
ኢድ ማለት በዓረብኛ ተመላላሽ ማለት ነው። በየዓመቱ ተመላልሶ የሚመጣ ማለት ነው። ኢድ የተከበረ ቀን ነው፤ በየዓመቱም ተመላልሶ ይመጣል። ይሄ ቀን ታሪክ አለው። ነብዩ መሐመድ ከመካ ተሰደው መዲና ሲገቡ እምነት አልባ ሰዎች በአካባቢው ይኖሩ ነበር። እነዚህ እምነት አልባ ሰዎች በዓመት ውስጥ ሁለት በዓላትን ያከብሩ ነበር። እነዚህ የክብረ በዓላት ቀናት ለጨዋታ እና ለጭፈራ ብቻ ነበር የሚያውሏቸው። ከጨዋታ እና ጭፈራ ውጭ ቁም ነገር አልነበራቸውም፡፡
ነብዩ መሐመድ መዲና ሲገቡ አላህ በራሱ ፈቃድ በቁርዓን አማካኝነት ትዕዛዝ አስተላልፎላቸው ነበር። እነዚህ በጭፈራ እና በዳንኪራ ያልፉ የነበሩ በዓላትን ወደ ምስጋና እና ሃይማኖታዊ በዓል እንዲለወጡ አላህ በመፍቀዱ ኢድ አልፈጥር እና ኢድ አልአድሃ በሚል ሁለት በእስልምና የተከበሩ ሃይማኖታዊ በዓላት ለመሆን ቻሉ። እነዚህም በዓላት የፍቅር፤ የአንድነት፤ የአብሮነት እና የመረዳዳት በዓላት በመሆን ዛሬ ድረስ ዘልቀዋል፡፡
ኢድ የደስታ በዓል ነው። ኢድ አልፈጥር የቅዱሱ ረመዳን ወር ጾም መፍቻ በዓል በመሆኑ በጾም ውስጥ ከምግብና ከመጠጥ እንዲሁም ከአላስፈላጊ ተግባራት ተቆጥቦ የቆየ ሰውነት ወደተለመደው የአመጋገብ ሥርዓት የሚመለሰብትና ይህንኑም ከወዳጅ ዘመድ ጋር ማዕድ አብሮ በመቋደስ በደስታ የሚዋልበት ቀን ነው።
ከኢድ ትሩፋቶች ውስጥ አንዱ መረዳዳት ነው። በረመዳን እና በኢድ ወቅት አቅም የሌላቸው ወገኖች እንዳይቸገሩ በማሰብ የሚፈጸሙ ሁለት ዓይነት የምጽዋት ዓይነቶች አሉ። ዘካተል ፊጥሪ እና ዘካለተል ማል በመባል ይታወቃሉ፡፡
ዘካተል ፊጥር ማለት ማንኛውም ሙስሊም የረመዳንን ወር ደርሶ የዒድ ሌሊትን ያገኘ የሆነሰው ለድሆች ሊሰጠው የሚገባ የተመጠነ የምግብ ዓይነት ነው። ዘካተል ፊጥር በረመዳን ወቅት ጾመኞች ጾመው ከማጠናቀቃቸው በፊት የሚሰጥ ነው። ዘካተል ፊጥር አንድ የእስልምናእምነት ተከታይ በጾም ወቅት ጾሙን የሚያጎሉበት ስህተት ቢፈጽም ያን ስህተት ለማስፋቅ እና ጾሙን ሙሉ ለማድረግ የሚሰጥ ስጦታ ነው። ስጦታው ደግሞ ለምስኪኖች እና ለጾም አዳሪዎች ነው፡፡
እያንዳንዱ ሰው ካለው ነገር ላይ እንዲሰጥ ተወስኗል። የስጦታው መጠንም በመካከለኛ እድሜ ባለ ሰው እፍኝ አምስት ወይም ሁለት ነጥብ አምስት ኪሎ ግራም የሚመዝን ነገር እንዲሰጥ የነብዩ መሐመድ (ሶዐወ) ተከታዮች ወስነዋል። ዘካ ግዴታ ነው፤ ማንኛውም የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ የሆነ ሁሉ ሊያወጣው የሚገባ ተግባር ነው፡፡
