ለትግራይ ሕዝብ የተሰጠ ታሪካዊ እድል!

የትግራይ ሕዝብ በኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ግንባታም ሆነ ፣ ሀገረ መንግሥቱን በማጽናት ሂደት ውስጥ ትልቅ አበርክቶ ያለው ሕዝብ ነው። ለሀገር ፍቅር ያለው ስሜት ፤ ለፍትህ እና ለነጻነት ያለው ቀናኢነትም ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የተለየ አይደለም። በየዘመኑ ስለ ሀገር ክብር ፤ ነጻነት እና ፍትህ ብዙ ዋጋ የከፈለ፤ ወደፊትም ለመክፈል ወደ ኋላ የማይል ሕዝብም ነው።

ከመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ብዙ መንፈሳዊ፣ ባህላዊ እና ማኅበራዊ እሴቶችን የሚጋራ ፤ የጋራ ማኅበረሰባዊ ማንነት ያለው ፣ ክፉ እና ደግ ቀናትን አብሮ ያሳለፈ ፤ ቀጣይ ዕጣ ፈንታውም ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወንድም እህቶቹ ጋር የተሳሰረ፤ ይህንን እውነት በአግባቡ የተረዳ እና ለዚህ እውነት ራሱን ያስገዛ ሕዝብ ነው። ይህም ከሀገረ መንግሥት ምሥረታው ጀምሮ በተጨባጭ የታየ ፤ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ አልፎ ዛሬም በሕዝቡ ውስጥ የሚስተዋል ሀቅ ነው ።

ላለፉት ሰባት አስር ዓመታት እንደ ሀገር ከገባንበት ችግር በተለይም ከሀገራዊ ትርክት መዛባት እና መፋለስ ጋር በተያያዘ በተፈጠሩ ግራ መጋባቶች ፤ የትግራይ ሕዝብ እንደ ሕዝብ ብዙ ያልተገቡ ዋጋዎችን ለመክፈል የተገደደባቸው ሁኔታዎች ተፈጥረዋል። ስለ ሰላም እያዜመ በግጭት አዙሪት ውስጥ እንዲያልፍ የሆነባቸው አጋጣሚዎችም ጥቂት አይደሉም።

ለአስራ ሰባት ዓመታት በተካሄደው የትጥቅ ትግል የትግራይ ሕዝብ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ልጆቹን አጥቷል ፤ ከድል ማግስት በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ክልሉ የጦርነት አውድማ ከመሆን ባለፈ ፤ ጦርነቱ የብዙ ትግራውያንን ሕይወት የቀጠፈ ነው። አጠቃላይ በሆነው የክልሉ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ሕይወት ላይም የነበረው አሉታዊ ተጽእኖ ቀላል አልነበረም።

በሀገራቱ መካከል የነበረው ጦርነት እና በጠላትነት የመፈላለግ ሁኔታ በሀገራዊ ለውጡ ማግስት ዓለምን ባስደመመ የሰላም ስምምነት መቋጫ ቢገኝም ፣ በሕወሓት እና በፌዴራል መንግሥት መካከል በተደረገ ተጨማሪ ጦርነት የትግራይ ሕዝብ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ለከፋ ሠብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመት ተዳርጓል። ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ በሕዝቡ ውስጥ የተፈጠረው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ምስቅልቅሎች አሁንም ሕዝቡን ብዙ ዋጋ እያስከፈሉት ነው።

አሁን ላይ የትግራይ ሕዝብ የትኛውንም ዓይነት ጦርነት ውስጥ የመግባት ፍላጎትም ሆነ ፤ ጦርነት የሚሸከም ትከሻ የለውም። ላለፉት ሰባት አስርት ዓመታት የሆነበት ካሰበው እና ከተጠበቀው በላይ ትናንቶቹን እና ዛሬዎቹን ብቻ ሳይሆን ነገዎቹንም አጨልሞበታል። ስለሆነም ባለው አማራጭ ሁሉ ከዚህ እንደጥላ ከሚከተለው ጦርነት ለዘለቄታው መውጣት ይፈልጋል።

ይህ የሁሉም ትግራዊ መሻት ነው ። ከጦርነት ወንድም እህቶቹን በሕይወት ከማጣት ፣ ሀብት ንብረቱን ፣ የነገ ተስፋውን ጭምር ከመቀማት ያተረፈው አንዳች ነገር የለም። ከጦርነት አዙሪት መውጣት ፤ ከሁሉም በላይ ይህንን ፍላጎቱን ተጨባጭ ሊያደርግለት የሚችል አመራር ይፈልጋል። ከትናንት ወጥቶ ተስፋ ያደረጋቸውን ዛሬዎች መኖር የሚያስችለውን መሪ ይሻል።

አሁን የትግራይ ሕዝብ የሚፈልገው ከሆነ ቡድን እና የቡድን አስተሳሰብ የሚያስተሳስር እና ከዚህ የሚመዘዝ አመራር ሳይሆን ፤ በተጨባጭ ከትናንት የተማረ እና ሕዝቡን ከትናንት ማሻገር የሚችል ፣ለዚህ የሚሆን ከዛሬ እና ከዛሬ እሳቤ ጋር የታረቀ ፤ ከጦርነት ፉከራ እና ቀረርቶ ወጥቶ ለሕዝቡ ሰላም እና ልማት የሚተጋ ፤ የሕዝብ ውግንና ያለው አመራር ነው።

ለዚህ ደግሞ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የፕሪቶሪያውን ስምምነት መሠረት ባደረገ መንገድ ሕዝቡ ይሻለኛል የሚለውን መሪውን እንዲመርጥ የሰጡትን ታሪካዊ ዕድል በአግባቡ ሊጠቀመበት ይገባል ። ከሥልጣን እና ከታሪክ ሽሚያ ወጥቶ የሕዝቡን መሻት እውን ለማድረግ ሁለንተናዊ ዝግጁነት ያለው መሪ መምረጥ የሚያስችለውን ይህንን መልካም አጋጣሚ ሊጠቀምበት ይገባል። ይህ በትግራይ ሕዝብ እጅ ያለ ታሪካዊ ዕድል ነው። ዕድሉን ለዘላቂ ሰላም እና ልማት መጠቀምም ከማንም በላይ የትግራይ ሕዝብ ትልቅ ኃላፊነት ነው!

አዲስ ዘመን መጋቢት 20 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You