
እ.ኤ.አ. መጋቢት 7 ቀን 2025 የተካሄደውን የቻይና 14ኛ ብሄራዊ ሕዝባዊ ኮንግረስ ሶስተኛው ስብሰባ አስመልክቶ በተካሄደው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋን ዪ “በመግባባት ላይ ተመሠረተ ምክክር (mutual consultation) ፣ መጋራት (sharing) እና የጋራ ግንባታ (joint construction)” የሚሉትን ሃሳቦች ደጋግመው በመጥቀስ የሁሉም ሀገራት ሕዝቦች ለጋራ ልማት እንዲተባበሩ፤ ለዓለም አቀፉ ደቡብ (global South) ድምፅ ትኩረት እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል።
በተጨማሪም በቻይና የአፍሪካ የትብብር ፎረም ላይ የቀረቡት አስር የትብብር የድርጊት መርሃ ግብሮች በቻይና እና በአፍሪካ መካከል የወደፊት የጋራ ማህበረሰብን ግብ እውን ለማድረግ ደረጃ በደረጃ ተግባራዊ እንደሚደረጉ አመልክተዋል። የሚኒስትሩ መግለጫ የወቅቱን “ዓለም ለሁሉም ናት!” የሚለውን ባህላዊ የቻይና የፖለቲካ ጽንሰ- ሃሳብ ውርስ እና እድገትን በጥልቀት የሚያንፀባርቅ ሲሆን ቻይና የዓለምን የተቀናጀ ልማት ለማራመድ ያላትን የፀና ቁርጠኝነት የሚያሳይም ነው።
“ዓለም ለሁሉም ናት!” የሚለው ጽንሰ-ሃሳብ የመነጨው ከጥንታዊው የቻይና መጽሐፍ “The Book of Rites” ነው። በፀደይ እና በመጸው ወቅት እና እርስ በእርስ በሚዋጉ መንግሥታት ዘመን፣ የባሪያው ማህበረሰብ እና ፊውዳል ማህበረሰብ ሲፈራረቁ፣ የኮንፊሽያውያን ሊቃውንት ” ታላቅ ስምምነት (Great Harmony)” እና “ዓለም ለሁሉም ናት!” የሚሉትን ማህራዊ የአመለካከትና የአሠራር ጽንሰ-ሃሳቦች አቅርበው ነበር።
እነዚህ ሊቃውንት “የንጉሡ የሀገር መሪነት ተቀዳሚ ተግባር የሕዝብን የዕለት ተዕለት ኑሮ ማሳለጥ ነው” ብለው ያምናሉ፣ “የአስተዳደሩ የፖለቲካ ባህሪ ከአድሎ የነፃ እና በፍትሃዊነት ላይ የተመሠረተ፣ የጋራ አስተሳሰብን የሚያራምድ እና መተማመንን እና የጋራ ስምምነትን የሚያጎለብት መሆን አለበት” ይላሉ። “ዓለም ለሁሉም ናት” የሚለው ይህ በጎ አስተሳሰብ ሲውል ሲያድር የቻይና ውብ ማህበረሰብ የፖለቲካ ሃሳብ በመሆን ቀስ በቀስ ቻይና በውጭ ግንኙነቷ የምትከተለው ፅንሰ-ሃሳብ ሆኗል። ይህ ጽንሰ-ሃሳብ በእኛ ዘመን በአዳዲስ ፍችዎች እየበለፀገ መጥቷል፡፡
የሰው ልጅ መጪውን ጊዜ ለመጋራት የሚያደርገው የማህበረሰብ ትብብር ጽንሰ-ሃሳብ ቻይና በዓለም አቀፍ አስተዳደር ላይ ያላትን ጥልቅ አስተሳሰብ የሚያንፀባርቅ ጥበብ ነው። በዓለም ላይ የአንድ ወገን የበላይነትና የጠባቂነት መንፈስ በተጋረጠበት ወቅት ታዳጊ ሀገራት ይህን ለመቋቋም የሁለትዮሽና የዓለም አቀፋዊ ፍትሃዊነትን እና ዕኩል ተጠቃሚነትን በጋራ ለማስከበር አንድነትን እና ትብብርን እያጠናከሩ መምጣት የዘመኑ አዝማሚያ ሆኗል። ይሄ ደግሞ “ዓለም የሁሉም ናት!” ከሚለው ሃሳብ ጋር በእጅጉ የሚስማማ ነው።
ቻይና እና አፍሪካ የወደፊት የጋራ ተጠቃሚነት ያለው ማህበረሰብ መገንባት መቻላቸው የዓለም አቀፋዊ ፍትሃዊነት መርህን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ተግባር ነው። የቻይና አፍሪካ ትብብር ፎረም ከተመሠረተ ወዲህ የቻይና አፍሪካ ግንኙነት የላቀ እድገት አስመዝግቧል። ከመሠረተ ልማት ግንባታ እስከ ህክምና እና ጤና ትብብር፣ ከክህሎት ማሳደግ እስከ ቴክኖሎጂ ፈጠራ ፍሬያማ ውጤት በማምጣት የሁለቱንም ወገኖች ሕዝቦች ተጠቃሚ አድርጓል።
ቻይና ለተከታታይ 16 ዓመታት በአፍሪካ ትልቋ የንግድ አጋር ሆና ቆይታለች። ቻይና እና አፍሪካ እጅ ለእጅ በመያያዝና እውነተኛ የባለብዙ ወገኖች ትብብርን (multilateralism) በጋራ በማሳደግ ሁሉም ተጠቃሚ የሚሆንበትን ትብብር ለማሳደግ የተለያዩ መድረኮችን ፈጥረዋል። የቻይና እና የአፍሪካን እድገት በማስተዋወቅ ረገድ ሁሉም ተሳታፊዎች የባህልና የአስተሳሰብ ልዩነቶችን በማሸነፍ የአየር ንብረት፣ የቴክኖሎጂ እና የጸጥታ ችግሮችን በውይይት፣ እርስ በርስ በመግባባትና በትብብር ለመፍታት የሚያስችል ሁሉንም ወገኖች የሚያሳትፍ ተስማሚ ዓለም አቀፍ የትብብር ሞዴል ፈጥረዋል።
ለቻይና እና ለአፍሪካ የወደፊት የጋራ ተጠቃሚነት ያለው ማህበረሰብ መገንባቱም ዓለም አቀፋዊ ደቡብ (global South) የሚለውን ሃሳብ ትርጉም አበልጽጎታል። ይህ ጽንሰ-ሃሳብ ጥልቅ ለውጦችንም በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ቀደም ባሉት ጊዜያት ጽንሰ-ሃሳቡ በዋነኛነት የደቡብ ሀገሮችን የልማት ጥያቄ የሚያንፀባርቅና ብዙውን ጊዜ እንደ “ያላደጉ ደሃ ሀገራት” ከመሳሰሉት መለያዎች ጋር ይዛመድ ነበር፡፡
የደቡባዊ ሀገራት ውክልና በዓለም አቀፍ የአስተዳደር ሥርዓት በቂ አይደለም፤ ድምፃቸውና የንግግር ኃይላቸው የተገደበ ነው፤ ከዚህም የተነሳ ፍላጎታቸው በአብዛኛው በዓለም አቀፍ አሠራርና አገልግሎት አሰጣጥ ሂደት ውስጥ ሙሉ በሙሉ አይንጸባረቅም ነበር፡፡
ነገር ግን ይህ የዓለም አቀፋዊው ደቡብ ጽንሰ ሃሳብ በአዲሱ ዘመን ሙሉ በሙሉ አዲስ መልክ አሳይቷል፤ በዓለምአቀፍ አስተዳደር ውስጥ በንቃት በመሳተፍ እና ልዩ ጥበብ እና ጥንካሬን በማምጣት ለዓለም እድገት ልዩ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ የታዳጊ ሀገሮች እና በማደግ ላይ ያሉ ሀገሮች ገበያ ለዓለም ኢኮኖሚ ዕድገት የሚያበረክቱት አስተዋፅኦ በየጊዜው እየጨመረ ለዓለም ኢኮኖሚ ማገገሚያ ወሳኝ ሞተር እየሆነ መጥቷል።
የደቡብ ሀገራት የኢንዱስትሪ መስፋፋት እና የከተሜነት ሂደቶች እንዲሁም የትምህርት እና የባህል ሥርዓታቸው እድገት ለዓለም ኢኮኖሚ እድገት ሰፊ እድሎችን ከፍቷል። የደቡብ ሀገሮች የበለጸጉ ባህላዊ ወጎች፣ ልዩ የልማት ተሞክሮዎች እና አዳዲስ የአስተዳደር ልማዶች ዓለም አቀፍ ተግዳሮቶችን ለመፍታት አዳዲስ ሃሳቦችን ይሰጣሉ።
