
የመድረክ ንግግር ዓውድ ይፈልጋል። ይሄ ማለት በጉዳዩ ላይ እና በታዳሚዎች የዕድሜና የሙያ ዘርፍ ሁኔታ ላይ ማተኮር ማለት ነው። ምናልባት ሥልጠና ካልሆነ በስተቀር መድረኮች ሁሉ በልዩ ዘርፍ ባለሙያዎች ላይ የሚያተኩሩ ላይሆኑ ይችላሉ። ማንኛውም ሰው የሚታደምባቸው መድረኮች አሉ። ይህም ቢሆን ግን ዓውድ ይፈልጋል። መድረክ የራሱ ቅልጥፍናና ቁጥብነት ስለሚፈልግ እሱን መጠቀም ማለት ነው። ብዙ ጊዜ ነገርን ሰፋ ሲያደርጉ የምናያቸው ደግሞ በእድሜ ገፋ ያሉ አባቶች ናቸው።
ከዓመታት በፊት ያጋጠመኝ ነው:: በአንድ መድረክ ላይ አንድ የዕድሜ ባለጸጋ ንግግር እንዲያደርጉ ተጋበዙ:: በአዳራሹ የሚበዙት ወጣቶች ናቸው:: ወጣቶች ናቸው ማለት እንግዲህ ምን ማለት እንደሆነ ግልጽ ነው:: ወጣቶች ምን አይነት ንግግር እንደሚፈልጉና አጭር መሆን እንዳለበት ይታወቃል ማለቴ ነው:: መድረኩም ለወጣቶች ቅርበት ያለው ነው::
መልዕክት እንዲያስተላልፉ የተጋበዙት አዛውንት ንግግራቸው በጣም ዘለግ አለ:: በእያንዳንዱ ወጣት ልብ ውስጥ ‹‹አይጨርሱም እንዴ!›› የሚል ምኞት ይነበባል:: ስልኩን ይነካካል፣ ያፋሽካል፣ ከጎን ያወራል፣ እየወጣ ይሄዳል፤ አዛውንቱ የቀደም ትዝታቸውን እያወሩ ይህን ትውልድም በነገር ወረፍ ያደርጋሉ::
አዛውንቱ ማሳረጊያ የሚመስል ዓረፍተ ነገር ሲናገሩ አዳራሹ በጭብጨባ ይናጣል፤ የሚያጨበጭቡት በተናገሩት ነገር ተደስተው ሳይሆን ‹‹እፎይ ሊጨርሱ ነው›› በሚል ደስታ ነው፤ እግረ መንገድም ይበቃዎታል የሚል መልዕክት መሆኑ ነው:: አዛውንቱ ግን የሞቀው ጭብጨባ ቀዝቀዝ ሲል ጠብቀው እንደገና አዲስ ታሪክ ይጀምራሉ፤ ታዳሚውም አዲስ ተስፋ መቁረጥ ይጀምራል:: በጭብጨባና በፉጨት አያስቆማቸው ነገር አዛውንት ናቸው፤ በዚህ በኩል ታዳሚው ይመሰገናል:: እንዲህ እንዲህ እያለ እንደምንም ጨረሱ::
መድረክ መሪው በጣም ጎበዝና አስተዋይ ነበርና የመድረኩን ድባብ ተረድቶታል:: ሰውየው ጨርሰው እንደወረዱ የተናገረው ነገር ታዳሚውንም ሰውዬውንም የማያስከፋ ምክንያታዊ ሀሳብ ነበር:: የመድረክ መሪው መልዕክት ሲጠቃለል፤ እንዲህ አይነት አባቶች የሚናገሩበት መድረክ ስላልፈጠርን፣ ከእነርሱ ለመማር ቁጭ ብለን ስላላደመጥናቸው፣ በዕድሜ ዘመናቸው ያካበቱትን የሕይወት ዘመን ልምድና ተሞክሮ ሁሉ የሚያወሩት እንደምንም መድረክ ሲያገኙ ነው ብሎ ሲናገር ልባዊ የአድናቆት ጭብጨባ ተችሮት ነበር::
ይሄ ነገር ለምን ተፈጠረ? ካልን በሁለት ምክንያት ይሆናል:: አንድ፤ በታዳሚው፤ ሁለት በራሳቸው በአዛውንቱ:: ታዳሚው ለምን እንዲህ አይነት እውቀት ሰለቸው? አዛውንቱስ የዕድሜ ዘመን ገጠመኛቸውን ሁሉ በአንድ መድረክ ያልቅ ይመስል ለምን ነገር ያስረዝማሉ?
