
የኢትዮጵያ እግር ኳስ እየተጓዘበት የሚገኘው መንገድ ማንኛውንም ኢትዮጵያዊ ቁጭት ውስጥ እንደሚከት ግልፅ ነው። እግር ኳሱ ከትናንት ዛሬ የተሻለ መሆን ሲገባው የቁልቁለት ጉዞው እየባሰበት ሲሄድ ማየት እንኳን ስፖርቱን በቅርበት ለሚከታተለው ማንኛውንም ኢትዮጵያዊ የሚያበሳጭና የሚያስቆጣ ነው።
ለእግር ኳሱ ከሚቆረቆሩ የስፖርት ቤተሰቦች አንስቶ እስከ ባለሙያዎች የሰላ ትችት ዘወትር መስማት አዲስ አይደለም። ብዙዎች በኢትዮጵያ እግር ኳስ ዙሪያ ቁጣቸውን ደብቀው ባያውቁም አንዳንድ ትችቶች፣ አስተያየቶችና ወቀሳዎች ግን ፈር እየሳቱ መጥተዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሰሞኑን ለ2026 የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ከግብፅና ከጅቡቲ ብሔራዊ ቡድኖች ጋር ጨዋታውን ከማድረጉ ቀደም ብሎ ሲሰነዘሩ የነበሩ አስተያየቶች መነጋገሪያ ሆነው ቆይተዋል። ትችቶቹና አስተያየቶቹ ለእግር ኳሱ ከመቆርቆርና ከቁጭት የመነጩ ናቸው። እንደዛ ናቸው ማለት ግን ትክክልና ተገቢ ናቸው ማለት አይደለም።
አንድ ጋዜጠኛ ብሔራዊ ቡድኑን በተመለከተ ሚዲያ ላይ ወጥቶ የሰጠው ትችት ወይም አስተያየት የኢትዮጵያን እግር ኳስ በተመለከተ በሃሳብ ደረጃ ትክክልና እውነት ነው። ይህንንም ብዙዎች አምነውበታል። ግን ትክክል የሆነ ነገር ሁሉ የሚነገርበት የቦታና የጊዜ አውድ ስህተት ሊሆን እንደሚችል ከሁሉም አቅጣጫ ማየት ተገቢ ነው።
የጋዜጠኛውን ትችት ተከትሎ የኢትዮጵያ ፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጫዋቾች ማህበር ያወጣው “አትድረሱብን” ዓይነት መግለጫም ተገቢነት የሌለውና ይባስ ብሎ በሚዲያውና በተጫዋቾች መካከል ቀጣይነት ያለው የብሽሽቅ ምዕራፍ የከፈተ ነው። ማህበሩ ያወጣው ማስፈራሪያ የሚመስል መግለጫ ብዙ ውሃ የሚቋጥር ስላልሆነ እሱ ላይ ጊዜ ማጥፋት አይገባም። ከዚያ ይልቅ ብሔራዊ ቡድኑ ላይ ስለሚሰነዘሩ ትችቶች ጉዳይ ምን መሆን ወይም ምን መምሰል እንዳለባቸው መነጋገሩ ለተሻለ ነገ ይበጃል።
ብሔራዊ ቡድኑ ከፊቱ ትልቅ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ እየጠበቀው ቡድኑን የሚያሳንስ፣ ተጫዋቾችን የሚያሸማቅቅ ቅስም ሰባሪ ትችትና አስተያየት የቱንም ያህል እውነት ቢሆን ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል። እግር ኳሱን ከገባበት አዘቅጥም ሊያወጣው አይችልም።
በቅድሚያ ብሔራዊ ቡድን ምንም ያህል ደካማ ቢሆን የሚወክለው ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ነውና ሊከበር ይገባል። ተጫዋቾቹም ቢሆኑ እግር ኳሱ አሁን ለሚገኝበት ደረጃ ተጠያቂ ተደርገው ሊወገዙ አይገባም። በዓለም አደባባይ እስከወከሉን ድረስ ልናከብርና ልናበረታታቸው ይገባል እንጂ የሀገራቸውን ማለያ በመልበሳቸው ልናሸማቅቃቸው የምንችልበት ምንም ዓይነት የሞራል ልዕልና ሊኖር አይችልም።
የእግር ኳሱ ችግር አሁን የሚጫወተው ብሔራዊ ቡድን አይደለም፣ የአስተዳደርና የሲስተም ነው። የእግር ኳሱን ደካማ አስተዳደርና ሲስተም መተቸትና ብሔራዊ ቡድንን መተቸት ደጎሞ ለየቅል ነው። ይሄ ብሔራዊ ቡድን ባለፉት በርካታ ዓመታት በተበላሸ የእግር ኳስ አስተዳደርና ሥርዓት ውስጥ የተፈጠረ ነው፣ በዚህ ሂደት ውስጥ የመጣን ቡድን አሁን ምን አድርግ ነው የምንለው?
