
ከስድስት ወራት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ የህዳሴው ግድብ ምርቃት እንደሚካሔድ ከሰሞኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል። ለምርቃቱ ስንበቃ ግድቡ ዕውን እንዲሆን ብዙ ዋጋ የተከፈለ መሆኑ አይዘነጋም ። ከ14ዓመት በፊት የመሠረት ድንጋይ ከተጣለበት ጊዜ ጀምሮ፤ የነበሩ ፈታኝ ጉዞዎች ለማንኛውም ኢትዮጵያዊ የሚረሱ አይደሉም፡፡
ከነበሩ ፈተናዎች መካከል ግንባር ቀደሙ የዓባይ ወንዝ ድንበር ተሻጋሪ በመሆኑ፤ የታችኛው ተፋሰስ አገሮች ጥቅማችን ይቋረጣል ብለው በመስጋታቸው በተደጋጋሚ በተለያየ መልኩ ጫና ለመፍጠር መሞከራቸው አንደኛው ነው።
የአማራ፣ የትግራይ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና የኦሮሚያ ክልልን መሬት እየሸረሸረ ለግብፅ ሲገብር የኖረው የዓባይ ወንዝ፤ በዛው ኢትዮጵያን መጉዳቱን እንዲቀጥል፤ መሬቷን ማራቆቱን እንዳይቀንስ፣ ሀገሪቱ እንዳታድግ እና በድህነት እንድትማቀቅ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው የታችኛው የተፋሰሱ ሀገሮች ደጋግመው አሳዩ።
ኢትዮጵያ ለዘመናት ዋጋ ስትከፍልበት የቆየችበትን የዓባይ ወንዝ እጠቀምበታለሁ ስትል፤ ግብፅ በግልፅ በተቃርኖ ቆማ የዓለም አቀፍ ሕግ መሠረታዊ መርሆችን ወደ ጎን በመተው ለማደናቀፍ ብዙ ደከመች። ሊፈፀም እና ሊሆን ማይችለውን የቅኝ ግዛት ስምምነት ይተግበር በማለት ኢትዮጵያ በወንዙ ላይ ያላትን የማልማት መብት ለመጋፋት ጮኸች።
ኢትዮጵያ ግን በወንዙ የመጠቀም መብት እንዳላት ከመጠቆም ውጪ ምንም አላለችም። ኢትዮጵያ ፍቅር እና ሰላም ላይ ተመሥርታ የባለሙያዎች ቡድን እንዲቋቋም ሱዳን ተጨምራ የሦስትዮሽ ውይይቶች እንዲካሄዱ ተስማማች።
ኢትዮጵያ ለንግግር እና ለድርድር በሯ ክፍት መሆኑን ደጋግማ አሳወቀች። አልፋ ተርፋ ብዙ ሁኔታዎችን አመቻቸች። ሆኖም ግብፆች በአግባቡ ከመነጋገር ይልቅ ግድብ መገንባቱ የግብፅን ጥቅም ይጎዳል በሚል ጭፍን አስተሳሰብ ጩኸታቸውን ቀጠሉ። የሚነጋገሩ ዜጎቻቸውን መልምለው ለውይይት ቢያቀርቡም፤ ተደራዳሪዎቹ ግብፃውያን ግትር አቋም ይዘው በመምጣት በተደጋጋሚ የተሳካ ምክክር እንዳይኖር ስብሰባዎችን ረግጠው ይወጡ እንደነበር አይዘነጋም።
ድንቅ የኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች አንድ ሦስተኛ አፈር እየሸረሸረ፤ ኢትዮጵያውያንን ለከፋ ረሃብ እያጋለጠ ግብፅን እያጠገበ ዘመን ሲያስቆጥር የኖረው ዓባይ ኢትዮጵያን መጥቀም እና ማገልገል አለበት ሲሉ በብልሃት እና በምርጥ ዲፕሎማሲያዊ መንገድ ብዙ ሞገቱ።የኢትዮጵያ አቋምም ሆነ ፍላጎት የታችኞቹን የተፋሰሱን ሀገሮች መጉዳት አለመሆኑን፤ ሆኖም ወንዙ
መጠቀም የሕልውናችን ጉዳይ መሆኑን ደጋግመው አስገነዘቡ።
ግብፅ አላረፈችም፤ ከመደራደር ጎን ለጎን የተለያዩ ሴራዎችን ስትሠራ ቆየች።ማንኛውም ድጋፍ እና ርዳታ እንዳይገኝ ከማድረግ ጀምሮ፤ መርዝ የበላች መድረሻ ያጣች ዓይጥ እንደምትሠራው በተለያዩ መንገዶች የግድቡን ግንባታ ማስቆም ሞከረች። ሆኖላት ጦር ባትሰብቀም፤ ኢትዮጵያን ለማመስ ሰማይ ለመቧጠጥ ሞከረች።
