ዓለማችን በተለያዩ ሃሳቦች እና አመለካከቶች በተሞሉ ሰዎች የተሰባጠረች ድንቅ ምድር ነች። ከዚህ የተነሳ በምድራችን ላይ ስንኖር የሌሎችን አስተያየት መረዳት እና ማክበር መማር በእጅጉ ወሳኝ ነው። ሰዎች ከተለያየ አስተዳደግ ባሕል፣ ልምድ እና እምነት የመጡ ሲሆኑ ያንን መረዳት የሚያስችል ክህሎት መገንባት ይኖርብናል።
በሰዎች መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶች ተፈጥሯዊ ቢሆኑም እነዚህን ክፍተቶች በብልሃት መፍታት ካልቻልን አሉታዊ ማኅበራዊ ግንኙነት እንዲኖረን ምክንያት ሊሆን ይችላል። ታዲያ በዛሬው የመጋቢ አዕምሮ ዝግጅታችን ላይ ይህንን አሉታዊ ጎን እንዴት መፍታት እንደምንችል እናያለን። በቀጣዩ መጣጥፍም የሌሎችን አስተያየት እንዴት መረዳት እና ማክበር እንዳለብን፣ ሌሎች ላይ የበታችነት ስሜት ሳናሳድር እንዴት መግባባት እንደሚቻል፣ እንዲሁም በኅብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት እንድናገኝ የሚያደርጉንን ሥነ ልቦናዊ እና ማኅበራዊ ክህሎቶችን እንዴት መገንባት እንዳለብን እንመለከታለን።
የሌሎች አስተያየትን መረዳት እና ማክበር
በሕይወት ስንኖር ትልቁ ስኬት ሊሆን የሚችል ከሰዎች ጋር የምንመሰርተው መልካም ግንኙነት ነው። ይህንን ከሚያጠነክሩልን መንገዶች ውስጥ ደግሞ የተለያዩ አስተያየቶችን (አመለካከቶችን) ማክበር ነው። ልዩ የሆኑ አመለካከቶችን የሚገነዘብ አዕምሮ ስናዳብር ሰላማዊ ውይይቶችን፣ ጠንካራ ግንኙነቶችን እና የተሻለ ውሳኔዎችን ለማድረግ ይረዳናል። ይህንን ችሎታ ደግሞ በመማር፣ ለሰዎች በምናሳየው ቀና ምልከታ እና ትብብር ልናዳብረው እንችላለን። ሳይንሳዊ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ለውይይት በራቸውን ክፍት የሚያደርጉ ለተለያዩ ሃሳቦችንና ምልከታዎች አክብሮት ያላቸው ሰዎች በሕይወታቸው ደስተኞች ናቸው። መሰል ባሕልን የሚያበረታቱ በሥራ ቦታዎች ከፍተኛ ምርታማነት እና የተሻለ የቡድን ስሜት መፍጠር ይችላሉ።
የሌሎችን አመለካከት ለመረዳት በትኩረት ማዳመጥና ለሰዎች አክብሮትን ማሳየት በጣም ጥሩ ከሆኑ መንገዶች አንዱ ነው። ለተናጋሪው ሙሉ ትኩረት መስጠት፣ ዓይንን እየተመለከቱ ማዳመጣችሁን ማሳየት እንዲሁም ትኩረትን የሚከፋፍሉ ነገሮችን ከማድረግ መቆጠብ የሰዎችን አመለካከት ለመረዳት ዝግጁ መሆናችንን ከሚያሳዩ መንገዶች መካከል ተመራጩ ነው። ምላሽ ለመስጠት ከመቸኮል ይልቅ ከንግግራቸው በስተጀርባ ያለውን ትርጉም መረዳት ላይ ማተኮር የተሻለ እንደሆነ ሳይንሳዊ ጥናቶች ይመክራሉ። ሌላው እና ዋነኛው ጉዳይ ፍርድን ማስወገድ ነው። ይህንን ማድረግ ለምናደርገው ውይይቶች እምነትና ሰላማዊነት ትልቅ እድል ይከፍታል። ከሰዎች ጋር የሚኖረንን መልካም ግንኙነትም ያጠናክርልናል።