አነስም በዛም በዚሁ የተበላሸ ሥርዓት ውስጥ የተገኙ ተጫዋቾች ሜዳ ላይ ለማሸነፍ ያላቸውን ሁሉ ይሰጣሉ፣ የቻሉትን ሁሉ ያደርጋሉ፣ ተጫዋቾች ባላቸው አቅም ሜዳ ላይ የቻሉትን ለማድረግ ይጥራሉ፣ ሲያሸንፉ ቀድመው የሚደሰቱት ሽልማትም ካለ የሚሸለሙት እነሱ ናቸው።
ሲሸነፉም ቀድመው ቅስማቸው የሚሰበረው የነሱ ነው። ውጭ ሆኖ ከሚናቆረው ይልቅ ማለያውን ለብሶ የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር ሲዘመር ምን ስሜት እንዳለው የሚያውቀው ተጫዋቹ ነው። ለዚህ ደግሞ ልናመሰግናቸው እንጂ የሌላቸውን አምጡ ብለን በቅስም ሰባሪ ትችቶች አፈር ከድሜ ማብላት ምክንያታዊም አይደለም።
እግር ኳስ የብዙ ነገሮች ድምር ውጤት መሆኑ ለማንም አይጠፋውም፣ ከነዚህ ነገሮች አንዱ ሥነ ልቦና ነው። ተጫዋቾቻችን አይችሉም ብለን እኛው ቀድመን ደምድመን በሚዲያ ሞራላቸው ላይ ቀዝቃዛ ውሃ ከቸለስን በኋላ ሜዳ ላይ ምን እንዲፈጥሩ እንጠብቃለን። በሁሉም ሀገር ብሔራዊ ቡድን ይተቻል፣ ብዙ አስተያየትም ይሰጥበታል።
ግን ክብር የሚነፍግና ቅስም የሚሰብርና ዝቅ የሚያደርግ አይደለም። የእኛ ግን በተቃራኒው ሆነ። ይባስ ብለን ሜዳ ላይ ሲታገልና ሲለፋ የሚታይን የብሔራዊ ቡድን ተጫዋች በተቀነባበረ ፎቶግራፍ የሌለውን ትክለ ሰውነት አልብሰን ማሸማቀቅን ፋሽን አድርገነዋል። ይሄ ነውር ነው!
ብሔራዊ ቡድኑ የፌዴሬሽኑ ኃላፊዎች አይደለም። የአሰልጣኙና የተጫዋቾቹም አይደለም። የሁሉም ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ነው። ድል ከመጣም እንደ ሀገር ኢትዮጵያ አሸነፈች ነው የሚባለው። ሽንፈትም ከሆነ ኢትዮጵያ ተሸነፈች ነው የሚባለው። ድሉም ሽንፈቱም የእኛ ነው። ለዚህ ነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን በሚመለከት የሚሰጡ አስተያየቶች ገደብ ሊበጅላቸው ይገባል የምንለው!
