
-ቁልቁሉ ኢጆ -በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ጽሑፍና ቋንቋ መምህርና የባሕል ተመራማሪ
ቋንቋ ጥቅም ላይ ካልዋለ በጊዜ ሂደት መጥፋቱ አይቀሬ መሆኑ ተደጋግሞ ይነሳል። የቋንቋ መጥፋት ችግር ያጋጠማቸው ሀገራት መኖራቸውንም መረጃዎች ያመለክታሉ። ለዚህም ነው አፍ መፍቻ(እናት) ቋንቋን ጠብቆ በማቆየት ከትውልድ ወደ ትውልድ ማሸጋገሩ ቋንቋን ከመጥፋት ይታደጋል የሚባለው። መንግሥታት ለአፍ መፍቻ ቋንቋ ልዩ ትኩረት እንዲሰጡና ቋንቋዎች ተጠብቀው እንዲቆዩ አጽንኦት ለመስጠት የተባበሩት መንግሥታት የዓለም የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት(ዩኔስኮ) የአፍ መፍቻ ቋንቋ ቀን በየዓመቱ እንዲከበር ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል። ይህን ቀን እያከበሩ ካሉ ሀገራት አንዷ የሆነችው ባንግላዴሽ እኤአ ከ1952 ጀምሮ እያከበረች እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
የቋንቋ ብዝሀነት ያላት ኢትዮጵያም ትኩረት በመስጠት ዜጎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩ በትምህርት ሥርዓት ውስጥ አካታ መተግበር ከጀመረች ዓመታት ተቆጥረዋል። ትምህርቱ በአፍ መፍቻ ቋንቋ መሰጠቱ በመማር ማስተማሩም ሆነ በተለያየ መንገድ ከፍ ያለ ጠቀሜታ እያስገኘ እንደሆነና መልካም ጎኖች መኖራቸው ይጠቀሳል። በአፍ መፍቻ ቋንቋ እየተሰጠ ባለው የላቲን የፊደልና የቃላት አጠቃቀም ላይ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት ይገለፃል። ክፍተቶቹ ምን እንደሆኑና ስለመፍትሔዎቹ፣ እንዲሁም በቋንቋ ፖሊሲ ዙሪያ ማብራሪያ እንዲሰጡን እንግዳ ጋብዘናል። እንግዳችን መምህር ቁልቁሉ ኢጆ ይባላሉ። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ጽሑፍና ቋንቋ መምህር እና የባሕል ተመራማሪ ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን፡- እስኪ በቅድሚያ እንደ ሀገር ስላለው የቋንቋ ፖሊሲና አስፈላጊነት ይግለጹልን?
መምህር ቁልቁሉ፡- ኢትዮጵያን የመሩ በነበሩ በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን የቋንቋ ፖሊሲ ቢኖርም የቋንቋ ፖሊሲ ነበር ለማለት የሚያስደፍር አልነበረም። የነበረው ፖሊሲ አማርኛን እንደ ሀገራዊ ቋንቋ መጠቀም የሚል ነው። ሌሎችን ቋንቋዎች ወደ ጎን ያደረገ ብዝሀነትን የማያመለክት ወይንም አካታች አልነበረም። የአፄ ኃይለሥላሴ ሥርዓት ውድቆ የተተካው ወታደራዊ የደርግ ሥርዓትም የነበረውን ፖሊሲ ነው የተጠቀመው። በኢህአዴግ ዘመን ደግሞ ከሕገ መንግሥት መጽደቅ ጋር ተያይዞ ብዝሀነትን ለማካተት ጥረት ተደርጓል። ሆኖም ግን የሕዝብን አመለካከትና ፍላጎት የሚያንፀባርቅ በጥናት የተለየ የቋንቋ ፖሊሲ አልተዘጋጀም። መመሪያ ነው የነበረው፤ እንደ ሀገር በሶስቱም ሥርዓት የቋንቋ ፖሊሲ አልነበረም። ከሀገራዊ ለውጥ በኋላ ነው እንቅስቃሴ የተጀመረው። ከዛሬ ስድስት ዓመት በፊት በትምህርት ሚኒስቴርና ሳይንስ አካዳሚ መሪነት እንቅስቃሴ ሲጀመር እኔም የፖሊሲ ቀረፃ ዝግጅት ውስጥ አንዱ ነበርኩ። ሥራው በቡድን ተከፋፍሎ በሁሉም የሀገሪቱ አቅጣጫዎች እንዲከናወን ተወስኖ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ተገባ። ለፖሊሲው ግብዓት የሚሆን ከኦሮሚያና ጋምቤላ ክልሎች መረጃ ለመሰብሰብ (ለጥናት ሥራ) የተሰማራውን ቡድን የመራሁት እኔ ነበርኩ።
ጥናቱ ዓለም አቀፍ ሕጎችን መሠረት ያደረገ ነው። ዓለም አቀፍ ሕጉ ዜጎች በራሳቸው ቋንቋ መማር፣ መዳኘት፣ ቋንቋቸውን ማሳደግ ሰብዓዊ መብት መሆኑን ይደነግጋል። ተማሪ በሁለተኛ ቋንቋ እንዲማር ማድረግ ወይንም ጫና ማድረግ ቋንቋን መግደል (ሊንጉስቲክ ጂኖሳይድ መፈፀም)ተደርጎ እንደሚወሰድ ነው ዓለም አቀፍ ሕጉ የሚደነግገው። ዜጎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መማር አለባቸው ሲባልም ሰብዓዊ መብት እንደሆነም ይጠቅሳል። ይህን መነሻ በማድረግ ነው ሀገርኛና የውጭ ቋንቋ የሚያጠና የጥናት ቡድን ተዋቅሮ ሥራዎች የተሠሩት። በመረጃ አሰባሰቡ ሂደት ጥናቱ የሚያመላክተው ታች ላይ ትምህርቱ መሰጠት ያለበት በዋናነት በአፍ መፍቻ ቋንቋ መሆን እንዳለበትና በተጨማሪ ግን አንድ ተጨማሪ አንድ የሀገርኛና አንድ የውጭ ቋንቋ ታክሎበት ይሰጥ የሚለው ሃሳብ ሚዛን የደፋ ነው። ተጨማሪ ቋንቋዎቹ ከስንተኛ ክፍል ጀምሮ ይሰጥ የሚለው ግን የተለያየ ነው። ከሶስተኛ ክፍል፣ ከአምስተኛ ክፍል ይጀመር የሚሉ ነበሩ። የቋንቋ ፖሊሲው በዚህ መልክ ተዘጋጅቶ ነው ለሚመለከተው ክፍል የቀረበው።
የቋንቋ ፖሊሲ ከተዘጋጀ በኋላ ደግሞ የትምህርት ፍኖተ ካርታ(ሮድማፕ) ተዘጋጀ። እዚህ ላይ ለማስታወስ፤ በወቅቱም ለቋንቋ ፖሊሲ ግብዓት የሚሆን መረጃ እንድናሰባስብ የተመረጥነው አንድ ነገር እንዲስተካከልም አስተዋጽኦ አድርገናል። የቋንቋ ፖሊሲ ሳይዘጋጅ የትምህርት ፍኖተ ካርታ(ሮድማፕ) ቀድሞ ተዘጋጅቶ ነበር። የተፈለገው በአፍ መፍቻ ቋንቋ ትምህርት እንዲሰጥ ነው። የትምህርት አሰጣጡ በምን መልክ መሰጠት አለበት የሚለውም መልስ ማግኘት አለበት። ለዚህ ደግሞ የቋንቋ ፖሊሲ መቅደም አለበት የሚል መከራከሪያ ሃሳብ ተነሳ። በወቅቱም ጉዳዩ በመገናኛ ብዙኃንም አነጋጋሪ ሆኖ ስለነበር ሃሳቡ ተቀባይነት አግኝቶ እንዲዘገይ ተደረገ። የቋንቋ ፖሊሲ የማዘጋጀቱ ሥራ ከተጠናቀቀ በኋላ የትምህርት ፍኖተ ካርታ(ሮድማፕ) ከቋንቋ ፖሊሲ ጋር ተጣጥሞ ተዘጋጅቶ ሥራ ላይ ውሏል፡፡
አዲስ ዘመን፡- እየተሰጠ ባለው የአፍ መፍቻ ቋንቋ ትምህርት የፊደል እና የቃላት አጠቃቀም ላይ መታረም ያለባቸው ነገሮች እንዳሉ በተለያዩ የውይይት መድረኮች ላይ ይነሳል። በትምህርት ቤት ውስጥ መታረም ካልቻለ ደግሞ በሥራ ላይ ሆነ በመገናኛ ብዙኃን በሚሰጡ መረጃዎች ጭምር ሊንፀባረቅ የሚችልበት እድል ይፈጠራልና እዚህ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድነው? ክፍተቶቹስ ምንድናቸው?