የግብፅ መንግሥታት ሥልጣን ላይ በወጡ ቁጥር በየመድረኩ የህዳሴውን ግድብ ማስቆም የአፋቸው ማሟሻ አደረጉት። የመጡ የሄዱ የግብፅ መንግሥታት የህዳሴው ግድብን ማስቆም ድጋፍ መሰብሰቢያ እና በግብፅ ሕዝብ ተቀባይነት ማግኛ አደረጉት። ነገር ግን እንደአፋቸው እና እንደምኞታቸው አልሆነም። ግብፅ የግድቡ ግንባታ ሦስት አራተኛው ተገባዶ የውሃ ሙሌት ሲጀመርም አላረፈችም። የውሃ ሙሌቱን በተመለከተ ‹‹ኡኡ..›› አለች።
የግድቡን የውሃ ሙሌት ጉዳይ በማጦዝ ዓለም አቀፋዊ ለማድረግም የተለያዩ ጥረቶችን አደረጉ። የውሃ ሙሌቱ ሲካሔድ የግብፅ ሕዝብ በረሃብ ያልቃል፤ አሞላሉ በብዙ ዓመታት የተከፋፈለ እና ከአስር ዓመት በላይ የሚፈጅ ሊሆን ይገባል ማለት ዓለም ይስማን አሉ።
የግንባታው ሂደት ከፈጀው ጊዜ ባልተናነሰ መልኩ የውሃ ሙሌቱም ብዙ ዓመታትን እንዲፈጅ መጎትጎታቸውን ቀጠሉ። በግብፅ ግፊት የዓረብ ሊግ አባል ሀገራት መግለጫ እስከማውጣት ደረሱ። በአሜሪካን አማካኝነት ጫና ለመፍጠርም ሮጡ። ነገር ግን ሁሉም አልሆነላቸውም፡፡
የውሃ ሙሌቱ ተጀመረ።ውሃ ይቀንሳል የሚል መነሻ ቢኖራቸውም፤ እንዳሉት አልሆነም።ቀድሞም ቢሆን ጥያቄያቸው ከስግብግብነት የመነጨ እንጂ እውነታ ላይ ያልተመሠረተ በመሆኑ ወደ ግብፅ የሚሔደው ውሃ እንኳን ሊቀንስ ጭራሽ በጎርፍ ተጥለቀለቁ።
መጀመሪያም ኢትዮጵያ የመጠቀም መብቴን አትንፈጉኝ አለች እንጂ፤ ማንንም የመጉዳት ፍላጎት እንዳልነበራትና ግራለች።በተደጋጋሚ የግድቡ መገንባት በፍሰቱ ላይ ጉልህ ለውጥ አይኖረውም ብላ ነበር።ይህ በአደባባይ እውነት መሆኑ ተረጋገጠ።ኢትዮጵያ ቃሏን ፈፀመች።ጊዜው ደርሶ ኢትዮጵያ ያለምንም ብዙ ችግር ሙሌቱን አጠናቀቀች።
በሌላ በኩል ሌላዎቹ ፈተናዎች የፋይናንስ እና በግንባታው ሂደት ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮች ነበሩ።ኢትዮጵያ ኃይል መንጫውን መገንባት የሕልውና ጉዳይዋ መሆኑን ብታስረዳም ዓለም ያንን ለመረዳት ፈቃደኛ አልነበረምና ገንዘብ ማግኘት አዳጋች ሆነ።ዓለም ባንክም ሆነ ሌሎች አበዳሪዎች ኢትዮጵያ የህዳሴውን ግድብ ለመገንባት የምትፈልገውን ገንዘብ ለማበደር ፈቃደኛ አልሆኑም።
ይህ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከግብፅ ሴራ ጋር የተገናኘ ነበር።ኢትዮጵያውያን በእልህ ለሚመጣ ለማንም የማይመለሱ በመሆናቸው፤ ዓለም የገንዘብ ድጋፍ አላደርግም ብሎ ቢያድምም ኢትዮጵያውያን ግን ‹‹ማንም ድጋፍ እና ርዳታ ባይሰጥም በራሳችን አቅም እንሠራዋለን›› ብለው ተነሱ።
በየትምህርት ቤት ካሉ ሕፃናት ተማሪዎች ጀምሮ ጡረተኞች ሳይቀሩ ሁሉም እንደየአቅሙ ለህዳሴው ግድብ ግንባታ የሚችለውን አዋጣ። በቢሊዮን የሚቆጠሩ ብሮች ተሰበሰቡ። የወጪው ችግርም ኢትዮጵያውያን ተባብረው ተወጡት።
በግንባታው ወቅት የአየር ፀባዩ እጅግ ሞቃታማ መሆኑ ግንባታውን የሚያከናውኑ ባለሙያዎች እና የግድቡን ግንባታ ሲጠብቁ የነበሩ የፀጥታ አስከባሪዎችን የፈተነ ነበር። በተጨማሪ ውሃው የሚተኛበትን መሬት ለማስተካከል ምንጣሮ በማካሔድ ሂደት ውስጥ ብዙዎች ዋጋ ከፈሉ፡፡
አሁን ግን ሕይወትን እስከመስጠት የደረሰ መስዋዕትነት የተከፈለበት የግድቡ ግንባታ የሚጠናቀቅበት ደረጃ ላይ መድረስ ተቻለ። ምስጋና ለተደራዳሪዎቻችን፣ ግንባታውን ላካሄዱት ባለሙያዎች እና በብዙ መንገላታት ውስጥ ሆነው ሳይቀር ያላቸውን ሳይሰስቱ ለሰጡ ኢትዮጵያውያውን ይሁንና ለምርቃት ደረስን። ለእዚህም ሁላችንንም እንኳን ደስ አለን እንላለን።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 22 ቀን 2017 ዓ.ም