ለብሔራዊ ቡድን ውጤት ማጣትና ተቆርቋሪነትን ማሳየት አንድ ነገር ነው። ግን ደግሞ ብሔራዊ ቡድን የሚደገፈው ውጤታማ ሲሆን ብቻ አይደለም። ውጤት በራቀውና ቀውስ ውስጥ በገባበት ወቅትም ወደሚፈለገው ደረጃ እንዲመጣ መደገፍ ለስፖርት ቤተሰቡ የሚነገር አይደለም።
እኛ ግን የያዝነው ተገቢ ያልሆነ ትችትና ዘለፋን እንደተቆርቋሪነት ነው። በተቃራኒው ቡድኑ በደከመና ውጤት በራቀው ሰዓት የምናዥጎደጉደውን ትችት ያህል ከስንት አንዴ በሚያሳየው ጥሩ ብቃትና ውጤት ማበረታታትና የጎደለውን በመሙላት ላይ ግን እምብዛም ነን።
በዚህ ምክንያት ለብሔራዊ ቡድን መጫወት የሁሉም ተጫዋች ጉጉትና ፍላጎት ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለብሔራዊ ቡድን ጥሪ ቀርቦላቸው “ይቅርብን” የሚሉ ተጫዋቾች እየተፈጠሩ ነው። ነገ ወጣቶች ለብሔራዊ ቡድን ሲጠሩ አመመኝ ብለው በሰበብ ባስባቡ እንዲቀሩ እየተሠራ ነው። ለብሔራዊ ቡድን መጫወት ክብር ሳይሆን ውርደት አድርገው እንዲቆጥሩ እየተደረገ ነው።
እግር ኳሱ በውስጡ በርካታ ገንዘብ ይዘዋወርበት እንጂ አሠራሩ እጅግ ደካማ ነው። የራሳቸው መለማመጃ ሜዳ ያላቸው ክለቦች እንኳን ስንት ናቸው? ስታዲየምና ጂምናዚየም ቅንጦት ነው። ብዙ ነገሮች ባልተሟሉበት ሁኔታ ተጫዋቾችና አሰልጣኞች በራሳቸው ጥረት ብሔራዊ ቡድን ደረጃ ይደርሳሉ፣ ችግሮቹም አብሯቸው ይሄድና ውጤት አልባ ጉዞ ያደርጋሉ።
ሕዝቡም ቀጥታ ሜዳ ላይ ያለውን ነገር ብቻ ስለሚያይ ይበሳጫል..ሕዝቡ ላይ አይፈርድም! ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት ግን መፍትሔ ማምጣትና ማቅረብ ሲገባቸው አብረው ቡድኑን ያወግዛሉ፣ ይሰድባሉ። በዚህ ሁኔታ ወደባሰ ነገር ውስጥ እና ተጫዋቾች በሰበብ ላለመጫወት ይወስናሉ እንጂ የሚመጣ ለውጥ የለም። ችግሩ ላይ መሥራት ብቻ ነው የሚያዋጣው።
የኢትዮጵያ እግር ኳስም ይሁን ብሔራዊ ቡድኑ ተመሳሳይ ድክመትና የማይቀየር ማንነት ይዞ መጓዝ የጀመረው ዛሬ አይደለም። እንደ ወርቃማ ጊዜ ልናነሳ ከምንችለው 1950ዎቹ እና 60ዎቹ ውጭ የኢትዮጵያ እግር ኳስ እና ብሔራዊ ቡድኑ ለግማሽ ክፍለ ዘመን ለሚጠጋ ጊዜ ደካማ ነበር። በመካከል የነበሩ ስኬቶች ከብልጭ-ድርግም ያለፉ አልነበሩም። እንደጉድ የሚወራላቸው የ70ዎቹ፣ 80ዎቹ እና 90ዎቹ ከዋክብት ከሴካፋ ድሎች ያለፈ አልነበራቸውም። ከማጣሪያ ተሳትፎዎች የዘለለ አፍን ሞልቶ ለመናገር የሚያስችል ታሪክ አልነበራቸውም።