መምህር ቁልቁሉ፡- ክፍተቶቹ የተለያዩ ናቸው። ለምሳሌ ብንጠቅስ አፋን ኦሮሞ ትምህርትና የሥራ ቋንቋ ሆኖ ሲመረጥ የአፋን ኦሮሞ ፊደል ቁቤ መሆኑ በክልሉ ምክር ቤት ፀድቋል። ሆኖም ግን የተለያዩ አመለካከቶች ይንፀባረቁ ነበር። ለምን በሳባ ፊደል አይጠቀሙም የሚሉ ነበሩ። ከክልሉ እውቅና ውጭ በሆነ መንገድ የቁቤ ፊደልን ቅደም ተከተል ለመቀየርም የተለያየ ጥረት ተደርጓል። ለመቀየር የተሞከረው ፊደልም (LGM)። ለዚህም እንደማሳመኛ ሲጠቀሙ የነበረው የፊደል መደጋገምን ቀላል እንደሚያደርገው ነው። የቁቤ የላቲን ፊደል ቅድም ተከተል (ABCD) አባጫዳ ነው።
የቁቤ ፊደል ቅደም ተከተልን ለመቀየር እየተደረገ ያለው ጥረት አግባብ እንዳልሆነ እኔም እንደ አንድ ባለሙያ ሃሳብ ከመስጠት አልተቆጠብኩም። በመጨረሻ ግን ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ክፍልና ምሁራንም አነጋግሮ ሰፊ ውይይት ተደርጎበት አግባብ እንዳልሆነ መግባባት ላይ ተድርሶ ለማስተካከል ተችሏል። የኦሮሚያን እንደ ምሳሌ አነሳሁ እንጂ በአጠቃላይ ክፍተቱ የነበረው በላቲን ፊደል የሚጠቀሙ እንደ ሲዳማ፣ ሶማሊያ ክልሎች ጭምር ነው።
እንዲህ ላለው ክፍተት መፈጠር ምክንያት የሚሆነው ለዚህ ሥራ ተብሎ ከዓለም አቀፍ ድርጅት የገንዘብ ድጋፍ ተገኝቷል። ገንዘቡን መጠቀም እንጂ ለሚመጣው የሥራ ውጤት ትኩረት አልተሰጠውም። በወቅቱ በተገኘው የገንዘብ ድጋፍ የትምህርት ውድቀት ላይ ሥራ እንዲሠራ ነው የሚል ነበር። ሆኖም የጥናቱ ዓላማ ግቡን ስቷል። ለትምህርት መውደቅ ምክንያቱ መጠናት ሲኖርበት የቁቤ ፊደል ቅደም ተከተልን ወደ መቀየር ተገባ። ይህ ሁኔታ የነበረው ከሰባት ዓመት በፊት ነው። የነበረውን ችግር ያነሳሁት ለፊደልና ቃላት አጠቃቀም ክፍተት መፈጠር አንዱ ምክንያት ይሆናል በሚል ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በፊደል ቅደም ተከተል አጠቃቀም ላይ የነበሩት ችግሮች ከተስተካከሉ አሁን ላይ ክፍተቱ ለምን ይነሳል?