ከምስራቃዊው ጥበብ እስከ አፍሪካዊ መፍትሄዎች፣ የደቡባዊ ሀገሮች የዓለም አቀፍ የእውቀት ሥርዓትን እንደ አዲስ በመቅረጽ ላይ ናቸው፡፡ ባጭሩ የደቡብ ሀገራት እንደ የአየር ንብረት ለውጥ፣ ዲጂታል ኢኮኖሚ እና ዓለም አቀፍ ፋይናንስ የመሳሰሉትን ሕጎችን በማውጣት ላይ በንቃት በመሳተፍ የበለጠ ፍትሃዊ እና ምክንያታዊ ዓለምአቀፍ የአስተዳደር ሥርዓት እንዲጎለብት በማድረግ ሕግና ትዕዛዝን ተቀባይ ከመሆን ወደ ሕግ ፈጣሪነትም እየተሸጋገሩ ነው።
ኮንፊሽየስ “ሶስት ሰዎች አብረው ሲሄዱ አንደኛው አስተማሪ መሆን ይችላል!”ብሏል። ይህም ማለት አንድ ሰው በዕውቀትና በዕድሜ ትልቅ ቢሆንም የራሱ የሆነ መሙላት የሚገባው ክፍተት ሊኖረው ስለሚችል በራሱ ብቁ ነኝ ብሎ መመካት ሳያሻው ከሌላ ከማንኛውም ሰው ትምህርት መውሰድ ይችላል ማለት ነው፡፡
ስለዚህ የትኛውም ሰው የራሱ የሆነ የሚጠቅም ዕውቀትና ጥበብ ስላለው አንደኛችን ከሌላኛችን መማር እንችላለን ማለት ነው፡፡ ከአፍሪካ ጋር በመተባበር ሂደት ውስጥ ቻይና የአፍሪካን ጥበብ እና ጥንካሬ እንዲሁም ወደፊት ለዓለም ልታበረክት የምትችለውን የላቀ አስተዋፅኦ በጥልቀት ተገንዝባለች፡፡ ይህ ደግሞ ቻይና ግጭቶችን ለመፍታት እና ተግዳሮቶችን በአንድነት ለመወጣት፣ የጋራ ምክክር እና ውይይት አስፈላጊ መሆኑን አበክራ የምትሻበት አንዱ ምክንያት ነው።
ቻይና እና የአፍሪካ ሀገሮች እንደ አጋርነታቸውና እንደ ዓለም አቀፋዊ ደቡብ ሀገሮች አባልነታቸው ለዓለም አቀፉ ፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ሥርዓት መረጋጋት አዎንታዊ አስተዋፅኦ እያደረጉ ነው። የዓለምአቀፋዊ ደቡብ ሀገራት ለዘመናዊነት የሚያደርጓቸው የጋራ ጥረቶች በዓለም ታሪክ ውስጥ ትልቅ ክስተት እና በሰው ልጅ የሥልጣኔ ሂደት ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ድንቅ ሥራ መሆን የሚችል ነው።
በቻይና-አፍሪካ ትብብር ፎረም የቤጂንግ የመሪዎች ጉባዔ ላይ የተነደፉት አስር የአጋርነት የድርጊት መርሃ ግብሮች በ2025 ደረጃ በደረጃ ተግባራዊ የሚደረጉ ሲሆን የመጀመሪያዎቹ ውጤቶችም በመታየት ላይ ናቸው። የቻይና እና የአፍሪካ ሕዝቦች “ዓለም ለሁሉም ናት!” የሚለውን የተቀደሰ ተስፋ በጋራ በመያዝ በቻይና እና በአፍሪካ እንዲሁም በዓለም ላይ ለሚገኙ ሁሉም ሀገራት ሰላምና ልማትን በጋራ ጥረት በማምጣት ፍትሃዊ፣ አድሎ የሌለበት፣ የበለጸገ እና ሁሉም ተስማምቶ የሚኖርበት ዓለም አቀፋዊ መንደር እንደሚገነቡ ተስፋ እናደርጋለን፡፡
ዶ/ር ስንቅነሽ አጣለ እና ፕሮፌሰር ሊ ሆንግፈንግ
(ቤጂንግ የውጭ ጥናት ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ጥናት ትምህርት ቤት)
አዲስ ዘመን መጋቢት 20 ቀን 2017 ዓ.ም