤትም በላይ ጎበዝ ናቸው ከተባለ፤ ምናልባትም የሚያስተምሩትን ትምህርት ገጽ በገጽ በታትነው የሚናገሩ፣ የቁጥር ፈለጣ ላይ ጎበዝ የሆኑ ሊሆኑ ይችላሉ። ጉብዝና ግን ይሄ አይደለም!

ትምህርት ማለት ሰዎችን ከአካባቢያቸው ጋር የሚያስተዋውቅ ሲሆን ነው። ወደ ተግባር ፈጠራ የሚወስድ ሲሆን ነው። አካባቢያቸውን ተረድተው የሚመራመሩበትና የሚሠሩበት ሲሆን ነው፤ በአካባቢያቸው ያሉትን ነገሮች (ለምሳሌ ዕፅዋትና እንስሳት) ወደ ተግባር አምጥተው ለተፈለገው ዓላማ ለማዋል የሚያስችል ሲሆን ነው፡፡

እስኪ ከዚህ አንፃር መምህራንን ልብ ብለን እናስተውል፤ ወደ ኋላ መለስ ብለን ምን ያህል መምህሮቻችን በዚህ ልክ ያስተምሩን ነበር የሚለውን እናስታውስ።

በተለይም እንደ ሒሳብ እና ፊዚክስ ያሉ የትምህርት አይነቶች የሚሰጡበት የማስተማር ልማድ ከአካባቢያዊ ሁኔታ ጋር የተራራቀ ነበር። አንድ መምህር ጎበዝ የፊዚክስ መምህር የሚባለው፤ ወይም አንድ ተማሪ ጎበዝ የፊዚክስ ተማሪ የሚባለው በቀመር ሥራ የማስተማሪያ ሰሌዳውን ቁጥር በቁጥር ሲያደርገው ነው። ይሄ ጥሩ ሆኖ ሳለ፤ ጽንሰ ሃሳቡ ላይ ተግባራዊ ገለጻ ከሌለ ግን ውጤቱም ከቁጥር አያልፍም። እያንዳንዱ ጽንሰ ሃሳብ በአካባቢያችን በሚገኙ ነገሮች ሊገለጽ የሚችል ነው። ሳይንስ ማለትም ይሄው ነው። ዳሩ ግን በብዛት የሚደረገው መጽሐፉ ላይ ያለውን ማብራሪያ መሸምደድ ነው። ይሄ ጽንሰ ሃሳብ ማለት በተግባር ይሄ ማለት ነው ተብሎ የማሳየትና የማስረዳት ችግሮች አሉ። ነገሩን ግልጽ ለማድረግ አንድ በጣም ቀላል ምሳሌ እንጠቀም።

መፈንቅል (Lever) የሚባል የፊዚክስ ንድፈ ሃሳብ አለ። ይህ ንድፈ ሃሳብ ገበሬዎች ትልቅ ድንጋይ ፈንቅሎ ከእርሻ ማሳ ላይ ወይም ለሆነ ጉዳይ ከተፈለገ ቦታ ላይ ለማንሳት የሚጠቀሙት ነው። ይህን ትልቅ ድንጋይ የማንሳት (የመፈንቀል) ሂደቱ ነው መፈንቅል የተባለው። ይህ ሂደት ሦስት ደረጃዎች አሉት። አንደኛ፣ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃ መፈንቅል ማለት ነው።

አንደኛ ደረጃ የሚባለው እርካብ በሃይል እና በጭነት (ክብደት) መካከል ሲውል ነው። እርካብ ማለት አንድን ትልቅ ድንጋይ ፈንቅሎ ለመጣል እርፍ በሚመስል እንጨት ሲፈነቅሉ ከእንጨቱ ሥር የሚያደርጉት ድጋፍ ነው፤ ለመኪና ‹‹ታኮ›› እንደሚባለው ማለት ነው። ጭነት ወይም ክብደት የሚባለው ደግሞ የሚፈነቀለው ድንጋይ ማለት ነው። ሃይል የሚባለው ደግሞ ድንጋዩን ለመፈንቀል ከእርፉ ጫፍ ላይ የሚያርፈው የሰዎች ጉልበት ነው። አንድን ድንጋይ ለመፈንቀል እርፍ ተጠቅመው፤ ከሥር እርካብ አስደግፈው ከላይ እርፉን በመጫን ድንጋዩን ከሚፈለገው ቦታ ላይ ፈንቅለው ይጥሉታል ማለት ነው። ይህ ቀላል ማሽን መሆኑ ነው።

ሁለተኛ ደረጃ እና ሦስተኛ ደረጃ የሚባሉት የመፈንቀል አይነቶች የክብደት፣ የእርካብ እና የሃይልን ቦታ በማቀያየር የሚከናወኑ ናቸው። እነዚህ ክንውኖች የሚፈፀሙት እንደ ክብደቱ ትልቅነትና ትንሽነት ነው። የትኛው ለየትኛው ያስፈልጋል የሚለውን በልማድ ያውቁታል። ሥራቸውን የሚያቀልላቸውን አሠራር ተላምደውታል።