መምህር ቁልቁሉ፡- እኔ እስከሚገባኝ ድረስ ለቃላቱ ለፊደሉ ትኩረት አለመስጠትና አለመጨነቅ ነው። ሌላው ብቃት ያላቸው መምህራንን አለመመደብ ነው። መምህራን የሥራ ምርጫ ያጡ መሆን የለባቸውም። ከሥር እውቀትና ክህሎት ይዞ የሚወጣ ተማሪ ለማፍራት ብቁ የሆኑ መምህራን መሆን ይኖርባቸዋል። ትክክለኛ የሆነ ፊደልና ቃላት አለመጠቀም ከባሕል፣ ከአካባቢ ነባራዊ ሁኔታ ጋር የሚያጋጭ ትርጉም ሊያስከትል ይችላል። ይሄ በቸልታ መታለፍ የለበትም ጥንቃቄ ሊደረግበት ይገባል። ችግሩ እየተከሰተ ያለው ጠብቆና ላልቶ ሲነበብ፣ እንዲሁም በአጭሩና በረጅሙ ሲነበብ የሚከሰት ችግር ነው እየተስተዋለ ያለው። አንድ ድምጽ ተቆርጦ ሁለት የሚሆንበት ወይንም ሁለት ተነባቢዎች ላይ ያለው ሥርዓተ ነጥብ(አፖስትሮፍ) በአግባቡ አለመጠቀም። ትኩረት ከተሰጠው ግን በቀላሉ ሊስተካከል የሚችል ጉዳይ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- እንደገለጹልን በትኩረት ማነስ የተፈጠረ ክፍተት ቢሆንም ማስተካከል የሚቻልበትም እድል አለ። ሆኖም ግን ችግሩ ተደጋግሞ እየተነሳ ነውና እንደ ምሁራን እርስዎን ጨምሮ ለማስተካከል ምን ተሠራ? ከማን ምንስ ይጠበቃል የሚለውን አክለው ይግለጹልን፡፡
መምህር ቁልቁሉ፡- መታረም አለበት። ለችግሩ ከሥር መፍትሔ እየሰጠን ካልሄድን ትንሹ ትልቅ ሆኖ ችግር ሊያመጣ ይችላል። በዚህ በኩል ምሁራንም ክፍተቱን ማሳየትና መፍትሔ የሚሆነውን በመጠቆም ድርሻ አላቸው። እኔ በኦሮምኛ ላይ የማስተውላቸውን ክፍተቶች በመለየት ለኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ እና ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ በተለያዩ መንገዶች ግብዓት እየሰጠሁ ነው። ሌሎችም የላቲን ፊደል ተጠቃሚዎች ክፍተቱን በማሳየት የመፍትሔ አቅጣጫ የሚሆን ይሰጣሉ ብዬ አስባለሁ።
በሥራ ላይ ያሉትም ቢሆኑ የቋንቋ ክህሎት ሥልጠና መውሰድ እንዳለባቸው፣በትምህርት ዘርፉም በተለይ ተማሪዎች ከታች መሠረት ይዘው እንዲወጡ ቋንቋን ጨምሮ መሠረታዊ በሚባሉ የትምህርት ዓይነቶች ብቃት ያላቸው መምህራንን መመደብ ላይ በልዩ ትኩረት እንዲሠራ ምሁራን ምክረ ሃሳብ ይሰጣሉ። ከዚህ ቀደም በነበረው የትምህርት ሥርዓት ሰልፍ ኮንቴንድ (አንድ አስተማሪ እስከ አራተኛ ክፍል ይዞ ይጓዝበት የነበረውና ፍሪ ፕሮሞሽን በሚባለው ተማሪዎች አራተኛ ክፍል እስኪደርሱ ድረስ ያለ ፈተና እንዲዘዋወሩ መደረጉ ለቋንቋ ጥራት መጓደል የራሱ አስተዋፅኦ ነበረው።
ከማን ምን ይጠበቃል ለተባለው። ድርሻው ይለያያል እንጂ የማይመለከተው የለም። አሁን ባለው ሁኔታ የትምህርት መዋቅሩ አሳሳቢ ነው። የትምህርት መዋቅሩ የጀርባ አጥንት መምህራን ናቸው። ሆኖም ግን በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ በሚፈለገው ልክ የጀርባ አጥንት የሚሆኑ መምህራን አሉን ወይ የሚለው ለእኔ ጥያቄ ምልክት ውስጥ ነው። በዚህ በኩል መታሰብ አለበት ሌሎች ሩቅ መሄድ ሳያስፈልግ ጎረቤት ሀገሮች የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ፣ በመምህራን አያያዝ የሚጠቀሟቸውን ዘዴዎች ተሞክሮ በመውሰድ ጭምር የትምህርት ዘርፉ ላይ መሠራት አለበት ብዬ አምናለሁ።
አዲስ ዘመን፡- የፊደልና የቃላት አጠቃቀም ላይ በተመሳሳይ ቋንቋ ተናጋሪዎችም አለመረዳዳትና አለመግባባት ሁኔታ አለ። በዚህ ላይ ምን ይላሉ?