እያንዳንዱ ሰው በሚኖርበት አካባቢ፣ ባሕል እና በእምነቱ ምክንያት የራሱ አመለካከትና ባሕሪ ይይዛል። በመሆኑም ይህንን ሰው አስቀድመን በአመለካከቱ ፍርድ ከመስጠታችንና ከመተቸታችን ይልቅ ንግግሮቹን፣ ሃሳቦቹን በጉጉት እና ለመረዳት ፈቃደኛ በመሆን ስሜት ውስጥ ለማዳመጥ ብንሞክር ጤናማ ውይይትን ከማበረታታቱም በላይ ያ ሰው ለእኛ የሚኖረው ግምት መልካም እንዲሆን ያግዛል።
ሌላው ክርክርን ማስወገድ ነው። ከመከራከር ይልቅ ጥያቄዎችን መጠየቅ ትርጉም ያለው ውይይት ያበረታታል። ‹‹እንዲህ እንድታስብ ያደረገህ ምንድን ነው? ስለ አንተ አመለካከት የበለጠ ልትነግረኝ ትችላለህ?›› በሚሉ መሰል ጥያቄዎች የሰውየውን ሃሳብ ለማዳመጥ ዝግጁ መሆንህንና እውነተኛ ፍላጎት እንዳለህ በማሳየት ከአስተያየቱ በስተጀርባ ያሉ ጥልቅ ምክንያቶችን ለመረዳት መሞከር ይገባል። ይህም የጋራ መግባባት ያመጣል። የጋራ መግባባትን መፈለግ ደግሞ ግንኙነቶችን ያጠናክራል። በአለመግባባት ውስጥ እንኳን አስተያየቶች ማዳመጥ ቢያንስ በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ ተመሳሳይ አቋም ለመያዝ ይረዳል።
ለራስ ከሚደረግ አድሎ መንፃት
እያንዳንዱ ሰው አመለካከቶች አሉት። እሱም በአስተሳሰቡ እና ለነገሮች በሚኖረው አመለካከትና በምላሹ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። ብዙ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ሰዎች ተቃራኒ አመለካከቶችን ችላ በማለት የራሳቸውን እምነት የሚደግፍ መረጃን ላይ ብቻ ማተኮርን ምርጫቸው ያደርጋሉ። ይህ ደግሞ የግል አድሎአዊነትን ያመጣል። ይህንን መረዳት መቻል ለራሳችን እንዳናደላ እና ግላዊ ፍላጎታችን ላይ ብቻ እንዳናተኩር ጥንቃቄ ለማድረግ ይረዳናል።
የተለያዩ አስተያየቶችን ወዲያውኑ ውድቅ ከማድረግ ይልቅ እነሱን ለማገናዘብ ጊዜ መስጠቱ ግንዛቤን ያሰፋል። እራስን ለተለያዩ አመለካከቶች ክፍት ማድረግ አድሎአዊነትን ለማስወገድ እጅግ አስፈላጊ ነው። መጻሕፍትን ማንበብ፣ ዘጋቢ ፊልሞችን መመልከት ወይም ከተለያዩ አስተዳደግ ካላቸው ሰዎች ጋር መወያየት አዳዲስ ግንዛቤዎችን እንዲኖረን ያስችለናል፤ ሚዛናዊ እይታን ለማዳበር ይረዳል። ለዚህ ነው ምላሽ ከመስጠትህ በፊት ትንሽ ጊዜ ወስደህ ስሜትና ፍርድ የተቀላቀለበት አስተያየት እንዳይኖርህ መከላከል የሚኖርብህ።
ሌሎች የበታችነት ስሜት እንዳይሰማቸው
ሰዎች ለሰዎች አክብሮት ሲኖራቸው ለማዳመጥ እና አዳዲስ አመለካከቶችን ለማጤን ፍላጎት ያዳብራሉ። በተቃራኒው ደግሞ ሰዎችን ስህተት እንደሆኑ እንዲሰማቸው ማድረግ እንዲርቁንና ስለ እኛ መጥፎ አመለካከት እንዲኖራቸው ሊገፋፋቸው ይችላል። ነገር ግን ውይይቶችን በፍፁም ቅን ልቦና እና በትዕግስት ማድረግና የራስን ሃሳብ ማቅረብ ትርጉም ያለው ውይይት ለማድረግ ይረዳል። ባላጋራችንም የበታችነት ስሜት እንዳይሰማው ያግዛል።