ሳይንስ ደግሞ ከእንደዚህ አይነት በልማድ ለዘመናት ሲያገለግሉ ከቆዩ ነገሮች የዳበረ ነው። በሂደት እየተሻሻለ እና እየዘመነ የመጣ ነው። የትኛውም የሳይንስ ጽንሰ ሃሳብ በአካባቢያችን ከሚተገበሩ ነገሮች ጋር በቀጥታ ግንኙነት ያለው ነው። በሌለ ነገር ላይ የተጠና ሳይንስ አይኖርም፤ ካሉት ነገሮች ተነስቶ ነው ያልነበሩትን ነገሮች የፈጠረው።

ወደ መማር ማስተማሩ ችግር እንምጣ

አብዛኞቹ መምህራን እንደዚህ በተግባር ከማስተማር ይልቅ ንድፈ ሃሳቡን የማስሸምደድ ሥራ ላይ የሚያተኩሩ ናቸው። ውጤትም የሚለካው በቁጥር ነው። ፈተናውም የሚወጣው ተግባርን የሚለካ ሳይሆን ‹‹ምን ይባላል? ዘርዝር! ጥቀስ!›› በሚሉ ተቆጥሮ የተሰጠውን ብቻ መቀበል ላይ የሚያተኩሩ ናቸው። ንድፈ ሃሳቡን ሸምድዶ በመያዝ ዘርዝር የተባለውን ነገር የዘረዘረ ተማሪ ከፍተኛ ውጤት(በቁጥር) ያመጣል፤ ጎበዝ ተማሪ ይባላል ማለት ነው።

እነዚህ የሳይንስ ጽንሰ ሃሳቦች ግን በአካባቢያችን ‹‹የትኛውን ነገር የሚገልጹ ናቸው?›› ቢባል ከተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር የማያያዝ ክህሎቱ የለም ማለት ነው። ከአካባቢያችን ነገሮች ጋር በተግባር የማያያዝ ክህሎቱ የለም ማለት ደግሞ የተማሩት ትምህርት ተግባር ላይ አልዋለም ማለት ነው። ወደ ሥልጣኔ እና ወደ ቴክኖሎጂ አይወስድም ማለት ነው።

ይህ ችግር የመምህራኑ ችግር ብቻ አይደለም፤ እንደ አጠቃላይ ሥርዓተ ትምህርቱ በይዘትም ሆነ በአቀራረብ ተግባራዊ እንዲሆን በሚገባ ስላልተሠራበት ነው። የሚያስተምረው መምህርም በዚሁ አይነት መንገድ የተማረ ነው። እሱም መምህር የሆነው ከንድፈ ሃሳብ ሽምደዳ ያለፈ ግንዛቤ ሳይኖረው ነው፤ ከአካባቢው ጋር ሳያቆራኝ ነው። በዚህ ሁኔታ ከቀጠለ ትምህርቱ የለብ ለብ ሆኖ ይቀጥላል ማለት ነው።

በነገራችን ላይ መምህር የሚሆነው ማን ነው? የሚለውንም ልብ ማለት የግድ ይላል። መምህርነት በተለይም ከቅርብ ዘመናት ወዲህ ብዙዎች የሚቀኑበትና ብዙዎች የሚመኙት የሙያ አይነት እየሆነ አይደለም። እንዲያውም ይባስ ብሎ ጎስቋላ ሕይወት የሚኖር፣ በኑሮ ብዙ የሚቸገር ተደርጎ ነው ትርክቱ የተገነባው። ይህ ደግሞ በየፊልሞችና ድራማዎች ብዙ ተሠርቶበታል። ስለዚህ ብዙዎች የሚመኙት ሙያ አልሆነም ማለት ነው። በዚህም ምክንያት ልጆች ከታች ጀምሮ የሚመኙት አይሆንም ማለት ነው። ዩኒቨርሲቲ ሲገቡ ከፍተኛ ውጤት የሚጠይቁ የትምህርት ዘርፎችን ሞልተው ያላገኙ ተማሪዎች የሚገቡበት ይሆናል ማለት ነው። ሕክምና ወይም ፓይለት እየተመኙ እንደሚያድጉት መምህርነት እየተመኙ አያድጉም ማለት ነው። እንዲያውም ይባስ ብሎ ‹‹መምህር እንዳትሆኑ›› እያሉ የሚመክሩ መምህራንም ይኖራሉ።

በአጠቃላይ፤ መምህርነት የሙያዎች ሁሉ አባት ነውና አማራጭ ያጣ ሰው የሚገባበት ሳይሆን ተመርጦ የሚገባበት እንዲሆን ይሠራ! የመማር ማስተማር ሥራውም ንድፈ ሃሳብ ማስሸምደድ ሳይሆን ከአካባቢያዊ ነገሮች ጋር የተገናኘ እንዲሆን ይሠራ!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 17 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You