የሰሞኑ ሽንፈቶችም ሆኑ ድሎች ካለፉት የተለዩ አይደሉም። ብሔራዊ ቡድኑ ካለፉት ዘጠኝ የፉክክር ጨዋታዎቹ ሁለቱን ብቻ አሸንፏል። የምድቡ የመጨረሻ ሆኖ ከአፍሪካ ዋንጫ ውድድር መውጣቱን አረጋግጧል። በዓለም ዋንጫ ማጣሪያም በምድቡ ጂቡቲን ብቻ በልጦ አምስተኛ ላይ ይገኛል። ለእግር ኳሱ እና ብሔራዊ ቡድኑ መቀንጨር የሚነሱ ምክንያቶችም ግን አልተቀየሩም። ቢያንስ የግል የስፖርት ጋዜጦች መታተም ከጀመሩበት 80ዎቹ አጋማሽ/መጨረሻ አንስቶ አስተዳደር (ፌዴሬሽን፣ ሊግ፣ ክለቦች…)፣ የተሰጥኦ እድገት፣ ሥልጠና፣ የተጨዋቾች ባሕሪይ…ወዘተ ዛሬም ቀጥለዋል።
የሚያስገርመው በዚህ ሁሉ ጊዜ ውስጥ የሜዳ ድክመቶቻችን እና ከስንት ጊዜ አንዴ ብልጭ የሚለው ጥንካሬያችን ተመሳሳይ መሆኑም ነው። የመከላከል መደራጀት፣ የመከላከል ሽግግር፣ የቆሙ ኳሶችን መከላከል፣ በወሳኝ ጊዜያት ትኩረት ማጣት፣ የኳስ ቁጥጥርን ወደጎል እድሎች እና ወደ አደጋዎች መለወጥ አለመቻል የማይታረሙ ችግሮቻችን ናቸው። ከኳስ ጋር ያለ ምቾት እና ማራኪ ቅብብል ብቻ በአንፃራዊነት የቡድኑ ጥንካሬ ናቸው። ሆኖም የዚህ ዘመን ደካማነት ከቀደሙት (70ዎቹ፣ 80ዎቹ፣ 90ዎቹ እና 2000ዎቹ) የከፋ መሆኑ ነው።
ለዚህ አንዱ ምክንያት የአፍሪካ እግር ኳስ ላለፉት 15 ዓመታት እየተቀራረበ መሆኑ፣ ቀድሞ እጅግ ደካማ የነበሩ ሀገራት ፍፁም ተሻሽለው ትልልቆቹን መፈተን መጀመራቸው፣ የእኛ ብሔራዊ ቡድን ግን ለዚህ አለመብቃቱ ነው። ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ኮሞሮስ፣ አንጎላ፣ ጋምቢያ፣ ማዳጋስካር፣ ኬፕ ቬርዴ፣ ዩጋንዳ፣ ሞሪቴኒያ በተደጋጋሚ ኃያላኑን እየተገዳደሩ፣ በአፍሪካ ዋንጫ በተደጋጋሚ እየተሳተፉ ይገኛሉ። እንደ ሱዳን፣ ቤኒን፣ ሞዛምቢክ፣ ታንዛኒያ፣ ቦትስዋና እና ዚምባቡዌ ዓይነቶቹም ዋሊያዎቹ በማይሳተፉበት ቀጣዩ አፍሪካ ዋንጫ ይወዳደራሉ። ቡድኑ ከ24 የአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊዎች መካከል አለመገኘቱ እጅግ አሳዛኝ ነው። ከአፍሪካ ሁለተኛውን የሕዝብ ብዛት የያዘች ለዚያውም ‘የወጣት ሀገር’ እና እግር ኳስ በተወዳጅነት ቀዳሚ የሆነባት ሀገር እዚህ ደረጃ ላይ መገኘቷ አስገራሚም የሚያስቆጭም ነው።