ለዚህ ነው አንድን ሰው ከመውቀስ ወይም ከመወንጀል ይልቅ ትህትናን ማሳየት ገንቢ ውይይት ይፈጥራል። ‹‹ተሳስተሀል›› ከማለት ይልቅ ‹‹እኔ ግን ጉዳዩን በተለየ መንገድ ነው የማየው›› በማለት ለውይይት ንግግሩን ክፍት ማድረግ ያስፈልጋል። አብሮን ለውይይት የተቀመጠን ሰውም በራስ መተማመን በማሳደግ ጥላቻን ያስወግዳል። ለዚህ ነው የግል አስተያየቶችን ከማቅረባችን በፊት ሌሎች አመለካከቶችን ማድነቅ የጋራ መከባበርን ለመገንባት እንደሚያግዝ መረዳት ያለብን። የተለያዩ አመለካከቶችን ለማስተናገድ ዝግጁ የሚሆኑ ሰዎች አለመግባባት በሚፈጠርበት ጊዜም እንኳ ሰዎችን ለማዳመጥ የበለጠ ፈቃደኛ ናቸው።
የሃሳብህን ትክክለኛነት ለማስረዳትና በሌሎች ላይ ተጽዕኖ ለማድረግ ታጋሽ መሆን አስፈላጊ ነው። የሰዎችን አመለካከትና አእምሮ በቅጽበት መለወጥ አትችልም። ሰዎችን ሃሳባችንን እንዲቀበሉ መጫን አዳዲስ ሃሳቦችን እንዲሸሹና እንዲቃወሙ ሊያደርግ ይችላል። ሰዎች የምትሰጣቸውን መረጃን አገናዝበው እንዲቀበሉ እና ወደ ድምዳሜያቸው በተፈጥሮ ሂደት እንዲደርሱ ጊዜ መስጠት ይኖርብሃል፤ ለሃሳብህ ተቀባይነት ማግኘትም ይህ መንገድ የበለጠ ውጤታማ ነው። ሰዎችን ወደ አንተ ሃሳብ በአርአያነት መምራትና ተፅዕኖን ለመፍጠር መሞከር ምርጥ መንገድ ነው። ሌሎችን በክርክር ለማሳመን ከመሞከር ይልቅ እምነትህን በተግባር ማሳየት የበለጠ ኃይል ሊሆን ይችላል። ሰዎች አንድን ሃሳብ አወንታዊ ውጤት ሲመለከቱ አመለካከታቸውን የመቀየር እድላቸው ሰፊ ነው።
ብልህነትን ምርጫህ አድርግ
ስሜትህን ግዛ፤ ብልህ ሁን። ውይይቶችን በስሜታዊነት ከማድረግ ይልቅ ራስህን በመግዛት ከስሜት የፀዳ ውይይት አድርግ፤ ብልህነት ሃሳብህን ለማስረፅ ቁልፍ ሚና ይጫወታል። ከፍተኛ የማሰብ ችሎታ ያላቸው ሰዎች ስሜታቸውን በማስተዳደር እና የሌሎችን ስሜት በማወቅ ረገድ የተሻሉ ናቸው። ስሜትን ማወቅና መቆጣጠር በአስተሳሰብ ልቆ ለመገኘት ይረዳል። ውይይቱ ብስጭት የሚያስከትል፤ አለመግባባትን የሚፈጥር ከሆነ ስሜትህን ለመቆጣጠር እንድትችልና የተቆጠበ ምላሽ እንዲኖር ያስችላል። ስሜት የተቀላቀለባቸው ምላሾችን መቆጣጠር አላስፈላጊ ግጭቶችን ይከላከላል። በጥልቀት መተንፈስ እና ቃላትን በጥንቃቄ መምረጥ ውይይቶችን በአክብሮት እና ፍሬያማ እንዲሆን ያደርጋል።
ማህበራዊ ተግባቦት እንዴት ትገነባለህ
ግልጽ እና ቀላል ቋንቋ መጠቀም ሰዎች እንዲረዱህ እና ሃሳቦችህን ለመቀበል እንዲችሉ ነገሮችን ቀላል ያደርግላቸዋል። ማብራሪያዎችህ በጣም ውስብስብ ሲሆኑ ፍላጎታቸውን ሊያጡ ወይም መልእክቱን በተሳሳተ መንገድ ሊረዱት ይችላሉ። አጭር እና ቀጥተኛ ዓረፍተ ነገሮችን መጠቀም ያስፈልጋል። ሃሳቦች በቀላሉ ሲገለጹ ሰዎች ለውይይት ፍላጎት የማሳየትና የመሳተፍ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው። ቴክኒካዊ ቃላትን ወይም የተወሳሰቡ ቃላትን አስወግድ። ቀላል ቃላት ከውስብስብ ቋንቋ ይልቅ መልእክትን ለማድረስ የበለጠ ውጤታማ ነው።