ዘካተል ፊጥር እንደሚሰጠው ስጦታ የሚሰጥበት ቀን ይለያያል። የሚሰጠው ነገር ወደ ምግብነት ያልተቀየረ ከሆነ ተቀባዩ የተቀበለውን ነገር ወደ ምግብነት ቀይሮ እንዲጠቀም ከአንድና ከሁለት ቀን ቀድሞ መሰጠት አለበት። የሚሰጠው ደግሞ የኢድ ሶላት ተሰግዶ ከማለቁ በፊት ነው። ከዚህ ካለፈ ምጽዋት ተደርጎ የሚቆጠር ይሆናል። ዘካተል ፊጥር ተሚር፣ ስንዴ፣ ገብስ፣ ዘቢብ እና ሌሎች ለምግብነት የሚያገለግሉ የእህል ዘሮች ሊሆኑ ይችላል። የእህል ዓይነት መስጠት ያልቻለ በገንዘብ ተምኖ መስጠት ይችላል፡፡
ሁለተኛው ዓይነት ምጽዋዕት ደግሞ ዘካተል ማል ይባላል። ዘካተል ማል በዓመት አንድ ጊዜ የሚሰጥ አቅም ያላቸው ሰዎች የሚሰጡት ምጽዋዕት ነው። አቅም ያላቸው ወገኖች ከፍ ያለ ገንዘብ ለድሆች የሚያከፋፍሉበት ሥርዓት ሲሆን ይህም ሰዎች ከተራዘመ ተመጽዋችነት ወጥተው ራሳቸውን የማስተዳደር አቅም እንዲኖራቸው የሚያስችል ነው። ይህ ደግሞ ተረጂነትን በዘላቂነት ለማስወገድ የሚያስችል ነው። ስለዚህም የዘንድሮውን 1446ኛውን የኢድ አልፈጥር በዓል ስናከብር እነዚህን ኢድ እሴቶች ከግምት ውስጥ በማስገባት ሊሆን ይገባል፡፡
የመረዳዳት ባሕሉ በሙስሊሞች ዘንድ ብቻ የሚታጠር አይደለም። ኢትዮጵያውያን ዘር፤ ቀለምና ሃይማኖት ሳይለዩ የተቸገረን መርዳት፤ የተራበን ማብላት፤ የተጠማን ማጠጣትና የታረዘን ማልበስ ያውቁበታል። እንኳን እርስ በእራሳቸው ይቅርና ባህር አቋርጦ፤ ድንበር ተሻግሮ ለመጣ ስደተኛ ጭምር በራቸውን ክፍት አድርገው፤ ያላቸውን አካፍለውና ፍቅር ለግሰው ማኖር የሚችሉ ሕዝቦች መሆናቸውን በርካታ የታሪክ መዛግብት የሚያወሱት ሃቅ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ስደተኞችን የመቀበል የቆየ ታሪክ ያላት ሀገር ነች። ኢትዮጵያውያን ከመካ የተሰደዱ የነብዩ መሐመድ ተከታዮችንና ቤተሰቦችን ተቀብላ በማስተናገድና በማኖርና የጎላ ታሪክ ያላትና ለእስልምና ሃይማኖትም ባለውለታ ተደርጋ የምትቆጠር ሀገር ከመሆኗም ባሻገር ይህ አኩሪ ታሪክ ሺህ ዘመናትን ተሻግሮ ዛሬም ድረስ ከ1 ሚሊዮን በላይ ስደተኞች ተቀብላ በእንክብካቤ የምታስተናግድ ሀገር ነች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተለያዩ የእስልምና በዓላትን ምክንያት በማድረግ የተለያዩ ስደተኞችን ማዕድ ሲያጋሩ ተመልክተናል። ሀገራቸውን ጥለው የተሰደዱና ኢትዮጵያን መጠጊያ ያደረጉ የሶማሌ፤ የሶሪያ፤ የየመንና የተለያዩ ሀገር ስደተኞችን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቤተመንግሥታቸው ድረስ ጠርተው አስፈጥረዋል፡፡
ከ98 በመቶ በላይ አማኝ የሆነው ኢትዮጵያ ሕዝብ ያለውን በማካፈል ያምናል። ሰዎች ሲቸገሩ የሚጨክን አንጀት የለውም። ከመሶቡ ቆርሶ፤ ከኪሱ ቀንሶ ያለውን ይሰጣል። የእርሱ ቤት ደምቆ የጎረቤቱ እንዲቀዘቅዝ አይፈቅድም። ይህም አኩሪ ባሕል ኢትዮጵያውያን በችግር እንዳይበረከኩና ችግርን ድል አድርገው እንዲኖሩ አድርጓቸዋል።