ለዚህ ውድቀት አንድ ወይም ጥቂት ወገኖችን ብቻ ተጠያቂ ማድረግ ግን ፍትሀዊ አይሆንም። ሜዳ ተገኝተው የሚጫወቱት ተጨዋቾች እና አሰልጣኞች ቀዳሚ ተወቃሽ ሊሆኑ የሚችሉት ጨዋታዎች ላይ በሚያሳዩት ብቃት ብቻ ነው። ነገር ግን ክለቦች፣ ሊጉ፣ ፌዴሬሽኑ፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ወይም መንግሥትም ከቀጥታ ተጠያቂነት አያመልጡም።
ከስፖርት ፖሊሲው ጀምሮ፣ የመሠረተ-ልማት፣ የዋናው ፌዴሬሽን እና የክልል ፌዴሬሽኖች አመራርና አሠራር፣ የክለቦች አስተዳደር፣ የወጣቶች እድገት፣ የአሰልጣኞች ሥልጠና እና እድገት፣ የአሰልጣኞች ለሙያው መሰጠት፣ ራስን ማብቃት እና ሥነ-ምግባር እንዲሁም የተጨዋቾች ዲሲፕሊን እና ፕሮፌሽናሊዝም…እና ሌሎች ያልተጠቀሱ ጉዳዮች ሁሉ የውድቀታችን ምክንያት ናቸው።
አሳዛኙ እና ለተስፋ መቁረጥ የሚያቃርበን በተዘረዘሩት ሁሉ እጅግ ደካሞች መሆናችን ነው። ታዲያ እንዴት መሻሻል እና ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን መገንባትን ልንጠብቅ እንችላለን?! ምናልባት እንደ 2004/05ቱ ቡድን አንድ ጥሩ ትውልድ ለጥቂት ዓመታት ሊያፎካክረን፣ የተሻሻልን ሊያስመስለን ይችላል። ግን በተጠና እና በተንሰላሰለ ሥራ የመጣ ስላልሆነ ዘላቂ ሊሆን አይችልም። በእነዚህ መሠረታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ላለፉት ዓመታት በጣም ብዙ ስለተባለ ከዚህ በላይ ማብራራት ረብ የለውም።
ጊዜ ወስደን በነዚህ መሠረታዊ ነገሮች ላይ ወንበር ስበን ከመወያየት ይልቅ ሁሉም ጥጉን ይዞ መዘላለፍና መበሻሸቅ እንጂ እግር ኳሱን ከሞተበት ለማንሳት የየራሱን ጠጠር ለመወርወር አልታደለም ወይም ፍላጎት የለውም። ይህ መበሻሸቅ ቡድኑ ጅቡቲን ካሸነፈ በኋላም እልህ ውስጥ በገቡ ተጫዋቾች ከድሉ በኋላ ባሳዩት ድርጊት ቀጥሏል።
ተጫዋቾችም ቢሆኑ ከእንዲህ ዓይነቱ ድርጊት ራሳቸውን ቆጥበው ፕሮፌሽናሊዝምን በተግባር ማሳየት አለባቸው። ይህ አንድ ቦታ መቆም አለበት፣ የግል ፀብ ያለ ይመስል በየማህበራዊ ሚዲያው መጠዛጠዙ ለእግር ኳሱ አንዳች ነገር አይፈይድም። ቅስም ሰባሪ ትችቶችና መበሻሸቅ እግር ኳሱን ቢታደግ ኖሮ የእስከዛሬው የዓለም ዋንጫ እንድናሸንፍ ባደረገን ነበር። ምን ብናደርግ ይሻላል? ብለን በሰለጠነ መንገድ እንወያይ፣ ወደ ቀልባችን እንመለስ!
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 22 ቀን 2017 ዓ.ም