ራስን ማወቅ ለማኅበራዊ ተቀባይነት ጠቃሚ ችሎታ ነው። ጥንካሬያቸውን እና ድክመታቸውን የተረዱ ሰዎች በሰዎች ዘንድ የበለጠ እምነት እና ተቀባይነት ያገኛሉ፤ በተጨማሪ ከተለያዩ ማኅበራዊ ግንኙነቶች ጋር ለመላመድ ይረዳል። ለለውጥ ክፍት መሆን፤ አዲስ ልምዶችንና አመለካከቶችን ለመቀበል ዝግጁ መሆን ከሌሎች ጋር ያለህን ግንኙነት ያሻሽላል። በራስ መተማመንህ ሰዎችን ይስባል፣ ትዕቢት ግን በተቃራኒው ይገፋቸዋል። ትሁት ሁን፤ በራስ መተማመንህንና ትህትናህን ማመጣጠን ከሰዎች ጋር የሚኖርህን መልካም ግንኙነት ያጠናክርሃል። የበላይነትንህን ከማሳየት ይልቅ ለሌሎች ሰዎች አመለካከት ራስህን ክፍት ማድረግ የበለጠ ለመማር የተሻለ እድል ይሰጥሃል።
ሰዎች ወዳጃዊ አቀራረብ እና ለተለያዩ አመለካከቶች ክፍት አስተሳሰብ ምቾት እንዲሰማቸው ያደርጋል። በፊት ላይ የእንኳን ደህና መጣችሁ አመለካከት ብታንፀባርቅ አወንታዊ ግንኙነት እንዲኖርህ ይረዳል። የጋራ ፍላጎቶች ላይ ማተኮር ንግግሮችን ቀላል ያደርጋል። የጋራ የትርፍ ጊዜ ማሳለፊያዎች፣ ልምዶች ወይም አመለካከቶች ላይ ትኩረት ማድረግ ለመልካም ግንኙነት መሠረት ይሰጣሉ። ጥሩ አድማጭ መሆን መተማመንን እና ፍላጎትን ይገነባል። ለሰዎች ከልብ ትኩረት የሚሰጡ እና ለሃሳቦቻቸው ፍላጎት የሚያሳዩት ጋር መልካም ግንኙነት ለመፍጠር ይፈልጋሉ። በመሆኑም አንተም በዚህ መልኩ ራስህን ብታዘጋጅ ማኅበራዊ ግንኙነትህ የተስተካከለና ጤናማ ይሆናል።
መልካም ማኅበራዊ መስተጋብር መፍጠርህ ለአጠቃላይ ደህንነትህና ደስታህ አስተዋጽኦ ያደርጋል። ጠንካራ ማኅበራዊ ግንኙነት ያላቸው ሰዎች ደስተኛ እና ጤናማ ይሆናሉ። አዎንታዊ ግንኙነቶች የአእምሮ ጤናን ያሻሽላል፤ ጭንቀትን ይቀንሳል። ትርጉም ባለው ውይይቶች ውስጥ መሳተፍ በራስ መተማመንህንና ከሰዎች ጋር ያለህን ትስስር ያጠናክራል። ጥሩ የሃሳብ ልውውጥ የማድረግ ችሎታ ለተሰማራህበት ሙያ እድገትና ለሥራ እድል በሮችን ይከፍታል። በተጨማሪ ጠንካራ ማኅበራዊ ክህሎቶች ሲኖሩህ ችግርን የመፍታት ችሎታህም የዚያኑ ያክል ይሻሻላል። ከሌሎች በሰላም እና በፍፁም ወዳጅነት መኖር መቻል፣ መተባበር እና የተለያዩ አመለካከቶችን መረዳት የተሻለ ሕይወት እንዲኖርህ መሠረት ይሆናል።
ለዚህ ነው በዛሬው የመጋቢ አዕምሮ አምድ ላይ የሌሎችን አስተያየት መረዳት እና ማክበር የግል እና ማኅበራዊ እድገትን የሚያጎለብት ጠቃሚ ችሎታ መሆኑን በጥልቀት መጫወትህ የወደድኩት። ሰዎችን በንቃት ማዳመጥ፣ ትዕግስት፣ ብልህነት ትርጉም ላለው ማኅበራዊ ግንኙነት እንደሚጠቅምህ ተገንዝበህ ዛሬውኑ ከነዚህ ክህሎት ጋር ራስህን አወዳጅ። ሰላም!!
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 20 ቀን 2017 ዓ.ም