ይህ የመተሳሰብ፣ የመረዳዳትና የመደጋገፍ እሴት በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተጠናክሮ ቀጥሏል። በተለይም በረመዳን የጾም ወቅት እና በኢድ አልፈጥር እና ኢድ አልአድሃ በዓላት ይህ አኩሪ ባሕል ጎልቶ ይታያል፡፡
በተመሳሳይም የክርስትን እምነት ተከታዮች በሚያከብሯቸው በዓላትም ወቅት የመረዳዳት እና የመደጋገፍ እሴቶቻችን ፈክተው ይታያሉ። በበዓላት ወቅት በአቅም ማነስ ምክንያት በቀን አንድ ጊዜ እንኳን ራሳቸውን መመገብ የማይችሉ ዜጎችን በጋራ ማዕድ እንዲቆርሱ በማድረግ ረገድ የተጀመሩት በጎ ተግባራት የኢትዮጵያውያንን በጎ እሴቶች ማስቀጠያዎች እየሆኑ ነው። በተለይም በበዓላት ወቅት አቅም ደካሞች በዓላትን በእኩል ተደስተው እንዲሳልፉ በበጎ ፈቃድ ወጣቶች ጭምር የሚከናወኑ የማዕድ ማጋራት በጎ ሥራዎችን ለተመለከተ በኢትዮጵያውያን መካከል ያለውን መተሳሰብና መረዳዳት የሚያመላክት ነው፡፡
በአጠቃላይ ኢትዮጵያውን ከመረዳዳትና ከመደጋገፍ ውጪ መገለጫም የላቸውም። ኢትዮጵያም ቆማ መቀጠል የቻለችው ዜጎቿ በሚከውኗቸው መልካም ተግባራት ነው፡፡
ኢትዮጵያዊነት ባለብዙ ቀለማትና ባለብዙ ፈርጅ ሆኖ ትላንትን ተሻግሮ ለዛሬውም ትውልድ ኩራትና ድምቀት ሆኗል። ኢትዮጵያዊነት ሲታሰብ መረዳዳት፤ እንግዳ ተቀባይነት፤ ጀግንነት፤ መስጠት፤ ደግነት፤ መከባበር፤ ለሀገር እና ወገን እራስን አሳልፎ እስከ መስጠት የዘለቀ ሚስጠር ነው፡፡
ታላቅን ማክበር፤ ለታናሽ ማዘን፤ የተቸገረን መርዳት፤ የታመመን ማስታመም፤ የሞተን መቅበር፤ የታሰረን መጠየቅ፤ ሀዘንተኛን ማስተዛዘን፤ የሕፃናትን ባሕሪ በጋራ ማረቅ፤ ሌብነትን መጠየፍ፤ የመሳሰሉት አኩሬ እሴቶችንም የያዘ ነው። እነዚህ አኩሪ እሴቶችም የእኛነታችን መለያ ሆነው ዛሬ ድረስ ዘልቀዋል። በተለይም እንደ ኢድ አልፈጥር ባሉ በዓላት እነዚህ ትውፊቶች ጎልተው ይታያሉ።
የኢድ አልፈጥር ትሩፋቶች ከሆኑት ውስጥ ሌላኛው የመጠያየቂያ (የመዘያየርያ) በዓል መሆኑ ነው። አግብተው የወጡ ወጣቶች እናት እና አባቶቻቸውን፤ ዘመድ አዝማድ እና ጎረቤት የሚጠይቁት በዚህ ወቅት ነው። ተሰባስቦ መብላት እና መጠጣቱ እንዲሁም የሞቀ ጨዋታው ኢድን አይረሴ እና ተናፋቂ ያደርገዋል፡፡
በኢድ አልፈጥር ከሚዘወተሩ ተግባራት ውስጥ ሌላኛው በዓሉ ስጦታ በዓል መሆኑ ነው። አባት ለሚስቱ እና ለልጆቹ ስጦታ ያበረክታል፤ እናት ለባለቤቷ እና ለልጆች ስጦታ በማበርከት በዓሉን በደስታ ማሳለፍ የተለመደ ነው። ይህ ደግሞ በዓሉ በተለይ ለሴቶች እና ለሕፃናት ልዩ ድባብ እንዲኖረው ያደርገዋል፡፡