መድረክ ላይ አንድ ችግር አለ፤ ጥልቅና ትንታኔ ያላቸው ነገሮች አይወደዱም:: የተለመደው የሚያስቅ ነገር ነው:: ከዚያ አለፍ ሲልም መንግሥትን ወይም የሆነን አካል የሚሳደብና የሚያስጨበጭብ ነገር ነው:: ለነገሩ አሁን አሁን በመድረክ ብቻ ሳይሆን በዋናዎቹ የመገናኛ ብዙኃንም የተለመደው ይሄው ሆኗል:: እንዲያውም እኮ መድረክ ሲዘጋጅ ታዳሚን ለማብዛት የሚጠቀሱት ሰዎች አስቂኝ ንግግር ያላቸውን ነው:: ጥልቅ ትንታኔ ያላቸው ነገሮች እየጠላን ነው:: እንዲያውም አንድ ሌላ ገጠመኝ ትዝ አለኝ::
የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ፍትሕ መጽሔት ወደ ገበያ ልትገባ በብሔራዊ ቴአትር የተዘጋጀ የምርቃት (ማስተዋወቂያ) የተዘጋጀ መድረክ ነበር:: በአዳራሹ መቆሚያ መቀመጫ እስከሚጠፋ ሰው ሞልቷል፤ አብዛኛው ወጣት ነው:: ዝግጅቱን አስመልክቶ አዝናኝም አስተማሪም አጫጭር ነገሮች ቀረቡ:: ፍትሕ መጽሔት ከዚህ በፊት ፍትህ ጋዜጣ ነበረች:: እናም ፍትሕ ጋዜጣን የሚዳስስ ጽሑፍ ሊያቀርብ ብርሃኑ ደቦጭ ተጋበዘ:: ገና ሲጀምረው የፍትሕን ብቻ ሳይሆን የሌሎችንም ጋዜጦች እያጣቀሰ ጥልቅ ትንታኔ ማቅረብ ጀመረ:: በትንታኔው ተመስጬ በጉጉት እያዳመጥኩ ሳለሁ ግን ሊቀጥል አልቻለም:: የ‹‹ይበቃሃል›› መልዕክት ያለው ጭብጨባ አስተጋባ:: ብርሃኑ ወረቀቱን ጠቅልሎ ወረደ:: በግሌ በጣም አፈርኩ፤ በጣም ተናደድኩ! ይህኔ እንቶፈንቶ አሉቧልታና ቀልድ ቢያወራ ኖሮ ጭብጨባው የአድናቆት ይሆን ነበር::
አንዳንድ ሰዎች ለምን ወደ መድረክ እንደሚሄዱ ሁሉ አይገባኝም:: ጉዳዩ ስለምን እንደሆነ በግልጽ ተነግሮ እያወቁት ይሄዳሉ:: አዳራሹ ውስጥ ሆነው ግን አይከታተሉትም፤ እንዲያውም ሌላም ሰው እንዳይከታተል ነው የሚረብሹት:: ፍትሕ መጽሔት ኮሜዲ አይደለም፤ እንዲያውም በጣም ጠንካራ (ሲሪዬስ) ነው የሚባለው ፖለቲካዊ ጉዳይ ላይ የሚያተኩር ነው:: እዚህ መድረክ የሄደ ሰው ታዲያ ምን ጠብቆ ነበር?
ወደ ዕድሜ ባለጸጎች እንመለስ:: ከእነዚህ አባቶች የምናገኘው እውቀት የመጀመሪያ ደረጃ መረጃ ነው፤ ያ ማለት ተናጋሪው የአይን እማኝ ናቸው ማለት ነው:: ያዩትን የኖሩትን ነው የሚነግሩን፤ ዳሩ ግን እንዲህ አይነቶቹን አንሰማም፤ ቆይ ግን እውነት አንወድም ማለት ነው?