መምህር ቁልቁሉ፡- ቋንቋውን ቢናገሩም መሠረታዊ የቋንቋ እውቀት አላቸው ማለት አይደለም። ከታች ጀምሮ በላቲን የተማረውና በሥልጠና ወይንም በግል ጥረቱ በላቲን መፃፍና ማንበብ የሚሞክረው እኩል ችሎታ ይኖረዋል ተብሎ አይጠበቅም። እነዚህ ሁሉ ናቸው ለክፍተቱ መፈጠር ምክንያት የሚሆኑት። እንዲህ ያለውን ችግር ለመፍታት እንደ ኦሮሚያ የፊደል አጠቃቀም ላይ መስፈርት (ስታንዳርድ) ወጥቷል። ትምህርት ቤቶች፣ የመገናኛ ብዙሃን፣ ሌሎችም ተቋማት የወጣውን መስፈርት ይጠቀማሉ ተብሎ ነው የሚጠበቀው። በኦሮምኛ የፊደል አጠቃቀም ላይ ክፍተቱ እየተፈጠረ ያለው የወጣውን መስፈርት ጠንቅቀው የማያውቁና የማይተገብሩ፣ በድፍረት ለመጠቀም ጥረት የሚያደርጉ ናቸው። የወጣው መመሪያ ተግባራዊ እንዲሆን ደግሞ መንግሥት ኃላፊነት አለበት፡፡
አዲስ ዘመን፡- እንደ ሀገር የሀገር ውስጥ ሀገር በቀል ቋንቋዎች በትምህርት ሥርዓት ውስጥ መተግበራቸው በመልካም ጎን ይወሰዳል። ግን ደግሞ በጥራትና በብቃት መተግበር ይኖርባቸዋልና ይህን መሠረት አድርገው ቀረ የሚሉት ሃሳብና መልእክት ካለዎት?
መምህር ቁልቁሉ፡- ከአፍ መፍቻ ቋንቋ በተጨማሪ አንድ የሀገር ውስጥ ቋንቋ በተጨማሪ በትምህርት ሥርዓት ውስጥ ተካትቶ እንዲሰጥ መደረጉና የማኅበረሰቡም ፍላጎት መሆኑ በጣም ጥሩ ነው ብዬ ወስዳለሁ። ምክንያቱም ማኅበረሰቡ እርስ በርሱ ለመግባባት ዕድል ይሰጣል። ያቀራርበዋል። አንዱ ስለሌላው ባሕልና ምንነት እንዲማር ያስችለዋል። ቋንቋ ላይ በጥራት ትምህርት ቢሰጥ ውጤታማ ተማሪዎችን ማፍራት እንችላለን። እኔ እስከማምነው ተማሪው ላይ የሚስተዋለው ችግር የቋንቋ ችሎታ እጥረት እንጂ የእውቀት አይደለም። ከፍተኛ ተቋም ዩኒቨርሲቲ ሲደርሱ በብዙ ተማሪዎች ላይ የሚስተዋለው ችግር የቋንቋ እጥረት ነው። ታችኛው ክፍል ላይ ጥሩ የቋንቋ ችሎታ ያላቸውን ተማሪዎች ማፍራት ከቻልን ግን ችግሩ ይፈታል። በአጫጭር ሥልጠናዎችም ተማሪዎች ቢታገዙ እንደ ሀገር የሚስተዋለውን የቋንቋ ክህሎት ክፍተት መፍታት ይቻላል። ተማሪዎችን የማብቃቱ ትልቁ ድርሻ መምህራን ላይ የሚወድቅ በመሆኑ ለመምህራንም ተከታታይ ሥልጠና በመስጠት እንዲበቁ ማድረግ ላይ ትኩረት ቢሰጥ እላለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ ከልብ እናመሰግናለን፡፡
መምህር ቁልቁሉ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 22 ቀን 2017 ዓ.ም