ሴቶችና ሕፃናት ውብ እና ደማቅ ልብስ ለብሰው፤ በእስላማዊ አደብ ተውበው በዓሉን ያሳልፋሉ። ጣፋጭ ኬኮችና ቼኮላቶች የበዓሉ ማድመቂያ ስለሚሆኑ ሕፃናት በየቤቱ እየዞሩ በዓሉን በደስታ ያሳልፉታል፡፡
የኢድ አልፈጥር በዓሉ ሌላኛው ትሩፋት ደግሞ በዓሉ ወላጅ አልባ ሕፃናት የሚታወሱበት መሆኑ ነው። ወላጅ አልባ ሕፃናት በእስልምና ከፍተኛ ቦታ ይሰጣቸዋል። ወላጅ አልባ ሕፃናትን መንከባከብ የእምነቱ አንዱ ግዴታ ነው። ስለዚህም በኢድ አልፈጥር እለት ወላጅ አልባ ሕፃናት ተከፍተው እንዳይውሉ ሙስሊሞች የመንከባከብ እና የመደገፍ ግዴታ አለባቸው፡፡
በኢድ አልፈጥር በዓል ወላጅ አልባ ሕፃናት ልክ ወላጅ እንዳላቸው ሕፃናት ተደስተው እንዲውሉ አልበሳትን ከማልበስ በሻገር ለበኣክ የሚሆኑ ግብዓቶችን የማሟላት ተግባራት በስፋት ይከናወናል። በዚህም ሕፃናቱ ተደስተው በዓሉን በሰላም ያሳልፋሉ፡፡
ኢድ አልፈጥር የአንድነት እና አብሮነት በዓል ነው። በኢድ እለት ከሕፃናት ጀምሮ ሁሉም ሰው የክት ልብሱን ለብሶ፤ ሽቶ ተቀብቶ ወደተዘጋጀው የመስገጂያ ቦታ ያቀናል። ፈጣሪን የሚያወድሱ እና የሚመሰግኑ ዱአዎችን (ጸሎቶችን) በማድረግ በጋራ ወደ መስገጂያው ቦታ ያቀናል፡፡
በዚህ ወቅት የሚታየው ህብር ልዩ ነው። አንድነቱ እና መተሳሰቡ ቅልብን ይገዛል። ሕፃናት ደምቀው፤ ሴቶች ተውበው፤ ወጣቶች አምረው፤ በእድሜ የገፉ ሰዎች ክብር ተጎናጽፈው በጀምዓ (በአንድነት) ሆነው ሲጓዙ ለተመለከታቸው ልዩ ደስታን ይሰጣሉ፡፡
የኢድ ሰላት በጀምዓ(በአንድነት) ከተሰገደ በኋላ ሁሉም ወደቤቱ ያቀናል። ቤቱ እንደደረሰም ሁሉም እንደ አቅሙ ያለውን ይቋደሳል። ቡና ይፈላል፤ ዳቦ ይቆረሳል፤ ጎረቤት ይጠራ እና ከቡናውም ከምግቡም ይዳረሳል። በተለይም የሌላ እምነት ተከታዮች ጎረቤት ያሉት ሰው ጎረቤቶቹን ታሳቢ ያደረገ ዝግጅት ማድረግ የተለመደ ነው። ጎረቤቶቹም የቀረበላቸውን ምግብ እና መጠጥ እየተቋሱ ስለሀገራቸው ሰላም ይጸልያሉ። ሀገራቸው ሰላም እንድትሆን ፈጣሪያቸውን ይማጸናሉ።
ይሄ አኩሪ ባሕል ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ እና የኢትዮጵያውያንም፣ ልዩ መገለጫ ሆኖ ዘመናትን የተሻገረ ነው። ኢትዮጵያውያን የእምነት ልዩነት ሳይበግራቸው ደስታንም ሆነ ሀዘንን በጋራ ያሳልፋሉ። የሀገራችውንም ዳር ድንበር ይጠብቃሉ፤ ወራሪን በጋራ ድል ይመታሉ፤ በልማት ይሳተፋሉ፤ ሀገራቸውን ጥሪ ስታደርግላቸው ያለምንም ማመንታት ከጎኗ ይቆማሉ። ይህ አንድነታቸውን አብሮነታቸውም ከበርካታ የዓለም ሕዝብ ዘንድ ትልቅ ክብርና ግርማ ሞገስ አጎናጽፏቸዋል። በአርአያነትም እንዲወሰዱ አድርጓቸዋል፡፡
እስማኤል አረቦ
አዲስ ዘመን እሁድ መጋቢት 21 ቀን 2017 ዓ.ም