በእርግጥ እንደ ወጣት ሆነን ካየነው በእርጅና ዕድሜ ላይ ያሉ ሰዎችም በባህሪያቸው ነገር ያስረዝማሉ፤ ምክንያቱ ግን ግልጽ ነው:: የሚናገሩበት ዕድል ስለሌላቸው ነው:: አንተ ወጣቱ በየገባህበትና በየሄድክበት ታወራዋለህ፤ ምክንያቱም ወጣት የሚንቀሳቀስበት አጋጣሚ ብዙ ነው፤ አዛውንቱ ግን ብዙ ቦታ አይሄዱም፤ ሲሄዱ ኖረው አሁን ቁጭ ብለው የሚናገሩበት ነበር፤ ሰሚ ቢገኝ ማለት ነው::
እንዲያውም ልብ ብለን ከሆነ መድረክ ላይ ሲወጡ ብቻ አይደለም ነገር የሚያስረዝሙት:: ታክሲ ውስጥም ይሁን የትም ቦታ ባገኛችሁት አጋጣሚ ልብ ብላችኋል? የሆነ ነገር ሲያዩ ወይም ሲሰሙ ዝም አይሉም፤ ይናገራሉ:: ባያዩና ባይሰሙ ራሱ ዝም ብለው ይናገራሉ:: ይመክራሉ፣ ይቆጣሉ፣ ይገስጻሉ:: ስሜታቸውን የማይረዳ ወጣት በውስጡም ቢሆን ‹‹ምን አገባው!›› ሊል ይችላል::
መድረክ ላይ ሲወጡ ነገር የሚያስረዝሙበት ምክንያት ይሄው ነው፤ የሚናገሩበት ዕድል ስላልነበራቸው ውስጣቸው ያለውን ለመናገር:: በነገራችን ላይ አዛውንቶች መድረክ ብቻ አይደለም ያሉት፤ መንደር ውስጥ ራሱ የሚያወሩበት ዕድል የለም:: ምናልባት የእነርሱ ዕድሜ እኩያ የሆኑ ካላገኙ በስተቀር ወጣቶች ከእነርሱ ጋር አያወሩም:: እነርሱ ደግሞ መምከርና መገሰጽ የሚፈልጉት ወጣቱን ነበር እንጂ አዛውንት ከአዛውንትማ ታሪካቸውና ገጠመኛቸው ይመሳሰላል::
እነርሱም እንዲህ የሚያወሩበትና የሚሰማቸው ሲያጡ ውስጣቸው የተጠራቀመውን ብሶት ሁሉ መናገር ይፈልጋሉ::
ምናልባት ግን መድረክ ላይ እንደዚያ በረጅሙ ካልተናገሩ ብሎ መፍረድም ይከብዳል:: ምክንያቱም መድረክ ማለት የተወሰነ ሰዓት ያለበት ነው፤ ሌሎች ፕሮግራሞችም የተያዙበት ነው:: ይህንን ዓውድ ደግሞ እነርሱ አይረዱም::
ከአባቶች እውቀት እንጠቀም ከተባለ ራሱን የቻለ መድረክ ማዘጋጀት፣ ያ እንኳን ባይቻል ቁጭ ብለን ብናዳምጣቸው፣ የመገናኛ ብዙኃን ዕድል ብንሰጣቸው:: ደግሞ እኮ ‹‹ተንቀሳቃሽ የቤት መጽሐፍ›› እያልን እንጠራቸዋለን፤ ግን አልተጠቀምንባቸውም::
መጽሐፍ እንኳን ስናነበው ‹‹ማነው የጻፈው?›› ብለን እንጠይቃለን:: የጸሐፊውን ምንነት እንጠይቃለን:: የብዙ ዓመት የሕይወት ልምድ ያላቸው ሰዎች ሲጽፉ የበለጠ ተፈላጊ ይሆናል፤ ይሄ ማለት የኖሩበትን ዘመን ለማወቅ እንጓጓለን ማለት ነው፤ የዓይን ምስክር ናቸውና ያጓጓል:: ስለዚህ በአንደበታቸው ሲናገሩም እንስማቸው!
የአባቶች እውቀት አይባክን!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 15 ቀን 2017 ዓ.ም